Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርትየእግር ኳሱ ደረጃና ሚዛን ያጣው ንፅፅር

  የእግር ኳሱ ደረጃና ሚዛን ያጣው ንፅፅር

  ቀን:

  ከዓመት እስከ ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሚያካሂዳቸው የነጥብም ሆነ የወዳጅነት ጨዋታዎች ከየአቅጣጫው የሚሰነዘሩት ገንቢም ሆኑ አሉታዊ አስተያየቶች ተጠናክረው በቀጠሉበት በዚህ ወቅት፣ የእግር ኳስ ጉዳይ ብዙዎቹ ታዳሚዎች ግራ አጋቢ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ድልንም ሆነ ሽንፈትን ተከትለው በሚሰነዘሩት በእነዚህ አስተያየቶች ምን ያህል ለውጥ መጣ? ወይስ ምን ያህል ጉዳት ተመዘገበ የሚለውን ማወቅ እንዳልተቻለም የሚናገሩ አሉ፡፡

  የአንድ ሰሞን ጫጫታ በሚመስል ሁኔታ የሚጧጧፈው አስተያየትና የትችት ናዳ ምንም እንኳ የብሔራዊ ቡድኑን ስኬት ከመናፈቅ የተነሳ ቢመስልም፣ ሚዛናዊነትን ያጣና በተለይም አግባብ ያልሆኑ የማነፃፀሪያ መሥፈርቶችን እንደ መለኪያ የሚያቀርብ በመሆኑ፣ ለእግር ኳሱ ተመልካቾች በግልጽ የሚታይ እውነታም እየሆነ ይገኛል፡፡

  እ.ኤ.አ. በ2017 ጋቦን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. የሲሸልስ ብሔራዊ ቡድንን ገጥሞ በአቻ ውጤት የተመለሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ)፣ እንደተለመደው ሁሉ አሁንም እነዚህን አስተያየቶች ከየአቅጣጫው ማስተናገዱን ቀጥሏል፡፡ በአንድ በኩል ‹‹እንዴት ዘጠና ሺሕ ሕዝብ ባላት ትንሽ አገር ነጥብ ይጣላል?›› የሚል አስተያየት ሲደመጥ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ውጤቱ ከሜዳ ውጪ የተገኘ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል፤›› የሚልም ይሰማል፡፡ አንዳንድ የእግር ኳሱ ተንታኞች በበኩላቸው፣ የብሔራዊ ቡድኑን የታክቲክ ስህተት ነቅሰው በማውጣት የካበተ ልምድ ባለቤት የሆኑትን የአውሮፓና መሰል በድኖችን ልምድ እንደ ማመሳከሪያ በመውሰድ ሒሳቸውን ያጠናክራሉ፡፡

  ይሁንና ለአብዛኛው ‹‹ገለልተኛ ተመልካች›› እነዚህ ሁሉ ትንታኔዎችና አስተያየቶች ውኃ የማይቋጥሩ ከመሆናቸውም በላይ፣ የአገሪቱን እግር ኳስ ነባራዊ እውነታን ግምት ውስጥ ያላስገቡ ስለመሆናቸው የሚናገሩ አሉ፡፡ እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች፣ የራስን አቅም በውል ያለመለየትና ያለመረዳት ችግር እየተስተዋለ መሆኑን እንደ ምክንያት ጠቅሰው፣ በሌላ በኩል ደግሞ የውጭውን ስፖርት በማጣጣም የተገኘን የተመልካችነት ዕውቀት ለብሔራዊ ቡድን ምዘና መጠቀም የራሱ የሆነ ችግር እንደሚፈጥርም ይናገራሉ፡፡

  ባለፈው ቅዳሜ ሁለተኛውን የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ከሲሸልስ አቻው ጋር ለማድረግ ወደ ሥፍራው ያቀናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በቦታው ተገኝተው ከተከታተሉ ተመልካቾች መካከል አቶ ልዑል ዓለሙ ይጠቀሳሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ዕድል ሲገጥማቸው የመጀመርያ ጊዜያቸው መሆኑን የሚናገሩት ተመልካቹ፣ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ባያስደስታቸውም፣ አጋጣሚው ግን የአገሪቱን እግር ኳስ ቀጣይ ዕጣ ፈንታና ሲነገርለት የቆየው ንፅፅር ምን ያህል የተራራቀ ለመሆኑ ማረጋገጫ እንደሆናቸው ያስረዳሉ፡፡

  አሁንም የማስተካከያ ጊዜ መኖሩን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪው፣ ከታች  እስከ ክለቦች ያለው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምን መምሰል እንሚገባው ተገቢው ዝግጅትና የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ፣ በተለይ ደግሞ የአገሪቱ ተጨዋቾች ለዘመናዊ እግር ኳስ እንግዳ የማይሆኑበት የአሠራር ሥርዓት ማመቻቸት የግድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን አንዱ በሌላው ላይ ጣት መቀሳሰሩ እንደማይበጅ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

  ሲሸልስ ተገኝተው ጨዋታውን ባይከታተሉትም ውጤቱንና የጨዋታውን እንቅስቃሴ በሬዲዮና መሰል የመረጃ መረቦች እንደሰሙት የሚናገሩት አሠልጣኝ ማቲያስ ከበደ በበኩላቸው፣ ‹‹ይህ ሁሉ ትርምስና ጩኸት ወደ ራሳችንን በደንብ ሳንመለከት፣ ለራሳችን በሰጠነው የተሳሳተ ግምት ያስከተለብን ችግር ነው፤›› ይላሉ፡፡ ምክንያቱም የሚሉት አሠልጣኙ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የገጠመው ውጤት በእግር ኳስ ዓለም ወደፊትም የሚቀጥል ነው፤›› ብለው፣ ሌላው ለዚህ የተሳሳተ ግምት ሲሉ የተናገሩት ደግሞ፣ ብሔራዊ ቡድኑን አሁን በማሠልጠን ላይ የሚገኙት አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የደደቢት እግር ኳስ ክለብን ይዘው በነበረበት ወቅት የሲሸልሱን ክለብ በሜዳውና በደጋፊው ፊት አሸንፈው መምጣታቸውን፣ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በየወሩ በሚያሳውቀው የአገሮች የእግር ኳስ ደረጃ፣ የኢትዮጵያ ደረጃ ከሲሸልስ በብዙ የቁጥር ልዩነት ልቆ መገኘቱ እንደሆነ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

   ከዚህ አኳያ ብሔራዊ ቡድኑ ያስመዘገበው አቻ ውጤት አሠልጣኙንም ሆነ ተጨዋቾቹን ክፉኛ እያስወቀሰ ይገኛል፡፡ ይሁንና ይኼ መሠረት የሌለው እግር ኳስ የሚያስከትለው የውጤት ቀውስ መሆኑን አሠልጣኙ ያምናሉ፡፡ ከዚህ አሠራር ለመውጣት ደግሞ፣ ‹‹ጣሪያው ላይ ወጥተን ከምንጨቃጨቅ መጀመሪያ ወደ ጣሪያው ለመውጣት ያስቀመጥነው መሠረት ምን እንደሚመስል መመልከት ይገባናል፤›› በማለት ለአገሪቱ እግር ኳስ ለወደፊቱ የሚበጀውን ይጠቁሟሉ፡፡

  ብሔራዊ ቡድን የክለቦች ነፀብራቅ እንጂ ከየትም እንደማይመጣ የሚናገሩት አሠልጣኝ ማቲያስ፣ ለዚህ ሌላው ትልቅ ማሳያ የሚሉት የአገሪቱ ክለቦች በአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮናና በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ሲቀርቡ ብዙም ሳይገፉ የሚወጡበት ዕድል የሰፋ መሆኑ ነው ያከሉት፡፡ በአሁኑ ወቅት በአንድም ሆነ በሌላ ብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ሲያጣ ብቻ የሰላ ትችትና ወቀሳ በመሰንዘር ዕድገት ሊመጣ እንደማይችል አስተያየታቸውን የሚቀጥሉት አሠልጣኙ፣ ጠንካራ የሚባሉት የአኅጉሪቱ ብሔራዊ ቡድኖች የጥንካሬያቸው መሠረት ክለቦቻው በመሆናቸው፣ በወቅታዊ የውስጥ ችግር እንኳ ተዳክሞ የማይታየውን የግብፅን ብሔራዊ ቡድን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡

  የአገሪቱ እግር ኳስ መሠረታዊ ጥያቄ ሊሆን የሚገባው፣ ‹‹እንደ ሲሸልስ ባለች ትንሽ አገር እንዴት እንሸነፋለን? የሚለው ሳይሆን ለወደፊቱ ሽንፈታችን የሚነግረን ምንድነው? ይህስ ለቀጣዩ እግር ኳስ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ምን ሊሆን ይችላል? ማስተካከል የሚቻለውስ እንዴት ነው?›› በሚለው ዙሪያ መነጋገሩና መተቻቸቱ እንደሚበጅ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂነትና ግልጽነት የአሠራሩ አካል መሆን እንዳለባቸው ጭምር አስረድተዋል፡፡

  ሌላው በዚሁ በሲሼልስና ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ማጣሪያ በተመለከተ ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ናቸው፡፡ አሠልጣኙ ለተገኘው ውጤት ተጨዋቾችን ተጠያቂ ማድረግ እንደማይፈልጉ ገልጸው፣ ቡድናቸው ሜዳ ላይ ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ለጎል የሚሆኑ ዕድሎችን ከሲሼልሶች በተሻለ አግኝቶ መጠቀም ሳይችል መቅረቱን ግን አምነዋል፡፡

  በወቅቱ በቦታው ለነበሩ ጋዜጠኞች በቡድኑ በተለይም በፕሮፌሽናሎቹና በአገር ውስጥ ተጨዋቾች መካከል በግልጽ የሚነበብ ክፍተት መስተዋሉና መሰል ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ሲመልሱ፣ የተገኙ የጎል ዕድሎችን የመጠቀም አቅም ማነስ ከመታየቱ በስተቀር የሚባለውን ነገር እንዳላስተዋሉ፣ ሆኖም አሁንም የጎል አስቆጣሪ ችግር ፈተና ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ ሌላው ለአሠልጣኙ የቀረበላቸው ጥያቄ፣ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ግልጽ የሆነ የአጨራረስ ብቃት እየተስተዋለባቸው በተጠባባቂ ሥፍራ በነበሩ ወጣት ተጨዋቾች ለምን አልተተኩም? የሚል ሲሆን፣ ለዚህም የአሠልጣኙ መልስ የተጠቀሱት ተጨዋቾች ካላቸው የካበተ ልምድ አኳያ ‹‹አንድ ነገር›› ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚል እምነት እንደነበራቸው ነው ያስረዱት፡፡ ከተጨዋቾቹ መካከል ደግሞ በዕለቱ ጨዋታ ተከላካዮችንና ጎል አስቆጣሪዎችን በጥሩ ብቃት ሲያገናኝ የነበረው ሽመልስ በቀለ ነው፡፡ በርካታ ዕድሎችን አግኝቶ መጠቀም ያልቻለው ጌታነህ ከበደ በቡድኑ ውስጥ የነበረው ክፍተት በአጠቃላይ ሜዳ ውስጥ በነበሩት ተጨዋቾች እንቅስቃሴ ሳይሆን፣ ለውጤት ቅርብ የነበሩ አጋጣሚዎችን ራሱን ተጠያቂ በማድረግ ጭምር መጠቀም አለመቻል መሆኑ ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል፡፡ የቡድን አጋሩ ሽመልስም ይህንኑ ሲያጠናክር ተደምጧል፡፡

   

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...