Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ20 በላይ የውጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ማምረት እንደሚጀምሩ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁና በጥቂት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃሉ የተባሉ ከ20 በላይ የውጭ ጨርቃ ጨርቃ ፋብሪካዎች ማምረት እንደሚጀምሩ የጨርቃ ጨርቅ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመጥር ናቸው የተባሉት ፋብሪካዎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተገነቡ ሲሆን፣ በዘርፉ ኢትዮጵያን ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ እንደሚያደርጓትም ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ባንቲሁን ገሰሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግንባታዎቻቸው ከተጠናቀቁትም ሆኑ በቅርቡ በመገባደድ ላይ ካሉት ፋብሪካዎች መካከል ስምንቱ በቦሌ ለሚ የኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ሌሎቹ በአዲስ አበባ አቅራቢያ ከተሞችና በተለያዩ የክልል ከተሞች ውስጥ እንደሚገኙም አመልክተዋል፡፡

እንደ አቶ ባንቲሁን ማብራርያ፣ በመቐለ የሚገነባው የዱባይ ቬሎሲቲ፣ በቢሾፍቱ የሚገኘው የህንዱ ካኖሪያ አፍሪካ፣ በኮምቦልቻ የተገነባው ሌላኛው የህንዱ ቪፒ ቴክስታይል፣ በሰበታ የሚገነባው የቱርኩ ዲኢምኬ፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የፓኪስታኑ ኤክስፔሪያንስ ክሎዚንግ፣ እንዲሁም ዱላል ዲቢኤ የተባለው የባንግላዴሽ ኩባንያ ዋና ዋናዎቹ የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ናቸው፡፡

የፋብሪካዎቹ አጠቃላይ የተጠናቀረ የኢንቨስትመንት ካፒታል ምን ያህል እንደሆነ ባይገለጽም፣ በ2008 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ሲገቡ አገሪቱ ከቀጣናው አገሮች ትልቋ የጨርቃ ጨርቅ አምራችና ላኪ እንደሚያደርጋት አቶ ባንቲሁን ገልጸዋል፡፡

የጨርቃ ጨርቅ ንዑስ ዘርፍ በቅርቡ በተጠናቀቀው የመጀመርያው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በመንግሥት ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ በመሆን፣ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ በአምስት ዓመቱ መጨረሻ ግን ዘርፉ ከታቀደለት በታች ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ ከተለያዩ አካላትም ትችት ቀርቦበታል፡፡ የተቋሙ ኃላፊዎችም በንዑስ ዘርፉ የተመዘገበው ዕድገት ከዕቅዱ በጣም የራቀ መሆኑን ባይክዱም፣ ከሌሎች ዘርፎች በተሻለ ዕድገት እያሳየ መምጣቱንም በመግለጽ ይሞግታሉ፡፡

‹‹ይህ ዘርፍ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዘመን መጨረሻ የታቀደውን ያህል ዕድገት ባያሳይም፣ ከዓመት ዓመት ያለው መሻሻል ተስፋ ሰጪ ነው፤›› በማለት የሚገልጹት አቶ ባንቲሁን፣ በ2003 እና በ2004 ዓ.ም. ከዘርፉ ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪ 23 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር በአምስት ዓመቱ መጨረሻ ግን በየዓመቱ እስከ 112 ሚሊዮን ዶላር እያደገ እንደሚመጣ ተብሎ ታቅዶ ነበር ብለዋል፡፡

በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተማረ ሰው ኃይል እጥረት ዋናው ችግር እንደነበር ያወሱት ኃላፊው፣ አሁን ይህ ችግር እየተቀረፈ መምጣቱና ለሁለተኛው የዕቅድ ዘመን የተሻለ ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችልም ዕምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ የሠለጠነ የባለሙያ እጥረትን ለመቅረፍ በመንግሥት የሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት ውስጥ በርካታ ወጣቶች መሠልጠናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም ብዛት ያላቸው ባለሙያዎች ወደ ህንድ በመላክ ማሠልጠን መቻሉንም አክለዋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ሊኖሩ የሚችሉ ተግዳሮቶችንም ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ኩባንያዎች ከ80 በመቶ በላይ ወደ ውጭ መላክ ሲገባቸው ምርትን በአገር ውስጥ ገበያ በገፍ ማቅረብ፣ በፋብሪካዎች አመራር የሠለጠነ ባለሙያ እጥረት፣ የኃይል መቆራረጥ፣ እንዲሁም በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተቀላጠፉ አገልግሎቶች አሰጣጥ ችግር ዋና ዋናዎቹ ተግዳሮቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ 136 የሚሆኑ መካከለኛና ከፍተኛ ፋብሪካዎች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች