Monday, February 26, 2024

ኢሕአዴግ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

– በድፍረት ድክመቶቹን ራሱ በማየት የመጀመሪያውን ሴሚስተር ፈተና አልፏል?

– ድክመቶቹን በቆራጥነትና በተግባር የሚያርምበት ማጠቃለያና የመጨረሻ ወሳኝ ፈተናስ ይጠብቀዋል?

አሥረኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ ከነሐሴ 22 እስከ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በትግራይ ክልል በመቐለ ከተማ ተካሂዶ ተጠናቋል፡፡ በዚሁ ጉባዔ በአራቱም አባል ድርጅቶች በድምፅ ተወክለው ከተሳተፉት ከሺሕ በላይ አባላት በተጨማሪ የድምፅ ውክልና የሌላቸው፣ የኢሕአዴግ አባላት ያልሆኑም ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሥራ ዘርፎች በታዛቢነት እንዲገኙ የተጋበዙም ነበሩ፡፡ ይህ ዘገባም የዚህ ጉባዔ የቅርብ ክትትልና ትዝብት ውጤት ነው፡፡

የጉባዔው ዋነኛ ዓላማ ከ9ኛው ጉባዔ እስካሁኑ 10ኛ ጉባዔ ድረስ በዕቅድ ተይዞ የነበረው ተግባር መገምገምና እስከ ቀጣይ ጉባዔ ድረስ ዕቅድ መንደፍና አመራርን መምረጥ ነው፡፡ በዚህ መሠረትም ስለነበረው እንቅስቃሴ ሪፖርት ቀርቧል፡፡ ሪፖርቱ ከውይይቱ በፊት ተሰራጭቶ የቡድንና የጋራ ውይይትም ተካሂዶበታል፡፡ አራቱ አባል ድርጅቶች ለኢሕአዴግ የማዕከላዊ ኮሚቴና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚወከሉትን በየራሳቸው ጉባዔ ከመረጡ በኋላ፣ በጋራ ደግሞ በዚሁ በ10ኛ ጉባዔም የግንባሩን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መርጠዋል፡፡ የኦዲትና የቁጥጥር ኮሚሽን አመራሮችም ተመርጠዋል፡፡

ኢሕአዴግ ገዥ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን የፓርቲውን እንቅስቃሴ፣ የጉባዔውን ሒደትና ውጤት በሚመለከት ኅብረተሰቡም በትኩረት ሲያስብበትና በርካታ ጥያቄዎች ሲያነሳ ሰንብቷል፡፡ ትልቁና ዋነኛ የሕዝብ ትኩረትና ጥያቄ የነበረውም፣ ኢሕአዴግ ድክመቶቹንና ጉድለቶች ዓይቶና መርምሮ፣ ተስተካክሎና ተጠናክሮ አገር መምራት ይችላል ወይ? የሚለው ነበር፡፡

የዚህ ጽሑፍ አንደኛውና ዋነኛ አጀንዳም ኢሕአዴግ ድክመቶቹንና ጉድለቶቹን በግልጽና በድፍረት አየ? መረመረ? ተቀበለ ወይ? ለቀጣይ የሚጠበቅበትስ ምንድነው? የሚለው ነውና በሁለት ተከፍሎ ይታያል፡፡

ክፍል 1

ኢሕአዴግ በድፍረት ራሱን በራሱ ድክመቶቹንና ጉድለቶቹን በመፈተሽ የመጀመሪያውን ሴሚስተር ፈተና አልፏል?

ቀደም ብሎ በአራቱም አባል ድርጅቶች በተካሄደው ጉባዔም ሆነ በዚህ በ10ኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ የተካሄደው የራሱን ድክመት የማየትና የመመርመር ሒደት በሪፖርቱ ከቀረበው በላይ ደማቅ፣ ደፋርና ግልጽ ውይይት የተካሄደበት ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ስለራሱ ድክመት በግልጽና በድፍረት ተወያይቶ አምኖ ተቀብሏል፡፡ የኢሕአዴግ ዋና ዋና ድክመቶች ተብለው በጉባዔው ግልጽ ውይይት ተደርጎባቸው ተቀባይነት ያገኙት እነዚህ ናቸው፡፡

 1. የኢሕአዴግ ሕዝባዊነት በግለኝነት እየተሸራረፈ ነው

ኢሕአዴግ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የሕዝብ ዓላማ ይዞ ሕዝብን ለማገልገል በቁርጠኝነት ሲንቀሳቀስ የነበረ መሆኑን፣ በአሁኑ ጊዜ ግን የሕዝብን ጥቅም ከማስቀደምና ሕዝብ የበላይ፣ ወሳኝና ተቆጣጣሪ መሆኑን እየተዘነጋ የግል ጥቅምና ምቾት ለማሳካት መንቀሳቀስ በኢሕአዴግ ውስጥ እየተስፋፋ መጥቷል ብሎ ጉባዔው በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በድፍረትም ተቀብሎታል፡፡

 1. የውስጥ ዴሞክራሲና የውስጥ ትግል እየተዳከመ ነው

ሕዝብን ለማገልገል በቆራጥነትና በከፍተኛ እምነት ትግል ይካሄድ በነበረበት ጊዜ፣ የውስጥ ትግልም ጠንካራና ግልጽ እንደነበር ተወስቷል፡፡ አመራርም ሆነ አባል ድክመት ሲያሳይ መገምገም፣ መውቀስ፣ ማስተካከልና ዕርምጃ መውሰድ ባህል ነበር፡፡ አሁን ግን ግምገማው እየተድበሰበሰና እየተዳከመ፣ እከከኝ ልከክህ እየበዛ፣ መቻቻልና መፈራራት እየነገሠ እንደሚገኝ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በግልጽም ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

 1. “ኪራይ ሰብሳቢነት” እና ሙስና እየተስፋፋ ነው

አገርንና ሕዝብን ለማገልገል ቅድሚያ ሰጥቶ ከመረባረብ ይልቅ የራስን ጥቅም ለማስከበር መረባረብ በግልጽ በአባላት እየታየ እንደሆነ ጉባዔው አረጋግጧል፡፡ ይህ ድክመት በገጠር የተሻለ ቢሆንም፣ አሁን አሁን በገጠርም እየተስፋፋ እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በከተማ ግን “ኪራይ ሰብሳቢነት” የበላይነት እየያዘ እንደመጣ ጉባዔው በግልጽ ተወያይቶበት፣ በግልጽ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

4 መልካም አስተዳደር እየጠፋ ነው

በየደረጃው ያለው አመራር በሚመራው ተቋም ውስጥ ብልሹ አሠራሮች በተለያዩ መልኮች እየተንፀባረቁ እንደሆነ ጉባዔው በግልጽ ተወይይቶበታል፡፡ ምግባረ ብልሹነት እንደተስፋፋ፣ ሕዝብ ባለጉዳይን ለማነጋገርና ችግር ለመፍታት አለመንቀሳቀስ፣ እንዲያውም ቢሮ እያሉ የሉም ማለት፣ ስብሰባ ሳይኖር ስብሰባ ላይ ናቸው እያሉ ችግርን አለመፍታት በግልጽ እየታየ እንደሆነ ተቀምጧል፡፡ በጥቅማ ጥቅም ካልሆነ በሕዝባዊነት መምራትና ማስተዳደር እየታየ እንዳልሆነ በግልጽ ተነግሯል፡፡ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

 1. የፍትሕ ሥርዓቱም እየተዳከመ ነው

ዳኞች፣ ዓቃቤ ሕጎችና ፖሊሶች ፍትሕን ዕውን በማድረግ አንፃር ከፍተኛ ድክመት እንደሚታይባቸውና የፍትሕ አካላት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ኅብረተሰቡን በተገቢው ደረጃ እያገለገሉ እንዳልሆነና እየተዳከሙ እንደመጡ በግልጽ ተነግሯል፡፡ ይህ ድክመት ታምኖበትም ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ከትምህርት ቤት በመውጣት በሥራ ሳይፈተኑ በቀጥታ ወደ ዳኝነት መግባት እንዳለ፣ በዳኞች ላይ በስልክና በሌላ ዘዴ ጫና ማሳደር እንደሚታይ፣ ዳኛ ስለሆንኩ ማንም አያገባውም እየተባለ ከሕገ መንግሥቱ በላይ መሆን እንደሚታይ፣ በእነዚህ ምክንያቶች ለሙስናም መጋለጥ በስፋት መታየቱ በድፍረት ቀርቧል፡፡ በድፍረት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

 1.  የአባላት ምልመላ፣ የማኅበራትና የሊጎች አደረጃጀትና አሠራር ብዛት ላይ እንጂ ብቃት ላይ አለማተኮሩ

ኢሕአዴግ በርካታ አባላት ያውም በሚሊዮን የሚቆጠሩ መልምሏል፡፡ እየመለመለም ነው፡፡ በርካታ ማኅበራት፣ የወጣትና ሌሎች ሊጎችም እየተቋቋሙ ነው፡፡ ሀቀኛና ጠንካራ አባላትና ወጣቶች እየተመለመሉና እያገለገሉ ቢሆንም፣ በብዛት ደግሞ በብቃት ሳይሆን ለሹመትና ለሥራ ማግኛ የሚመለመሉ አባላትና የማኅበር አባላት የሚሆኑ እንዳሉም ጉባዔው ተወያይቶበታል፡፡ ይህም ትክክል ተብሎ ድክመት አለ ብሎም ጉባዔው ተቀብሎታል፡፡ በብቃት ላይ ከማተኮር ይልቅ በብዛት ላይ ማተኮር ከፍተኛ ድክመት እንደሆነ ተሰምሮበታል፡፡

 1. ተጠያቂነት እየጠፋ ነው

ከሕዝባዊነትና ከውስጥ ትግል መላላት፣ ከመልካም አስተዳደር መጥፋትና ከሙሰኝነት ጋር ተያይዞ የሚታየው ሌላው ከፍተኛ ድክመት ደግሞ፣ ተጠያቂነት እየጠፋ መምጣቱ እንደሆነ ጉባዔው በግልጽ አስቀምጧል፡፡ የሚያጠፉትንና በደል የሚያደርሱትን ከማጋለጥ፣ ከመቅጣትና ከማረም ይልቅ አንድ መሥሪያ ቤት ላይ ያጠፋውን ሌላ መሥሪያ ቤት ወስዶ መሾም እየታየ እንደሆነ በግልጽ ተነግሮ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በሥራና በውጤት ላይ ተመሥርቶ ሰውን ገምግሞ ጥሩ የሠራውን ማበረታታት፣ በተገቢው መንገድ ያልሠራውን አጥፊ ተጠያቂ ማድረግ እየቀረ በመምጣቱ ለምግባረ ብልሹነት ማበረታቻ ሆኗል ብሎ ጉባዔው በድፍረት ተቀብሎታል፡፡

 1.  የሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የብሔርተኝነት አክራሪነትም እየታየ ነው

ጎልቶ የሚሰማው የሃይማኖት አክራሪነት ይሁን እንጂ፣ የብሔር አክራሪነትም እንደሚንፀባረቅ በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ በውይይቱ ወቅትም በግልጽ ተነግሯል፡፡ ድክመት ነው ተብሎም በግልጽ ታምኖበታል፡፡ በትምክህተኝነትና በጠባብነት የሚገለጽ አክራሪነት እንደሆነም ጉባዔው ተወያይቶ ድክመቱን ተቀብሎታል፡፡

 1.  ሥልጠናዎች የተፈለገውን ውጤት እያመጡ አይደለም

ከታች እስከ ላይ ባሉ የአመራር አካላት የተለያዩ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ፡፡ ሥልጠና አስፈላጊ ቢሆንም አድርባይነት፣ ግለኝነት፣ ጠባብነት፣ ትምክህተኝነት፣ ቡድንተኝነት፣ ሙሰኝነት፣ ወዘተ እስካሉና ትግል እስካልተደረገ ድረስ ሥልጠና ሰውን አይለውጥም፣ አመራርን አያበቃም ተብሏል፡፡ ስለሆነም መሠረታዊ ለውጥ ላይ ትኩረት ሳይደረግ ጠንካራ፣ ቆራጥና ሕዝባዊ ትግልና ግምገማ ሳይካሄድ በሥልጠና ብቻ ብቁ አመራር እንደማይገኝ ጉባዔው ተወያይቶበታል፡፡ ጉድለት እንዳለም አምኖ ተቀብሎታል፡፡

 1.  መተካካት የሚባለው በተሟላ ሁኔታ እየተካሄደ አይደለም

መተካካት ምንጊዜም ያለና መኖር የሚገባው ነገር ቢሆንም፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ይህ ጅምር ተግባራዊ ቢደረግም በተሟላና በተፈለገው መንገድ ከብቃት ጋር እየተያያዘ እንዳልሆነ ታምኖበታል፡፡ አንዳንዱ መተካካት ከላይ ብቻ የሚደረግ እንጂ እታችም እንደማይደረግ፣ መተካካትን ለማሳካት ብቁ ኃይል እየፈጠሩና እያጠናከሩ መጓዝ እንደሚያስፈልግ መዘንጋቱ ተነግሯል፡፡ ጅምር ቢኖርም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጉባዔው አምኖ ተቀብሎታል፡፡ መተካካት ማለት ማስወገድ ሳይሆን፣ በተለየ መንገድና አሠራር ያለውን አቅም መጠቀም እንደሚያስፈልግም ታምኖበታል፡፡

 1.  በርካታ አዎንታዊ ኢኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገት ቢመዘገብም በዚህ ዙሪያም ድክመቶች አሉ

የጉባዔው ሪፖርትም ሆነ ውይይት ያተኮረው በዴሞክራሲ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በፍትሕ፣ ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ ጥቅሞች፣ ወዘተ ላይ ብቻ አልነበረም፡፡ አዎንታዊው እንዳለ ሆኖ በዚህ የልማትና የኢኮኖሚ ዕድገት ዙሪያም ያሉትን ድክመቶች፣ ጉድለቶችና ችግሮች በግልጽ አስቀምጧል፡፡

 1. የግብር አሰባሰብ ችግር አለ

አንዳንዱ ሪፖርት ከተጠበቀው በላይ ግብር ተሰበሰበ ቢልም፣ በትክክል ምን ያህል ለመሰብሰብ ተጠብቆ ነበር? ምን ያህሉስ ተሰበሰበ? የሚለው በግልጽ የሚታወቅ አለመሆኑ፣ ጥሩ አሠራር እንዳለ ሁሉ በዚህ ዙሪያም አላስፈላጊና ኪራይ ሰብሳቢነት የተላበሰ አካሄድም ይታያል ብሎ ጉባዔው አስቀምጧል፡፡ መንግሥት ማግኘት የሚገባውን እያገኘ አንዳልሆነና በዚህም መልካም አስተዳደር እንደሚጎድል ሰፍሯል፡፡ የግብር ሥርዓቱ ይሻሻል ተብሏል፡፡

 1. የአገልግሎት አቅርቦት ችግር አለ

የስልክ፣ የመብራት፣ የውኃና የትራንስፖርት አቅርቦቶችን ለማሳደግና የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ በርካታ ፕሮጀክቶች በበርካታ በጀት እየተገነቡ መሆናቸውና ለውጥም እየታየ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ ሆኖም ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም አሁንም የእነዚህ አገልግሎቶች አቅርቦት በሚመለከት ችግር እየታየ እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

 1. የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን በማስተናገድና በማበረታታት ላይ ድክመት ይታያል

የውጭ ኢንቨስትመንት ለማበረታታት ጥረት ቢደረግም፣ ነገር ግን አንዳንዱ የውጭ ኢንቨስተር ባልሆነ መስክ ሲገባና ሕግንና ሥርዓትን ሳያከብር ሲንቀሳቀስ መታየቱ፣ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስተር በተፈለገው ደረጃ ወደ ማኑፋክቸሪንግ እየገባ አለመሆኑ ተነስቷል፡፡ የውጭ ኢንቨስተር የሚሠራውን እየዘጉ ለአገር ውስጥ ብቻ ማለት እንደማይቻል፣ ነገር ግን ለውጭ ኢንቨስተር ሳይፈቀድ ለአገር ውስጥ ኢንቨስተር ብቻ የሚፈቀድ ዘርፍ መኖሩ ተገልጿል፡፡ እነዚህን ግልጽ እያደረጉና እያበረታቱ ኢንቨስትመንትን ማጠናከር ይበልጥ ጥረትና ግፊት የሚያስፈልገው እንደሆነ ጉባዔው በግልጽ ተወያይቶ አምኖበታል፡፡

 1.  የኤክስፖርትና የውጭ ምንዛሪ ችግር አለ

ጉባዔው በሪፖርቱም ሆነ በውይይቱ የኤክስፖርት ጥንካሬው እንደተፈለገው እንዳልሆነና የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ አለመሆኑን በግልጽ አስታውቋል፡፡ አንዱ ምክንያትም ለኤክስፖርት የሚሆን ምርት በተፈለገው ደረጃ አለመጨመሩ እንደሆነ ተቀምጧል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲከሰት ያደረገው አንዱ ይኸው ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን እየጎዳ እንደሆነ ተወስቷል፡፡ ሆኖም ከዚህ ጋር ተያይዞም በንግድ ዙሪያ ሪፎርም እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል፡፡

 1. በመንግሥት ሆነ በግል ቁጠባ መስፋፋት ቢኖርበትም ድክመት አለ

ከመጀመሪያውና ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር በተያያዘ ሌላው የተነሳው ትልቁ አጀንዳ የቁጠባ ጉዳይ ነበር፡፡ በአገሪቱ በርካታ ዓበይት ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ገንዘብ የለም ተብለው መዘጋትና መቋረጥ የለባቸውም፡፡ ግን ደግሞ በብድር ይካሄዱ ቢባል ብድሩ የሚያስፈልገው የዕዳ ክፍያና ወለድ ከፍተኛ ስለሆነ በከፍተኛ ደረጃ አገራዊ ቁጠባ መጀመርና ማሳካት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ ከውጭ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለመበደር 50 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ያስከፍላል፡፡ ከራስ ቁጠባ ከሆነ ግን አላስፈላጊ ክፍያ አይኖርም፡፡ ስለዚህ ኤክስፖርትን እያሳደጉና ቁጠባን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋት የግድ እንደሚልና አስተማማኝ መሆኑ ተቀምጧል፡፡

 1. የግብርናን ድክመት አርሞ ማሳደግ ያስፈልጋል

ግብርናው ዕድገት ቢያሳይም በጥናትና በምርምር ላይ ተመሥርቶ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ በጉባዔው ታምኖበታል፡፡ በግብርና ጥናትና ምርምር ላይ ድክመት እንዳለም ጉባዔው በግልጽ ተናግሯል፡፡ አንዳንድ የሚቀርቡ ሪፖርቶችም ጉድለት እንዳለባቸው በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ ከድህነት ለመላቀቅና ቀጣይ ዕድሎችን ለማሳካት በግብርና ላይ የሚታየውን ድክመት ማስወገድና ድርሻውን ማሳደግ ያስፈልጋል ተብሎ በግልጽ ታምኖበታል፡፡

12 . ለታዩት ድክመቶችና ጉድለቶች በዋነኛነት ተጠያቂው የበላይ አመራር ነው

ጉባዔው በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ መስኮች የሚስተዋሉትን ድክመቶች ሲመረምር ከላይ እስከ ታች፣ በከተማና በገጠር፣ በተለያዩ አደረጃጀቶች የሚታዩትን ድክመቶች ፈትሿል፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የአመራር አካላትና መዋቅሮች ተጠያቂዎች እንደሆኑም ተግባብቷል፡፡

ነገር ግን በግልጽና በድፍረት ዋነኛው ተጠያቂ የበላይ አመራር ነው ብሎ ጉባዔው በግልጽና በማያሻማ መንገድ አስፍሯል፡፡ ይህንም ለመሸፋፈን የተደረገ ሙከራ አልነበረም፡፡

ራሱ የበላይ አመራር አካል ማለትም ሥራ አስፈጻሚውና ማዕከላዊ ኮሚቴው ጭምር ዋነኛው ተጠያቂ ላይ ያለነው ነን ብሎ አምኖ ተቀብሏል፡፡ ከላይ ከተስተካከለ ታችም መስተካከል እንደሚቻል፣ ላይ ካልተስተካከለ ታቹ እንደማይስተካከል፣ ስለዚህ ያለምንም ሰበብ ዋነኛ ተጠያቂዎች ላይ ያለነው ነን ብሎ በግልጽ አምኗል፡፡ ጉባዔተኛውም አምኖ ተቀብሏል፡፡ የአመራር ችግሩ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

በዚህ ጉባዔ ላይ ከታዩት አዎንታዊ ነገሮች አንዱና ዋነኛውም የበላይ አመራሩ ራሱ ዋናው ተጠያቂ እኔው ነኝ ብሎ ማመኑ ነው፡፡ ይህ የተንፀባረቀው ደግሞ ከአራቱም ድርጅቶች ነው፡፡ “በየድርጅታችንም በኢሕአዴግም ያለው ችግር ከላይ ይጀምራል፤” ብለው ተቀብለውታል፡፡ በአራቱ ድርጅቶችም ልዩነት አልታየም፡፡ ሁሉም በአንድ አቋም በጋራ አመለካከት መቀበላቸው ለጉባዔው አዎንታዊ ሆኖለታል፡፡

ክፍል 2

ኢሕአዴግ ድክመቶቹን በቁርጠኝነት በተግባር የሚያርምበት የማጠቃለያና የመጨረሻ ወሳኝ ፈተና ይጠብቀዋል?

ኢሕአዴግ በ10ኛው ጉባዔው ቀደም ብሎ የተጠቀሱትን ዓበይት ድክመቶች የራሱ ስህተት እንደሆኑና ዋናው ተጠያቂውም የበላይ አመራሩ እንደሆነ ደፍሮ አምኖ ተቀብሏል፡፡

ስለዚህ ቀጣዩ ጥያቄ “አርማቸዋለሁ!” “አስተካክላቸዋለሁ!” የሚላቸውን ይመለከታል፡፡

ኢሕአዴግ ከልብ ካመነ፣ ካንጀት ካለቀሰ ድክመቶቹን ሊያርም የሚያስችሉት አመቺ ሁኔታዎች እንዳሉት ይታመናል፡፡ ሦስቱን ዓበይት አመቺ ሁኔታዎች እንዲህ ይገለጻሉ፡፡

ሀ. ድክመቶቹን አይቶ፣ አምኖ፣ ደፍሮና ፈቅዶ ተቀብሏል? በጉባዔው ወቅት ማንም አስገድዶትና ገፍቶት ሳይሆን ራሱ አምኖ ተቀብሎዋቸዋል፡፡ ተሳስቻለሁ ደክሜያለሁ ብቻ ሳይሆን ያለው፣ በ2007 ዓ.ም. ምርጫ ሕዝብ አደራ ስለሰጠኝ ካላስተካከልኩ ግን ሕዝብም አይቀበለኝም ብሏል፡፡ በግልጽ ተናግሯል፡፡ ይህ ራሱን ለማስተካከል ጥሩ መነሻና ድጋፍ ይሆነዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡

ለ.  ጥሩ አመራር ካገኘ የሚደግፍና ከጎኑ የሚሠለፍ ጠንካራ ሕዝብ መኖሩን ተቀብሏል፡፡ ይህን እንዳላደርግ ሕዝብ አደናቀፈኝ፣ ሕዝብ አልደገፈኝም የሚል ምክንያት ኢሕአዴግ ማቅረብ እንደማይችልም እንዲሁ፡፡ ኢሕአዴግ ራሱን ለማስተካከል ዝግጁ ከሆነና ሕዝባዊ አገልጋይነቱንና ታማኝነቱን ካረጋገጠ የሕዝብ ድጋፍ በእርግጠኝነት እንደሚያገኝ፣ ለዚህ ዝግጁ የሆነ ሕዝብ መኖሩም ሌላው አመቺ ሁኔታ መሆኑ ግንዛቤ ተይዟል፡፡

ሐ. ሊያደናቅፈው የሚችል ብቃት ያለው ተቃዋሚ ፓርቲ ወይም ተቃዋሚ ኃይል እንደሌለ፣ በእርግጥ በርካታ ተቃዋሚ ድርጅቶች እንዳሉ ነገር ግን በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ የሚታገሉት ኢሕአዴግ ይበልጥ ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ከሆነና መልካም አስተዳደር ካመጣ ለአገር የሚጠቅሙ እንጂ የሚጎዱ እንዳልሆኑ እሳቤ አለ፡፡ በሰላማዊና በሕጋዊ ትግል የማያምኑት ደግሞ ዋናው ክህሎታቸው ራሳቸውን ማደናቀፍና ከሕዝብ መገንጠል እንጂ ኢሕአዴግን ማደናቀፍ እንዳልሆኑ፣ ስለዚህም ኢሕአዴግ በእነሱ ሊያሳብብ እንደማይችል ይታሰባል፡፡

በመሆኑም ኢሕአዴግ ስህተቶቹን አርሞ ሕዝባዊ፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሐዊ፣ ቆራጥና የልማት ኃይል ሆኖ መምራት ከፈለገ ምርጫው የራሱ በመሆኑ በሌላ ሊያሳብብ እንደማይችል፣ ስለሆነም ኢሕአዴግ ወሳኝ የፈተና ወቅት ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የተግባራዊነት ፈተና አለበት፡፡ ለዚህም ተግባር! ተግባር! ተግባር ብቻ!! እያለ ሕዝብ እየጠበቀ እንዳለ ከጉባዔው መንፈስ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ይኼ የመጨረሻ ፈተና ነው፡፡ የማጠቃለያ ፈተና ነው፡፡ ወሳኝ ፈተና ነው፡፡ ይህንን የተግባር ፈተና ማለፍና መዝለቅ ከፈለገ ኢሕአዴግ ማከናወን ካለበት ተግባሮች መካከል ዋነኛዎቹ የሚከተሉትን እንደሚያካትት ይታሰባል፡፡

 1. በራሱ በኢሕአዴግ ውስጥ ለውጥ የማይፈልጉ፣ ሙስና፣ ግለኝነት፣ አክራሪነት፣ ምግባረ ብልሹነት እንዲጠፋ የማይፈልጉ፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ እንዲኖር የማይፈልጉ፣ ጥራትና ግምገማ እንዳይኖር የሚፈልጉና በፅናት የሚታገሉ እንዳሉ ማመን

በኢሕአዴግ ውስጥም ሆኑ በአራቱም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ያሉት አባላት በሙሉ አንድ ዓይነት አይደሉም፡፡ ሀቀኞች እንዳሉ አስመሳዮች አሉ፣ ቅኖች እንዳሉ ምላጮች አሉ፣ ሕዝባዊ እንዳሉ ፀረ ሕዝቦች አሉ፣ የሚለው ድምዳሜ ብዙዎችን ያስማማል፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ ራሱን ለማስተካከል በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ከውስጥ እንቅፋት እንደሚያጋጥመው ከወዲሁ አውቆና አምኖ መታገል እንዳለበት እንዲሁ ስምምነት አለ፡፡ የተደራጀ የውስጥ ተቃውሞ ደግሞ ካስፈለገም ከጠላት ጋር ሊያብርበት እንደሚችል ከወዲሁ ኢሕአዴግ ማወቅ እንደሚኖርበት የሚያሳስቡም አሉ፡፡ ይህ ቀላል ትግል እንደማይሆን፣ ቆራጥነትና መስዋዕትነት የሚጠይቅ ትግል በመሆኑ እጋለጣለሁ፣ እከሰሳለሁ፣ እታሰራለሁ ብሎ የሚፈራው ኃይልም ከውስጥ ስላለ ይህ ትግል የሞት ሽረት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡

 1. ሕዝብን ከጎን ማሠለፍ

በዚህ ወሳኝና የሞት ሽረት ትግል ውስጥ ሕዝባዊ ተሳትፎ የግድ ማለቱ፣ ሕዝብን የማሳተፍ አስፈላጊነት፣ ሕዝባዊ ድጋፍ ሲባልም የተለመደው “ተደነቀ”፣  “ተወደሰ” የሚሉ የቃላት ድጋፍና መግለጫዎች እንዳልሆኑ፣ ይህ ትግል ከተሳካና ድክመቶች ከተወገዱ ሕዝብ ፍትሕ አገኛለሁ፣ የመልካም አስተዳደር ባለቤት እሆናለሁ፣ ልማቴና ሰላሜ የተረጋገጠ ይሆናል፣ ከድህነት እላቀቃለሁ ብሎ ከልብ አምኖ ከልብ የሚሳተፍበት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይኖራል ተብሎ ተስፋ ተጥሏል፡፡ በተግባር የሚታይ መሆን አለበት በማለት፡፡ ሕዝብ በተግባር የሚሳተፍበትና የሚያጣጥመው መሆን ስላለበት ካለሕዝብ ድጋፍ የሚገኝ ድል ድል አለመኖሩም ይወሳል፡፡

 1. “ቲንክ ታንክ” ኃይሎች መፍጠርና ማሳተፍ

ኢሕአዴግ ድክመቶቹን  አስወግዶ የሕዝብ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ለመፍታት ፍላጎት፣ እምነትና ቆራጥነት ካለው ይህን እውን ለማድረግ የሚያግዙ ባለሙያዎች ከጎኑ ማሠለፍ እንደሚያስፈልገው ከበፊት ጀምሮ ሲነገረው ነበር፡፡

የኢኮኖሚ ችግሩን እንዴት እንደሚፈታ፣ የግብርናውን፣ የኢንዱስትሪውን፣ ኢነርጂውን፣ የቴሌውን፣ የውኃም መሰል ችግሮች እንዴት እንደሚፈቱ የሚያማክሩ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ፣ ዕውቀትም የአገር ፍቅርም ያላቸው መኖራቸው፣ የፖለቲካውን ችግር፣ የሚዲያውን ችግር፣ የጤናን ችግር፣ የትምህርትን ችግር በሚመለከት የሚያማክሩም አሉ፡፡ እነዚህን በየዘርፉ እየለዩና እየመረጡ፣ እያደራጁና እያበረታቱ ሙያዊ ምክር እንዲሰጡና አገራዊ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ማድረግ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡ “ካድሬ ካለ ሁሉም አለ” ብሎ ማጠቃለሉ ትክክል እንዳልሆነ ጭምር ተገልጿል፡፡

 1. ሚዲያውን ማበረታታት፣ ማጠናከር፣ ማሳተፍና ድርሻውን እንዲጫወት ማድረግ

መረጃ የሌለው ሕዝብ መሳተፍ አይችልም፡፡ ወሳኝ የሕዝብ ሚና ዕውን የሚሆነው በጉዳዩ ላይ ሕዝብ መረጃ ሲኖረው ነው፡፡ ሕዝብ መረጃ የሚያገኘው ከሚዲያ ነው፡፡ ሚዲያው ነፃና ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ እንዲሠራ በር መክፈትና ማበረታታት አስፈላጊነት የወቅቱ ዓቢይ ጥያቄ ሆኗል፡፡ የግሉንም የመንግሥትንም ሳይለዩ ራሱ ሚዲያው መረጃ አባዝቶ ለሕዝብ መረጃ እንዲያስተላልፍ ማድረግ፣ ማበረታታና ማጠናከር መደገፍ ኢሕአዴግ ከሚጠብቁት ተግባራዊ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ሆኗል፡፡

 1. ድክመቶች በአንዴ ባይፈቱም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከአሁኑ ማሳየት

ግምገማዎች የተድበሰበሱ፣ የውስጥ ዴሞክራሲን የማያሳዩ፣ ተጠያቂነት የማያስከትሉ እንደነበሩ ተተችቷል፡፡ አሁን ግልጽ፣ ደፋር፣ ጥፋተኛን ተጠያቂ የሚያደርግና መልካሙን የሚያመሰግን ወሳኝ ግምገማ ይጀመር እየተባለ ነው፡፡ በዝርዝር የተቀመጡ ድክመቶች ላይ ትግል እንዲጀመር፣ ለምሳሌ ሕዝብን አለመስማት፣ በስብሰባ በሥራ እያመካኙ በር መዝጋት ይብቃ እየተባለ ነው፡፡ አሁን ሕዝብን ማስተናገድና በር ክፍት ማድረግ ይጀመር፡፡ ይታይ የሚለው ብርቱ ጥሪ ሆኗል፡፡

በዳኞች አመዳደብ፣ በአቃቤ ሕግ አሠራር፣ በፀረ ሙስና ትግል ከወዲሁ ብቁና ንቁ ኃይል እየተመደበ እንቅስቃሴው ይጀምር ይቀጥል የሚለው የሕዝብ ድምፅ ነው፡፡

ኢሕአዴግ በድክመት የተቀመጡትን እያስወገደ ትክክለኛ አሠራር የሆነውን በተግባር በቆራጥነትና በድፍረት ከሕዝብ ጋር ሆኖ ሥራ ላይ ማዋል መጀመር የግድ እንደሚለው፣ ይህንን የማይፈልጉና የሚያደናቅፉ እየጋለጡ በጠንካሮች መተካት እንዳለባቸው የብዙዎች እምነት ነው፡፡

 1. የተቋማትና የሥርዓት ግንባታ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል

በኢትዮጵያ ያለው አንዱና ትልቁ ችግርና ድክመት ተቋማትን አለመገንባትና ሥርዓት አለመፍጠር መሆኑ ይወሳል፡፡ መሥሪያ ቤቶች አለቆቻቸውን ነው የሚመስሉት ይባላል፡፡ አለቆቹ መሥሪያ ቤቶቹን መምሰልና ማንፀባረቅ አለባቸው እንጂ፣ መሥሪያ ቤቶቹ ግለሰቦቹን መምሰል የለባቸውም የሚል ትችት አለ፡፡ አቶ እከሌም ይምጣ ወ/ሮ እከሊት ተቋማት ተቋማትን መምሰል እንዳለባቸው፣ ሰዎች ሲቀያይሩ የሚቀያየሩ ተቋማት መሆን እንደሌለባቸው፣ ሰዎች ሲቀያየሩ አሠራራቸውና ሥርዓታቸው የሚቀያየር መሆን እንደሌለበት በተደጋጋሚ መወሳቱ ይታወሳል፡፡

የኢሕአዴግ ዋነኛውና ትልቁ ችግር ጠንካራ ተቋማትን አልፈጠረም፣ ግለሰቦች የሚያሽከረክሩዋቸው መሥሪያ ቤቶች ናቸው ያሉት ይባላል፡፡ ግለሰቦቹ ወይም አለቆቹ እንደፈለጉ ያጠቧቸዋል፣ ያሰፏቸዋል፣ ይኮረኩሟቸዋል፣ ካልተስማማቸው ያፈርሷቸዋል፣ ከእነሱ በኋላም እንዲቀየሩና እንዲሻሻሉ አይፈልጉም የሚሉ ስሞታዎች ይቀርባሉ፡፡ በአጭሩ ጫማን ከእግር ጋር ከማስማማት ይልቅ ከጫማ ጋር እንዲስማማ ተብሎ እግር ሲከረከም እየታየ ነው የሚባለው ጎልቶ ይሰማል፡፡

ስለዚህ ለተቋማት ግንባታ በጣም ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ፣ ሁሉም ሥራ በሥርዓት እንዲከናወን፣ የታክስ ሥርዓቱ፣ የኢንቨስትመንት ሥርዓቱ፣ የንግድ ሥርዓቱ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ፣ ወዘተ አስፈላጊነት አፅንኦት ይሰጠዋል፡፡ ሁሉም የሥራ መስክ በአስተማማኝ ተቋም የሚሠራ እንዲሆን፣ ገጠመኝ ሳይሆን ሥርዓት ይኑር እየተባለ ነው፡፡ ተቋማቱ አሠሪዎቻቸውን ይፈትሹ፣ ይመርምሩ፣ ያሻሽሉ፣ ይቀየሩ፣ ያጠናከሩ ነው ጥያቄው፡፡

ነገሮች ከተበላሹ በኋላ ከመጮህ ከመጀመሪያው የሚቆጣጠሩ፣ ተጠያቂ የሚያደርጉ፣ ሥራን የሚከታተሉ፣ ለመንግሥትም ለሕዝብም ለፓርላማም የሚያሳውቁ አካላት በየደረጃው የመፍጠር አስፈላጊነት ትኩረት እንዲሰጠው ተጠይቋል፡፡ ከውጭ ለመማር ጥናትና ምርምር ይካሄድ በማለት ጭምር፡፡

በአጠቃላይ ኢሕአዴግ አሁን ድክመቶቹንና ጉድለቶቹን ከማየት አንፃር ሲመዘን አመራሩን በሚገባ አይቷል፣ ራሱን ፈትሿል፣ ድክመቱን ተቀብሏል ተብሏል፡፡ ተጠያቂ ነኝ ማለት ብቻ ሳይሆን ዋናው ተጠያቂ የበላይ አካል የሆነው ጠያቂ ሕዝብ እንደሆነ አምኗል፡፡

በቃል ብቻ ተናግሮ በተግባር አለማሳየት ሕዝብን አለማክበርና ራስንም ለአደጋ ማጋለጥ ስለሆነ ኢሕአዴግ ይህን አይቶና አስተውሎ ለለውጥ፣ ለሕዝባዊነት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለፍትሕ፣ ለተሻለ ልማትና ከድህነት የተላቀቀች የተከበረች አኩሪ አገር ለመፍጠር ይንቀሳቀስ ተብሏል፡፡ ተቃዋሚዎችም የራስን ድክመትን ለማየት ከዚህ ልምድ ይማሩ እየተባለ ነው፡፡

ሕዝብ ድጋፍ መስጠት ብቻ ሳይሆን ኢሕአዴግ ግዳጁን ካልተወጣ ዝም እንደማይለው፣ “ጨው ለራስህ ብለህ ጣፍጥ አለበለዚያ ድንጋይ ነህ ብለው ይጥሉሃል” እንደሚባል መዘንጋት እንደሌለበት የሚያሳስቡ አሉ፡፡   

ለእርምትና ለህዳሴ ሕዝብን ለማገልገልና አገርን ለማሻሻል ኢሕአዴግ ከልብ የሚንቀሳቀስ ከሆነም “መንገድህን ጨርቅ ያድርግልህ” እንደሚባል፣ ውጤቱን ግን በቃላት ሳይሆን በተግባር ማየት ያስፈልጋል የሚለው ሕዝብ ነው፡፡ ይህንንም ማሳሰቢያ ሕዝብ ተግባር! ተግባር! አሁንም ተግባር! እያለ ነው፡፡

           

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -