ዘመን መለወጫ ላይ ስለ አዲስ ዓመት ተስፋ ብቻ ሳይሆን ያለቀውስ እንዴት አለፈ? ምን ተወጥኖ ከዳር ደረሰ የሚሉና ሌሎችም ተያያዥ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ባለቀው ዓመት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከሕዝብ ዕይታ ውስጥ የገቡና ሌሎችም ያለፈውን ዓመትና የአዲስ ዓመት ዕይታቸውን እንዲህ ያስቀምጡታል፡፡
ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰ
ባለፈው ዓመት የየኛ ፕሮጀክት ስኬት የተደሰትኩበት ትልቅ ነገር ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ የፈጠረው ተፅዕኖ ትልቅ ስለነበር፡፡ በሌላ በኩል ራሴን የግል የምርጫ ተወዳዳሪ አድርጌ ማቅረቤን እንደ ትልቅ ዕርምጃ የማየው ነገር ነው፡፡ አዲስ ነገር የደፈርኩበትም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ፖለቲካ በግል ሕይወቴ፣ ሥራዬ ላይ እንዴት ተፅዕኖ ሊያደርስ ይችላል በሚሉና በሌሎችም ነገሮች ላይ አስቤ ቀላል ባልነበረው ሒደት ውስጥ ለማለፍ መወሰኔ እንደ ስኬትም የማየው ነው፡፡ ይህው አጋጣሚ የተፈተንኩበትና ባለመሳካቱ ያዘንኩበትም ነው፡፡
በመጪው አዲስ ዓመት ብዙዎችን ይደርስ ዘንድ የየኛ ፕሮጀክትን ማስፋት ቀዳሚው ዕቅዴ ነው፡፡ በግሌ ደግሞ በቀጣይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሳትፎዬ እንዴት ይሆናል? ሌላ መንገድ አለ ወይስ በጀመርኩት እቀጥላለሁ በሚሉት ነገሮች ጋር ከራሴ ጋር የምነጋገርበት ነው፡፡
ሠዓሊ ብሩክ የሺጥላ
ለዓመታት ሳልመው የነበረው በብሔራዊ ሙዚየም የሥዕል ዓውደ ርዕይ የማዘጋጀት ዕቅድ እውን የሆነው ባለፈው ዓመት ነበር፡፡ ብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ዓውደ ርዕይ ማዘጋጀት ቀላል አይደለም፡፡ የተለያዩ መሥፈርቶችን ማሟላት ይጠይቃል ለዚህም ነው የተደሰትኩት፡፡
በዚሁ ዓመት ጋለሪ የመክፈት ሕልም ነበረኝ፡፡ ይህንኑ ለማሳካትም ብዙ ነገሮችን አድርጌአለሁ፤ ከሞላ ጐደል ዘጠና በመቶ የሚሆነውን መንገድ ተጉዤ ነበር፡፡ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ አለመሳካቱ የፈተነኝ ነገር ቢሆንም፣ በሒደቱ ብዙ ተምሬአለሁኝ፡፡ እንኳንም ያልተሳካ እስከማለት የደረስኩበት አጋጣሚም አለ፡፡
በዚህ አዲስ ዓመት መስከረም ወይም ጥቅምት ላይ ጋለሪውን እንደምከፍት ተስፋ አደርጋለሁኝ፡፡ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ጥበብ ላይ የሚያተኩር የቴሌቪዥን ሾው ለመጀመር እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ይህ ቀዳሚው ዕቅዴ ነው፡፡
ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ
ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ የሙዳይ በጐ አድራጐት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ነች፡፡ ድርጅቱ ሕፃናትና ሴቶችን የሚደግፍ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ከባድ የፋይናንስ ችግር ውስጥ ገብቶ መዘጋት አፋፍ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ሌሎችም እጃቸውን በመዘርጋታቸው ተስፋ መታየቱን ወ/ሮ ሙዳይ ትናገራለች፡፡ በዚህ ረገድ ኮሜዲያኖች ገቢ ለማሰባሰብ መርካቶ ላይ ጫማ የጠረጉበት ፕሮግራም የሚጠቀስ ነው፡፡ ወ/ሮ ሙዳይም ሁኔታውን በማስመልከት የሚከተለውን ብላለች፡፡
ዓመቱ እጅግ ፈታኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ሊነጋ ሲል ይጨልማል እንደሚባለው በዓመቱ ማብቂያ ላይ ተስፋ ማየት ጀመርን፡፡ የድርጅቱን ሥራ በሚገባ አካሂዳለሁ የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ ነገር ግን ሁኔታዎች ከባድ ሆኑ፡፡ ቢሆንም በመጨረሻ ብዙዎች ደርሰውልኛል፡፡
በዚህ ዓመት ድርጅቱ ተጠናክሮ እንዲቆም ማድረግ የመጀመሪያው ትኩረቴ ነው፡፡ ድርጅቱ ሁሌም ተረጅ መሆን የለበትም ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህም የራሱን ገቢ የሚያገኝባቸውን ሥራዎች የማስጀመር ሐሳብ አለኝ፡፡
አቶ ቢንያም በለጠ
የመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መሥራች ነው፡፡ ባለቀው ዓመት የምንረዳቸውን ሰዎች ቁጥር ከፍ አድርገን ከ825 በላይ ማድረግ ችለናል፡፡ በማዕከሉ የሚረዱት ሕሙማንና አረጋውያን በመሆናቸው ወጪያችን ከፍተኛ ነው፡፡ ምንም እንኳ ሰዎች በገንዘብ ረገድ ጥሩ እንደሆንን ቢያስቡም፣ ይህ ዋናው ተግዳሮታችን ነው፡፡
ከመንግሥት 30 ሺሕ ካሬ መሬት አያት ኮንዶሚኒየም አካባቢ ማግኘታችን የዚህ ዓመት ትልቁ ስኬታችን ነው፡፡ የተሰጠን መሬት ከብዙ ነገር አንፃር የተመቸ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ትልቅ ነገር ነው ያደረገልን፡፡ በዚሁ ዓመት ሦስት መቶ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞችን ማግኘታችንም ሌላው መልካም ነገር ነው፡፡
በዚህ በአዲሱ ዓመት የተሰጠን መሬት ላይ ግንባታ እንጀምራለን ብለን እናስባለን፡፡ ግንባታው ሦስት ሚሊዮን ብር ወጪ ይሆንበታል ተብሎ የሚገመት ሲሆን በዚህ ዓመት የመጀመርያውን ደረጃ ግንባታ አጠናቅቀን የሚረዱ ሰዎችን ቁጥር 2000 እናደርሳለን ብለን እናስባለን፡፡
አትሌት ማሬ ዲባባ
በነሐሴ 2007 ዓ.ም. በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በማራቶን አሸናፊ እንድትሆን ያደረገች ናት፡፡
ያለፈው ዓመት ጥሩ ውጤት ያገኘሁበት በተለይም በቤጂንግ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማራቶን ያሸነፍኩበት በመሆኑ ለእኔ ጥሩ ጊዜ ነው፡፡ ያደረግኩት ሥልጠና ከባድ ነበር፡፡ ግን በእግዚአብሔር ዕርዳታ ውጤት ማስመዝገብ ችያለሁ፡፡
በዚሁ ዓመት ቦስተን ማራቶን ላይ አሸናፊ ለመሆን ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ እንዳሰብኩት ማሸነፍ አልተሳካልኝም በራሴ ስህተት ሦስተኛ ሆኜ ውድድሩን ጨርሻለሁ፡፡ በአዲሱ ዓመት ይበልጥ ሠርቼ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ነው የማስበው፡፡
ሸዋዬ አጠላ
ሃያ ሁለት ዓመቴ ነው፡፡ ትውልድና ዕድገቴ በአማራ ክልል ነው፡፡ እስከ አሥረኛ ክፍል ድረስም እዚያው ተምሬያለሁ፡፡ በትምህርቴ መካከለኛ ከሚባሉት ተርታ የምመደብ ብሆንም ለመሰናዶ ትምህርት የሚያበቃ ውጤት ማስመዝገብ አልቻልኩም፡፡ አጋጣሚው ተስፋ ሲያስቆርጠኝ የትውልድ ቀዬዬን ለቅቄ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ የተለያዩ የቀን ሥራዎችን እየሠራሁ ኑሮዬን እገፋለሁ፡፡
በአናጺነት የምሠራው መገናኛ አካባቢ በሚገኘው ከስለሺ ስህን ሕንፃ ጐን እየተገነባ ባለው ሕንፃ ውስጥ ነው፡፡ ያለፈው 2007 ዓ.ም. ከሞላ ጎደል በመልካም አሳልፌዋለሁ፡፡ የሳይት መሀንዲስ ለመሆን የሚያስችለኝን ትምህርት በአዲስ ኮሌጅ መማር የጀመርኩት ባለፈው ዓመት ነው፡፡ በአዲሱ ዓመትም በርትቼ በመማር ጥሩ ውጤት ማስመዝገብና ለተሻለ ሥራ መብቃት እፈልጋለሁ፡፡
መስፍን አበበ
32 ዓመቴ ነው፡፡ ኑሮን የምገፋው ስቴዲየም አካባቢ መኪና በማከራየትና በማለማመድ በማገኘው ገቢ ነው፡፡ በሥራዬ ከተሰማራ አምስት ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ፡፡ ሥራው መታወቅ የጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ገና እንደታወቀ አካባቢ ገበያው ብዙ ነበር፡፡ ይሁንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ መጥቷል፡፡ ባለፈው ዓመት የነበረኝን ዲኤክስ መኪና በቪትስ ብቀይርም ያሰብኩትን ያህል መሥራት አልቻልኩም፡፡ ያለፈው ዓመት ለእኔ ጥሩ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ በአዲሱ ዓመት የራሴን ቢሮ በመክፈት መኪና የማከራየቱንም ሆነ ሌሎች መሰል ሥራዎች የመሥራት ዕቅድ አለኝ፡፡ ካልሆነ ይህንኑ አጠናክሬ እቀጥላለሁ፡፡ በ2008 ዓ.ም. በሥራዬ አመርቂ ለውጥ ለማምጣት አስቤያለሁ፡፡
ዳዊት ሀብተማርያም
21 ዓመቴ ነው፡፡ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ ተማሪ ነኝ፡፡ ዩኒቨርሲቲውን የተቀላቀለኩት በ2007 ዓ.ም. ሲሆን፣ ለዓመቱ የተለየ ስሜት እሰጠዋለሁ፡፡ በሕይወቴ ትልቅ ለውጥ ያመጣሁበት ዓመት ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት የጀመርኩበት ነው፡፡ ከዚህ በላይ ለእኔ ትልቅ ነገር የለም፡፡ በአዲሱ ዓመትም ንግድ የመጀመር ፍላጐት አለኝ፡፡ እናቴ ከምትሠራበት ፀጉር ቤት ጐን የኮስሞቲክስ ሱቅ የመክፈት ፍላጐት አለኝ፡፡
ሕዝቅኤል ቡሪ
24 ዓመቴ ነው፡፡ በፊታውራሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ መምህር ነኝ፡፡ በሥራዬ ዓለም ከተሰማራሁ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ፡፡ ጋዜጠኛ የመሆን ፍላጐት ነበረኝ፡፡ መምህር ከመሆኔ አስቀድሞም ጋዜጠኛ ለመሆን ብዙ ጥሬያለሁ፡፡
በምሠራበት ሙያ ብዙም ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ሥራ እፈላልጋለሁ፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የደመወዜ ማነስና ኅብረተሰቡ ለሙያው ያለው አመለካከት ነው፡፡ በይበልጥ የሚገፋኝ ግን የደመወዙ ማነስ ነው፡፡ በወር የማገኘው 2,000 ብር ነው፡፡ ከላዩ ለቤት ኪራይ 600 ብር እከፍላለሁ፡፡ በሚቀረው ገንዘብ አስቤዛና ልዩ ልዩ ወጪዎችን ለመሸፈን እቸገራለሁ፡፡
ከዚህ ችግር ለመውጣትም ሌላ ሥራ እያፈላለግሁ ነው፡፡ የሥራዬ ሁኔታ ቢያስከፋኝም፣ ከባልደረቦቼ ጋር ስወያይ የማገኘው ጠቃሚ የሕይወት ተሞክሮ ደስ ያሰኘኛል፡፡ ይሁን እንጂ በሕይወቴ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት አልቻልኩም፡፡ ዓመቱም ብዙ አላስደሰተኝም፡፡ በአዲሱ ዓመትም በተቻለኝ ሁሉ ሥራ ለመቀየር እጥራለሁ፡፡
በምሕረት አስቻለውና በሻሂዳ ሁሴን