Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሰመጉ በልማት ስም ዜጐችን ማፈናቀል እንዲቆም ጠየቀ

ሰመጉ በልማት ስም ዜጐችን ማፈናቀል እንዲቆም ጠየቀ

ቀን:

በአፋር ክልል የአሳይታና የአፋምቦ ወረዳዎች ነዋሪዎች በልማት ስም በተለያዩ አካባቢዎች መሬታቸውን እንዲለቁ በመደረጉ ከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን፣ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) አስታወቀ፡፡ በልማት ስም ዜጎች መፈናቀል የለባቸውም ብሏል፡፡

ሰመጉ ይህን ያስታወቀው ነሐሴ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ‹‹በልማት ስም በዜጐች ላይ የሚፈጸም ማፈናቀልና ንብረት ማውደም በአስቸኳይ ይቁም›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫው ነው፡፡

ጉባዔው በክልሉ ተፈጸሙ ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በዝርዝር ያቀረበ ሲሆን፣ የዜጐች ከቤት ንብረት መፈናቀል ዋናው ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ በተጨማሪ ‹‹በክልሉ ዞን አንድ አሳይታ ወረዳ በዋሙሌ ቀበሌ ኩሰራሌና ዋሪ አይቶ በሚባሉ ጣቢያዎች ውስጥ ተተክለው የነበሩ የቴምር ዛፎች ከሕዝብ ጋር ምክክር ሳይደረግ፣ ያለ ማስጠንቀቂያና ምንም ዓይነት ካሳ ሳይከፈል በግሬደር መጨፍጨፋቸው ሕገወጥ ድርጊት ነው፤›› በማለት ተቃውሞውን ገልጿል፡፡

በወረዳው የተጨፈጨፈው የቴምር ዛፍ ብዛት 8,527 እንደሆነ፣ ተጐጂዎቹም ምንም ዓይነት የካሳ ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው በሥፍራው የተገኙ የሰመጉ ባለሙያዎች አረጋግጠዋል በማለት በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መግለጫው ተጐጂዎቹ ስለደረሰባቸው ጉዳት ለፌደራልና ለክልሉ መንግሥት፣ እንዲሁም ሌሎች ተቋማት እንዳመለከቱ የገለጹ ቢሆንም፣ ችግሩን የሚፈታ አካል እንዳልተገኘ አመልክቷል፡፡ የፌደራልና የክልሉን መንግሥታት ለጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጡም ጠይቋል፡፡

ስለጉዳዩ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ወርቄ ሲመልሱ፣ ‹‹በልማት የሚነሱ ከሆነ ሙሉ ካሳ ተከፍሎ ነው የሚነሱት፡፡ ያፈሩት ቋሚ ሀብት ካለም ሙሉ ሀብቱ ተገምቶና ተሰጥቶ ነው የሚነሱት፡፡ ነገር ግን አሁን በሥፍራው በልማት የተነሳም ሆነ የተፈናቀለ ሰው እንደሌለ በሥፍራው የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸውልኛል፡፡ ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም የቀረበ ጥያቄ የለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እንዲህ ያለ ነገር ሊፈጸም አይችልም፡፡ በልማት የሚነሱ ካሉ መጀመርያ ተጠንቶ ለሕዝቡ አገልግሎት የሚውል ከሆነ የሰፈሩበትና ቋሚ ሀብት ያፈሩበት ሙሉ ካሳው ተከፍሎና ምትክ ተሰጥቶ ነው የሚከናወነው እንጂ፣ እንዲሁ ለልማት ተብሎ ሊነሱ አይችሉም፤›› በማለት አቶ አበበ አክለው አብራርተዋል፡፡

ምንም እንኳን አቶ አበበ ይህን ቢሉም ሰመጉ የመብት ጥሰቱ የተፈጸመው በልማት ስም ነው በማለት ከመውቀስ ባሻገር፣ የተሰጠ ምንም ዓይነት የካሳ ክፍያ እንደሌለ በመግለጽ፣ ‹‹ከሕግ ውጪ የቴምር ዛፋቸው ለወደመባቸው የአፋር ከፊል አርብቶ አደሮችና ከፊል አርሶ አደሮች ተገቢው ካሳ ይከፈል፤›› በማለት ጥያቄውን ለመንግሥት አቅርቧል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) የዛሬው የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) የተቋቋመው በ1984 ዓ.ም. ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲዳብር፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍንና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...