Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልዕይታ የሳበ ትሩፋት

ዕይታ የሳበ ትሩፋት

ቀን:

የሥነ ጥበብና መገናኛ ብዙኃን ሽልማት በ1980ዎቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚጠቀሱ ተቋማዊ ሽልማቶች አንዱ ነበር፡፡ ሠዓሊ ታደሰ መስፍን ሽልማቱን ካገኙ መካከል ነው፡፡ ሠዓሊው ከሥነ ጥበብ ትምህር ቤት በማዕረግ ሲመረቅ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የወርቅ ሰዓት ሸልመውት እንደነበርም ይታወሳል፡፡ የበጎ ሰው ሽልማት የ2007 ዓ.ም. የሥነ ጥበብ ዘርፍ ተሸላሚም ይኸው ሠዓሊ ሆኗል፡፡

ታደሰ ሥዕል የጀመረው በልጅነቱ ወልዲያ ውስጥ እረኛ በነበረበት ወቅት፣ እጅና እግሩ ላይ በእንጨት እየሣለ ነበር፡፡ ከሥነ ጥበብ ትምህር ቤት ከተመረቀ በኋላ በተለይም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ የሠራው ዲዛይን ችሎታውን የመሰከረ ነበር፡፡ ሠዓሊው ሁለተኛ ዲግሪውን በተማረበት የሩስያው ሬፒን አካዳሚ ከፍተኛ ውጤት አምጥቶ የክብር ተሸላሚ በመሆን የመጀመርያው የውጭ አገር ዜጋ ለመሆን ችሏል፡፡

በደርግ ሥርዓት ከሠራቸው ሥዕሎችና ፖስተሮች የሶሻሊስት ኢትዮጵያ ዓርማ ተጠቃሽ ነው፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ መድረክና አልባሳት ዲዛይኖቹም አይረሴ ናቸው፡፡ ትግራይ ባለው የሰማዕታት ሐውልትና በአማራ የሰማዕታት ሐውልት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከቅርብ ጊዜ ሥራዎቹ ይጠቀሳሉ፡፡ ሠዓሊው በ25 እና በ50 ሳንቲም ላይም አሻራውን አኑሯል፡፡ አሁን በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በማስተማር ላይ ይሚገኘው ታደሰ፣ የበጎ ሰው ሦስተኛ ዙር ሽልማት ካገኙ መካከል አንዱ ነው፡፡ በተሸለመበት ዘርፍ አቶ አለ ፈለገሰላም፣ እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ፣ አቶ ተስፋዬ አበበና አቶ አባተ መኩሪያ ዕጩዎች ነበሩ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሌላው የውድድር ዘርፍ የቅርስና ባህል ዘርፍ ሲሆን፣ ‹‹የቱሪዝም አባት›› በሚል የሚታወቁት አቶ ኃብተሥላሴ ታፈሰ ተሸልመዋል፡፡ የ13 ወር ፀጋ በሚለው መርሐቸው በይበልጥ የሚታወቁት አቶ ኃብተሥላሴ፣ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትን በመመሥረትና በሌላም መልኩ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዕድገት ሠርተዋል፡፡

የቱሪስት መስህብ የሆኑ የአገሪቱን ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ሀብቶች በፖስተርና በፖስት ካርድ ላይ በማተም አገሪቱን በማስተዋወቅ ስማቸው ይጠራል፡፡ አቶ ዓለማየሁ ፈንታ፣ አቶ ዓለሙ አጋ፣ ማኅበረ ቅዱሳንና የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍት ማይክሮ ፊልም ድርጅት የቅርስና ባህል ዘርፍ ዕጩ ሆነው ነበር፡፡

በሌላ በኩል ከአምስት አሠርታት በላይ በኢትዮጵያ በእንግሊዝኛ ጋዜጠኛነት ታሪክ ስማቸው የሚጠራው አቶ ያዕቆብ ወልደማርያም በጋዜጠኝነት ዘርፍ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ አሁን ዘ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በኤዲተርነት የሚሠሩት አቶ ያዕቆብ፣ የኢትዮጵያ ሔራልድ ጋዜጣ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ ናቸው፡፡ በመነን መጽሔት፣ በቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ፣ ዘሰንና ፎክስ ላይ የሠሩ ሲሆን፣ በ1995 ዓ.ም. ግለ ታሪካቸውን የሚያትት መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ በዘርፉ ዕጩ የነበሩት አቶ መአረጉ በዛብህ፣ አቶ ነጋሽ ገብረማርያም፣ አቶ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስና አቶ ቴዎድሮ ፀጋዬ ነበሩ፡፡

የዚህ ዓመት የበጎ ሰው ሽልማት የተሰጠው በዘጠኝ ዘርፎች ሲሆን፣ የቢዝነስና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ ይገኝበታል፡፡ በዘርፉ አቶ ገብረሚካኤል፣ ሰላም ባልትና፣ አዋሽ ባንክ፣ ካፒቴን ሰሎሞን ግዛውና ካልዲስ ቡና ለውድድር ቀርበዋል፡፡ ያሸነፈው የቤተሰብ ኩባንያው ሰላም ባልትና ነው፡፡ ጉልት ላይ ይሸጡ የነበሩ እናታቸው አቅም ሲዳከም ወደ ባልትና ሙያ የገቡት ልጆቻቸው ነበሩ፡፡ የባልትና ውጤቶችን በላስቲክ አሽጎ በማሰራጨት የሚታወቀው ሰላም ባልትና፣ በዘርፉ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡

ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ አቶ ደሳለኝ ራህመቶ፣ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ፣ ፕ/ር ሺፈራው በቀለና ፕ/ር በላይ ካሳ በማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ ለውድድር የቀረቡ ዕጩዎች ናቸው፡፡ ያሸነፉት በግብርናና ገጠር ተኮር ጥናቶቻቸው የሚታወቁት አቶ ደሳለኝ  ናቸው፡፡ ለዓመታት ማኅበራዊ ጥናት መድረክን በዋና ዳይሬክተርነት የመሩት አቶ ደሳለኝ፣ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን ለአገሪቱ አበርክተዋል፡፡

ፕ/ር አበበ በጅጋ የሳይንስና ምርምር ዘርፍ አሸናፊ ናቸው፡፡ በዓይን ሕክምና  ቀደምት ከሆኑ ባለሙያዎች መካከል በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያገለግሉት ፕሮፌሰሩ፣ ከሕክምናው ጎን ለጎን በመምህርነትና በጥናትና ምርምር አበርክቷቸው ይጠቀሳሉ፡፡ በዘርፉ ፕ/ር ኢ/ር አበበ ድንቁ፣ ኬሚካል መሐንዲስ ጌታሁን ሔራሞ፣ ፕ/ር አሥራት ኃይሉና ዶ/ር ይርጉ ገብረሕይወት ተወዳድረዋል፡፡

በጉሙዝ ባህል የሴት ልጅ ደም ርኩስ እንደሆነ ስለሚታመን ሴቶች ከማኀበረሰቡ ተገልለው በጫካ እንዲወልዱ ይገደዳሉ፡፡ የእናቶችና ሕፃናትን ሕይወት የሚቀጥፈውን ይህን ልማድ ለማስቀረት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ የምትታወቀው ወ/ሮ ትርሐስ መዝገበ በበጎ አድራጎት ዘርፍ ተሸላሚ ሆናለች፡፡ ወ/ሮ አበበች ጎበና፣ አቶ አስመሮም ተፈራና አቶ ስንታየሁ አበጀ በዚሁ ዘርፍ ዕጩ ነበሩ፡፡

መንግሥታዊ ኃላፊነትን በብቃት በመወጣት በተሰኘ ዘርፍ አቶ ግርማ ዋቄ፣ አቶ መኰንን ማንያዘዋል፣ አቶ ሽመልስ አዱኛ፣ ኢ/ር ስመኘው በቀለና አማኑኤል ስፔሻላይዝና የአዕምሮ ሆስፒታል ተወዳድረው ነበር፡፡ አሸናፊው አቶ ሽመልስ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትርና በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ አቶ ሽመልስ የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት እንዲሁም በሌሎች ተቋማት በርካታ ሰብዓዊ ሥራዎች በመተግበር ይታወቃሉ፡፡

ሌላው የስፖርት ዘርፍ ሲሆን፣ ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ አሸንፈዋል፡፡ የአትሌቲክስ አሠልጣኙ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን ባሠለጠኑባቸው አምስት ኦሊምፒኮች 28 ሜዳሊያዎች አስገኝተዋል፡፡ ስማቸውም የአገሪቱን ስም ከሚያስጠሩ በርካታ ዕውቅ ሯጮች ጋር ተያይዞ ይጠራል፡፡ በስፖርት ዘርፍ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ መምህር ስንታየሁ፣ አትሌት መሠረት ደፋርና ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ ተወዳድረዋል፡፡

የውድድሩ ዕጩዎች የተለዩት በሕዝብ ጥቆማ ሲሆን፣ ለመጨረሻ ዙር ካለፉት ተወዳዳሪዎች መካከል አሸናፊዎቹ የተለዩት በዳኞች ምርጫ ነው፡፡ አሥር አባላት ባሉት የበጎ ሰው ኮሚቴ ልዩ ተሸላሚ ተብለው የተመረጡት በ2001 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ፊታውራሪ አመዴ ለማ ናቸው፡፡ የአክሱም ሐውልትን በማስመለስ፣ በአገር ሽማግሌነትና በሃይማኖት መቻቻል ያበረከቷቸው አስተዋጽኦዎች ለልዩ ሽልማቱ እንዳበቋቸው አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...