Tuesday, December 5, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ዳግም ምዝገባ ሲያካሂድ መሠረታዊ ችግሮችን ይመልከት!

በአዲስ አበባ ከተማ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች የተመዘገቡ ነዋሪዎች እንዳቅማቸው ዳግም ምዝገባ እንዲያደርጉ፣ መንግሥት እያመቻቸ እንደሆነ ሰሞኑን አስታውቋል፡፡ ቀደም ሲል በነበረው ሥሌት መሠረት በአቅማቸው መሠረት ምዝግባ የፈጸሙ ወገኖች፣ ከወቅቱ ተጨባጭ ገበያ አንፃር አቅማቸውን እየፈተሹ በመረጡት ዳግም ምዝገባ እንዲያደርጉ ዕድል መሰጠቱ ጥሩ ነው፡፡ በ10/90፣ በ20/80 እና በ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮግራሞች ከመኝታ ቤቶች ብዛትና ከራሳቸው ከፕሮግራሞቹ ጋር በተነፃፀረ ሁኔታ ዳግም ምዝገባው ሲፈቀድ በአዎንታዊ ጎኑ መታየት አለበት፡፡ ነገር ግን ከዳግም ምዝገባው ጎን ለጎን መነሳት ያለባቸው ዓበይት ጉዳዮች ስላሉ፣ መንግሥት በአንክሮ ሊያያቸው ይገባል፡፡ መሠረታዊ ችግሮችንም ማወቅ አለበት፡፡

በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው አንድ ሚሊዮን ሊደርስ ትንሽ የሚቀረው ዜጎች የመኖሪያ ቤት ለማግኘት ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ሲገኙ፣ የዚያኑ ያህል ቁጥር የሚኖራቸው ሌሎች ቤት ፈላጊዎች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ከዚህ የገዘፈ ቁጥር ያለው ቤት ፈላጊ ሕዝብ ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ መንግሥታዊ ዕርምጃ ያስፈልጋል፡፡ ዳግም ምዝገባው ሲከናወን አብሮት የቤቶቹ የዋጋ ክለሳ ስለሚኖር፣ ተመዝጋቢዎች ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አለባቸው፡፡ ይህ መረጃ ተመዝጋቢዎች አቅማቸውን ያገናዘበ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ከማድረጉም በላይ፣ በጋራ የመኖሪያ ቤቶች የግንባታ ዋጋ ሥሌትና አፈጻጸም ላይ የሚታየውን የግልጽነትና የተጠያቂነት አለመኖር ያስወግዳል፡፡

ባለፈው ጊዜ በተካሄደው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምዝገባ ለምሳሌ በ20/80 ፕሮግራም አንድ ተመዝጋቢ ለባለ አንድ መኝታ ቤት በወር 274 ብር ሲቆጥብ ቆይቶ፣ በዕጣ መኖሪያ ቤቱ ሲደርሰው የቤቱን 20 በመቶ 33 ሺሕ ብር ከፍሎ በየወሩ 1,293 ብር ክፍያ ይፈጽማል፡፡ ይህ ነባር ተመዝጋቢ በ15 ዓመታት የክፍያ ማጠናቀቅ መርሐ ግብር መሠረት ይህንን ዓይነቱን ሒደት ሲያልፍ፣ ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ለሚከራየው ቤት ወርኃዊ ክፍያ እየፈጸመና ጫና የበዛበት ኑሮውን እየመራ ነው፡፡ አሁን ከፍ ወዳለ ፕሮግራም ለማደግ ወይም ዝቅ ብሎ ለመመዝገብ ሲፈልግ፣ የሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም ወቅታዊውን የቤቶቹን የዋጋ ሥሌት ሊያቀርብለት ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን መወሰን አይችልም፡፡

ከዚህ ቀደም በተለይ በአሥርኛው ዙር የኮንዶሚኒየም ዕጣ አወጣጥ ወቅት የተስተዋለው እጅግ ከፍተኛ የሚባል የዋጋ ክለሳ በተመዝጋቢዎቹ ላይ ያመጣው ጫናም መዘንጋት የለበትም፡፡ ለ10/90፣ ለ20/80 ወይም ለ40/60 የቤቶች ግንባታ ፕሮግራም ዜጎች ያዋጣናል ብለው ምዝገባ አካሂደው፣ አቅማቸውን አውቀው ወስነው ከገቡበት በኋላ፣ ህልውናቸውን የሚፈታተን አዲስ የዋጋ ክለሳ ሲመጣባቸው ለበርካቶች ከሚሸከሙት በላይ ሆኗል፡፡ ወደፊትስ ይህ የአሁኑ የዋጋ ክለሳ ይደረግበታል? የሚደረግ ከሆነስ አሳማኝ ነው የሚባለው የዋጋ ጭማሪ በግልጽነት ቀርቦ መተማመን ይፈጠርበታል? ወይስ ዜጎች ተሸከሙት ተብሎ ነው የሚጫንባቸው? ይህም በአንክሮ መታየት አለበት፡፡ የሕዝብን አቅም የማያገናዝቡ ዕርምጃዎች መልሰው የሚጎዱት ሕዝብን ነውና፡፡

እንደሚታወቀው በጋራ የመኖሪያ ቤቶች ሁሉም ፕሮግራሞች ውስጥ የሚታዩ በሽታዎች ሕክምና ያስፈልጋቸዋል፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በአገሪቱ ትልልቅ ከተሞች የመኖሪያ ቤቶች ችግር የፈጠራቸው ፈተናዎች የአገሪቱ ትልቅ ተግዳሮት ሆነዋል፡፡ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደረው የከተማ ነዋሪ በመንግሥት ድጋፍ በተነፃፃሪ ለኑሮ ምቹ የሆኑ መኖሪያ ቤቶች ማግኘት ካልቻለ ኑሮው የከፋ ይሆናል፡፡ ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ የከተተ ትልቅ ፕሮጀክት ሲነደፍ ደግሞ ችግሮች ቢኖሩ እንኳ፣ ካለው የፍላጎት ግዝፈትና አጣዳፊነት አኳያ ግን ችግር የሚያባብሱ ክፍተቶችን መድፈን ተገቢ ነው፡፡ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የተስተዋለው ግን የንብረቶች ብክነት፣ ለሙስናና ለብልሹ አሠራር የሚያጋልጡ ተግባራት፣ ስርቆትና ማጭበርበር፣ የጥራት ጉድለት፣ የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር የተጠናከረ አለመሆን፣ ብልሹ አሠራሮች ላይ ዕርምጃ አለመውሰድና የመሳሰሉት ችግሮች ይነሳሉ፡፡ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም በእነዚህ ተግባራት ላይ ዝርዝር ጥናት አካሂዷል፡፡ በእነዚህ ችግሮች ምክንያት የሚደርሰውን የአገር ኪሳራ ቤት ፈላጊዎች እንዲሸከሙ መደረጉ ትክክል አይደለም፡፡ ይህም የመንግሥት የቤት ሥራ ነው፡፡

በሌላ በኩል የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታና አስተዳደርን በተመለከተ ውስጡ በሚገባ መፈተሽ አለበት፡፡ መንግሥት ለጋራ ቤቶች ግንባታ መሬት በነፃ አቀርባለሁ ሲል ይደመጣል፡፡ በተለይ ይህ የቤቶች ጉዳይ የሚመለከታቸው ሹማምንት ይህንን ጉዳይ በተደጋጋሚ ያነሱታል፡፡ ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ መሠረት መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው እየተባለ ሕዝብን ያገለለ አስተዋጽኦ መለፈፍ የለበትም፡፡ የመሬት አቅርቦት በገንዘብ እየተሰላ፣ አንድ ተመዝጋቢ በዜግነቱ ማግኘት የሚገባውን መሬት በምፅዋት እንደተሰጠው መንገር የተጠያቂነትና የኃላፊነትን ወሰን የማያሳይ ተግባር ነው፡፡ ይህ መታረም አለበት፡፡ በሌላ በኩል በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት አማካይነት የሚቀርቡ ጥራታቸው የተጓደለ የግንባታ ማቴሪያሎችን በደንታ ቢስነት ማስተናገድ፣ በኮንትራት አስተዳደር የሚፈጸሙ ሙስናዎችን ዝም ማለት፣ በሕገወጥ መንገድ ግዢዎች ሲፈጸሙ እንዳላዩ መሆንና የጥቅሙ ተጋሪ መሆን በስፋት ይታያል፡፡ ይህም ዕርምጃ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ መንግሥት ይህንንም ያስብበት፡፡

እስካሁን ድረስ መንግሥት በቤቶች ግንባታ ቀጥታ ተሳታፊ በመሆኑ የተገኘው ውጤት ሲገመገም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ መንግሥት የተቆጣጣሪነት ሥራውን አጠናክሮ ለአገር ውስጥና ለውጭ ኩባንያዎች ፕሮጀክቶችን ቢሰጥ ኖሮ የበለጠ ውጤት እንደሚመዘገብ ይታሰባል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው አሁን የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችን በቤቶች ግንባታ ለማሳተፍ ከረፈደም ቢሆን ጥረት እየተደረገ ያለው፡፡ የመኖሪያ ቤቶች ፈላጊዎች ቁጥር ከመቸውም ጊዜ በላይ እየጨመረ ስለሚሄድና ኩባንያዎቹም ይኼንን ሰፊ ገበያ ሊያልፉት ስለማይፈልጉ እነሱን በስፋት ማሳተፍ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ጠንካራ ተቆጣጣሪ አካል መሰየም የግድ ይሆናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ መንግሥት ከኩባንያዎቹ ጋር ሲዋዋል የቤት ተመዝጋቢዎችን ተጠቃሚነት ከፍ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ኩባንያዎቹ ከሰፊው ፍላጎት አንፃር ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ የዚያኑ ያህል ቤት ፈላጊዎች እንዲጠቀሙ መደረግ አለበት፡፡ ይህም የቁጠባውን ገንዘብ መጠን በመቀነስና ክፍያው የሚጠናቀቅበትን ጊዜ ጭምር በማራዘም ይሆናል፡፡ በዚህም የሌሎችን አገሮች ልምድ ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር አዛምዶ ማየት የመንግሥት ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶች በስኬት ተገንብተው ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለሕዝቡ መዳረስ አለባቸው፡፡ በቅርቡ በተደረገ ፍተሻ ግን 14 ሺሕ ያህል ተገንብተው የተጠናቀቁ ቤቶች ተዘግተው ተገኝተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ዓይን ያወጣ አሳፋሪ ተግባር ተፈጽሞ ሲታይ መንግሥትን ከነአመራር አካሉ ማሸማቀቅ ነበረበት፡፡ ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሌለበት አሳፋሪ ድርጊት ስለሆነ የሚመለከታቸው አካላት ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ቤቶቹ ተገንብተው ዓመታት ካስቆጠሩ በኋላ ተዘግተው ተገኙ ሲባል ለምን ተግባር ሊውሉ ነበር የተገነቡት ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ዕርምጃ መውሰድም እንዲሁ፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግር የዘመኑ አሳሳቢ ፈተና መሆኑ እየታየ በሕዝብ ላይ መቀለድ ያሳፍራል፡፡ በአጠቃላይ መንግሥት ዳግም ምዝግባውን ሲያካሂድ ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች በሙሉ ከሥር መሠረታቸው ይመልከታቸው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...