Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የዝናብ እጥረትን ምክንያት በማድረግ ዋጋ ለመጨመር የሚሯሯጡ እንዳሉ ተጠቆመ

የዘመን መለወጫን በዓል ምክንያት በማድረግ በተለይ በሥጋና የሥጋ ተዋጽኦዎች፣ በወተትና የወተት ተዋጽኦዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ፣ የማያዳግም (ከንግድ ውጭ የማድረግ) ዕርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት መጠናቀቁን፣ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ነሐሴ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መርከቡ ዘለቀ በተለይ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በሚያከብሩት የፍልሰታ ፆም መፍቻ ላይ የተጨመረውን ከፍተኛ የሥጋ ዋጋ አስታውሰዋል፡፡ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች እጥረት እንዲፈጠር ባደረጉት ቅስቀሳ መሆኑ ስለተደረሰበት፣ ማጣራት ተደርጐ ፈቃዳቸውን እንዲነጠቁ ከማድረግም ባለፈ በወንጀል ለማስቀጣት ክስ ተመሥርቶባቸው በሒደት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከባለድርሻ አካላት ጋር ማለትም ከምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ባለሥልጣን፣ ከንግድ ሚኒስቴር፣ አዲስ አበባ ንግድ ቢሮ፣ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ልዩ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡ ቁጥጥሩ በዓሉን ብቻ ምክንያት ያደረገ ሳይሆን፣ በቀጣይ ከክልል መንግሥታትም ጋር በመሆን ቁጥጥሩና ዕርምጃው የሚቀጥል መሆኑን ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡

ቁጥጥሩና ዕርምጃው ዋጋ በሚጨምሩት ላይ ብቻ ሳይሆን ሸቀጦችን በሚደብቁ፣ በሚያከማቹ፣ መጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ምርቶች ግርግርን ተጠቅመው ለሽያጭ የሚያቀርቡትንና የተሳሳተ ወሬ በማውራት ከአምራች አርሶ አደሩ ጀምረው እስከ ነጋዴው ድረስ ለዋጋ መጨመር ምክንያት በሚሆኑ ሕገወጥ ደላሎች ላይ ጭምር እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

ባለድርሻ አካላቱ የሥራ ድርሻ በመከፋፈል እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የተናገሩት አቶ መርከቡ፣ ከጥቂት የግብርና ውጤቶች ማለትም ከምስርና ከበርበሬ በስተቀር፣ በሁሉም የግብርና ምርቶች ላይ የጨመረ እንጂ የቀነሰ ምርት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

የአንድ ወር የዘይት ኮታ በአዲስ አበባ 27 ሺሕ ሊትር የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ወደ 44 ሺሕ ሊትር ከፍ ማለቱን፣ ስንዴ ከ500 ሺሕ ኩንታል ወደ 700 ሺሕ ኩንታል ከፍ ማለቱን፣ ስኳር እስከ ጳጉሜ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ 250 ሺሕ ኩንታል በሸማቾች ማኅበር በኩል የሚከፋፈል መሆኑንና 320 ሺሕ ኩንታል ደግሞ ጨረታ ወጥቶ እየተሸጠ በመሆኑ ምንም ዓይነት እጥረት እንደማይከሰት አስረድተዋል፡፡ በወሬ የተሸበሩ ነዋሪዎች ግን ከነቤተሰባቸው ለተጠቀሱት ምርቶች እየተሠለፉ መሆኑን ጠቁመው፣ ትክክል ባለመሆኑ ሊረጋጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖራቸው ዋጋ ለመጨመር በሚንቀሳቀሱ ፋብሪካዎች ላይ ጥብቅ ዕርምጃ እንደሚወሰድ በድጋሚ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ዕርምጃ ሲባል ቀጥቶ ወደ ሥራ መመለስ፣ መምከርና ማስጠንቀቅ ሳይሆን ከሴክተሩ ማስወጣትና ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድን ይጨምራል፤›› ብለዋል፡፡ ከክልሎችም ጋር አብረው ለመሥራት የቢጋር (TOR) ዝግጅት እያጠናቀቁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የባለሥልጣኑ ትኩረት በአዲስ አበባ ላይ ብቻ መሆኑ ችግሩን እንዴት ሊቀርፍ እንደሚችል የተጠየቁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ቢጋሩ ሲፀድቅ በክልልም እንደሚቀጥል ተናግረው፣ ለጊዜው ያላቸው ሥልጣን በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች [አዲስ አበባና ድሬዳዋ] ላይ የተወሰነ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በክልሎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ሥልጣኑ የክልሎች መሆኑን ተናግረው በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብም ተመሳሳይ ዕርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጁ በመሆናቸው እንቅስቃሴው በቅርቡ አገር አቀፍ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት የተቋቋሙት ለትርፍ ባለመሆኑ፣ ከስግብግብ ነጋዴ ጋር በመመሳጠር ለትርፍ የሚሸጡ ማኅበራት ላይ ዕርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከግብርና ሚኒስቴርና ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን የሚወጡ ማስረጃዎች የሚያመለክቱት የምርት ችግር እንደሌለ መሆኑን ጠቁመው፣ ኢኮኖሚያዊ አመክንዮ በሌለበት ሁኔታ ዋጋ ለመጨመር መሯሯጥ ወንጀል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከነዳጅ ውጪ የትርፍ ህዳግ ሕግ ስለሌላት መወሰን እንደማይቻል አክለዋል፡፡

መንግሥት በነፃ ገበያ ውስጥ ገብቶ ዋጋ መተመን ስለማይችል፣ ከዓመታት በፊት በ18 የንግድ ዕቃዎች ላይ ጥሎት የነበረውን የዋጋ ጣሪያ ስህተት እንደነበር አቶ መርከቡ ተናግረዋል፡፡ በተለይ በሥጋ ዋጋ ላይ መዘግየታቸውንና አሁን ግን ከንግድ ቢሮ፣ ከንግድ ሚኒስቴርና ከቄራዎች ድርጅት መረጃ ተሰብስቦ በመጠናቀቁ ዕርምጃ እንደሚወሰድ በድጋሚ አስጠንቅቀዋል፡፡ ሸማቹም የራሱን አቋም ቢወስድ ነጋዴው ለምኖ የሚሸጥበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ‹‹የባሰ ዋጋውን እንዳያባብሱት›› የሚል ሥጋት ውስጥ መግባት እንደሌለበትና በፍፁም እንደማይባባስ መንግሥት ቆርጦ መነሳቱን አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት ቆርጦ የተነሳው ነጋዴውን ለማስፈራራት ሳይሆን፣ ነጋዴው ሕግን አክብሮና ፈርቶ እንዲሠራ እንዲሁም መብቱን በአግባቡ በመጠየቅ ግዴታውንም እንዲወጣ መሆኑን አቶ መርከቡ አስረድተዋል፡፡   

     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች