Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የያቤሎ ሜታገፈርሳ መንገድ ግንባታ መጠናቀቅና የአዳዲሶቹ ኮንትራክተሮች የወደፊት ዕጣ ፈንታ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

   በ2002 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ውስጥ በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ተሳታፊ የነበሩ ኮንትራክተሮች ቁጥር 15 ብቻ እንደነበሩ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መረጃ ያመለክታል፡፡ እነዚህን ያህል ኮንትራክተሮችን ይዞ መጠነ ሰፊ ነው የሚባለውን የመንገድ ዘርፍ ልማት መከወን አዳጋች ነበር፡፡ ይህንን ክፍተት በማየትም በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አገር በቀል ኮንትራክተሮችን በአቅም ግንባታ ፕሮግራም በማሳደግ በመንገድ ግንባታ ውስጥ ሊሳተፉ የሚችሉ አገር በቀል ኮንትራክተሮችን ቁጥር ወደ አንድ መቶ ለማድረስ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዚሁ ፕሮግራም አጋዥነት በመንገድ ግንባታ ውስጥ የሚሳተፉ አገር በቀል  ኮንትራክተሮችን ቁጥር 94 ማድረስ መቻሉን ባለሥልጣኑ ይገልጻል፡፡

በዚሁ መሠረት ነባሮቹን ጨምሮ ወደ መንገድ ግንባታ ከገቡ አገር በቀል ኮንትራክተሮች መካከል በደረጃ አንድ ኮንትራክተርነት የተመዘገው ሼድ ጠቅላላ የሥራ ተቋራጭ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አንዱ ነው፡፡

ቀደም ብሎ በሕንፃ ግንባታ ዘርፍ ውስጥ ሲንቀሳቀስ የቆየው ሼድ ኮንስትራክሽን ወደ መንገድ ግንባታ በመግባት በዘርፉ የመጀመርያው የሆነውንና የያቤሎ – ሜታገፈርሳ ኮንትራክት ሦስት ፕሮጀክት የሚል ስያሜ ያለውን የጠጠር መንገድ በጨረታ አሸንፎ ወደ ሥራ በመግባት ግንባታውን ማጠናቀቅ ችሏል፡፡

የሼድ ጠቅላላ ተቋራጭ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለም ኃይሉ እንደገለጹትም ይህንን 30 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት ያገኙት መንግሥት የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን ለማሳደግ ባወጣው የአቅም ግንባታ ፕሮግራም መሠረት ተሳታፊ በመሆን ነው፡፡

የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ወደ መንገድ ግንባታ እንዲገቡ ያወጣውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግም ቀድሞ የነበሩትን የጨረታ መመዘኛዎች ዝቅ በማድረግ እንዲሳተፉ በማድረግ ነው፡፡  በዚሁ ዕድል መሠረት በወጣ ጨረታ መሠረት አሸናፊ በመሆን የመንገድ ሥራ ዘርፉን መቀላቀል እንደቻሉ አቶ ዓለም ያመለክታሉ፡፡

ይህ የመንግሥት ፕሮግራም በመንገድ ልማት ዘርፍ ፕሮግራሙ መሠረት መንግሥት ለአገር በቀል ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች ተሳትፎ በሰጠው ልዩ ትኩረት ከፍተኛ ለውጦችና መሻሻሎች እየታየባቸው መሆኑንም የባለሥልጣኑ መግለጫ ያመለክታል፡፡ እንዲህ ያሉ ከ20 ያላነሱ በፌዴራል የመንገድ ሥራ ዘርፍ ተሳትፈው የማያውቁ ኮንትራክተሮች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመንገድ ግንባታ ሥራዎች ተሰጥቷቸዋል፡፡

ለትራፊክ ክፍት የሆነው የያቤሎ ሜታገፈርሳ ኮንትራት ሦስት የመንገድ ፕሮጀክት በአቅም ግንባታ ፕሮግራሙ በአዲስ አገር በቀል የሥራ ተቋራጭና አማካሪ መሠራቱም አንድ ማሳያ እንደሚሆን የባለሥልጣኑ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ገልጸዋል፡፡

እንደ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መረጃ የሞምባሳ-ናይሮቢ-አዲስ አበባ ኮሪደር ከሆነውና ከአገረ ማርያም መስመር ጋር የሚገናኘው የያቤሎ ሜታገፈርሳ መንገድ ፕሮጀክት በሦስት ተከፍሎ የተሠራ ሲሆን፣ ሦስቱም ፕሮጀክቶች ለመንገድ ሥራ ጀማሪ በሆኑ ኮንትራክተሮች የተሠሩ ናቸው፡፡

ኮንትራት ሦስት የሚል ስያሜ ያለው በሼድ የተሠራው መንገድ ለትራፊክ ክፍት መሆን የተሽከርካሪዎችን የጉዞ ጊዜና ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ከመቀነሱም በላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ደቡብ፣ ኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎችን የሚያስተሳስር ስለመሆኑም የባለሥልጣኑ መረጃ ያስረዳል፡፡

የዚህ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ የተካሄደው በአዲስ አገር በቀል ተቋራጭና አማካሪ ድርጅት መሆኑ የውጭ ምንዛሪን ከማዳንና የኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት ከማሳደግ አኳያ የሚሰጠው ጠቀሜታ የጎላ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡

ከአዲስ አበባ ከ580 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ግንባታው የተጠናቀቀው የዚህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም ምንም መንገድ ያልነበረበት ነው፡፡ ለዚህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በወጣው ጨረታ መሠረት ሼድ ኮንስትራክሽን አሸናፊ ሆኖ ሥራውን የተረከበው በ90 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት በኋላ ሥራውን ሲያጠናቅቅ ግን ጠቅላላ ወጪው ፕሮጀክቱ ይጠናቀቃል ተብሎ ከታሰበው በላይ ሆኗል፡፡

እንደ አቶ ዓለም ገለጻ ለዚህ ፕሮጀክት በሚሊዮን የሚቆጠር ተጨማሪ ወጪ አውጥተውበታል፡፡ እንዳላተረፉበትም ይናገራሉ፡፡ ይህ መንገድ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ቢሆንም ሥራው እጅግ ከባድ ነበርም ተብሏል፡፡ አስቸጋሪ ነበር የተባለውም ኮንትራክተሩ ለመንገድ ግንባታ አዲስ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ መንገዱ የተገነባበት አካባቢ መልከዓ ምድር አስቸጋሪ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡

የፕሮጀክቱ ወጪ ከኮንትራክት ውሉ በላይ ወጪ ሊጠይቅ የቻለበት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ መንገዱ የሚያልፍበት ቦታ ተፈጥሮ ከታሰበው በላይ አስቸጋሪ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡

በመንገድ ግንባታ የመጀመርያ መሆናቸውም አንድ ምክንያት ሊሆን ቢችልም በአንዳንድ የመንገዱ ክፍሎች የነበረውን አለት ለመቁረጥ የተሠራው ሥራ ከታሰበው በላይ ወጪ ጠይቋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ መሣሪያዎቻቸውንም የአገልግሎት ጊዜ ያሳጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በአካባቢው የአየር ንብረት በረሃማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለግንባታው ወሳኝ ግብዓት የሆነውን ውኃ ለማግኘት አለመቻላቸው ከፍተኛ ተግዳሮት ከመሆን አልፎ ለግንባታ ወጪያቸው መናር ሌላው ምክንያት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

‹‹ቦታው አሸዋማ በመሆኑ ለሥራው ከፍተኛ ውኃ ያስፈልግ ነበር፡፡ አጋጣሚ ሆኖ በአካባቢው ወንዝና ሐይቅ የሚባል ነገር የለም፡፡ ውኃ ለማግኘት በተለያዩ አካባቢዎች ጉድጓድ ቆፍረን ያደረግናቸው ሙከራዎች ባለመሳካቱ ወራት ጠብቆ ዝናብ እስኪዘንብ መጠበቅ ግድ ነበር፤›› በማለትም ገልጸዋል፡፡ በዝናብ የተገኘውን ውኃም አቁሮ በመጠቀም የፕሮጀክቱን ሥራ ማከናወናቸው ደግሞ ግንባታውን በተያዘው ፕሮግራም መሠረት እንዳያካሂዱ እንቅፋት ነበር፡፡

አለታማ ቦታዎችን ለመሰባበርም የነበረው ችግር ከፍተኛ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዓለም፣ በሌላ ግንባታ ከስድስት እስከ 12 ወሮች ይጠቀሙባቸው የነበሩ የመቁረጫ መሣሪያዎች ሳይቀሩ እዚህ ፕሮጀክት ላይ በአንድና በሁለት ወር መቀየር ግድ ይል እንደነበርም በማስታወስ ግንባታው ምን ያህል ፈታኝ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

እንዲህም ቢሆን ሥራቸውን ማጠናቀቃቸው ለኩባንያቸው ትልቅ ነገር መሆኑንና በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ለመቀጠል አቅም እንደፈጠረላቸው ይገልጻሉ፡፡ በአቅም ግንባታ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ በመሆን ወደ መንገድ ግንባታ መግባታቸው እንዳለ ሆኖ በቀጣይ ግን አገር በቀል ኮንትራክተሮች በተለይ እንደእሳቸው ከሕንፃ ግንባታ በቀጥታ ወደ መንገድ ሥራ የገቡ ከ15 በላይ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ጉዳይ ሳያሳስባቸው አልቀረም፡፡

 እንደ አቶ ዓለም ገለጻ የመንግሥት የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት በእርግጥም አገር በቀል ኮንትራክተሮችን ተወዳዳሪ ከማድረግ በላይ ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ የሚጠቅም መሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ በኋላ እነዚህ አገር በቀል ኮንትራክተሮች መጪ ዕድል ላይ ካልታሰበበት ክፍተት ሊፈጠር ይችላልም ይላሉ፡፡

አዳዲሶቹ ኮንትራክተሮች በመጀመርያው ሥራቸው ብዙ ትምህርት ያገኙ ሲሆን፣ በመንገድ ግንባታ ሥራም ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያሳዩ በመሆናቸው ይህ መልካም ዕድል ተጨማሪ ሥራዎችን እያገኙ እንዲቀጥሉ መደረግ እንደሚኖርበት ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ኢንዱስትሪው በውጭ ኮንትራክተሮች የበላይነት የተያዘ መሆኑን በማስታወስም ዘርፉ በአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የሚታገዙበት የተለያዩ አሠራሮች ሊዘረጉ ይገባል በማለት ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ለአዳዲሶቹም ሆኑ ለሌሎች አገር በቀል ኮንትራክተሮች በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ውስጥ እንዲቀጥሉ በተለየ የሚስተናገዱበት ዕድል ሊኖር ይገባል፡፡ ለዚህም መፍትሔ ይሆናል ብለው በምሳሌነት የጠቀሱት የጨረታ መስፈርቶች ዝቅ ማድረግ ነው፡፡ ኮንትራክተሮች በአሁኑ ወቅት የሚጠየቁትን የጨረታ መስፈርት በመከለስ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲሠሩ ካልተደረገ ለሀብት ብክነትና ለአገር በቀል ኮንትራክተሮች መንገጫገጭ መንስዔ ይሆናል በማለት አቶ ዓለም ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

 ‹‹በተለይ አሁንም በተለያዩ ጨረታዎች ላይ የሚታየው የጨረታ መወዳደሪያ መስፈርት ከፍተኛ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ጨረታ መስፈርቶች የሚደርሳቸው አይደለም፤›› የሚሉት አቶ ዓለም፣ እነዚህ መስፈርቶች ተሻሽለውና ዝቅ ብለው አገር በቀል ኮንትራክተሮች በቀጥታ እንዲሳተፉበት መደረግ ይኖርበታል ይላሉ፡፡

በአንፃሩ ግን የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በማጠናቀቃችሁ በመንገድ ግንባታ ጥሩ ልምድ ማግኘታቸውን የሚገልጹት አቶ ዓለም፣ በቀጣይም በትልልቅ የመንገድ ሥራ ግንባታዎች ላይ ለመወዳደር የሚያስችል አቅም ማግኘታቸውንም ያመላክታሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢንዱስትሪውና በውጭ ኮንትራክተሮች ቁጥጥር ሥር እየሆነ መሄዱን በመቀየር፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች መረከብ ስለሚኖርባቸው ቀጣዩ የመንገድ ልማት ዘርፍ ፕሮግራምም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ መሆን ይገባዋል የሚል አስተያየታቸውንም ሰጥተዋል፡፡

የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን ተሳትፎ ከማሳደግ አኳያ የአቶ ዓለም ሥጋትን በተመለከተ አቶ ሳምሶን እንደገለጹት ደግሞ፣ በመንግሥት ሲደረግ የነበረው ድጋፍ የሚቀጥል መሆኑ ነው፡፡ እንደ አቶ ሳምሶን ገለጻ በአሁኑ ወቅት ካሉት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ በአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የተያዘ ነው፡፡ ይህም በፕሮጀክት ድርሻ ደረጃ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን የሚያመለክትም ነው ይላሉ፡፡

በገንዘብ ደረጃ ወይም ትልልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግን በውጭ ኮንትራክተሮች የተያዘዙ መሆናቸውን ያልሸሸጉት አቶ ሳምሶን፣ ይህንን ክፍተት ለመድፈን በቀጣዩ የዕቅድ ዘመንም ለአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች አቅም ማሳደግ ዓብይ ዓላማ ተደርጎ ተቀምጧል፡፡ በመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ የጨረታ መስፈርቶቹንም መፈተሽ እንደሚሆን አስታውሰዋል፡፡ የሥራ ተቋራጮችን አቅም ያገናዘበ ፕሮጀክት በመቅረፅ አዳዲስ ኮትራክተሮች እንዲገቡ የማድረግ ውጥን ጭምር ስለመኖሩም አቶ ሳምሶን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በውጭ ተቋማት ፋይናንስ በሚደረጉ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የውጭ ኮንትራክተሮች ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዝ የተናገሩት አቶ ሳምሶን፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በዋናነት እየተሳተፉ ያሉት በኢትዮጵያ መንግሥት ፋይናንስ በሚደረጉ ፕሮጀክቶች ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ግን ይህ በውጭ ተቋማት ፋይናንስ በሚደረጉ ፕሮጀክቶች ላይ ጭምር አገር በቀል ተቋራጮች መሳተፍ እንዲችሉ መንግሥት የራሱን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ግን አገር በቀል ኮንትራክተሮችም በውስጣቸው ያለውን የማኔጅመንት ችግር ማየት ይጠበቅባቸዋል የሚሉት አቶ ሳምሶን፣ ኮንትራክተሮች በራሳቸው መንገድ ባለሙያዎችን የማፍራት ልምድ ማዳበርና አቅማቸውንም ለማሳደግ መጣር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ በመንግሥት ድጋፍ ብቻ የትም እንደማይደረስ ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ዓለም በበኩላቸው አገር በቀል ኮንትራክተሮችን ለማሳደግ የሚደረገው ድጋፍ ከጨረታ መስፈርቶች ዝቅ ከማድረግ ባሻገር በፋይናንስ የሚደገፉበት መንገድ ሊመቻች ይገባል ብለዋል፡፡ ማሽነሪዎችን በዱቤ የሚያገኙበት መንገድ መመቻቸትም ለአገር በቀል ኮንትራክተሮች ዕድገት ወሳኝ እንደሆነም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች