Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል​​​​​​​በዓልን ከቤት ውጪ

​​​​​​​በዓልን ከቤት ውጪ

ቀን:

በዓላት ሲቃረቡ አዲስ አበባን ከሚያደምቋት አንዱ አነስተኛ ከሚባሉት እስከ ዓለም አቀፎቹ የመዝናኛ ሥፍራዎች የሚያሰናዱት ልዩ የበዓል ዝግጅት ነው፡፡ ዝግጅቶቹን ለመታደም እንዲሁም በዓላት ከቤት ውጪ ለማሳለፍ የሚሻውም ብዙ ነው፡፡ በአንዳንድ በዓሎች በቤቱ የቀረ ሰው ያለ እስከማይመስል ድረስ፣ የከተማው መንገዶች በሰው ይሞላሉ፡፡ ብዙዎች ከአንዱ መዝናኛ ወደ ሌላው እየተዘዋወሩ ዋዜማና በዓልን ያሳልፋሉ፡፡

በዓልን ጠብቀው ለመዝናናት ከሚወጡ አንዱ ያፌት መልካሙ፣ እሱና ጓደኞቹ በይበልጥም የአዲስ ዓመትና የልደት ዋዜማን በጉጉት እንደሚጠባበቁ ይናገራል፡፡ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር ካልገጠማቸው፣ የበዓላትን ዋዜማ ቤታቸው አያሳልፉም፡፡ በተለያዩ ክለቦችና ሆቴሎች የሚዘጋጁ የበዓል ዝግጀቶችን አስቀድመው ካጠኑ በኋላ፣ ዋዜማውን ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ያሳልፋሉ፡፡

በእሱ እምነት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በበዓላት የመዝናኛ አማራጭ የሆኑ ቦታዎች ተበራክተዋል፡፡ በሃያዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኘው ያፌት፣ በእሱ ዕድሜ ካሉ ወጣቶች አብዛኞቹ በተመሳሳይ መልኩ በዓልን ሲያሳልፉ ያስተውላል፡፡ ዋዜማን ከቤት ውጪ ሲያሳልፍ የበዓል ቀን ስለሚደክመው እረፍት ያደርጋል፡፡ ከቤተሰቦቹ ጋር በዓልን ሙሉ በሙሉ አለማሳለፉ ቤተሰቦቹን ቅር እንደሚያሰኛቸው ቢያውቅም፣ ‹‹አማራጭ የለኝም›› ይላል፡፡

ዘመን ዘመንን ሲተካ፣ ማኅበረሰቡ ለበዓል የሚሰጠው ቦታና የበዓላት አከባበር ለውጥ ያሳያል፡፡ በበዓል አከባበር ከሚታዩ ለውጦች መካከል ዐውደ ዓመትን ምክንያት አድርጎ ከቤት ውጪ መዝናናት አንዱ ነው፡፡ በዓላት በተለምዶ ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ የሚሰባሰቡበት፣ ጎረቤት ከጎረቤቱ እየተጠራራ ከአንድ መዓድ የሚቋደስበትም ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው በዓልን ከቤት ውጪ ማሳለፍ የሚመርጡ አሉ፡፡

ቤተሰብ በአንድነት ተሰባስቦ በዓል በቤቱ ማክበር እንዳለበት የሚያምኑ ሰዎች፣ ከቤት ውጪ ያለውን ድባብ ዘመናዊነትን ከመላበስ ጋር ተያይዞ እንደሚመጣ ያምናሉ፡፡ በተለይም ከከተሜነት መስፋፋት ጋር በተያያዘ የበዓል አከባበር መለወጡን ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ ከቤት ውጪ የሚኖሩ የበዓል ዝግጅቶችን መታደም ከዕድሜና ከገንዘብ አቅምና ከፍላጎት ጋር ይያያዛል፡፡ አንዳንዶች ከበዓላት ጋር ተያይዞ የሚመጣው የምሽት ድባብ መለመድ እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በዓል ለማክበር የግድ ከቤት መውጣት አስፈላጊ እንዳልሆነ ያምናሉ፡፡

በአንፃሩ የበዓል አከባበር መለወጥ ለባህላዊና ዘመናዊ መዝናኛዎች ጥሩ የቢዝነስ መንገድ የከፈተ ይመስላል፡፡ በዓላትን አስታከው ልዩ ዝግጅት የሚያሰናዱ መዝናኛዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ከአዘቦት ቀን የተለየ ነገር የማያሰናዱም አሉ፡፡

ለበዓላት ልዩ ዝግጅት ካላቸው ክለቦች አንዱ ጆሊ ባር ነው፡፡ ለዘንድሮው ዓመት ከውጪ አገር ዲጄ አምጥተዋል፣ ከአንድ ድርጅት ጋር በመስማማት ቅናሽ ያደረጉበት መጠጥም አለ፡፡ አዲስ ዓመት መግባቱን ለማብሰር ካውንት ዳውን (አዲስ ዓመት የሚጀመርበት ሰዓት ድረስ ያሉ ጥቂት ሰከንዶችን መቁጠር) ይደረጋል፡፡ በባሩ ለሚገኙ የቀን መቁጠሪያም ይሰጣል፡፡ የጆሊ ባር ባለቤት አቶ ይህደጎ አቤሴሎም እንደሚናገረው፣ ለበዓላት ስጦታ በመስጠትና ክለቡን በማሳመር ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ፡፡  ያለውን የበዓል አከባበር አውቀው ወይም በአዘቦት ቀን ያለውን ድባብ ጠብቀውም ወደ ባሩ የሚያመሩ አሉ፡፡

ለበዓል የወጣት ሴቶች፣ የዳያስፖራዎችና የባለትዳሮች ቁጥር እንደሚጨምር ይናገራል፡፡ በዓልን ከቤት ውጪ የሚያከብሩ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ለመጨመራቸው እንደ ምክንያት የሚጠቅሰው የከተሜነት መስፋፋትን ነው፡፡ በከተማ ቀመስ አካባቢዎች ብዙ የመዝናኛ አማራጮች ይቀርባሉ፡፡ ተጠቃሚውም ከፍላጎቱ ጋር የሚጣጣም ወጪ አውጥቶ የመዝናናት አቅሙ ስላደገ አማራጮቹን ይጠቀምባቸዋል፡፡ ሰዎች ለዘመናዊ አኗኗር ያላቸው ተጋላጭነት ሲጨምር በነፃነት ይዝናናሉ ብሎ ያምናል፡፡

በዓላት ከተለመደው ወጣ ባለ ሁኔታ እንዲከበሩ ጊዜው መንገድ መክፈቱን አቤሴሎም ይናገራል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ዘመናዊም ይሁን ባህላዊ መዝናኛዎች የሰውን ፍላጎት የሚያስተናግዱበት መንገድ መስፋት አለበት፡፡ አንድ አገር ያለውን አጠቃላይ ገጽታ ከመለወጥና ከቢዝነስ አንፃርም በዓልን ምክንያት አድርገው የሚዝናኑ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ  ጠቀሜታው ይጎላል፡፡

የበዓላት መስተንግዶ ፈታኝ የሚሆንበትም ጊዜ አለ፡፡ መዝናኛ ሥፍራዎች ያላቸው አቅምና የተጠቃሚዎች ቁጥር የማይመጣጠንበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም፡፡ በመዝናኛዎች ከበዓል ቀን አስቀድመው ቦታ የሚይዙ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ በቅድሚያ ቦታ ሳያሲዙ የበዓል ዕለት ተገኝተው መስተናገድ የሚፈልጉ ሰዎችን መመለስም ግድ ይሆንባቸዋል፡፡

የሰዎች ቁጥር ከቁጥጥር ውጪ መሆኑ እንደሚፈትን የሚስማማው የዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ የምግብና መጠጥ ክፍል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ፈቃዱ ነው፡፡ ብዙዎች ለመዝናናት ሲወጡ ቦታ አለማግኘትን ከግምት ስለማያስገቡ መጨናነቅ ይፈጠራል፡፡ በሌላ በኩል ግን በዓል ብዙዎች በነፃነት የሚዝናኑበት መሆኑ መዝናኛዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

ሐሳቡን የሚጋራው ይህደጎ፣ በአዘቦት ቀን ወጥተው የመዝናናት ልማድ የሌላቸው ሰዎች ለበዓል እንደሚገኙ ይናገራል፡፡ ዳንኤል በበኩሉ በበዓላት ለባህላዊ ሁነቶች የበለጠ ትኩረት ስለሚሰጥ፣ ወደ ባህላዊ መዝናኛዎች የሚመያሩ ብዙዎች ናቸው ይላል፡፡

በዮድ አቢሲኒያ ልዩ ዝግጅት የሚደረገው ለአዲስ ዓመትና መስቀል ነው፡፡ በበዓላቱ ከባህላዊ ምግቦችና መጠጦች ጎን ለጎን ባህላዊ የበዓል ሙዚቃ ይቀርባል፡፡ በአዘቦት ቀን ከሚዘፍኑ ሙዚቀኞች በተጨማሪ አንጋፋ ባህላዊ ዘፈን አቀንቃኞች ይጋበዛሉ፡፡ በአዲስ ዓመት መባቻ እኩለ ለሊት ላይ ሻማ ይበራል፡፡ ለበዓል የሚዘጋጀው ይህ ልዩ መሰናዶ ከሌላው ቀን የበለጠ ክፍያ ይጠየቅበታል፡፡

 በበዓላት ቤቱን ከሚያዘወትሩ መካከል የውጪ አገር ዜጎችና ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦችን ዳንኤል ይጠቅሳል፡፡ ኢትዮጵያን የሚጎበኙ ቱሪስቶች የበዓላትን አከባበር ለመቃኘት ወደ ባህላዊ መዝናኛ ቦታዎች ያመራሉ፡፡ በመዝናኛ ሥፍራዎች በዓልን በተለያየ መንገድ የሚያከብሩ ሰዎችን የሚያዋህድ ዝግጅት ስለሚያቀርቡ፣ በዓልን በቤት ከማሳለፍ ወጥቶ መዝናናትን የሚመርጡ እንደሚበዙ ያምናል፡፡ በመዝናኛዎች በዓልን አስታከው የሚቀርቡ ዝግጅቶች ቤት ውስጥ ካለው ድባብ የደመቁና ወጥነት ያላቸው እንደሆኑ፣ ‹‹ሁሉም በየቤቱ የሚያዘጋጀው ቢኖርም፣ ከቤት ውጪ ያለው ድባብ የሞቀ ስለሆነ ሰውን ይስባል፤›› በማለት ይገልጻል፡፡

በበዓል ዋዜማ ወይም በዕለቱ፣ ከተማው በሚላበሰው ድባብ የሚደሰቱ እንዳሉ ሁሉ፣ ጥያቄ የሚያነሱም አሉ፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡን አንዱ የፈንድቃ መሥራች መላኩ በላይ፣ በዓላትን ምክንያት በማድረግ የሚሰናዱ ዝግጅቶች ከመጠን በላይ የተጋነኑ እንደሆኑ ይናገራል፡፡ የበዓላት ትርጓሜ ሲዘነጋና ለመዝናኛ ምክንያት ብቻ ሲሆኑ ይስተዋላል ይላል፡፡

በፈንድቃ ለበዓል ልዩ ነገር አይዘጋጅም፡፡ ቄጤማ በመጎዝጎዝ፣ ችቦ በማብራትና በዓል ተኮር ዘፈኖች በመጫወት በዓላትን ቢዘክሩም፣ የተለየ ነገር አያቀርቡም፡፡ እሱ እንደሚለው፣ በበዓላት ወቅት የሚዝናናው ሰው ብዙ በመሆኑ ግርግር ይፈጠራል፡፡ ግርግሩ ሰዎች ተረጋግተው የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያጣጥሙ የሚያመች አይደለም፡፡ አንጋፋ ሙዚቀኞችና ተወዛዋዦች ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ ቢዘጋጅ እንኳን ለትዕይንቶቹ ቦታ የሚሰጣቸው ሰው አናሳ ነው ይላል፡፡

ሰዎች ለበዓላት የግድ ከቤት መውጣት እንዳለባቸው መታሰቡ አግባብ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ ‹‹በዓል ስሜታዊነት የበዛበት ሰዎችም ለዕይታ የሚወጡት እየሆነ መጥቷል፤›› ይላል፡፡ ለበዓል መውጣት እንደ ዘመናዊነት መገለጫ የሚታይበት ጊዜ አለ፡፡ በዓላት ከጀርባቸው ያለው ትርጓሜና የበዓላት አከባበር ባህላዊ እሴት እንዳይዘነጋ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ያስረዳል፡፡ ከቤት ውጪ ያለው የበዓል አከባበር አካሄድ ቆም ተብሎ ሊታሰብበት ይገባል ይላል፡፡

ሐሳባቸውን ካካፈሉን ሌላው የክለብ ኢሉዥን ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት የዐውደ ዓመት ልዩ ዝግጅት ቢያሰናዱም ለ2008 ዓ.ም. አዲስ ዓመት የተለየ መርሐ ግብር የላቸውም፡፡ ሥራ አስኪያጁ፣ እንደ ምክንያት የሚጠቅሰው በእያንዳንዱ መዝናኛ በሚያስብል ደረጃ ሁሉም ቦታ የበዓል ዝግጅት መኖሩን ነው፡፡ ብዙ አማራጮች ስላሉ ቤቱ የተለመደ አገልግሎት ቢሰጥ እንደሚሻል ያምናል፡፡

ቀድሞ ለበዓላት በሚያዘጋጇቸው ልዩ ምሽቶች ብዙ ተዝናኞች ይታደሙ ነበር፡፡ በዘንድሮው አዲስ ዓመት ከአዘቦት ቀን የተለየ ድባብ አይጠብቁም፡፡ በእሱ እምነት፣ በአዲስ አበባ ዝግጅቶች መበራከታቸው በይበልጥ የወጣቱን ትኩረት ስቧል፡፡ በዓልን ከቤት ውጪ በመዝናኛዎች የማሳለፍ ልማድን በቀጥታ ከኢኮኖሚ ጋር ያያይዘዋል፡፡ በበዓል የተሻለ ገቢ ያላቸውና የቤተሰብ ኃላፊነት ውስጥ ያልገቡ እንደሚበዙ ይናገራል፡፡

የ2000 ሐበሻ የባህል ምግብ አዳራሽ ሥራ አስኪያጅ አቶ አረጋዊ ገብረሥላሴ በበኩላቸው፣ ባህላዊ መዝናኛ ቦታዎችን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ባህል ለመመልከት የሚመርጧቸው አሉ፡፡ በዓልን ልዩ የሆነ ትዕይንት ለመታደም የሚጠቀሙበትም ጥቂት አይደሉም፡፡ በኢትዮጵያ ባህል በዓልን ምክንያት አድርጎ መሰባሰብ የተለመደ መሆኑን በማጣቀስ፣ ባህሉ መልኩን የለወጠው ጎረቤት ከጎረቤቱ ጋር አብሮ በመሆን ፈንታ ቤተሰብ ወይም ጓደኛሞች ተሰባስበው ወደ መዝናኛዎች ማምራታቸው ነው ይላሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...