Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኪንግናም ከኢትዮጵያ የመውጣት ዕቅድ እንደሌለው ገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኪንግናም ኢንተርፕራይዝስ የተሰኘው ግዙፍ የደቡብ ኮሪያ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከኢትዮጵያ ገበያ የመውጣት ዕቅድ እንደሌለው አስታወቀ፡፡

ኪንግናም በደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ የሙስና ክስ ከተመሠረተበት በኋላ የኩባንያው ሊቀመንበር ራሳቸውን ያጠፉ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ ኩባንያው ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቋል፡፡

የኪንግናም ኢትዮጵያ ቢሮ ረዳት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተመስገን በቀለ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኩባንያው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ማሽኖችና ተሽከርካሪዎች ሸጦ ሊወጣ እንደሆነ ተደርጎ የሚሠራጨው መረጃ ስህተት ነው፡፡ ኩባንያው ማሽነሪዎቹንና ተሽከርካሪዎችን እየሸጠ ያለው ሲያካሂዳቸው የነበሩትን ስድስት ያህል የመንገድ ፕሮጀክቶችን በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቁ እንጂ፣ ከኢትዮጵያ ለመውጣት በማሰብ እንዳልሆነ አቶ ተመስገን ገልጸዋል፡፡

‹‹ማሽነሪዎቹ እ.ኤ.አ. በ2007 በጊዜያዊ የጉምሩክ ቦንድ የገቡ ናቸው፡፡ የቦንዱ ዕድሜ ሊጠናቀቅ ስለሆነ ተገቢውን የጉምሩክ ቀረጥና ግብር ከፍለን ማሽኖቹን መሸጥ አለብን፡፡ ማሽኖቹ እየተሸጡ ያሉት በዚህ ምክንያት ነው እንጂ እንደተባለው ከኢትዮጵያ ለቆ ለመውጣት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ኪንግናም ኢንተርፕራይዝስ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ስለገጠመው አበዳሪዎች 913 ሚሊዮን ዶላር ብድር እንዲከፍላቸው እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡ የኩባንያው ኃላፊዎች እንደተናገሩት፣ ኩባንያው ያለበትን የገንዘብ ችግር በመቅረፍ ህልውናውን ለመታደግ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ የኪንግናም ማኔጅመንት በቬትናም የሚገኘውን ባለ 72 ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ በመሸጥ የኩባንያውን ብድሮች ከፍሎ፣ ኩባንያውን እንደ አዲስ ለማንቀሳቀስ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኪንግናም ማሽነሪዎቹን ሳርፌ ቢዝነስ የተባለ ኩባንያ በሽያጭ ወኪልነት ቀጥሮ በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ ምንጮች ኩባንያው ማሽኖቹን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በመሸጥ ላይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ የኪንግናም ማኔጅመንትና የሳርፌ ቢዝነስ ኩባንያ ኃላፊዎች ውንጀላውን አስተባብለዋል፡፡

የሳርፌ ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክብርይስፋ ተክሌ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኩባንያቸው የሽያጭ ውክልናውን ያገኘው በሕጋዊ መንገድ ነው፡፡ ‹‹የሽያጭ ወኪል ለመቅጠር ኪንግናም በ2006 ዓ.ም. ያወጣውን ጨረታ ከአምስት ኩባንያዎች ጋር ተወዳድረን አሸናፊ ሆነናል፡፡ የጨረታ ሰነዶቹ የኪንግናም ዋና መሥሪያ ቤት ወደሚገኝበት ደቡብ ኮሪያ ሲኦል ተልኮ የኩባንያው ዋና ማኔጅመንት ነው ያፀደቀው፡፡ የኢትዮጵያ ኪንግናም ቢሮ በራሱ እንዲህ ዓይነት ከባድ ውሳኔ ማሳለፍ አይችልም፡፡ ዋና መሥሪያ ቤቱ ሳይፈቅድ አንድም ማሽን መሸጥ አይቻልም፤›› ብለዋል አቶ ክብርይስፋ፡፡

ጨረታውን ካሸነፉ በኋላ 305 ያህል ማሽኖችና ተሽከርካሪዎች ለመሸጥ ከኪንግናም ጋር ሕጋዊ ውል መፈረማቸውን የሚናገሩት አቶ ክብርይስፋ፣ በውሉ መሠረት ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚከፈል ገንዘብ ኩባንያቸው እንደሚያቀርብ፣ ተገቢው የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ተከፍሎ ማሽኖቹ ከተሸጡ በኋላ የከፈሉት ገንዘብ ለኩባንያቸው ተመላሽ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሁሉንም ነገር የምንሠራው የአገሪቱን ሕግ ተከትለን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ደንቦችና መመርያዎችን ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ በርካታ ተመሳሳይ ሥራዎች ሠርተናል፡፡ ይህ የመጀመሪያችን አይደለም፤›› የሚሉት አቶ ክብርይስፋ፣ እስካሁን ኩባንያቸው 45 የኪንግናም ማሽኖችና ተሽከርካሪዎች መሸጡንና ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ገቢ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ሳርፌ ቢዝነስ ከኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር በቅርበት እንደሚሠራ፣ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ኦቨር ድራፍት ብድር ባንኩ እንደሚሰጠው አቶ ክብርይስፋ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኪንግናም ሁለት አማራጮች አሉት፡፡ አንዱ ማሽኖቹን አገር ውስጥ መሸጥ፣ ሁለተኛው አማራጭ ወደ ውጭ መላክ ነው፡፡ አገር ውስጥ የሚሸጥ ከሆነ ኪንግናም መቶ በመቶ ቀረጥ ይከፍላል፡፡ ወደ ውጭ ከላከው ግን የሚከፍለው ቀረጥ አምስት በመቶ ብቻ ይሆናል፤›› ያሉት አቶ ክብርይስፋ፣ ማሽኖቹ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተሸጡ መንግሥት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሰበስብ፣ ይህም መንግሥት ለሚያካሂዳቸው የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ሊውል የሚችል ገንዘብ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ መንግሥት ተጠቃሚ የሚሆነው ማሽኖቹ በአገር ውስጥ ቢሸጡ እንደሆነ ገልጸው፣ ማሽኖቹን በሕጋዊ መንገድ በመግዛት ላይ የሚገኙት አገር በቀል ኮንትራክተሮችም እንደሚጠቀሙ አስረድተዋል፡፡

ኪንግናም ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ1989 ዓ.ም. ነው፡፡ የመጀመርያ ፕሮጀክቱም የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የአውሮፕላን ማኮብኮቢያ ግንባታ ሥራ ነበር፡፡ በመቀጠልም ሞጆ-አዋሽ-ገዋኔ፣ ሂርና-ቁልቢ፣ አዘዞ-ገነቴ-መተማ፣ ሆሳህና-ሶዶ፣ አላባ-ሁምቦ፣ አፖስቶ-ኢርባሙዳ፣ ጂማ-ቦንጋ-ሚዛን መንገዶችን ገንብቷል፡፡ የጂማ-ቦንጋ መንገድ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ የተመረቀ ሲሆን፣ የቦንጋ-ሚዛን መንገድ ሥራ 97 በመቶ ተጠናቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች