Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየአውሮፓውንን ድንበር ለስደተኞች ያስከፈቱ ክስተቶች

የአውሮፓውንን ድንበር ለስደተኞች ያስከፈቱ ክስተቶች

ቀን:

ጀርመን ወደ አውሮፓ ብሎም ወደ አገሪቱ የሚጎርፉትን ስደተኞች ለመርዳት ስድስት ቢሊዮን ዶላር ለማውጣት ተስማምታለች፡፡ የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል ውሳኔ ግን ትችት እየተሰነዘረበት ነው፡፡

 ‹‹ጀርመን ድንበሯን ለስደተኞች ክፍት ማድረጓ አደገኛ ውሳኔ ነው፤›› ሲሉ የመርከልን ሐሳብ አንዳንዶች ሲያናንቁ፣ በሌላ በኩል የጀርመን የግዙፍ ፋብሪካ ባለቤቶች የስደተኞችን ወደ አገሪቷ መጉረፍ በጉጉት እየጠበቁት ነው፡፡ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ የጀርመን ግዙፍ ፋብሪካ ባለቤቶች በርካሽ ጉልበት ለማምረት ከዚህ የተሻለ መልካም አጋጣሚ የላቸውም፡፡

ጀርመናውያን መርከል አገሪቷን ለስተደኞች ክፍት ማድረጋቸውንና በጀት መመደባቸውን ጎዳና በመውጣት ነበር የደገፉት፡፡ በአሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችና ጎልማሶች ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ›› የሚል መፈክር ይዘው የጀርመን ጎዳናዎችን አጨናንቀዋል፡፡ አንዳንዶች የጀርመናውያንን እንግዳ ተቀባይነት ሲያደንቁ፣ አንዳንዶች ደግሞ ‹‹ጀመርን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የሠራችውን ግፍ ለመሸፈን ያደረገችው ነው፡፡ ሕዝቡም በነቂስ ወጥቶ ስደተኞች ይግቡ ያለው ያለፈ መጥፎ ታሪካቸውን በበጎ ለመቀየር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ጀርመን ስደተኞችን ለመቀበል መልካም ፈቃዷን ማሳየቷና ከሳምንታት በፊት በራቸውን ለስደተኞች ዝግ አድርገው የነበሩት ኦስትሪያና ሃንጋሪ መለሳለሳቸውን ተከትሎ፣ በሳምንት ውስጥ ብቻ 18 ሺሕ ስደተኞች ወደ አገሮቹ ገብተዋል፡፡ ጀርመን ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2015 ብቻ 500 ሺሕ ስደተኞች የመቀበል አቅም እንዳላት አስታውቃለች፡፡ የኦስትሪያ ቻንስለር ወርነር ፌይማን፣ ስደተኞች ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወደ አውሮፓ በመጉረፋቸው፣ በአውሮፓ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ ማብቃት አለበት ብለዋል፡፡

‹‹ስደተኞች የአውሮፓን መለሳለስ ዓይተው አመጣጣቸውን ቀስ በቀስ መደበኛ ያደርጉታል፤›› በማለት ሥጋታቸውን የገለጹት ደግሞ የሃንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር አርባን ናቸው፡፡ ሃንጋሪ ለስደተኞች ዝግ አድርጋ የነበረውን ድንበር ባለፈው እሑድ በመክፈት ስደተኞችን ወደ ኦስትሪያ ማጓጓዝ የጀመረች ቢሆንም፣ የስተደኞች መጉረፍ ሊቀነስ አልቻለም፡፡ ይልቁንም በሃንጋሪና በሰርቢያ ድንበር አካባቢ በብዛት እየጎረፉ ነው፡፡

በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን በሶሪያ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካና በዓረብ አገሮች መረጋጋት እስካልተፈጠረ ድረስ የስደተኞች ቁጥር ሊቀንስ አይችልም፡፡ በተለይም አይኤስ እና አልቃይዳ በኢራቅና በሊቢያ እንዲሁም በሶሪያ እያደረሱ ያለው ጥቃት አገሬው ቀዬውን ለቆ ወደ አውሮፓ እንዲጎርፍ ዋና ምክንያት ሆኗል፡፡ ኤርትራውያንም ወደ አውሮፓ በብዛት ከሚሰደዱ ዜጎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህም የአውሮፓ አገሮች የችግሩ የመጀመሪያ ተጠቂ ሆነዋል፡፡

የስደተኞቹ ከዓረብ አገሮች ወደ አውሮፓ መጉረፍ ግን ለአውሮፓውያን ሌላም ራስ ምታት ነው፡፡ ሚስተር አርባን እንደሚሉት፣ ስደተኞች ወደ አውሮፓ የሚጎርፉት በአገራቸው ሰላም ስላጡ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም በጀርመን ያለውን የተቀናጣ ኑሮ  ስለሚፈልጉ ነው፡፡ ይህም አውሮፓውያንን አደጋ ላይ ይጥላል ብለዋል፡፡

ወደ አውሮፓ የሚጎርፉት ስደተኞች በር እንዲከፈትላቸው ካስቻሉ ክስተቶች አንዱ፣ ባለፈው ሳምንት በዓለም መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆኖ የቆየው የአንድ ስደተኛ ሕፃናት አስከሬን በባህር ዳርቻ ተንጋሎና ውኃ ላይ ተንሳፎ መታየቱ ነው፡፡ ብዙዎች አስተያየየት ሰጪዎች ሕፃኑ የእንግሊዝ ወይም የአሜሪካ ወይም የጀርመን ዜጋ ቢሆን ኖሮ ዓለም ምን ይል ነበር? ሲሉ ትዝብት አዘል ትችት አጉርፈዋል፡፡ የቱርክ ባህር በርና የሜዲትራኒያን ባህር በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን መና አስቀርቷል፡፡ እንዳለፈው ሳምንት ክስተት ግን ዓለምን ያነጋገረ አልነበረም፡፡ የሕፃናት አስከሬን በባህር ውስጥ ተደፍቶና ተንጋሎ መታየቱ የሃይማኖት መሪዎችን ሳይቀር አነጋግሯል፡፡ አውሮፓ በራን ለስደተኞች ትክፈት እንዲሉም አስችሏል፡፡

የካቶሊክ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንሲስ በቫቲካን ሁለት የስደተኛ ቤተሰቦች እንደሚያስጠልሉ ተናግረው፣ ሁሉም በአውሮፓ የሚገኙ አብያት ክርስቲያናትና ገዳማት እንደሳቸው እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ከሶሪያ ወደ ካናዳ ለመግባት ከቱርክ ኮስ ደሴት በጀልባ ተነስትው ብዙም ሳይጓዙ በማዕበል ካለቁት 14 ሰዎች መካከል፣ ከሶሪያ ኩርድ ቤተሰቦቹ ጋር የነበረው የሦስት ዓመት ሕፃን ከወንድሙና ከእናቱ ጋር መሞቱ በቱርክ የሚገኙ በጎ ፈቃደኞችን ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝ የሚገኙትንም ማስተባበር ችሏል፡፡ የእንግሊዝ ጋዜጦች የሕፃኑን አስከሬን ከባህር ዳርቻ ታቅፎ ሲወስድ የነበረን የቱርክ ፖሊስ ባልደረባ ምሥል በፊት ለፊት ገጻቸው ይዘው ከወጡ በኋላ፣ ከአየርላንድ ሪፐብሊክ የገንዘብና የቁሳቁስ ዕርዳታ በማሰባስ ኮስ ደሴት ላይ በበጎ ፈቃደኝነት ለሚሠሩ የሚለግሱ ግለሰቦች ብቅ ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ሆኖም የመንግሥታት ትብብር ካልታከለበት በጎ ፈቃደኞች ለብቻቸው የሚያደርጉት እገዛ የስደተኞችን መጉርፍ ሊገታውም ሆነ ሊያቃልለው እንደማይቻለው እየተነገረ ነው፡፡

ቀድሞውንም በር ለመክፈት በውይይት ላይ ነበሩት የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች፣ በተለይም በራቸውን ዘግተው የነበሩት የተለሳለሰ አቋም ይዘው ስደተኞችን መቀበል ጀምረዋል፡፡ በዓረቦች የመዋጥ ሥጋታቸውንም ግን ከወዲሁ እየተናገሩ ነው፡፡ ቀድማ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለስደተኞች የመደበችውና በስደተኞች ጉዳይ መልካም አመለካከት ያላት ጀርመን ከኮሶቮ፣ ከአልባኒያ እንዲሁም ከሞንቴኔግሮ ከሚመጡ ስደተኞች በስተቀር ለማስተናገድ ሽርጉድ እያለች ነው፡፡ ሦስቱ አገሮች ሰላማዊ አገር በመሆናቸው በጀርመን ጥገኝነት የማያገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ አገሮች ወደ አገሪቱ ገብተው የተገኙም ወዲያውኑ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋሉ፡፡

ጀርመን 150 ሺሕ ስደተኞችን ሊያስተናግዱ የሚችሉ ተጨማሪ ስደተኛ  የመቀበያ ጣቢያዎች ለመገንባት ያቀደች ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ተጨማሪ ሦስት ሺሕ የፌዴራል ፖሊሶችን ታሰማራለች፡፡ ለስደተኞች ከዚህ ቀደም ይቆረጥላቸው የነበረው ገንዘብ የሚቆም ሲሆን፣ በምትኩ አስፈላጊው ቁሳቁስ በዓይነት ይሟላላቸዋል፡፡  አብሮ የመኖርና የቋንቋ ትምህርትም ተጠናክሮ ይሰጣል፡፡ ስደተኞቹም በ16 የጀርመን ፌዴራል ስቴቶች ይኖራሉ ተብሏል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ሥራ አስኪያጅ አንቶኒዮ ጉተርስ፣ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ከተባበሩ ስደተኞች በአውሮፓ ላይ የፈጠሩትን ጫና ማቃለል ይቻላል ሲሉ፣ ሃንጋሪ ግን ምንም እንኳን በስተደኞች ጉዳይ እየተለሳለሰች ብትመጣም ጀመርንን ከመውቀስ አልተቆጠበችም፡፡ ‹‹ጀርመን ስተደኞችን ያለገደብ ለመቀበል መወሰኗ ችግር ያለበትም ሆነ የሌለበት ወደ አውሮፓ እንዲጎርፍ ምክንያት ሆኗል፤›› ሲሉ ባለሥልጣናት ወቅሰዋል፡፡

ኮስ የተባለችው የግሪክ ደሴት ቀደሚዋ የስደተኞት መዳረሻ ናት፡፡ የሶሪያና የአፍጋኒስታን ስደተኞች የኮስ ደሴትን አጨናንቀዋል፡፡ በደሴቷ የሚገኙ የዕርዳታ ሠራተኞች እንደሚሉት ሰባት ሺሕ ስደተኞች በወደቧ ይገኛሉ፡፡ ስደተኞቹ ግን በቂ ዕርዳታ እያገኙ አይደሉም፡፡ በጎ ፈቃደኞች በሚሰጧቸው ዕርዳታና አገልግሎት ከወደቡ ተነስተው ወደተመኙት አገር ለመግባት የሚሄዱበትን ቀን ይጠባበቃሉ፡፡

በዓረብ አገሮችና በአፍሪካ ቀንድ ያለው ችግር ከሥር መሠረቱ ባለመቀረፉ ምክንያት ከጥር እስከ ነሐሴ 2007 ዓ.ም. ብቻ 350,000 ስደተኞች ወደ አውሮፓ ገብተዋል፡፡ የግሪክም ሆኑ የአውሮፓ ባለሥልጣናት መፍትሔ እንደሚሰጡ ሲነገር ቢቆይም፣ ችግሩ እየተባባሰ ሄዷል፡፡ በተለይ ከሶሪያ፣ ከአፍጋኒስታንና ከኤርትራ የሚጓዙ ስደተኞች አውሮፓን ተፈታትነዋል፡፡

በዚህ ወቅት 322,914 ስደተኞች ወደ አውሮፓ ሲገቡ፣ ከእነዚህ ውስጥ 2,432 በጉዞ ላይ ሞተዋል፡፡ 209,457 በግሪክ፣ 111,197 በጣሊያን እንዲሁም 2,166 በስፔን የሚገኙ መሆኑንም ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል፡፡

ኢራን አውሮፓ ስደተኞችን ለመቀበል በሯን መክፈቷን ስታደንቅ፣ በሌላ በኩል ትችት ገጥሟታል፡፡ ኢራን በሶሪያ ላለው ብጥብጥ ከኋላ ሆና ትረዳለች፡፡ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ሶሪያውያን ከአገራቸው እንዲሰደዱ አንዱ ምክንያት የኢራን ድጋፍ ነው ተብሏል፡፡

በሶሪያ ለሦስት ዓመታት የዘለቀው ብጥብጥ በሶሪያውያን ብቻ የተጠነሰሰ አይደለም፡፡ አሜሪካ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድን ለመጣል ሸማቂዎችን ስትረዳ፣ ኢራንና ሩሲያ ደግሞ የበሽር አል አሳድ መንግሥትን ይደግፋሉ፡፡ ጦርነቱ በምድረ ሶሪያ ይካሄድ እንጂ ፍቲጊያው ያለው በአሜሪካ፣ በሩሲያና በኢራን መካከል ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሶሪያውያን ወደ አውሮፓ ሲሰደዱ፣ ብዙዎችም አልቀዋል፡፡

በሊቢያም ሆነ በአፍጋኒስታን ያለው ብጥብጥ ከሶሪያ የተለየ አይደለም፡፡ ኃያላኑ ፍላጎታቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የሚመዙት ሰይፍ ለንፁኃኑ ስደትና ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ አሁን ደግሞ ችግሩ አውሮፓ ላይ ነግሷል፡፡ በአውሮፓ ጦርነት ባይኖርም በጦርነት የተሸበሩ ሕዝቦች እየጎረፉባት ነው፡፡ አሜሪካ በአገሮች የምታደርገው ጣልቃ ገብነት በተዘዋዋሪ አውሮፓውያን በሐሳብ እንዲከፋፈሉ፣ አንድ አቋም እንዳይዙ ብሎም በስደተኞች ሳቢያ ላልተጠበቀ ችግር እንዲጋለጡ እያደረገ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቱርክ ከማንም አገር በበለጠ በአሁኑ ጊዜ ከሶሪያ የተፈናቀሉ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን አስጠልላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...