በቁርጥራጭ ብረትና ያገለገሉ ማሽኖች ንግድ የተሰማራው ሳርፌ ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የግንባታ ብረታ ብረቶች ማምረቻ ፋብሪካ በዱከም ከተማ ለመገንባት በዝግጅት ላይ እንደሆነ አስታወቀ፡፡
የሳርፌ ቢዝነስ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክብርይስፋ ተክሌ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኩባንያው እስካሁን ቁርጥራጭ ብረቶች ከውጭ በማስመጣትና ከአገር ውስጥ በመግዛት ለብረት አቅላጮች ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ የቤት መኪኖች ከውጭ በማስገባት አገር ውስጥ የሚሸጥ ሲሆን፣ ያገለገሉ ማሽኖች ግዢና ሽያጭ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገትና ፈጣን የግንባታ ኢንዱስትሪ መስፋፋት በመመልከት ሳርፌ ቢዝነስ የብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ለመገንባት መወሰኑን አቶ ክብርይስፋ ተናግረዋል፡፡ ‹‹መንግሥት በአሁኑ ወቅት ባለሀብቱ ከንግድ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገባ በማበረታታት ላይ ይገኛል፡፡ እኛም ይህን የመንግሥት ፖሊሲን በመከተል ዘመናዊ የብረታ ብረት ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት ወስነናል፤›› ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ክብርይስፋ ገለጻ ሳርፌ ቢዝነስ የሚገነባው ፋብሪካ ቁርጥራጭ ብረቶችን በማቅለጥ የተለያዩ መጠን ያላቸው ፌሮ ብረቶችን የሚያመርት ነው፡፡ ፋብሪካው በቀን ከ160 እስከ 200 ቶን ፌሮ ብረት የማምረት አቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡
የብረት ማቅለጫው ማሽኖች ከህንድ ተገዝተው የሚመጡ ሲሆን፣ የብረት መዋቅሩ ደግሞ ከቻይና ይገዛል፡፡ የፋብሪካው ጠቅላላ የኢንቨስትመንት ወጪ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት የተናገሩት አቶ ክብርይስፋ፣ ፋብሪካው ለ300 ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
ሳርፌ ቢዝነስ ለብረት ፋብሪካው ግንባታ የሚሆን 30,000 ካሬ ሜትር ቦታ በሊዝ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከዱከም ከተማ አስተዳደር በቅርቡ መረከቡን ገልጸው፣ ኩባንያቸው ተገቢውን የአዋጭነት ጥናት ማሠራቱን አስረድተዋል፡፡
የፋብሪካው ግንባታ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሮጀክቱን በገንዘብ እንዲደግፍ የብድር ጥያቄ ለባንኩ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹በአገር ውስጥ ሠርተን ባገኘነው ገንዘብ አገራችን ውስጥ ኢንቨስት አድርገን ለወገኖቻችን የሥራ ዕድል የመፍጠር ከፍተኛ ጉጉት አለን፤›› የሚሉት አቶ ክብርይስፋ፣ መንግሥት ለሥራቸው መቃናት እያደረገላቸው ላለው ድጋፍ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ሳርፌ ቢዝነስ በ2003 ዓ.ም. በሦስት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች (አቶ ክብርይስፋ ተክሌ፣ አቶ በደይ ነጋሽና አቶ ባህሩ ወልደ ትንሳይ) በ500,000 ብር ካፒታል የተመሠረተ መሆኑን፣ በዋነኝነት በብረታ ብረት ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ የግል ኩባንያ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡