ውብ የአበባ-ማር መጣጭ (Beautiful Sunbird-Nectarinia pulchella) ረጅም ቀጭን መንቆር ያላቸው ትናንሽ ወፎች፡፡ ወንዶቹ ከላይ አብለጭላጭ አረንጓዴ ቀለም፣ በደረታቸው ላይ ደግሞ በጎኑ ብጫ የሆነ ደማቅ ቀይ ጥብጣብ አላቸው፡፡ የከብድ ቀለማቸው ግን ከአንዱ አንዱ ይለያያል፡፡ ረጅም ጅራትም አላቸው፡፡ ሴቶቹ ከላይ ወይራ ቀለም፣ ከታች ደግሞ ደብዘዝ ያለ ብጫ ደረትና ሆድ አላቸው፡፡ ከዓይናቸውም በላይ ነጣ ያለ ሰረዝ ይታያል፡፡ በደንም ሆነ በሜዳም ሥፍራ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በሚያብቡ ተክሎችና በግራርማ አካባቢ ይታያሉ፡፡
********
ግራጫ የአበባ-ማር መጣጭ
ግራጫ የአበባ-ማር መጣጭ (Amani Sun Bird-Anthreptes reichenowi) አመዳማ ሰማያዊ መልክ ያላቸው ትንሽ ወፎች፡፡ ወንዶቹ ከላይ አመዳማ ሰማያዊ፣ ከታች ደብዘዝ ያለ ብጫ ሎሚ፣ ቀለም አላቸው፡፡ ከግንባራቸውና ከጉሮሮአቸው ላይ አብለጭላጭ ጥቁር ሰማያዊ እራፊም ይታያል፡፡ ሴቶቹ ግን በወንደቹ ግንባርና ጉሮሮ ላይ የሚታየው ሰማያዊ ቀለም አይታይባቸውም፡፡ በጫካማ ሥፍራዎች በዛፎች ጫፍና ከሥር ከሚበቅሉ አትክልቶች ውስጥ ይገኛሉ፡፡
- ከበደ ታደሰ ‹‹የኢትዮጵያ መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ወፎች የኪስ መጽሐፍ›› (2000)