Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለቤቶች ግንባታ የሚውል የአርማታ ብረት ግዥ ጨረታ ቅሬታ አስነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራ ጀመረ

      የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ የሚውል አርማታ ብረት ግዥ ያወጣው ጨረታ ቅሬታ አስነሳ፡፡ በአርማታ ብረት ግዥ የቀረበው ቅሬታ ለፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የደረሰ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ በቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የብረት ግዥ ጨረታ ላይ ምርመራ መጀመሩ ታውቋል፡፡

      ፀረ ሙስና ኮሚሽን ነሐሴ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ለአዲስ አበባ አስተዳደር ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ፣ ጽሕፈት ቤቱ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ያካሄዳቸው የአርማታ ብረት ግዥ መረጃዎች በሙሉ እንዲላኩለት ጠይቋል፡፡

በዋነኛነት በአርማታ ብረት ግዥ ጨረታው ቅሬታ የቀረበው በብረት አቅራቢ ነጋዴዎች ነው፡፡ የቅሬታው ማጠንጠኛም የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለአገር ውስጥ አምራቾች ብቻ ውስን ጨረታ በማውጣቱና ለብረት አቅራቢዎች ለውድድር በሩን መዝጋቱ ነው፡፡

የቤቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት ለአምስት አምራቾች ብቻ ውስን ጨረታ በማውጣት ለአንድ ኪሎ ግራም የቀረበው የመጫረቻ ዋጋ እጅግ የተወደደ በመሆኑ፣ ከቀረበው ዋጋ በተነፃፃሪ ባነሰ ዋጋ ማቅረብ እየተቻለ ሆን ተብሎ ከውድድር እንድንወጣ ተደርገናል የሚል ቅሬታ ከብረት አቅራቢ ነጋዴዎች ቀርቧል፡፡ ቅሬታውን ያቀረቡት በብረት ንግድና በሚስማር ማምረት የተሰማሩ ባለሀብቶች ሲሆኑ፣ ቅሬታቸውን ባቋቋሙት የኢትዮጵያ ሚስማር አምራቾች ማኅበር አማካይነት ማቅረባቸው ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ብረት አቅራቢዎቹ አጣዳፊ ጉዳይ በሌለበት ሁኔታ ውስን ጨረታ መውጣቱን ተቃውመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ባወጣው ውስን ጨረታ አምስት አምራቾችን ጋብዟል፡፡

ከተጋበዙት ኩባንያዎች አራቱ ግዥ እንዲፈጽሙ የተፈለገው 20 ሺሕ ሜትሪክ ቶን አርማታ ብረት እንዲያቀርቡ ከተመረጡ አምስት አምራቾች መካከል ብረት ለማቅረብ ፍላጎት ያሳዩ አራቱ ናቸው፡፡

ነገር ግን እነዚህ ኩባንያዎች ያቀረቡት የመጫረቻ ዋጋ ከፍተኛ ነው በሚል ምክንያት ቅሬታ በመነሳቱ፣ የጨረታው ውጤት እንዲሰረዝ መደረጉ ተገልጿል፡፡

ተወዳዳሪ ኩባንያዎቸ ለአንድ ኪሎ አርማታ ብረት ያቀረቡት የመወዳደሪያ ዋጋ ከ21 ብር በላይ ስለሆነና የዓለም አቀፍ የአርማታ ብረት ዋጋ የወረደ በመሆኑ፣ በቀረበው ቅሬታ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጨረታው እንዲሰረዝ ማድረጉ ታውቋል፡፡

ከዚህ በኋላም የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. አሥር ሺሕ ሜትሪክ ቶን አርማታ ብረት ለመግዛት ለእነዚህ አምራች ኩባንያዎች ውስን ጨረታ አውጥቷል፡፡

በዚህ ውስን ጨረታ አንድ ድርጅት ለወጣው ጨረታ በአግባቡ ሰነድ ባለማቅረቡ የተሰረዘ ሲሆን፣ የተቀሩት ተወዳድረዋል፡፡ እነዚህ ተጫራቾች በአንድ ኪሎ ግራም ያቀረቡት የመጫረቻ ዋጋ አሁንም ከፍተኛ ነው በማለት ቅሬታ የሚያቀርቡ ብረት አስመጪዎች፣ ከዚህ ዋጋ ባነሰ የሚፈለገውን ብረት ማቅረብ እንደሚችሉ በመጥቀስ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በማኅበራቸው አማካይነት የሚገልጹት ቅሬታ መንግሥት ለብረት ፋብሪካዎች በርካታ ጥቅሞችን ሰጥቷል፡፡ ከተሰጣቸው ጥቅም ውስጥ ጠገራ ብረት ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ፣ ፋብሪካ የሚገነቡበት ብድር በማቅረብ የአምስት ዓመት የታክስ ዕፎይታ ጊዜና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ነገር ግን በጨረታው ሒደት ቅድሚያ እየተሰጣቸው ከመሆኑም በላይ ለውድድር የሚያቀርቡት ዋጋ ከፍተኛ ስለሆነ ጉዳዩ ሊታይ ይገባል እያሉ ነው፡፡

‹‹እኛ ይህ ዕድል ሳይሰጠን ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ቀረጥ ከፍለን የምናቀርበውን ብረት ከዚህ ባነሰ ዋጋ መሸጥ እንችላለን፤›› በማለት መንግሥት ጉዳዩን እንዲያጤነው ነጋዴዎቹ በደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገነባቸው ቤቶች በአነስተኛ ዋጋ ተገንብተው ለኅብረተሰቡም በአነስተኛ ዋጋ እንዲከፋፈሉ የሚያደርግ ዓላማ የያዘ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ንጉሥ ተክላይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቤቶች ግንባታ ወቅት ዋጋ፣ ጥራትና ጊዜ ለድርድር አይቀርቡም፡፡

‹‹እነዚህ ሦስት አንኳር ነጥቦች ከተሟሉ ከአገር ውስጥ ብረት አምራቾች ግዥ ይፈጸማል፤›› በማለት ጽሕፈት ቤቱ የሚከተለውን መርህ አስረድተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የአገር ውስጥ አምራቾችን የሚያበረታታ መሆኑን አቶ ንጉሥ ገልጸው፣ ነገር ግን የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማሳደግ ተብሎ ብቻ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የተነሳበትን መርህ አይጥስም ብለዋል፡፡ አቶ ንጉሥ ጨምረው እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም የወጡ የብረት ግዢ ጨረታዎች ሒደት ረዥም ጊዜ የወሰደ በመሆኑ በአስቸኳይ ለግንባታ የሆነ ብረት እጥረት ተፈጥሯል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ሲባል ውስን ጨረታ መውጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የወጣው ጨረታና በሒደት ላይ ቢሆንም ቀደም ብሎ ለወጣው ጨረታ ከፍተኛ ዋጋ በመቅረቡና ጨረታ በሚወጣበት ወቅት ስህተት በመፈጠሩ ምክንያት ጨረታው እንዲሰረዝ መደረጉን አቶ ንጉሥ ገልጸዋል፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ብረት አቅራቢ ነጋዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ የአርማታ ብረት ግዥውን ለአምራቾችም ለአቅራቢዎችም ክፍት ማድረግ አለበት፡፡ በተለይ የፋይናንስ ጨረታ ከተከፈተ በኋላ በዋጋ ድርድር ቢደረግ አስተዳደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዋጋ ሊያገኝ ይችላል በማለት ተናግረዋል፡፡

በ2007 ዓ.ም. በግንባታ ላይ ከዋለው 6.3 ቢሊዮን ብር ውስጥ አራት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለተለያዩ የግንባታ ዕቃዎች ግዥ የዋለ ነው፡፡ ለቤቶች ግንባታ አርማታ ብረት፣ ሲሚንቶ፣ የፕላስቲክ ውጤቶችን ጨምሮ 528 ዓይነት የግንባታ ዕቃዎች አገልግሎት ላይ ይውላሉ በማለት አቶ ንጉሥ ተናግረዋል፡፡ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለሚያካሂደው ግንባታ በዓመት 140 ሺሕ ሜትሪክ ቶን አርማታ ብረት ይፈልጋል፡፡ ከዚህ ውስጥ በአገር ውስጥ አምራቾች አቅም የሚሸፈነው ከ40 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እንደማይበልጥ አቶ ንጉሥ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች