Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበዝናብ እጥረት ለተጐዱ ወገኖች ከዕርዳታ ሰጪዎች ምላሽ አልተገኘም

በዝናብ እጥረት ለተጐዱ ወገኖች ከዕርዳታ ሰጪዎች ምላሽ አልተገኘም

ቀን:

– ከአገር ውስጥ ገበያ እህል ግዥ ተጀመረ

ዕርዳታ ሰጪዎች በሌሎች አገሮች አንገብጋቢና ወቅታዊ ችግሮች በመጠመዳቸው ምክንያት፣ በዝናብ እጥረት ለተጐዱ 4.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ምላሽ የመስጠት አዝማሚያ አለማሳየታቸው ተጠቆመ፡፡ መንግሥት የተፈጠረውን ችግር በራስ አቅም ለመወጣት በፌዴራል፣ በክልልና በዞን ደረጃ የመጠባበቂያ ፈንድ ማቋቋሙም ተገልጿል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ምትኩ ካሳ ነሐሴ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፣ ዕርዳታ ሰጪዎች በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ችግር ውስጥ ለገቡ፣ በርዕደ መሬት ለተጐዳው የኔፓል ሕዝብና ወደ አውሮፓ በሚጐርፉ ስደተኞች ጉዳይ በመጠመዳቸው ለኢትዮጵያ ጥሪ ምላሽ አልሰጡም፡፡

‹‹መንግሥት እስካሁን የሚያስፈልገውን ሁሉ በመሸፈን ላይ ነው፤›› በማለትም መንግሥት የተፈጠረውን ችግር ብቻውን እየተወጣ እንደሚገኝ አቶ ምትኩ ገልጸዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ከተነደፉ አራት ዕቅዶች መካከል አንዱና ዋነኛው ለተጐዱ ወገኖች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ማቅረብ ነው፡፡ አቶ ምትኩ እንዳሉት፣ ይህንንም ለማሳካት ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር የእህል ግዥ በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ ‹‹500 ሺሕ ኩንታል በቆሎ፣ 100 ሺሕ ኩንታል ማሽላ፣ 30 ሺሕ ኩንታል አልሚ ምግብ ከአገር ውስጥ ገበያዎች ግዥ እየተፈጸመ ነው፤›› ያሉት አቶ ምትኩ ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹2.2 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከውጭ አገር ግዥ ለመፈጸም በሒደት ላይ እንገኛለን፤›› በማለት መንግሥት ችግሩን ለማቃለል እያከናወነ ያለውን ተግባር አስረድተዋል፡፡ መንግሥት የዝናብ መዛባት ያስከተለውን ችግር ለመፍታት ለነደፋቸው አራት ተግባራት ማስፈጸሚያ እንዲሆን 700 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን መግለጹ ይታወሳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ችግሩ ከተከሰተባቸው ለምሳሌ ለኦሮሚያ ክልል 505 ሚሊዮን ብር በጀት ሲመድብ፣ ለዞኖች 20 ሚሊዮን ብር በነፍስ ወከፍ በመመደብ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ መሆኑን አቶ ምትኩ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ለአደጋ ጊዜ ካስቀመጠው የመጠባበቂያ እህል ክምችት ወጪ በማድረግ ዕርዳታ በማከፋፈል ላይ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሰባት ቦታዎች የሚገኘው የመጠባበቂያ እህል ክምችት 451 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ነው፡፡ አቶ ምትኩ እንዳብራሩት፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ የአገሪቱን የመጠባበቂያ እህል ክምችት ወደ 1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ለማሳደግ ታቅዷል፡፡

ቀጣዩ የመጠባበቂያ እህል ክምችት ሦስት ዓላማዎች እንዳሉት የገለጹት አቶ ምትኩ የመጀመሪያው በአደጋ ወቅት አውጥቶ መጠቀም፣ ሁለተኛው ለገበያ ማረጋጋት ሥራ የሚውል እህል ከአገር ውስጥ ገበያ ግዥ በመፈጸም ለተጠቃሚዎች ማቅረብ፣ ሦስተኛው አደጋ በሌለበትና የገበያ ማረጋጋት ሥራ በማይኖርበት ወቅት ኤክስፖርት ማድረግ ናቸው፡፡

መንግሥት ባለፈው በጀት ዓመት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ገበያ ለማረጋጋት ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከውጭ አስገብቷል፡፡ በቀጣይ ግን ይህንን ስንዴ በአገር ውስጥ ምርትና ገበያ ለማሟላት ታስቧል፡፡

በእህል ክምችት ወቅት ያለሥራ የሚቀመጠውን እህል ጠብቆ ለማቆየት የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ ስለሚሆን፣ አደጋ በሌለበት ወቅት ወደ ውጭ ኤክስፖርት ለማድረግ መታቀዱን አቶ ምትኩ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን ባካሄደው ጥናት፣ 4.5 ሚሊዮን ወገኖች በዝናብ እጥረት ምክንያት መጐዳታቸውንና ለዚህም 230 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...