Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኢትዮጵያን ድርቅና አረንጓዴ ልማት የሚያስቃኝ ዶክመንተሪ ተሠራ

የኢትዮጵያን ድርቅና አረንጓዴ ልማት የሚያስቃኝ ዶክመንተሪ ተሠራ

ቀን:

የኢትዮጵያን ገጽታ ለዓለም የሚያስተዋውቅ ‹‹ኢትዮጵያ ራይዚንግ፣ ሬድ ቴረር ቱ ግሪን ሬቮሉሽን›› የሚል ፊልም ባሳለፍነው ሳምንት ተመርቋል፡፡ በዓለም ባንክና በአፍሪካ ቀንድ የአካባቢ ማዕከልና ኔትወርክ እገዛና ትብብር የተሠራውና በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል የታየው ይኸው የ45 ደቂቃ ፊልም፣ ከ1960ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ ወቅቶች የተከሰተው ድርቅ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተለይም በትግራይ ክልል ያስከተለው ጉዳት፣ እንዲሁም ኅብረተሰቡ የየግሉን መሣሪያ ይዞ በመውጣት የተጎሳቆለውን መሬት በአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ እንዴት እንዳለማው የሚያሳይ ነው፡፡

ፊልሙ፣ ትኩረት ያደረገው በትግራይ ክልል በድርቅ ክፉኛ ተጎድቶ በነበረው የአብረሃ አጽበሃ መንደር ላይ ነው፡፡ ፊልሙ በገሪእልታ ወረዳ ነዋሪ የሆኑትና ከፍተኛ የሆነ የደን ፍቅር ያደረባቸው አቶ ገብረሚካኤል ግደይ፣ ታዳጊ ወጣት በነበሩበት ወቅት ታላቅ እህታቸው ወደሚገኙበት አብርሃ አጽባሃ መንደር ሄደው ኑሮዋቸውን በዛው መሠረቱ፡፡ በዚህም ጊዜ አካባቢው የተራቆጠና መሬቱም በእጅጉ የተጎሳቆለ መሆኑን በመገንዘብ ለልማት መነሳታቸውን ያሳያል፡፡

ኅብረተሰቡን ሰብስበው በጉደዩ ላይ በሰፊው እንዲወያዩበት ካደረጉ በኋላ ሁለት አማራጮች እንዲቀርብ አደረጉ፡፡ አንደኛው አማራጭ ለኑሮና ለእርሻ ተስማሚ ወደሆነው ሌላ አካባቢ ሄዶ መስፈር ሲሆን፣ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ አካባቢውን በማልማት ወደ አረንጓዴነት መለወጥና ለእርሻ ተስማሚ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡

ኅብረተሰቡም ሁለተኛውን አማራጭ በመደገፍ አለምንም ተቃውሞ በሙሉ ድምፅ በመቀበሉ የተነሳ በየተራራው፣ በየሜዳውና በየሸለቆው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ማከናወኑን ተያያዘው፡፡ በዚህም የተነሳ ዛፍና ልዩ ልዩ ዓይነት ቁጥቋጦዎች መብቀልና በተራሮች ስርም ውኃ መፍለቅ ጀመረ፡፡ በዛው ልክም የመስኖ እርሻ ተስፋፋ፣ የአካባቢውም ኅብረተሰብ አቶ ገብረሚካኤልን ‹አባሐዊ› ብሎ ጠራቸው፡፡ በትግርኛ ትርጉሙም ቀልጣፋ፣ ሥራ ወዳድ፣ ፈጣንና እሳት እንደማለት ነው፡፡

ኅብረተሰቡን የማስተባበሩ ሥራ እንደሽፋን ሆኖ ለሕወሓት ሚስጥር ያቀብላሉ በሚል እምነት አባሐዊን ደርግ ውቅሮ ወህኒ ቤት ውስጥ ለእስር እንደዳረጋቸው፣ ከወህኒ ቤት እንደተፈቱም ውለው ሳያድሩ ኅብረተሰቡን በአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ላይ የማሰማራቱን ተግባር እንደቀጠሉ በመካከሉ ኢሕአዴግ መላ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ኅብረተሰቡን የማስተባበር ሥራ በስፋት እንደተያያዙት ፊልሙ ይተርካል፡፡

ልምዳቸውንም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተዘዋወሩ ለየአካባቢው አርሶ አደሮች ሲያካፍሉና ሲያስተምሩ የሚያሳየውም እንቅስቃሴ ትረካው ውስጥ ተካቷል፡፡ በአብርሃ አጽበሃ መንደር አካባቢ ያሉት ከፍታ ቦታዎች በአሁኑ ጊዜ በደንና በዕፅዋት፣ እንዲሁም ገላጣ ቦታዎችም ለከብት መኖ በሚሆኑና በልዩ ልዩ ዓይነት ሰብሎች የተሸፈኑ ሲሆን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪም ነፃ ሆነዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ከብቶችን ወደ ግጦሽ ከማሰማራት ተቆጥቦ በረት ውስጥ እንዲቆዩ አድርጓል፡፡ አስፈላጊው መኖም ይቀርብላቸዋል፡፡

አቶ በለጠ ታፈረ የአካባቢና ደን ሚኒስትር ፊልሙን በመረቁበት ሥነ ሥርዓት ላይ ግብርና መር የሆነ የልማት ፕሮግራም በአርሶ አደሩ ማኅበረሰብ ተሳትፎ ተቀርጾ ወደ ተግባር መገባቱን፣ በዚህም የማኅበረሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ መከናወኑን ቻይናና ህንድ ከመሳሰሉ አገሮችም ጠቃሚ ልምድ መቀሰሙን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ውስጥ የትግራይ ሕዝብ በተለይም አርሶ አደሩ የተጎሳቆለው መሬት ተመልሶ አንዲያገግም በማድረግና በየዓመቱም በየአካባቢያቸው ለ30 ቀናት ያህል የሚቆይ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ በማከናወን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ገልጸዋል፡፡

ሌሎቹም ክልሎች ይህን ዓይነቱን ልምድ በመቅሰም ተመሳሳይ የሆነ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ እንዳከናውኑ፣ በተለይም አርሶ አደሩና የከተማው ነዋሪዎችም የተሳተፉበትና በአጠቃላይ ወደ 26 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በአገር አቀፍ ደረጃ በየዕለቱ የአፈርና ውኃ ጥበቃና የደን እንክብካቤ ሥራ በነፃ በማከናወን በአካባቢው ልማት የጎላ ተሳትፎ አበርክቷል፡፡

የመልሶ ማልማት ሥራ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የአፈር ለምነትና የውኃ መፍለቅ ታይቷል፡፡ ይህም የግብርናውን ምርት ከማሳደጉም በላይ የመስኖ ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ለገጠሩ ማኅበረሰብ በተለይም ለወጣቱና መሬት አልባ ለሆኑ ሁሉ ጥሩ የሥራ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡

የፊልሙ አዘጋጅ ሚስተር ማርክ ዶድ ፊልሙ የተዘጋጀው በደርግ ሥርዓት የነበረውን የአገሪቱን ሁኔታና አባሐዊ በግል ጥረታቸው ያከናወኗቸውን ተግባር አንድ ላይ በማቀነባበር ነው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለው የአገሪቱ የአካባቢ ፖሊሲ ለቀረው ዓለም በአስተማሪነት እንደሚታይ አስረድተዋል፡፡

ሚስተር ክሪስ ሪጂ በዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ አማካይነት እኩልነትና ብልፅግና እንዲስፋፋ ለማድረግ የሚያስችል የምርምር ሥራ በማካሄድ የሚታወቀው የወልርድ ሪሶርስ ዓለም አቀፍ ተቋም ተወካይ፣ ፊልሙ በደርባን፣ ብራስልስ፣ አውስትራሊያ፣ ስዊድን፣ ዋሽንግተንና በሌሎችም የአውሮፓ አገሮች በሚገኙ ታላላቅ ከተሞችና ተቋማት እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር አርዓያ አስፋው የአፍሪካ ቀንድ የአካባቢ ማዕከልና ኔትወርቅ ዳይሬክተር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፊልሙን ለመሥራት ከሁለት ዓመት በላይ የፈጀ ሲሆን ዋና ዓላማውም ለውጭ ዓለም ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን የተከናወኑት የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ ሥራዎች በሳይንቲፊክ ጆርናል ከመውጣት በስተቀር በዶክመንተሪ ፊልም አልተያዙም፡፡ በአጭር ፊልም ዶክመንተሪ ቢሠራ ሰው በቀላሉ ሊያየውና ሊረዳው ይችላል ከሚል እምነት በመነሳት በድርጅታቸውና በዓለም ባንክ ግፊት ፊልሙ ሊሠራ እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

ፊልሙ በእንግሊዝኛና በትግርኛ ቋንቋ የተሠራ ሲሆን፣ ወደፊት በኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለየክልሉ በማስተማሪነያነት እንዲያገለግል ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ከዶ/ር አርዓያ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በፊልሙ ላይ የቀረቡት አቶ ገብረመድህን ግደይ ወይም አባሐዊ በሰጡት አስተያየት፣ በ18 ዓመታቸው የደን ፍቅር እንዳደረባቸው፣ ሰዎች ለማገዶ ዛፍ ለመቁረጥ ሲሞክሩ በመከላከል ስለ ደን ጥቅም ሲያስረዱ መቆየታቸውን አውስተዋል፡፡ በደርግ ሥርዓት ማኅበረሰቡን አስተባብረው በአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ላይ በማሠማራት ውጤታማ የሆነ ተግባር ያከናወኑ ሲሆን፣ ለዚህም የአገርና የዓለም አቀፍ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡ አቶ ገብረመድን በአሁኑ ጊዜ 54 ዓመታቸው ሲሆን፣ ባለትዳርና የልጆች አባት ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...