(ፎቶ በታምራት ጌታቸው)
*********
ይቅርታ
ዘመን ላልሻገር በተሰጠኝ ዕድሜ
ለምን እኖራለሁ ስንቱን አስቀይሜ
ላለፈው በደሌ ጠይቄ ይቅርታ
በፍቅር ተክቼ የጥላቻን ቦታ
ጊዜያዊ ነውና የምድር ቆይታ
ቂም በቀሌን ሽሬ ልኑር በይቅርታ
በሲስኮ (Sisco Ne)
*********
መስኮቱ
ባልና ሚስት ቤት ቀይረው አዲስ ሰፈር ገብተዋል፡፡ በነጋታው ቁርስ እየበሉ ሚስት በመስኮቱ በኩል ልብስ እያሰጣች ያለች ጎረቤቷን አየት አድርጋ ‹‹ልብስ አስተጣጠብ አትችልም እንዴ? እየው ቆሻሻ ልብስ ስታሰጣ!›› አለቺው ለባሏ፡፡ ባሏ ቀና ብሎ መስኮቱን አንዴ አየት አደረገና ምንም ሳይናገር ወደ ቁርሱ ተመለሰ፡፡ ይኼ ነገር ለብዙ ቀናት ተደጋገመ፡፡ አንድ ቀን ጠዋት ግን ሚስት ‹‹ኧረ ጎረቤቴ አለፈላት፤ ዛሬ ንፁህ ልብስ አሰጣች፡፡ ለመሆኑ በትክክል ማጠብ ማን ያስተማራት ይመስልሃል?›› አለች በአድናቆት ባል ከቁርሱ ቀና ብሎ ሚስቱን አየት አደረገና ‹‹ትላንት ማታ መስኮቱን ወልውዬ አፅድቼዋለሁ›› ብሎ መለሰላት፡፡
- ከድረ ገጽ
*******
…ይሻለኝ ነበር ባላውቅ
…ይሻለኝ ነበር ባላውቅ ማን ምን እንደሆነ፡፡ የወደድኩትን እንደወደድኩ ባልፍ፡፡ ያመንኩትን እንዳመንኩት፡፡ ስለዓለም አቀፍ ፍቅር ያስተማሩኝ ያገሬ ምሁራን እንዳልሰለጠኑ …ጉያቸው ተደብቆ የሚያዛቸው ብርማ ከርፋፋነት እንደነበረ ገባኝ፡፡
ዛሬ መልሰው ‹‹የሰው ልጅ›› የሚባል የለም፤ ያለው ‹‹የጅረቴ ልጅ›› ነው አሉኝ፡፡
የድብርት አብዮት ብቻ ቀረኝ፡፡ ውሽክሽክ ትልሞች ትልልቆቹን ሲጥሉ አየሁ፡፡ በጥቂት ስህተት ትልቅ መረገም ማን ተጎናጸፈ? በሚመስለኝ ተመታሁ፡፡ የወንድሜ እግር ተረጋግቶ ፊቴ ላይ ተረማመደ::
በቅርብ ያልነገሩኝን በሩቅ ሰማሁ፡፡
ቁርበቴን አይተው ስም ሰጡኝ፡፡
መሮጫ ጎዳናዬ እንዳለቀ ገባኝ፡፡
‹መሸሸጊያውም አልቋል› አልኩ……
- አዳም ረታ ‹‹ይወስዳል መንገድ፣ ያመጣል መንገድ››
*****
የመንግሥትነት የቅቤና የወተት ባህርይ
ቅቤ ከወተት ይወጣል፡፡ አይብም የሚወጣው ከወተት ነው፡፡
ይሁን እንጂ ቅቤ አንድ ጊዜ ከወተት ከወጣ በኋላ ተመልሶ ወተት ይሆናልን? አይብም አንድ ጊዜ ከሆነ በኋላ በቅቤነትና በአይብነት ልዩ ባህርይ ፈጥረው ይኖራሉ እንጂ ተመልሰው ወተት ይሆናሉን?
ታዲያ ሕዝብና መንግሥት አንድ ነው የሚባለው አነጋገር ስህተት አይመስሎትም?
እንደ ቅቤና እንደ አይብ መንግሥትነትም የሚወጣው በእርግጥ ከሕዝብ ነው፡፡
ነገር ግን አንድ ጊዜ መንግሥት ሆኖ ከወጣ በኋላ የመንግሥት ባህሪን ይዞ ይዘልቃል ወይም ይከስማል እንጂ ተመልሶ ሕዝብ የሚሆን ይመስሎታል?
ቅቤና አይብ ከተት የተለየ ጠቀሜታ እንዳለው ሁሉ መንግሥትነትም በመንግሥትነቱ ልዩ ጠቀሜታ ያለው አይመስሎትም?
ቅቤና አይብን የምንጠቀምባቸው ከወተት በተለየ በልዩ ይዞታና እንክብካቤ እንደመሆኑ መጠን መንግሥትነትንም ለመጠቀም የምንችለው ልዩ ቁጥጥርና ልዩ እንክብካቤ ሲኖረን ብቻ አይምስሎትም?
ታደለ ደርሰህ ‹‹ከዴሞክራሲ ሌላ ለሰላምና ለዕድገት ምን ይበጃል?›› 2003 ዓ.ም.
********************
ንጉሡና ወፉ
የአንድ አገር ገዢ የነበረ አንድ ንጉሥ ነበር፡፡ ይኸው ንጉሥ ለወትሮ እንደሚያደርገው ሁሉ አንድ ቀን ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳል፡፡ ይህ ፍርድ ቤት ንጉሥ ፍርድ በይፋ የሚሰጥበት ልዩ ችሎት ነው፡፡ ንጉሡም ወደዛው ችሎት ሄዶ ሙሉ ቀን እዚያው ከዋለ በኋላ በመመለስ ላይ እያለ እቤቱ ሳይደርስ ዝናብ መዝነብ ጀመረ፡፡
ታዲያ ሁልጊዜ ከዝናብ ለመጠለያነት የሚያገልግሉ መንታ ዛፎች በአካባቢው ነበሩና እንደዚህ ዓይነቱ ዝናብ በዚያ ጎዳና ላይ በዘነበ ጊዜ ሰዎች በዛፎች ስር ይጠለሉ ነበር፡፡ እነዚህ ዛፎች በዚህ ግልጋሎታቸው በሰፊው ይታወቁ ነበርና ንጉሡም በዚህ ቀን ከዝናቡ በእነዚህ ዛፎች ስር ተጠለለ፡፡
ንጉሡም በዛፎች ስር ተጠልሎ ሳለ ዝናቡ ዘንቦ፣ ዘንቦ፣ ዘንቦ፣ ኃይለኛ ንፋስ የቀላቀለ ማዕበልም ስለነበረ አንደኛው ዛፍ ሌላኛው ዛፍ ላይ እንዲወድቅ አደረገ፡፡ ንጉሡም ከሌላው ዛፍ ላይ ተጣበቀ፡፡ ሆኖም ንጉሡ ከዛፉ ጋር ይጣበቅ እንጂ አልሞተም ነበር፡፡ ነገር ግን ከአደጋው አምልጦ መሄድ ስላልቻለ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳለ ያለ ምንም አጋር በስፍራው ብቻውን ስለነበረ ንጉሡ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገባው፡፡
ቀኑም እየመሸ ነበር፡፡ በኋላም አንድ ቁራ መጥቶ በወደቀው ዛፍ ላይ ቁጭ ሲል ንጉሡ አይቶት ‹‹አንተ ማነህ እዚያ ላይ ከንጉሡ ዛፍ ላይ የተቀመጥከው?›› ብሎ ተጣራ፡፡
ቁራውም ‹‹እኔ ነኝ፣ ቁራ›› ብሎ ሲመልስ ንጉሡም ‹‹እባክህ አንድ መልዕክት ታደርስልኛለህ?›› አለው፡፡
ቁራውም ‹‹ጌታዬ ሆይ! ለንጉሡማ እንዴት መልዕክት አላደርስም፣ አደርሳለሁ እንጂ!›› አለ፡፡
መልዕክቱን ስትወስድ እንዴት ብለህ ትናገራለህ›› ብሎ ንጉሡ ሲጠይቀው ቁራውም እየጮኸ ‹‹ቁዋ፣ቁዋ እያልኩ ነው የማደርሰው፡፡›› አለው፡፡
‹‹ቁዋ፣ቁዋ አባክ ይጥፋና! ሂድ ከዚህ ጥፋ!›› አለ ንጉሡ፡፡ በዚህ ጊዜ ቁራው ንጉሡን ትቶት ሄደ፡፡
ከዚያም አንድ ወፍ መጥቶ ዛፉ ላይ ተቀመጠ፡፡
አሁንም ንጉሡ ‹‹ማነህ አንተ እዚያ ላይ በንጉሤ ዛፍ ላይ የተቀመጥክ? ማነህ? ማነህ?›› ብሎ ተጣራ
‹‹እኔ ወፍ ነኝ፡፡››
‹‹መልእክት ብልክህ ታደርሳለህ?››
‹‹አዎ ላከኝ፡፡››
‹‹መልእክቱንስ እንዴት ነው የምትነግረው?››
‹‹ጭር፣ጭር፣ምጭጫ ጩ፣ ንጭጫ ጩ እያልኩ አደርሳለሁ፡፡››
‹‹ምጭጫ ጩ አባክ ይጥፋ!››
ከዚህም በኋላ ሌላ አይነት ወንጂ የምትባል ወፍ መጥታ ዛፉ ላይ አረፈች፡፡ ንጉሡም እንደበፊቱ ‹‹ከንጉሡ ዛፍ ላይ የተቀመጥክ አንተ ማነህ?›› ብሎ ጠየቀ፡፡
‹‹እኔ ወፏ ወንጂ ነኝ፡፡››
‹‹መልዕክት ብልክሽ ታደርሻለሽ?››
‹‹አዎ! አደርሳለሁ፡፡››
‹‹መልዕክቱን እንዴት ነው የምትነግሪው?››
‹‹መልዕክቱን እንደዚህ እያልኩ በግጥም/በዘፈን አደርሳለሁ፤
‹‹ንጉሱ ወደ ስብሰባ ሄደ
ንጉሱ በችሎቱ ተሰየመ
ወደ ችሎቱም በሄደ ጊዜ ማካፋት ጀመረ
ከችሎቱም ሲመለስ እንደበፊቱ አካፋ
በሁለት ቀጋ ዛፎች ስርም ተጠለለ
ዛፎቹ ወድቀው አጣበቁት
ከትልቁ ቤት ላይ ትልቅ የብረት ቁራጭ
ከትንሹ ቤት ላይ ትንሽ የብረት ቁራጭ››
ይህም ማለት ንጉሡ ሁለት ሚስቶች ስለነበሩት ከዋናዋ ሚስቱ ቤት ትልቅ መጥረቢያ ከሁለተኛ ሚስቱ ቤት ትንሽ መጥረቢያ መምጣት እንዳለበት የሚያመላክት ነው፡፡
‹‹ከትልቁ ቤት ትልቅ በሬ፣
ከትንሹ ቤት ትንሽ ወይፈን፣
ገዝታችሁ እንድትመጡ፡፡››
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ‹‹በጣም ጥሩ ነው፡፡ በይ ሄደሽ ንገሪ፡፡›› ብሎ ወፏን ላካት፡፡
ወፏም ክንፏን እያርገበገበች ወደ ንጉሡ ቤት ሄዳ ሚስቱ ተቀምጣ ወደምትሰራበት የቤት ጓሮ ካለው ቁጥቋጦ ስር በመሆን ‹‹ኩሉ፣ ኩሉ፣ ኩሉ›› እያለች ድምጽ ስታሰማ (‹‹ኩሉ›› ማለት በሲዳምኛ ‹‹ልናገር፣ ልናገር›› ብሎ መጠየቅ ነው፡፡) ሴትየዋ ‹‹ኩሉ አባትሽ ይጥፋ፤›› አለቻት፡፡
ወፏም በርራ ከሄደች በኋላ ተመልሳ መጥታ ጩኸቷን ደገመችው፡፡ በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ‹‹ይህች ወፍ ምን ሆናለች?›› አለች፡፡
(የዚህች ወፍ ጩኸት እንደ ትንቢት ይቆጠር ስለነበረ አሁንም ክፉ ነገር ይዛ እንደሆን ብለው ሰዎቹ ፈሯት፡፡)
መጥፎ ዜና ይዛም መጥታ ይሆናል ብለው አባረሯት፡፡
ነገር ግን ወፏ ደጋግማ ስትመላለስ ‹‹በይ እሺ ንገሪን፤›› አሏት፡፡
‹‹ንጉሱ ወደ ችሎት ሄደ
ወደዚያም ሲሄድ ዝናብ ማካፋት ጀመረ
ሲመለስም ያካፋ ነበር
በሁለት ቀጋ ዛፎች ስርም ተጠለለ
ዛፎቹ ወድቀው አጣበቁት
ከትልቁ ቤት ላይ ትልቅ የብረት ቁራጭ
ከትንሹ ቤት ላይ ትንሽ የብረት ቁራጭ”
‹‹ከትልቁ ቤት ትልቅ በሬ፣
ከትንሹ ቤት ትንሽ ወይፈን፣
ይዛችሁ እንድትመጡ ብሏል፡፡››
በዚህ ጊዜ ሰዎቹ በፍራቻ ተውጠው የተጠየቁትን ነገሮች ይዘው ሄዱ፡፡ መጥረቢያዎቹ ዛፎቹን መቁረጫ ስለነበሩ የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ንጉሱን ለማዳን ሲረባረቡ በሬዎቹ ደግሞ በእንደዚህ ያለ አደጋ ጊዜ አለ ተብሎ የሚታመነውን የሰይጣን መንፈስ ለማባረር ደማቸው የሚፈስ ነው፡፡ በዚህ አይነት ንጉሡ ሳይጎዳ ወደቤቱ ሲመለስ ወፏን ይዟት ተመለሰ፡፡
ከተመለሰ በኋላም ንጉሡ ብዙ የእህል ማከማቻ ጎተራዎች ስለነበሩት ወፏን በአንደኛው ውስጥ አስቀመጣች፡፡ ወፏም ጥሬዋን ከጎተራው እየበላች እዚያው መኖር ጀመረች፡፡ ንጉሡም ወደ ችሎት ሄዶ ሲመለስ ግቢው ውስጥ እንደገባ በአንድ አይነት ድምጽ እንዲህ ይላታል፤
‹‹በክፉ ግዜ ከአደጋ አትርፈሽኛል
ከስቃይም አድነሽኛል፣ የእኔ ወፍ ሆይ አለሽልኝ?››
ወፏም ‹‹ጥሬው አለቀብኝ እንጂ እኔስ አለሁ፡፡›› አለች፡፡
ከዚያም ንጉሡ ካለችበት ጎተራ አውጥቶ ሌላኛው ውስጥ ያስቀምጣታል፡፡ ታዲያ በዚህ አይነት ሲኖሩ፣ሲኖሩ፣ሲኖሩ ለረጅም ጊዜ እርሱ ሄዶ ሲመለስ እርሷም እንደወትሮ ስትመልስ ቆይተው አንድ ቀን ንጉሡ ወደ ችሎቱ ሄዶ ብዙ ክርክሮችን ማስተናገድ ስለነበረበት ቶሎ መጨረስ ያቅተውና ከተለመደው ሰዓትና እመለሳለሁ ካለበት ጊዜ አርፍዶ ስለቆየ የወፏ ጥሬ በማለቁ ወፏ ከጎተራዋ ወጥታ በቤት ውስጥ ጥሬ መለቃቀም ጀመረች፡፡
የንጉሡ ሚስት የሆነ ነገር እየወቀጠች ወደ ነበረችበት ቦታ ስትሄድ ሚስቱ ‹‹አይ አንቺ ወፍ! አትረብሺኝ እባክሽ! ካለበለዚያ እመታሻለሁ፡፡›› አለቻት፡፡
ወፏም ‹‹እኔ እኮ የንጉሡ ልጅ ነኝ፡፡ እስኪ ንኪኝና የሚሆነውን ታያለሽ፡፡›› አለቻት፡፡
ይህንንም ብላ ጥሬዋን መልቀም ቀጠለች፡፡ ንግስቲቱንም አስቸገረቻት፡፡ ከዚያም ንግስቲቱ “የንጉሡ ልጅ ብትሆኚ የምተውሽ ይመስልሻል?” ብላ ወፏን ስትመታት ወፏ ሞተች፡፡
ወፏ በሞተች ጊዜ ታዲያ ንግስቲቱ ፈራች፡፡ ምን ማድረግ እንዳለባትም አላወቀችም፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ከችሎቱ ተመልሶ በተለመደ ድምጹ ወፏን ቢጣራም መልስ የሚሰጠው አጣ፡፡ ደጋግሞ ቢጣራም ምንም ድምጽ አጣ፡፡ ልጆቹንም ጠርቶ በየጎተራው ውስጥ እንዲፈልጓት ቢያደርግም ወፏ ልትገኝ አልቻለችም፡፡
በመጨረሻም ንጉሡ ‹‹ያዳነችኝ ወፌ በሌለችበት ቤት ውስጥ መኖር አልፈልግም፡፡›› ብሎ ራሱን ሰቅሎ ሞተ፡፡
የበኩር ልጁም ‹‹አባቴ በሌለበት ቤት ውስጥ መኖር አልፈልግም፡፡›› ብሎ ራሱን ሰቅሎ ሞተ፡፡
የንጉሡም እናት ‹‹ልጄና የልጅ ልጄ በሌሉበት ቤት ውስጥ መኖር አልፈልግም፡፡›› ብለው ተሰቅለው ሞቱ፡፡
በዚህ ሁኔታ እያንዳንዳቸው ሌላው ሰው በሌለበት ቤት አንኖርም እያሉ አለቁ፡፡
አመሰግናለሁ፡፡
በአበበ ከበደ የተተረከ የሲዳማ ተረት