Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ትራንስፖርት ባለሥልጣን የበጀት ዓመቱ ዕቅድ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን አመነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹አገልግሎቱን ማሻሻል የሚቻለው የተቋሙ አደረጃጀት ሲሻሻል ነው›› ባለድርሻ አካላት

የትራንስፖርት ባለሥልጣን የ2007 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን ባቀረበው ሪፖርት አስታወቀ፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም እንደገለጹት፣ በበጀት ዓመቱ በርካታ ሥራዎች የተከናወኑ ቢሆንም አፈጻጸሙ አርኪ አልነበረም፡፡ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ጥረት ቢደረግም የአደጋውን መጠን መቀነስ አለመቻሉን፣ ሕገወጥ ሥምሪትና የሌሊት ጉዞ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አለመቻሉ፣ አፈጻጸሙ ዝቅ እንዲል ካደረጉት በርካታ ደካማ ጐኖች ጥቂቶቹ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በትራንፖርት ዘርፍ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን መቅረፍ አለመቻሉን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት ማኅበራት የደረጃ መሥፈርት፣ የአሽከርካሪ ማሠልጠኛና የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት በአገር አቀፍ ደረጃ በስታንዳርዱ መሠረት ተግባራዊ አለመደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

በርካታ ተግዳሮቶች ለገጠሙት የትራንስፖርት ዘርፍ በሕዝብና በጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የአፈጻጸም ችግሮችንና አመለካከቶችን ለመቅረፍ፣ የማሻሻያ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ለተቋሙ የውስጥና የውጭ ተገልጋዮች እርካታ ጥናት መካሄዱን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ የውጭ ተገልጋዮች እርካታ ከ63 በመቶ በላይ መሆኑን፣ የውስጥ ተገልጋዮች (ፈጻሚዎች እርካታ) 39 በመቶ መሆኑንና ዝቅተኛ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የአይቲ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ከመሆን አንፃር በ8181 በነፃ የስልክ መስመር በመደወል ኅብረተሰቡ የሚጠቀምበት ሥርዓት መዘርጋቱን አስረድተዋል፡፡ በርካታ ተግባራትን ያከናወነ ቢሆንም፣ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ የታየው አፈጻጸም ግን ዝቅተኛ መሆኑን በድጋሚ ተናግረዋል፡፡ አገልግሎቱን ለማሻሻል የተለያዩ ሥልጠናዎችና ግንዛቤ መፍጠሪያ መንገዶችን መጠቀማቸውን አክለዋል፡፡

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በተደረገው እንቅስቃሴ በበጀት ዓመቱ የትራፊክ መረጃ እንደሚያሳየው በ1,000 ተሽከርካሪዎች የነበረው የ64 ሰዎች ሞት ወደ 60 ዝቅ ብሎ መገኘቱን አቶ ካሳሁን በሪፖርታቸው አካተዋል፡፡ በአምስት ዓመቱ የትራንስፎርሜሽንና ዕድገት ፕሮግራም ወደ 27 ዝቅ ለማድረግ የታቀደ ቢሆንም አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

ባለድርሻ የሆኑት የጭነት ተሽከርካሪዎች ማኅበራት፣ የሕዝብ ማመላለሻ ማኅበራት፣ የተሽከርካሪ ብቃት ማሠልጠኛ ተቋማት፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች አስመጭዎች ሲሆኑ፣ አቶ ካሳሁን ባቀረቡት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

የጭነት ተሽከርካሪዎች ማኅበራት በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፣ የጎማና የመለዋወጫ ዋጋን በመቆጣጠር፣ የታሪፍ ዋጋ እንደሚሻሻል በ2006 በጀት ዓመት የተነገረ ቢሆንም ተግባራዊ አልሆነም፡፡ በጉምሩክና ዕቃዎችን ከማራገፍ ጋር በተገናኘ የዲመሬጅ ክፍያ ሕግ አልፀደቀም፡፡ ችግር ሲደርስባቸው ምላሽ አለመስጠት፣ በባህር ትራንዚትና መፈተሻ ጣቢያዎች ለቀናት እንዲቆሙ መደረጋቸውን፣ ሚዛን ላይ ከፍተኛ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዳለ አስረድተዋል፡፡ ባለሥልጣኑ በጂቡቲ ተርሚናል እንደሚያስገነባ በተደጋጋሚ የተገለጸ ቢሆንም፣ ላለፉት ሰባት ዓመታት ተግባራዊ አለመሆኑን የገለጹት ማኅበራቱ፣ በየቦታው ለማቆም መቸገራቸውንና አዳጋች እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡ መርከቦች ተደራርበው ሲገቡ በግዳጅ ሌላ ሥራ ትተው እንዲሄዱ መደረጉን የተቃወሙት ማኅበራቱ፣ ችግሩ መሥሪያ ቤቱ ዕቅድ አውጥቶ ባለመሥራቱና በሴክተሩ ካሉ ተቋማት ጋር ግንኙነት አለመፍጠር ያመጣው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጭነት ተሽከርካሪዎች ማኅበራት በርካታ ቅሬታዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ በጂቡቲ ያለው የድለላ ሥርዓት አለመወገዱ፣ በየኬላዎች ላይ መንገላታትና ሌሎችም በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹አገልግሎቱን ማሻሻል የሚቻለው የመሥሪያ ቤቱን አደረጃጀት ማሻሻል ሲቻል ነው፤›› የሚሉት የሕዝብ ትራንስፖርት ማኅበራት፣ በዓመቱ 100 ሺሕ ኪሎ ሜትር ለመሸፈን ታቅዶ የተሸፈነው 50 ሺሕ ኪሎ ሜትር መሆኑ እየታወቀ 103 ሺሕ ኪሎ ሜትር ነው መባሉ ሐሰት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመስመር ብዛት 62 መባሉንና ‘ፍራንቻይዝ’ የተደረጉ መስመሮች 38 መሆናቸው ቢገለጽም፣ አሥር እንደማይሞሉ ተናግረዋል፡፡ ችግሩን የሚያውቁ ዳይሬክቶሬቶች ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዳይሰጡ መደረጉን የተቃወሙት ማኅበራቱ፣ ዋና ዳይሬክተሩ ሁሉንም ያውቃሉ የሚል ግምት እንደሌላቸውና አግባብም አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከ25 ኪሎ ግራም በላይ የጫነ ተሳፋሪ ለዕቃው እንዲከፍል ዕቅድ የተያዘ ቢሆንም፣ በየመናኸሪያው ግን ዝም ብሎ የተጋነነ ክፍያ እንዳስከፈሉ በማስመሰል የሚጣልባቸውን ቅጣት ተቃውመዋል፡፡

መንግሥት ሕግን ሊያስከብር እንደሚገባ የሚናገሩት ማኅበራቱ፣ ሕገወጥ ሥምሪትና ሕገወጦች የሚሠሩት ተግባር ሌላ ነገር ሊያመጣ ስለሚችል አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡

የተሽከርካሪ አደጋ ሲደርስ ሁልጊዜ የሚወቀሰው አሽከርካሪው ብቻ መሆኑን የሚናገሩት ማኅበራቱ፣ ማሠልጠኛ ተቋማቱ የሚያሠለጥኑባቸው ተሽከርካሪዎች ያረጁ መሆናቸውና የሚያሠለጥኑዋቸው ሰዎች ብቃት አናሳ መሆኑ ባለሥልጣኑ ሊያውቅ እንደሚገባና ችግሩን መቅረፍ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ሠልጣኙ ከላይ በተገለጹት ተሽከርካሪዎች ሠልጥኖ ዘመናዊ ተሽከርካሪ ሲይዝ ችግሩ እንደሚከሰትም አክለዋል፡፡ ይኼ ካልተስተካከለ ዝም ብሎ መናገር ብቻ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ ተሽከርካሪዎች የሚያስመጡ ነጋዴዎች ደግሞ የተላላፊ ሰሌዳ ቅዳሜና እሑድ እንዳይሠራ መከልከሉ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ሲገልጹ፣ ‹‹ወንጀል ስለሚሠራበት ነው የተከለከለው›› በማለት ዋና ዳይሬክተሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት አቶ ካሳሁን የተወሰኑ ጥያቄዎችን ያለፉ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ ችግሮች የመሥሪያ ቤቱ ብቻ ሳይሆኑ የማኅበራቱ መሆናቸውን ጠቁመው በጋራ በመሥራት ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች