Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅ‹‹መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ . . .››

‹‹መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ . . .››

ቀን:

መስከረም መስከረም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የተለየ ወር ነው፡፡ አስራ ሶስት ወር ያለውን ማን ሀገር አለ? የማን ሀገር ዘመን መለወጫ ምድሩ በአበባ ፈክቶ አፍላጉ ከደለል ይጠራል፡፡ ሲጀመር ማንስ ቀን ቀምሮ? በዓለም ከአንድ እጅ ጣት ቁጥር የማይበልጡ ህዝቦች ስልጡን የቀን አቀማመር ስልት አላቸው፡፡ አንዱ ነን፡፡ እኛ ዘመን የምንለውጥበት ወር መስከረም ይባላል፡፡

ስልጤዎች ጳጉሜን ናት ቀን ያደለችው ይላሉ፡፡ በተረካቸው ጳጉሜን ሲገልጿት ለራሷ ብዙ እላለሁ ብላ እጇ ላይ አምስት ቀረ ሲሉ ይነግሩላታል፡፡ ጳጉሜን 13ኛዋ ወራችን ናት፡፡ ከዓለም አንድ ርቀን ትርፍ ወር የምንኖርባት የብልጠትና የእውቀት እሴታችን ማሳያ፤ ለዚህም ነው የመስከረም ዋዜማ የሆነችው፡፡

ብዙዎች ቀን በራሳችን የምንቆጥር ነን ስንል አይገረሙበትም፤ ሊያውም የኛ ሰዎች፤ መጀመሪያ ሰው ቀንን ያገኘበት ቁጭ ብሎ አይቀምረውም፡፡ ዕለት ሳምንት ወርና ዓመታት በስልት ባይቀመሩ ትናንት ዛሬና ነገ ብቻ ብለን መኖር እንዳንችል ማወቃችን ብቻውን በበቃ፤ ግና ባሕረ ሐሳብ ከዚህ ይልቃል፡፡ ጥበብ ነው፡፡ ሰማያት መጥቆ ከከዋክብት የሚነጋገር ከጨረቃ የሚመካከር፤ ዝም ብለን አንድ አንልም፤ ዝም ብለንም ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀን የለም፡፡ ከመሬት ተነስተን ጳጉሜን ስድስት አንከታትም፡፡ ዘመን ማስላት ዘመን የማይሽረው ጥበብ ነው፡፡

ደግሞ እንለያለን የምንለው ከሌላው ለመብለጥ አይደለም፡፡ መለየት መብለጥ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ መፈጠር ነው፡፡ አዲስ ዓመት ስንል አዲስ አበባ እናያለን፤ አዲስ ወፍ ትመጣለች፡፡ አዲስ መስቀል እናከብራለን፡፡ ከንባታዎች ስንት መስቀል ኖረሃል ይላሉ፡፡ መስቀልን ሲያሰሉ ዘመን ይቆጥራሉ፤ መስቀል የወርሃ መስከረም ውበት ነው፡፡

ወንዞቻችን በሰው ተመከሩ አንልም፤ ይልቅስ ተፈጥሮ ከአበቅቴው አስማምታ ከዘመን ጋር ትሞሽራቸዋለች፡፡ ‹‹መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ እንኳን ሰው ዘመዱ ይጠይቃል ባዳ›› ብለው ያዜሙት ከያኒያን ከሰማይ የወረደላቸውን መገለጥ አይደለም፤ ከዘመናቸው የኖሩትን ነው፡፡ የመስከረምና የአዲስ ዘመን ብስራት ኑሮአችን ነውና እንለየዋለን፡፡ የኛ ይለያል ስንል ከሚዘልቅ ስሜቱ ጋር ነው፡፡

መስከረም አንድ ጠዋት አብያተ ክርስቲያናት ባሕረ ሐሳብን ያውጃሉ፡፡ ዓመቱ መስከረም አንድ ይተነተናል፡፡ መስከረም ከሴቶቻችን ማጀት እስከ አደባባዮቻችን ድረስ የአዲስ ዘመን ቅርጽን ዳግም የሚይዙበት የክት ወር ነው፡፡ ጳጉሜን እድለኛነቷ ከሚናፈቀው ወር ቀድማ መጥታ ሳታሰለች ትከርማለች፡፡ በገበሬው ቁጥር መጠጋት የጀመረው የወር ደመወዝተኛ ጳጉሜን ደመወዝ አልባ የሚያሳልፍባት በመሆኑ ስንት ዘመን ከአባቶቻችን ጋር በስስት የኖረችዋ ወር እንደተረገመች ተቆጠረች፡፡ ግና ደመወዝተኛ ሳይኖር ጳጉሜን ከኢትዮጵያውያን ጋር ነበረች፡፡

ግና ሰላሳ ቀን ሠርቶ አንድ ቀን መከፈል የሚባል ብልጠት ሳይመጣ ጳጉሜን ኢትዮጵያውያን በናፍቆት ተጠባብቀዋል፡፡ ጳጉሜ ተመን የሌላት ከደፈረሰ ወንዝ ማዶ ያለች መዝለያ ናት፡፡ ጳጉሜን እንደ ላብ በሩፋኤል ጠበል ስናጥባት፣ ጳጉሜን ከነወዟ በራሷ ካፊያ ስናጸዳት አዲስ ዘመን ይቀበለናል፡፡ ነው መስከረም፡፡ ትምህርት ቤት ክረምት መከፈት ሳይጀምር፣ ወዳጅ ዘመድ ድልድይ ረግጦ ሳይጠያየቅ፣ ወንዞች የጎርፍ ድርቅ ሳይመታቸው በፊት የነበረው መስከረም ሁሌም አለ፡፡ ከአደይና ጠፍታ ከምትመጣው ወፍ ጋራ፡፡

  • ሔኖክ ስዩም በፌስቡክ ገጹ እንደከተበው

***************

እኔ እወድሻለሁ

             በገብረክርስቶስ ደስታ

 ብዙ ሺሕ ዘመናት
እልፍ አእላፍ ሌሊት
ሚሊዮን መሰለኝ
ፍቅሬ አንችን ስወድሽ ቀኑ ረዘመብኝ።
እኔ እወድሻለሁ
የሰማይ መሬቱን
የባህር ስፋቱን
የዓለም ዳርቻ የርቀቱን ያህል
እንደ ፅጌረዳ
እንደ አደይ አበባ
እንደ ሎሚ ሽታ፡፡
እንደ እጣን ጢስ እንጨት፣ እንደ ከርቤ ብርጉድ፣
እኔ እወድሻለሁ፣
አበባ እንዳየ ንብ፡፡
እንደ ቢራቢሮ ጫካ እንደሚያስሰው
ፍቅርሽን በፍቅሬ በፍቅርሽ ልቅመሰው
ማር ወለላዬ ነሽ ከረሜላ ስኩዋር
አማርኛ አይበቃ፤
ወይ ጉድ!
ባለም ቋንቋ ሁሉ ቢወራ ቢነገር፣
እኔ እወድሻለሁ
እንደማታ ጀንበር።
እንደ ጨረቃ ጌጥ፣ እንደ ንጋት ኮከብ፣
እኔ እማልጠግብሽ
ስወድሽ፣ ስወድሽ፣ ስወድሽ፣ ስወድሽ፡፡
ጡት እንዳየ ህፃን ወተት እንዳማረው
ጠጋ በይ ዘመዴ አፍሽ ህይወቴ ነው።
ጣይ እንዳየ ቅቤ
ገላዬ ገላሽን ሲነካ የሚያልቀው፣
አፈር መሬት ትቢያ ውሃ እንደሚበላው፣
ፍቅሬ አንቺን ስወድሽ
ብዙ ሺህ ዘመናት
እልፍ አእላፍ ሌሊት
ውድ እወድሻለሁ፣
ዐይኖችሽን ባይኔ ተዳክሜ እያየሁ
ስወድሽ ስወድሽ እኔ እወድሻለሁ።

***************

ኢትዮጵያ የቀለንቶን (ካሌንደር) ሀብታም

አዲሱ ዓመት መጣ!! አዲስ ምድር!! አዲስ ተስፋ…..የኔ አገር ዘመኗን የምትቀይረው ወረቀት ላይ አይደለም፡፡ ዘመኗ ከተፈጥሯ የተመሳጠረ ነው፡፡ እውነቷን ተፈጥሮ ትጋራታለች፡፡ የጠፋች ወፍ ዳግም የምትታይበት፣ አስፈሪ አፍላግ አደብ የሚገዛበት፣ እንደ ሰከረ ሰው ዓይን ገላው የደፈረሰ ኩሬ ጋቢ የሚመስልበት የሆነ አስማት፤ አስማተኛ ሀገር፣ አስማታዊ የዘመን ቀመር፤
አሉ እንጂ ወረቀት ላይ ዘመን የሚቀይሩ፣ ከበረዶ ወደ በረዶ፣ በረዶው ሲያልፍ በረዶ ሲመጣ፣ የጥላሁን ገሰሰ ክረምት አልፎ በጋ ዘፈን የማያውቁ፤ ደግሞ አንዳንዱ አለ ከኔም ሀገር ቀን መቁጠር ጥበብ የማይመስለው፡፡ የዚህን ዓይነቱ ሰው ሞኝነት እንደ ክረምቱ ጭጋግ ይግፈፍለት፡፡

አሥራ ሦስት ወር ያለው ሀገር የለም፡፡ በእርግጥ አሥራ ሦስተኛ ወርን ሠርቶ የወር ደመወዝ የተነፈገ ህዝብ የሚኖርበት ሀገርም የለም፤ ከእኛ ውጪ….
መስከረም የብዙ ነገራችን መልክ ነው፡፡ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ገጽ ከመስከረም አዲስ የተስፋ ምስጢር ጋር ይመሳጠራል፡፡ መስኩ በአደይ ያሸበርቃል፡፡ አደይ ሳይመቻት ቀርታ ሀገሬ ተራቁታ አታውቅም፡፡ ለመስከረም ቢጫ ልብስን የምትጎናጸፍ ሀገር ከእኔ ሀገር ውጪ ያለ አይመስለኝም፡፡ ቢኖርም አልኮራበትም….የምኮራበትን አደይ በየዓመቱ እዘፍነዋለሁ፡፡

ብዙው ያላወቀው ትልቅ ጉድ የኔ ሀገር የቀለንቶን (ካሌንደር) ሀብታም መሆኗን ነው፡፡ ሲዳማ የራሱ ቀን አቆጣጠር፣ የራሱ የስነ ከዋክብት ልኬት ጥበብ አለው፡፡ ፊቼ ጨምባላላ የሲዳማ ዘመን መለወጫ ነው፡፡ ጠንባሮ በሪ ወሊሶ ይለዋል የዘመን ቀመሩን የጠንባሮ

አዲስመት መጋቢት ነው፡፡ ኮንሶ ደግሞ አለላችሁ በወርሀ ጥር ዘመኑን የሚቀይር፤ የያም ኢልቅ የስልጤዎች የዘመን መለወጫ ነው፡፡ መሰሮ ይሉታል ሰኔ ወርን የስልጤ አዲስ ዓመት ሰኔ ወር፡፡ በመስከረም ዘመን የሚቀይሩት ጊዲቾዎች የቀን ቀመራቸው ከጨረቃ ስሌት ጋር ይቆራኛል፡፡ ደግሞ ጳግሜ አምስት ቀን አለችላችሁ የዳውሮዎች ዘመን መለወጫ ቶክቢያ ይሉታል፡፡ መስከረም የዚህች ሀብታም የቀለንቶን ምድር የወል ፌሽታ ነው፡፡ የጋራ እሴት መሆኑን ከዳር ዳር በአደይ ውበት እውነት ይታወጃል፡፡ የመስቀልና የእሬቻ ጥላ መስከረም ለእኔ ሀገር ዘመን መለወጫ ብቻ አይደለም ከዓለም ሀገሬን የለያት ድንቅ የፈጣሪ ስጦታም ነው፡፡
የሀገሬ ሰው……. መስከም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ እንኳን ሰው ዘመዱ ይጠይቃል ባዳ ይላል፡፡ ባዳ የሚጠይቅበት መስከረም፡፡

መስከረም ከጉጌ እስከ ዶርዜ መንደር፣ ከአምበርቾ እስከ ቱላ ሰገነት፣ ከዘቢዳር እስከ ዳሞታ በመስቀል በዓል ይናወጣሉ፡፡ የሸካ ጥቅጥቅ ደኖች፣ የቤንች ፏፏቴዎች፣ የማጂ ተራራዎች የካፋ ውብ መልከዓ ምድር፤ መስከረም የሁሉም ነው፤ ለሁሉም ነው፡፡ ከጉና ጫፍ እስከ ባሌ….ከጎዴ አናት እስከ ጋምቤላ…..ከአቡነ ዮሴፍ እስከ ቧሂት….ከአክሱም ጫፍ እስከ ጅንካከአሲምባ ካራ ማራከዳሉል እስከ ራስ ደጀን ምድር የምታጌጥበት ደዴሳ….ግዮንአዋሽ….ባሮ….ኦሞ….ግቤ….ጎጀብ….ተከዜ….ዋቤገናሌ የሀገሬ ወንዝ በርበሬ ከመምሰል እፎይ የሚልበት፣ ለምለም ወርየቀለንቶን ሀብታሟ ሀገሬ ልዩ ስጦታ መስከረም፡

******

ጊዜ አለው . . .

ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ለመረዳት፣ ላለመረዳት፣ ለመሳሳት፣ ለመስተካከል፣ ቀና ለማለት፣ ለመጉበጥም፣ስኳር ከሰማይ የሚረግፍበት ዘመን አለ፣ ጥብስም የሚመለክበት፣ የመጠጣት ጊዜ አለው፣ የመጥመቅ ጊዜ አለው፣ ጠጥቶም የመሽናት፣ የመውለድ ጊዜ አለው፣ የማደግም ጊዜ አለው፣ የመጎርመስም ጊዜ አለው፣ ጎርምሶ የመውደድም፣ ብስክሌት የመጋለብ፡፡ የጋለቡትንም የመስበር፡፡ የሰበሩትንም የመጠገን፡፡ የጠገኑትን መልሶ የመጋለብ፡፡ ጊዜ አለው በሬ የሚያርስበት፡፡ ለስጋም ወደ ገበያ የሚነዳበት፣ ከገበያም ተወስዶ የሚታረድበት፡፡ ጊዜ አለው ወደ ጥብስ የሚለወጥበት፡፡ ጊዜ አለው ማዕዳችን ላይ የሚከነበልበት፡፡ ጊዜ አለው ዲያቆን መሆን፣ ጊዜ አለው ነጋዴም መሆን፣ በተፃብኦ ማፍቀር እሱም አልፎ በቀን ሕልም መውደድ፣ ቀለበትን የማጣት እሱንም መልሶ የማግኘት፣ ጊዜ አለው ለማፍቀርም፣ ጊዜ አለው አፍቅሮ ለመለያየትም ጊዜ አለው ገመና ገመና ላይሆን፡፡ ጊዜ አለው ግዙፉ አውድ ረቂቅ አውድ የሚሆንበት፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው ይላል ይሄ እዝራ ታዚና……

አዳም ረታ ‹‹መረቅ››

**************

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...