Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹ሰውየውም ይኑር ዛፉም ይኑር››

‹‹ሰውየውም ይኑር ዛፉም ይኑር››

ቀን:

የ2008 ዓ.ም. መምጣትን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከወትሮው በተለየ መልኩ ተጨናንቀዋል፡፡ የመገበያያ ሥፍራዎችም ደምቀዋል፡፡ ሁሉም በአንድነት የሚያከብሩት የዘመን መለወጫ በዓል መዳረሻ ቀናት ከየገበያ አዳራሹና ሱቆች በተለቀቁ የዐውድ ዓመት ሙዚቃዎች ደምቀው ነበር የከረሙት፡፡ በተለይም በኤግዚቢሽን ማዕከል ያለው ድባብ የተለየ ነበር፡፡

ምንም እንኳን የመግቢያ ትኬቱ ከወትሮው ጭማሪ ቢያሳይም ማዕከሉ በሸማቹ ተጨናንቆ ነበር፡፡ በማዕከሉ ከየዳሱ የሚሰሙ የመዝሙር፣ የአዲስ ዓመት ዜማዎች፣ የልጆች ሙዚቃና የምርት ማስታወቂያ ጥሪዎች ያስተጋባሉ፡፡

ከመግቢያው ትንሽ እልፍ እንዳሉ የማዕከሉን መግቢያና መውጫ የሚከፍለውን  አረንጓዴ ስፍራ ያገኛሉ፡፡ አልፎ አልፎ ከቆሙት የዘንባባ ዛፎች መካከል ለየት ያለ ነገር እንደተመለከቱ ሁሉ አንዳንድ ሰዎች ቆም ብለው በአግራሞት ሲወያዩ ይታያሉ፡፡

አልፎ አልፎ ከቆሙት ዛፎች መካከል አንደኛው ቀልባቸውን ስቧል፡፡ የተወሰኑት ጥያቄ ይሰነዝራሉ፣ የተቀሩት ደግሞ ስለተመለከቱት ነገር እርስ በርሳቸው ሐሳብ ይለዋወጡና ወደየጉዳያቸው ይመለሳሉ፡፡ ዛፉ ከወትሮው የተለየ ነው፡፡ በተፈጥሮ የበቀለ አይደለም፡፡ በሻማ የተሠራ ሰው ሠራሽ ዛፍ እንጂ፡፡ ልዩ ያደረገው ከሻማ መሠራቱ ብቻም አልነበረም፡፡ እንደ ዛፉ ሁሉ ከሻማ የተሠራ በመጥረቢያ ዛፉን የሚቆርጥ ሰውም ነበር፡፡ የተሰነዘረው መጥረቢያ ዛፉን የተወሰነ ድረስ ቆርጧል፡፡ የመጥረቢያው አናት ላይ ሻማው የሚበራበት ክር ተበጅቶለታል፡፡ በመክፈቻው ዕለት ተለኩሶ ስለነበረም የተወሰነ ተቃጥሏል፡፡

‹‹ሰውየውም ይኑር ዛፉም ይኑር፣ መጥረቢያው ግን ይታሰብበት የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው›› ያለው ዛፉን በሻማ ከሠሩት ሦስት ወጣቶች መካከል አንዱ ሚካኤል ታምራት ነው፡፡ ሚካኤል የአይላቭ ካንድል ማርኬቲንግ ማኔጅር ሲሆን፣ ዛፎች እንዳይጨፈጨፉ ለሰዎች ሌላ አማራጭ ኃይል በሚገባ መቅረብ አለበት ይላል፡፡

ድርጅቱ ልዩ ልዩ የሻማ ጥበቦችን እንደሚሠራ ይናገራል፡፡ ‹‹ሻማዎችን ጥበባዊ በሆኑ መንገዶች ማዘጋጀትና ለገበያ ማቅረብ ተቀዳሚ ተግባራችን ነው›› ይላል፡፡ ወቅታዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸውን ሻማዎች ያዘጋጃሉ፡፡ እንዲሁም የሥነ ጥበብ ሥራዎችንም ለገበያ ያቀርባሉ፡፡

አሥር ሜትር ከ20 ሳንቲ ሜትር ርዝማኔ ያለውን የሻማ ዛፍ ሲያዘጋጁም ወቅታዊ ሁኔታውን ተንተርሰው እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹ሐሳቡ የደን መጨፍጨፍ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለማሳየት ነው፡፡ መጥረቢያ የያዘው ሰው ዛፎች እየተጨፈጨፉ መሆናቸውን የሚያሳይ ሲሆን፣ ከሻማ መሥራታችን ደግሞ እየጠፋ፣ እየቀለጠ ያለው የደን ሀብታችንን ያሳያል፡፡ እንዲሁም ዛፎች ተጨፍጭፈው ሲጠፉ እኛም ቀልጠን እንጠፋለን የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ታስቦ ነው፤›› በማለት ዛፉ የኮሶን ዛፍ እንደሚወክል ይናገራል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ የኮሶ ዛፍ አገር በቀልና ብርቅዬ ቢሆንም፣ እየተመናመነ ይገኛል፡፡ የኮሶ ዛፍ በባህላዊ ሕክምና ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ሲሆን፣ በአሁን ሰዓት በመጥፋት ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ዛፎች ከማኅበረሰቡ ጋር የሚኖራቸው ቁርኝት ላይ እክል መፍጠሩ እሙን ነው፡፡ ‹‹አፋጣኝ መፍትሔ ያሻዋል፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ ትልቅ የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ የኮሶ ዛፍ መቁረጥ በሕግ እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ይህ በቂ አይደለም፡፡ በግዴታ ሳይሆን በፈቃዳችን ዛፍ እንዳይጨፈጨፍ መጣር አለብን፤›› ብሏል፡፡

ይህንንም ለማስተማር በጽሑፍና በንግግር ከሚተላለፉ ሐሳቦች ውጪ ጥበባዊ በሆነ መልኩ መዘጋጀቱ የአብዛኛውን ቀልብ እንደሚስብና ለማስተላለፍ የታሰበውን መልዕክትም ለብዙኃኑ በቀላሉ ማድረስ እንደሚቻል ያምናል፡፡

ሥራውን ሠርቶ ለመጨረስ አንድ ወር ከ15 ቀናት ፈጅቶባቸዋል፡፡ በኤግዚቢሽን ማዕከሉም ለ21 ቀናት ያህል እንደሚቆይ ተናግሯል፡፡ ሙሉ ወጪውን የቻሉትም የአዲስ ዓመት የንግድ ኤክስፖ ያዘጋጀው ሀበሻ ዊክሊ መሆኑን ሳይገልፅ አላለፈም፡፡ ከሻማው ጥበብ ለጥቆ የሚገኘው 65 ሜትር ስኩዌር ስፋት ያለው ከብራና የተዘጋጀ ፖስት ካርድ ነው፡፡ ፖስት ካርዱ አካባቢውን በቆዳ ሽታ አውዶታል፡፡ ከስፋቱ አንፃር ሲታይ ግዙፍ የመልዕክት ማስተላለፊያ ቢልቦርድ እንጂ ፖስት ካርድ አይመስልም፡፡ ‹‹መልካም አዲስ ዓመት ከሀበሻ ዊክሊ ለመላው ዓለም›› የሚል የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት ሰፍሮበታል፡፡ በህብረ ቀለማት ያሸበረቁ ጥለቶች፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና የወላይታ ከተማ ባህላዊ ልብስ ድንጉዛም ፖስት ካርዱን ካደመቁት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ (ዘመን አመልካቹ ቁጥር በኢንዶ ዐረቢክ 2008 በትክክል ቢጻፍም፣ በግእዝ የተጻፈው ፪፻፻፰ ግን 20,008 ነው፡፡ መጻፍ የነበረበት ፳፻፰ ነበር)

አቶ አዶኒክ ወርቁ የሀበሻ ዊክሊ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደእሳቸው ገለፃ፣ ፖስት ካርዱን ለማዘጋጀት አንድ ወር ፈጅቷል፡፡ አሥር ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን፣ በርካታ ቆዳዎችም ተጠቅመዋል፡፡ ‹‹ቆዳውን ለማግኘት ብዙ ለፍተናል፡፡ እስከ ባህር ዳር ድረስ መሄድ ነበረብን፡፡ ኦርጅናል የብራና ጽሑፍ ለመጠቀምም አስበን ነበር፡፡ ለዚህም በባህር ዳር በሚገኙ የተለያዩ ገዳማት ተዘዋውረናል›› የሚሉት አቶ አዶኒክ፣ ብራናውና ቀለሙ የሚዘጋጅበትን መንገድ በቆይታቸው ማወቅ ቢችሉም፣ ካጋጠመው የጊዜ እጥረት አኳያ ቀለሙን ማዘጋጀት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በዘመናዊ ቀለም እስፕሬይ ተጠቅመው ለማዘጋጀት ተገድደዋል፡፡ ብራናውን ለማዘጋጀት በአጠቃላይ 150,000 ብር የፈጀ ሲሆን፣ የሦስት ወር የማሰላሰያ ጊዜ ወስዷል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ ልዩ ነው፡፡ ይህንን ለዓለም ለማስተዋወቅም እንጥራለን፤›› ይላሉ፡፡ ድርጅቱ በሚያዘጋጃቸው ዝግጅቶች ላይም የተለያዩ አዳዲስ ነገሮችን እንደሚያቀርቡ ይናገራሉ፡፡ በዐውደ ርዕዩ ያዘጋጇቸውን የሻማ ጥበብና የብራና ፖስት ካርድ በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ለማስመዝገብ እንቅስቃሴም ጀምረዋል፡፡ ‹‹የመመዝገብ ዕድሉን ካገኘን በዓለም ተዟዙረን ለማሳየትና አገሪቱን ለማስጠራት እንፈልጋለን፡፡ ሥራዎቹም ለኅብረተሰቡ መልዕክት የሚያስተላልፉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ለሁለቱም ዝግጅት ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ እንደወጣ የተናገሩት የሀበሻ ዊክሊ አስተዳዳሪ አቶ ናትናኤል ኢቲቻ ናቸው፡፡ ሥራዎቹን በሌሎች መሰል ፕሮግራሞች ሁሉ እንደሚጠቀሟቸውም ገልጸዋል፡፡ እንደእሳቸው ገለፃ፣ ዐውደ ርዕዩን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...