Sunday, June 4, 2023

ኤርትራ የኢትዮጵያ ወረራ ያሰጋኛል አለች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ጳጉሜን 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ኤርትራን ለመውረር እያስፈራራች እንደሆነ አስታወቀ፡፡ ሚኒስቴሩ በመግለጫው ለዚህ አዝማሚያ በዋነኛነት ሕወሓትን ተጠያቂ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ ማስፈራሪያዎችን ከመጠቀም በተጨማሪ የተለያዩ አካላት ከኤርትራ ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲበላሽ እያሴረች እንደሆነም ይከሳል፡፡ ምንም እንኳ የመረጃው ምንጭ ማን እንደሆነ ባይታወቅም፣ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ኤርትራን ለመውረር የአሜሪካን ይሁንታ ማግኘቷን በይፋ መግለጿ አዲስ ነገር እንደሆነም አካቷል፡፡

በ2003 ዓ.ም. ኤርትራ በአዲስ አበባ የሚካሄውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ለማወክ ቦምብ ለማፈንዳት ያደረገችው ዝግጅትን መንግሥት እንዳከሸፈ ከገለጸ በኋላ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ የኤርትራን ትንኮሳ ወደፊት በዝምታ እንደማታልፍና ጠንካራና የማያወላዳ ዕርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቀው ነበር፡፡

ከአቶ መለስ ሕልፈተ ሕይወት በኋላ ኢትዮጵያን መምራት የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በ2005 ዓ.ም. ወደ ኳታር ባቀኑበት ወቅት ከአልጄዚራ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታሻሽል ‘አስመራ ድረስ ሄደው መነጋገር’ እንደሚፈልጉ መግለጻቸው የፖሊሲ ለውጥም ተደርጎ ተወስዶ ነበር፡፡ ይሁንና ከዚያ በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል ሰፍኖ የቆየው ውጥረት እየተባባሰበት እንጂ ለውጥ እየታየበት አለመምጣቱም አይዘነጋም፡፡

ይባስ ብሎ በሰኔ ወር ፓርላማ ቀርበው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ኤርትራን አስመልክቶ ሲናገሩ፣ ‹‹የኤርትራ መንግሥት አሁን በያዘው ፖሊሲ የሚቀጥልና ኢትዮጵያንና ሌሎች አጎራባች አገሮችን ለማተራመስ የያዘውን ስትራቴጂ የማይቀይር ከሆነ፣ ተገደን ዕርምጃ የምንወስድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይኼ በሚሆንበት ጊዜ የኢትዮጵያን ሕዝብ በማሳወቅ አስፈላጊውን ዕርምጃ ለመውሰድ የምንገደድበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ይኼንን ለዓለም ማኅበረሰብም አሳውቀናል፡፡ ሰላማችንን ለማስከበርና ራሳችንንም ለመከላከል አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰዳችን አይቀርም፤›› ማለታቸው የሁለቱ አገሮች በቃል የተገደበና አልፎ አልፎ መጠነኛ የአየር ጥቃት በማድረግ የታጀበውን ግንኙነት ወደ ተጠናከረ ወታደራዊ ግጭት ሊመራው ይችላል ተብሎም ተሰግቶ ነበር፡፡ በተለይ ‹‹መውሰዳችን አይቀርም›› የሚለው አባባል ጊዜው ባይታወቅም ጦርነት መኖሩ አይቀሬ ነው ተብሎም ተተርጉሞ ነበር፡፡

ነገር ግን የኤርትራ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት ሳይሰጥ ቆይቶ ነበር፡፡ ከሁለት ወር ዝምታ በኋላ ግን ጉዳዩ ሥጋት እንደፈጠረበት መግለጫ ማውጣቱ ጉዳዩን ይበልጥ ውስብስብ እንዳደረገው አስተያየት ሰጪዎች እየገለጹ ነው፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ አስተያየት ሰጪ ግን፣ በሁለቱ አገሮች መካከል በቅርብ ጦርነት ይነሳል ብለው አይገምቱም፡፡ ‹‹የኤርትራ ተቃዋሚዎች በኢትዮጵያ ሠልፍ ለማድረግ ያወጡት ዕቅድ አለ፡፡ ይኼ የኤርትራ መንግሥት ተመሳሳይ ሠልፍ በኤርትራ ለማድረግ እንዲረዳው ያወጣው መግለጫ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ውጪ የኤርትራ መንግሥት ለውስጥ ችግሮቹ ሁሉ የትኩረት ማስቀየሻው ኢትዮጵያ ነች፤›› ብለዋል፡፡

ኤርትራ ኢትዮጵያን ትቋቋማለችን?

በማንነታቸው በመኩራራትና የዓላማ ጽናት እንዳላቸው ከበፊት ጀምሮ በመደስኮር በተለየ ሁኔታ የሚታወቁት ኤርትራዊያን፣ ያለፍላጎታችን የኢትዮጵያ አካል ሆነናል በማለት ለ30 ዓመታት ያደረጉት የትጥቅ ትግል በ1983 ዓ.ም. ሲደመደም፣ ከሁለት ዓመታት በኋላ እስከ አሁንም ድረስ አወዛጋቢ በነበረው ሪፈረንደም (ነፃነት ወይስ ባርነት) አማካይነት ነፃነታቸውን ተቀዳጅተው ከኢትዮጵያ መገንጠላቸው ይታወሳል፡፡ ይሁንና ጦርነቱን ለማሸነፍ በአገር ውስጥና በውጭ ያለው ኤርትራዊ ሀብቱንና ጉልበቱን ቢያቀናጅም ይህንን በአዲሷ ኤርትራ ማስቀጠል ተስኖታል፡፡ ትንሽ ብትሆንም በተፈጥሮ ሀብት የታደለች በመሆኗ ‘በነፃነት ታጋዩ’ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካይነት ድል ማስመዝገቧ አይቀርም ተብሎ በምዕራባውያን የተገመተችው ኤርትራ የሰቆቃዎች ሁሉ ማዕከል ወደ መሆን መሸጋገሯን ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ ልትወረን ትችላለች በማለት እያስፈራሩ ተቃዋሚዎቻቸውን ፀጥ ማድረግና ኤርትራን ወታደራዊ አገር ለማድረግ አፍታም አልቆዩም፡፡ በአፍሪካ ሕገ መንግሥት አልባ በመሆን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ባለማሳተፍና ምንም ዓይነት ምርጫ ባለማድረግ፣ እንዲሁም የተቃውሞ ሐሳቦችን ባለማስተናገድ ምናልባትም ብቸኛዋ አገር ሳትሆን አትቀርም፡፡

የወርቅ ማዕድን ክምችቷን ማውጣት መጀመሯ በኢኮኖሚው ላይ መንሰራራት ፈጥሯል ተብሎ ቢነገርም፣ የኤርትራ ኢኮኖሚ የተንሰራፋውን ድህነትና ጉስቁልና መቋቋም የሚችል እንዳልሆነ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ በሚሰጡት ቀጭን ትዕዛዝ የኤርትራ እስር ቤቶች ከአፍ እስከ ገደፋቸው ሙልት እንዳሉ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ በኤርትራ እየደረሰ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የፖለቲካ ጭቆና ወደ ዘር ማጥፋት መሸጋገሩን በቅርቡ የወጣው የተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ሪፖርት ያሳያል፡፡ በኤርትራ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በገመገመው ኮሚሽን አማካይነት የወጣው ሪፖርት መጠነ ሰፊ የሆኑና አሰቃቂ የመብት ጥሰቶች የሥርዓቱ መገለጫ እንደሆኑ ይፋ አድርጓል፡፡

በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኤርትራን የግል ንብረቱ በማድረግ ያለተጠያቂነት የፈለገውን እንደሚያደርግ የጠቆመው ሪፖርቱ የሐሳብ ነፃነት፣ የመሰብሰብና የመደራጀት ነፃነትን ጨምሮ የፖለቲካ ነፃነት ባለመኖሩ የሰው ልጅ ሕይወት በቀላሉ በየቀኑ እየተቀጠፈ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

ተመድ ከዚህ በፊት ባወጣቸው ሪፖርቶችም የኤርትራ መንግሥት በዜጎቹ ላይ ከሚያደርሰው መጠነ ሰፊ ስቃይ በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ አጎራባችና አካባቢያዊ አገሮችን በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እየበጠበጠ እንደሆነ መደምደሙ ይታወሳል፡፡ በተለይ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውንና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው በይፋ የሚናገረውን አሸባሪውን ቡድን አልሸባብን ትረዳለች መባሉን በምርመራ አረጋግጫለሁ ካለ በኋላ፣ በኤርትራ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦች መጣላቸውም የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጣዊና ውጫዊ ውጥረት ውስጥ የምትገኘው ኤርትራ ጦርነት ቢቀሰቀስ ኢትዮጵያን ትቋቋማለች ወይ በሚል ጥያቄ የሚነሳውም ለዚህ ነው፡፡

‹‹የሁሉም ነገር ተጠያቂ ኢትዮጵያ ነች!››

ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለሚደርስባት ውግዘት ኤርትራ ሁሌም የችግሩ ምንጭ ኢትዮጵያ ነች በማለት ማሳበቧ የተለመደ ነው፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴር መግለጫው የኤርትራ ወጣቶች ከኤርትራ የሚሰደዱት የኢትዮጵያን ጥቃት በመፍራት ነው ሲል፣ በቅርብ ጊዜ ትልቅ ትኩረት የሳበው ችግር መነሻን ወደ ኢትዮጵያ አስተላልፏል፡፡

ተገደው ወታደር እንዲሆኑና የግዴታ የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ መደረጉን በዋነኛነት ተቃውመው ከኤርትራ የሚሰደዱት ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የተመድ ሪፖርቶች በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡ በየወሩ እስከ 5,000 ኤርትራዊያን እንደሚሰደዱ የሚጠቁሙት ሪፖርቶች፣ ዋነኛው ምክንያት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑንም ያስገነዝባሉ፡፡ ከሶሪያና ከአፍጋኒስታን ቀጥሎ ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩት በብዛት ኤርትራዊያን እንደሆኑም ይጠቁማሉ፡፡

የኤርትራ መንግሥት መሰል ወቀሳዎችን በኢትዮጵያ ላይ ማቅረቡ የተለመደ ሲሆን፣ ለአብነትም በጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም. የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥትን (ኢጋድ) እንዳትቀላቀል ኢትዮጵያ መሰናክል እንደሆነች በኬንያ የኤርትራ አምባሳደር አቶ በየነ ርዕሶም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ አምባሳደር በየነ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የምታቀርባቸው ወቀሳዎች በሌሎች አገሮች ተቀባይነት እያገኙ በመምጣታቸው አሳሳቢ እንደሆነም ገልጸው ነበር፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ተለያይተው በሰላም ለመኖር ከ1985 ዓ.ም. እስከ 1990 ዓ.ም. የሞከሩ ቢሆንም፣ በ1990 ዓ.ም. በሁለቱ አገሮች መካከል ጦርነት ተነስቶ የብዙ ሺሕ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ሕይወት መቀጠፉ ይታወሳል፡፡ በ1992 ዓ.ም. የተደመደመው ጦርነት ዘላቂ መፍትሔ እንዳልተገኘለት ግን በርካታ የድኅረ ጦርነቱ ድርጊቶች ያሳያሉ፡፡

ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ይሰጣሉ የተባሉት የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔዎችም በሁለቱም አገሮች በጋራ ተቀባይነት ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ኤርትራ ድንበሯን አስመልክቶ የምታቀርበው ክርክር በጣሊያን እ.ኤ.አ. በ1934 የተፈረመውን ስምምነት መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ግን እ.ኤ.አ. በ1908 በአፄ ሚኒሊክ በተፈረመው ስምምነት ላይ ትመሠረታለች፡፡

በየካቲት 1992 ዓ.ም. በተደረገው የአልጀርስ የሰላም ስምምነት መሠረት እንዲቋቋም የተደረገው የኢትዮጵያና የኤርትር ድንበር ኮሚሽን ጦርነቱን የጀመረችው ኤርትራ መሆኗን የወሰነ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ እንድትለቅ የወሰናቸው ቦታዎችን መቃወሟ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ቦታዎችን ያለ አሳማኝ ምክንያት ከመክፈል በድርድር ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት የተሻለ አማራጭ ነው በሚል ትከራከራለች፡፡

ሁለቱ አገሮች ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ መጠነኛ ትንኮሳዎችን አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ከማድረግና አንዳቸው የሌላኛቸውን ተቃዋሚ በግልጽም ይሁን በድብቅ ለመርዳት ከመሞከር ውጪ፣ ወደ ሙሉ ጦርነት የመመለስ አዝማሚያን በግልጽ አሳይተው አያውቁም፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት የታዩት ምልክቶች ግን አንዳንድ ወገኖችን ጥርጣሬ ላይ ከመጣል አልተመለሱም፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ አንዳንድ ወገኖች ግጭቱ የጥቂት ልሂቃን በመሆኑ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር መልካም ጎረቤት አገሮች እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ኤርትራ እንደ አገር መቀጠሏ አጠራጣሪ ነው የሚሉ ሌሎች ወገኖች ደግሞ ድኅረ ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ ጋር መልሳ እንድትቀላቀል ይፈልጋሉ፡፡ ኢሕአዴግ በተለይ ሕወሓት የመልካም ጉርብትና ጉዳይን የሚቀበል ቢሆንም መልሶ መቀላቀል የሚለውን ጉዳይ አምርሮ ይቃወማል፡፡

ሪፖርተር በኤርትራ መንግሥት መግለጫ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተለያዩ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -