ሊቢያ ኦይል ሊሚትድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ኢንቨስትመንትና የነዳጅ ንግድ ሥራ ለማስፋፋት መወሰኑን አስታወቀ፡፡
ዱባይ ከሚገኘው የሊቢያ ኦይል ሆልዲንግ ዋና መሥሪያ ቤት ወደ አዲስ አበባ የመጣው ኮርፖሬት ማኔጅመንት፣ ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል የአንድ ሳምንት ጉባዔ አካሂዷል፡፡ ከ18 የአፍሪካ አገሮች የሊቢያ ኦይል ሥራ አስኪያጆች በስብሰባው ላይ ተሳትፈዋል፡፡
የሊቢያ ኦይል ኢትዮጵያ የሽያጭና ማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘካሪያስ ወሊቃ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ማኔጅመንቱ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት በመገምገም ኩባንያው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ኢንቨስትመንትና የነዳጅ ንግድ እንቅስቃሴ ለማስፋፋት ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የኩባንያው ባለአክሲዮኖች ካፀደቁት ኢትዮጵያ ውስጥ የ150 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ለማካሄድ አቅዷል፡፡
ኩባንያው በ124 ሚሊዮን ብር የሞተር ዘይቶችና ቅባቶች ማምረቻ ለማቋቋም፣ የቡታ ጋዝ ማከፋፈል ሥራ ለመጀመር፣ የሬንጅ አቅርቦት ሥራውን ለማሳደግና የኢንዱስትሪ ኬሚካሎች ለማቅረብ ማቀዱንም ገልጸዋል፡፡
ሊቢያ ኦይል በአውሮፕላን ነዳጅ አቅርቦት ላይ በስፋት እየሠራ እንደሆነ አቶ ዘካሪያስ ተናግረዋል፡፡ በአውሮፕላን ነዳጅ ገበያ የ42 በመቶ የገበያ ድርሻ እንዳለው ጠቁመው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ለ30 ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ አየር መንገዶች የአውሮፕላን ነዳጅ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡
ኩባንያው በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚገኘውን የአውሮፕላን ነዳጅ ዴፖ ማስፋፋቱን፣ አምስት ዘመናዊ የአውሮፕላን ነዳጅ መሙያ ማሽኖች ገዝቶ ጥቅም ላይ ማዋሉን ተናግረዋል፡፡
ሊቢያ ኦይል ለቀለምና ፕላስቲክ ፋብሪካዎች በግብዓትነት የሚያገለግሉ ኬሚካሎች ለማቅረብ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ‹‹ለጊዜው ኬሚካሎቹን ከውጭ በማስገባት የምናከፋፍል ሲሆን፣ በሒደት አገር ውስጥ የማምረት ዕቅድ አለን፤›› ብለዋል አቶ ዘካሪያስ፡፡
ሊቢያ ኦይል ከኢትዮጵያ የተሰናበተውን ሼል ኢትዮጵያ ሊሚትድ በመግዛት የኢትዮጵያን የነዳጅ ገበያ የተቀላቀለው በ2000 ዓ.ም. ነበር፡፡ ኩባንያው ኢትዮጵያ ውስጥ 143 የነዳጅ ማደያዎች ሲኖሩት፣ 24 በመቶ የገበያ ድርሻ አለው፡፡ ኩባንያው በየዓመቱ ዘጠኝ ማደያዎች በመክፈት እ.ኤ.አ. በ2020 የነዳጅ ማደያዎቹን ቁጥር 185 ለማድረስ፣ የገበያ ድርሻውን ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ አቅዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኩባንያው ዓመታዊ ሽያጭ 13 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል፡፡
ሊቢያ ኦይል 50 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የአቪዬሽን ነዳጅ ዲፖ ማስፋፊያና በአዲስ አበባ ጎተራ አካባቢ በሚገኘው የነዳጅ ዲፖ የኤታኖል ማደባለቂያ ገንብቷል፡፡ ኩባንያው እስከዛሬ እንደ አዲስ የገነባቸው ስምንት የነዳጅ ኩባንያዎችን ብቻ ነው፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ለግንባታ የሚሆን ቦታ የማግኘት ችግር በመኖሩ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዘካሪያስ፣ ከሼል ኩባንያ ግዢ ጋር የተፈጠረው የታክስ ክርክር የኩባንያውን ዕድገት እንደጎተተው ያስረዳሉ፡፡ የታክስ ክርክሩ እልባት ያገኘ በመሆኑ ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለውን ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት ቆርጦ መነሳቱን አስታውቋል፡፡
ሊቢያ ኦይል ባለፈው ሐሙስ ነሐሴ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ አዳዲስ የሞተር ዘይትና ቅባቶችን አስተዋውቋል፡፡ የላቀ አፈጻጸም ላሳዩ የሊቢያ ኦይል የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች፣ የሊቢያ ኦይል ምርቶች አከፋፋዮችና የትራንስፖርት ኩባንያዎች የሊቢያ ኦይል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሙስባሕ ኤልቤሽቲ ሽልማቶች አበርክተዋል፡፡ ሚስተር ኤልቤሽቲ ባደረጉት ንግግር፣ ሊቢያ ኦይል ለአፍሪካ ልዩ ትኩረት በመስጠት በመሥራት ላይ መሆኑን ገልጸው፣ በኢነርጂ መስክ አፍሪካ ውስጥ አስተማማኝ አጋር ሆኖ መሥራት እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ሊቢያ ኦይል በ18 የአፍሪካ አሮች 1,015 የነዳጅ ማደያዎች አሉት፡፡ ሊቢያ ኦይል ሆልዲንግ በሊቢያ ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን እ.ኤ.አ. በ2004 የተመሠረተ ኩባንያ ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ያሉትን ቢዝነስ የገዛው ከሼልና ከኤክሶን ሞቢል ኩባንያዎች ነው፡፡
በቅርቡ ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) ሊቢያ ኦይል ጂቡቲን በ450 ሚሊዮን ብር መግዛቱን አስታውቋል፡፡ ሊቢያ ኦይል የጂቡቲ ንብረቱን አለመሸጡንና ኖክ ኩባንያውን የገዛው ከጂቡቲ መንግሥት እንደሆነ አስረድቷል፡፡ ሊቢያ ኦይል ወደ ጂቡቲ ከመግባቱ ከብዙ ዓመታት በፊት በተፈጠረ የባህር ውኃ ብክለት ምክንያት የጂቡቲ መንግሥት ከፍተኛ የካሳ ክፍያ በመጠየቁ በተፈጠረ አለመግባባት፣ የጂቡቲ መንግሥት የኦይል ሊቢያ ጂቡቲና የቶታል ጂቡቲ ንብረቶችን ወርሷል፡፡ የጂቡቲ መንግሥት የሊቢያ ኦይልና የቶታል ንብረቶችን ለሽያጭ አቅርቦ ሊቢያ ኦይል ጂቡቲን ኖክ፣ ቶታልን ደግሞ አንድ የፈረንሣይ ኩባንያ መግዛታቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡