Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ልበ ሙሉ ያደረገኝ ወላጆቼ በእኔ ላይ የነበራቸው እምነት ነው››

ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሥራችና የመጀመሪያዋ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ዶክተር እሌኒ ገብረ መድኅን የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በመፍጠራቸው ይታወቃሉ፡፡ የመጀመሪያዋ ዋና ሥራ አስፈጻሚም ነበሩ፡፡ በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ተመሳሳይ ተቋማትን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ስኬታማ የሚባል ሕይወት ካላቸው እንስቶች ተርታም የሚመደቡ ናቸው፡፡ በግል ሕይወታቸውና ከሥራቸው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ የቆይታ እንግዳ በማድረግ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እንኳን አደረሰዎት?

ዶ/ር እሌኒ፡- እንኳን አብሮ አደረሰን፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲያው በልጅነት ጊዜ እንዲህ ዘመን ሲለወጥና እንቁጣጣሽ ሲባል ከባልንጀሮችዎ ጋር ሆነው እንቁጣጣሽ ጨፍረዋል?

ዶ/ር እሌኒ፡- ጨፍሬ አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

ዶ/ር እሌኒ፡- ብዙም አላውቅማ! አላደግኩበትም፡፡

ሪፖርተር፡- በልጅነትዎ ጊዜ የት ነበሩ?

ዶ/ር እሌኒ፡- ታዳጊ በነበርኩበት ጊዜ ለተወሰነ ጊዜ እዚህ (አዲስ አበባ) ነበርኩ፡፡ ከዚያ በልጅነቴ ከአገር ወጣሁ፡፡ እንቁጣጣሽ የሚዘፈነው ደግሞ ከ10 እስከ 15 ዓመት አካባቢ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ በዚህ ዕድሜዬ ውጭ ስለነበርኩ አልዘፈንኩም፡፡  

ሪፖርተር፡- እንደ እንቁጣጣሽ ያሉ በዓላትን እንዴት ነው የሚያከብሩት?

ዶ/ር እሌኒ፡- እዚህ ቤቴ ሲሆን የሐበሻ ልብስ ለብሼ እውላለሁ፡፡ በግ ይታረዳል፣ ዶሮ ይሠራል፡፡ ቄጤማ ይጐዘጐዛል፡፡ በቃ ለበዓል መደረግ ያለበትን ሁሉ አድርጌ ዘመድ ተጠርቶ አንድ ላይ ሆኜ አከብራለሁ፡፡ ከዚያም ከቤቴ ውጭ ደግሞ ልጆቼን ይዤ ወደ ዘመድ ቤት እሄዳለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- እንዲህ ዓይነቱን የበዓል አከባበር እዚህ ከመጡ በኋላ የሚያደርጉት ነው?

ዶ/ር እሌኒ፡- አሜሪካማ የሚታረድም በግ የለም፡፡ ሥጋውን ከግሮሰሪ ነው የምንገዛው፡፡   

ሪፖርተር፡- እንዲያው ለበዓል የሚታረደውን ዶሮም ሆነ በግ አጣፍጦ መሥራቱ ላይ እንዴት ነዎት?

ዶ/ር እሌኒ፡- በመጠኑ … ማለት ሐሳቡ አለ፡፡ ዕውቀቱም አለ፡፡ መጠባበሱንም ሆነ ዶሮ መሥራቱን አውቃለሁ፡፡ ግን ቤት ሰው ስላለኝ እኔ በአብዛኛው በማኔጅመንት ደረጃ ነው የምሳተፈው፡፡ ማቀነጃጀቱ ላይ ማለቴ ነው፡፡ ከበዓል ውጪ ግን የቤት ሠራተኛዬ በሌለችበት ጊዜ ምግብ የምሠራው እኔ ነኝ፡፡ የሚቀናኝም የውጭ ምግብ መጠባበስ ነው፡፡ በተለይ የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ምግብ መሥራት እወዳለሁ፡፡ መመገቡንም እንዲሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኛውን ዕድሜዎን ከኢትዮጵያ ውጭ በተለያዩ አገሮች እንዳሳለፉ አውቃለሁ፡፡ ለረዥም ጊዜ ውጭ የመቆየትዎ ምክንያቱ ምንድነው? ከኢትዮጵያ አወጣጥዎስ እንዴት ነበር?

ዶ/ር እሌኒ፡- የተወለድኩት እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ ግን በታዳጊ ዕድሜ ላይ እያለሁ ነው የወጣሁት፡፡ በጃንሆይ ጊዜ ነው፡፡ ዕድሜዬ አራት ዓመት ነበር፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር ወደ ኒውዮርክ ሄድን፡፡ ኒውዮርክ ከሄድኩ በኋላ አማርኛ ረስቼ አፍ መፍቻ ቋንቋዬ እንግሊዝኛ ሆነ፡፡ እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ተመለስን፡፡ አብዮት ፈነዳ፡፡ አሁንም ተመልሰን ወደ ሩዋንዳ ሄድን፡፡ ይህ ምልልስና ረዥም ጊዜ ውጭ መቆየቴ የኢትዮጵያን ባህል ብዙ እንዳላውቅ አድርጐኛል፡፡ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ወደዚህ በምንመጣበት ጊዜ ደግሞ አማርኛ ረስተን ነበር፡፡ ወላጆቻችን የአሜሪካ ትምህርት ቤት ነበር ያስገቡን፡፡ በዚህ የተነሳ አማርኛ ደካማ ነበርኩ፡፡ ግን ዕድሜዬ ከፍ እያለ ሲመጣ ስለኢትዮጵያ ብዙ ማሰብ የጀመርኩ፡፡ በተለይ ሩዋንዳ ስንሄድ አሥር ዓመቴ ነበር፡፡ ቤተሰቦቼም በቃ አሁን ቤት ውስጥ አማርኛ እንጂ ሌላ ቋንቋ መናገር አይፈቀድም አሉ፡፡ ይኼኔ ጫና መጣ፡፡ እኔና እህቴ ትምህርት ቤት የምንማረው በፈረንሳይኛ ነው፡፡ እርስ በርሳችን በእንግሊዝኛ ነው የምናወራው፡፡ ከዚያ ቤት ስንገባ ደግሞ በአማርኛ ማውራት እንሞክራለን፡፡ አማርኛ የማወቅ ጉጉት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ የሆኑ ባህላዊ ነገሮችን መመልከት ጀመርኩ፡፡ ለማወቅ የነበረኝ ፍላጐት እያደገ መጥቶ ስለኢትዮጵያ የማወቅ ጉጉቴ ጨመረ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ፍላጐት ቢኖረኝም በደርግ ወቅት ለመምጣት ከባድ ነበር፡፡ ደርግ እየቆየ ሲሄድ ደግሞ ቀይ ሽብር መጣ፡፡ ስለዚህ ለዕረፍት እንኳን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አልተቻለም፡፡ እንዲያውም በወቅቱ ስለኢትዮጵያ የምንሰማው ነገር ሁሉ ያስጨንቃል፡፡ እዚህ ስላሉ ቤተሰቦቻችንም በማሰብ መጨነቅ ጀመርን፡፡ የአክስት የአጐት ልጆቻችንን ጭንቀት ስሰማ ደግሞ የሚረብሽ ነገር ነበረው፡፡ ስለዚህ በዚያን ወቅት ለኢትዮጵያ ሥጋትም ጉጉትም ኖሮኝ ነው ያደግኩት ማለት እችላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሩዋንዳም ሆነ ወደ አሜሪካ የመጓዛችሁ ምክንያት ግን ምን ነበር?

ዶ/ር እሌኒ፡- አባቴ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኛ ነበረ፡፡ በጃንሆይ ጊዜ ለሥራ ተመድቦ ሲሄድ አብረነው ሄድን፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰን ትንሽ ከቆየን በኋላ ደግሞ ከአብዮቱ መፈንዳት ጋር ተያይዞ ሌሎች አምልጠው ከአገር እንደወጡት ሁሉ፣ እኛም በአባቴ ሥራ ምክንያት ተደርጐ ወጣን፡፡ ያኔ እንዲያውም ኤርፖርቱ ተዘግቶ ስለነበር ሰው ከአገር የሚወጣው በሌላ መንገድ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተስ እንዴት ወጣችሁ?

ዶ/ር እሌኒ፡- እኛ የወጣነው በልዩ ፈቃድ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተባባሪነት በሥራ ምክንያት እንደምንሄድ ተደርጐ ነው የወጣነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትዎን የት ነው የተማሩት?

ዶ/ር እሌኒ፡- የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተማርኩት ኬንያ ነው፡፡ ከሩዋንዳ ቆይታችን በኋላ እዚሁ አፍሪካ አገሮች ነው የቆየሁት፡፡ እኔ አፍሪካ ውስጥ ነው ያደግኩት የምለውም ለዚህ ነው፡፡ የፓን አፍሪካኒዝም አመለካከት አለኝ ብዬ የማምነው፡፡ አሁንም ለሥራ የጠቀመኝ ነገር ቢኖር ከልጅነቴ ጀምሮ አፍሪካ ውስጥ መኖሬ ነው፡፡ ሩዋንዳ ከኖርኩ በኋላ ለአዳሪ ትምህርት ቤት ወደ ኬንያ ተዛወርኩ፡፡ እኔ ወደ ኬንያ ስሄድ ወላጆቼ ደግሞ ወደ ቶጐ ሄዱ፡፡ ከቶጐ ወደ ማላዊ ተዛወሩ፡፡ ስለዚህ በዕረፍት ጊዜዬ ወደ ቶጐና ሌሎች የምዕራብና የደቡብ አፍሪካ አገሮች ከእህቶቼ ጋር እሄዳለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት አፍሪካን በደንብ የማወቅ ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ስዋህሊና ፈረንሣይኛን  ተማርኩ፡፡ ደቡብ፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብና መካከለኛ አፍሪካን ተዟዙሬ በማወቄ የአፍሪካን ጣዕም ማጣጣም ቻልኩ፡፡ በዚህ ምክንያት እኔ ፓን አፍሪካኒስት ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- በአፍሪካ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትዎን ከተከታተሉ በኋላ የከፍተኛ ትምህርትዎን ኒውዮርክ እንደተማሩ ይታወቃል፡፡ የሚፈልጉትን ትምህርት ነው መማር የቻሉት?

ዶ/ር እሌኒ፡- ለከፍተኛ ትምህርት አሜሪካ እንድገባ ያገዘኝ አንዱ ምክንያት በኬንያ የተማርኩበት የአሜሪካ ሚሽን ትምህርት ቤት መሆኑ ነው፡፡ ወደ አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ለመሄድ የተመቸ ነበር፡፡ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ጥሩ ውጤት ስለነበረኝ ወደ አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ለመግባት የሚያስችለውን ፈተና 99 በመቶ አገኘሁ፡፡ ቶፍል አያስፈልግሽም ተባልኩ፡፡ ስለዚህ ባገኘሁት ማርክ ብቻ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ይጽፉልኝ ጀመር፡፡ እኔ ኮርኔል ዩኒቨርሲቲን መረጥኩ፡፡ ሙሉ ስኮላርሽፕ ሰጡኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የመረጡት ትምህርት ምን ነበር?

ዶ/ር እሌኒ፡- ኢኮኖሚክስ፡፡  

ሪፖርተር፡- በመጀመሪያ ተቀጥረው የሠሩበትን ቦታ ያስታውሱታል?

ዶ/ር እሌኒ፡- በፕሮፌሽናል ደረጃ ሳይሆን እየተማርኩ በነበረበት ጊዜም ቢሆን ሥራ ተቀጥሬ ሠርቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አሜሪካ በትምህርት ላይ እያሉ ማለት ነው? ምን ዓይነት ሥራ ነበር የሚሠሩት?

ዶ/ር እሌኒ፡- አዎ፡፡ አሜሪካ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን እማር በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀጥሬ የሠራሁት ደግሞ በርገር ኪንግ በሚባል ምግብ ቤት ውስጥ አስተናጋጅ ሆኜ ነው፡፡ በዕረፍት ጊዜዬ ትምህርት ቤት ሲዘጋ የአስተናጋጅነቱን ሥራ ለተወሰነ ጊዜ ሠርቻለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- የመስተንግዶውን ሥራ ፈልገው ነው የሠሩት?

ዶ/ር እሌኒ፡- እንዴ አዎ! ፈልጌው ነው የሠራሁት፡፡ ትንሽ ገንዘብ ለማግኘት ስል ገብቼበታለሁ፡፡ ተማሪ ስትሆን እኮ ብር የለም፡፡ ስኮላርሽፑም የተወሰነ ስለሆነ እንዲህ እየሠራህ በምታገኘው ገንዘብ የምትፈልገውን ነገር ታሟላበታለህ፡፡

ሪፖርተር፡- በመስተንግዶ ሥራው ምን ያህል ይከፈልዎ ነበር?

ዶ/ር እሌኒ፡- ይመስለኛል … በሰዓት ሦስት ወይም አራት ዶላር ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- ከበርገር ቤቱ አስተናጋጅነት ሌላ የሠሩት ሥራ የለም?

ዶ/ር እሌኒ፡- ሌሎች ጥቃቅን ሥራዎችንም ሠርቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

ዶ/ር እሌኒ፡- ቢሮ ውስጥ በረዳትነት የፎቶ ኮፒ የማንሳት ሥራ፣ ፋይል መደርደርና የመሳሰሉትን ሥራዎች እየተማርኩ ሠርቻለሁ፡፡ ግድ ነው፡፡ መሥራት አለብህ፡፡  

ሪፖርተር፡- እንደሰማሁት ብዙም ችግር አልነበረብዎትም፡፡ የትምህርት ቤት ወጪም አልነበረብዎትም፡፡ ወላጆችዎ እዚያው የነበሩ ይመስለኛል፡፡ ይህ ከሆነ እንዲህ ያለውን ሥራ ለምን አስፈለገ ብዬ ነው?

ዶ/ር እሌኒ፡- ያኔ ወላጆቼ ደቡብ አፍሪካ ነበሩ፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሠራተኞች ልጆች የሚሰጠው ድጋፍ ነበር፡፡ ነገር ግን ለሌሎች ወጪዎች ግን ራሴ ሠርቼ ነበር የማገኘው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚያን ወቅት የመጀመሪያ ክፍያዎን ምን እንዳደረጉት ያስታውሳሉ?

ዶ/ር እሌኒ፡- … እም … ብዙም አላስታውስም፡፡ ግን የወቅቱን ባህሪዬን ሳስታውስ በእርግጠኝነት ልብስ ወይም ጌጥ ነው የምገዛበት፡፡ ሌላ ነገር ልገዛበት አልችልም፡፡ አንዳንዴም ከማገኘው ክፍያ ከእህቴ ጋር ስለነበርኩ ለቤት ኪራይም የረዳኋት ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ጌጣጌጥ ይወዳሉ ማለት ነው?

ዶ/ር እሌኒ፡- እወድ ነበር፡፡ እወዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የከፍተኛ ደረጃ ትምህርትዎን ሲከታተሉ የኢኮኖሚክስ ትምህርቱንስ እንዴት አገኙት? የፈለጉት የትምህርት ዘርፍ ነበር?

ዶ/ር እሌኒ፡- ዩኒቨርሲቲ ከመግባቴ በፊት ምን ልማር እንደምችል ቀድሜ ወስኜ ነበር፡፡ ለምን እንደምማር እንኳን የራሴ የሆነ ዕቅድ ነበረኝ፡፡ እንዲያውም ሩዋንዳ እያለሁ በ15 ዓመቴ አካባቢ ራሴ እመራበታለሁ ያልኩትን የአሥር ዓመት ዕቅድ አውጥቼ ነበር፡፡ ከ15 እስከ 25 ዓመቴ ባለው ጊዜ ውስጥ ልሠራቸው ይገባል ያልኳቸውን ሥራዎች በዝርዝር ያስቀመጥኩበት የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ነበረኝ፡፡ አሁን አገሮች የአምስት የአሥር ዓመት ዕቅድ እንደሚያወጡ ሁሉ፣ እኔም ሕይወቴን የምመራበት ዕቅድ አወጣሁ፡፡ ኢኮኖሚክስ የመማሬም ነገር የዚህ ዕቅድ አካል ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ለአንድ ሕይወትዎ እንዲህ ያለውን የአሥር ዓመት ዕቅድ ለማውጣት ያነሳሳዎት ምንድነው?

ዶ/ር እሌኒ፡- አሁን ነገሩን ወደኋላ ሳስበው ይገርመኛል፡፡ ብዙ ሰው እንዲህ ያለ ልምድ የለውም፡፡፡ እህቶቼም እንዲህ ሲያደርጉ አላየሁም፡፡ አድርጊ ተብዬም አይደለም፡፡ ግን እንደማስታውሰው አባቴ በሩዋንዳ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩኤንዲፒ ኃላፊ ነበርና ብዙ ቦታ አብረን እንሄዳለን፡፡ አንድ ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት ወይም የተለያዩ ፕሮጀክቶች ሲመረቁ ከእነሱ ጋር ፕሮግራሙ ላይ የመገኘት ዕድል ነበረኝ፡፡ የተለያዩ ሙያ ያላቸው ሰዎች ቤታችን በብዛት ይመጡ ነበር፡፡ እራት ላይ የተለያዩ ውይይቶች ይደረጋሉ፡፡ ወላጆቼም ቅረቢያቸው አዋሪያቸው እያሉ በጣም ይገፋፉኝ ነበር፡፡ እናቴም የተመድ ሠራተኞች ባለቤቶችን (ሚስቶችን) አሰባስባ ማኅበር ፈጥራ በመላው ሩዋንዳ እየተዘዋወረች የበጐ አድራጐት ተግባር ላይ ትሳተፍ ነበር፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቶቹን ምሳሌዎች ይዤ ስለዕድገት፣ ስለአገር ልማት፣ አሉ ስለሚባሉ የተለያዩ ችግሮች እያሰበኩ ማደጌም የራሱ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ በተለይ ደግሞ በአንድ ወቅት ቤት ውስጥ የነበረና (ሃው ኢሮፕ አንደር ዴቨሎፕድ አፍሪካ) የሚል መጽሐፍ አነበብኩ፡፡

አውሮፓ እንዴት አፍሪካን በዝብዛ ድህነት ውስጥ እንደጣለቻት የሚገልጽ ነው፡፡ እዚህ መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ አፍሪካውያን የራሳቸውን መፍትሔ አላመጡም ይላል፡፡ ሁሌ የውጭ ሰው በሚነግራቸው የሚሄዱ ስለመሆናቸውና ከቅኝ ግዛት ቢወጡም አስተሳሰባቸው አሁንም በቅኝ ግዛት ሥር እንዳሉ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ አፍሪካውያን ፈረንጅ የነገራቸውን እንጂ የራሳቸውን ማጐልበት የማይሹ ስለመሆናቸው ሁሉ ይገልጻል፡፡ የራሴ ዕቅድ እንዲኖረኝ ይህም መጽሐፍ አንድ ምክንያት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ለአሥር ዓመታት አከናውነዋለሁ ብለው ያወጡት ዕቅድ ጥቅል ይዘት ግን ምንድን ነበር?

ዶ/ር እሌኒ፡- የመጀመሪያው የዕቅዴ ይዘትና መነሻ የአፍሪካ የድኅነትና የኋላ ቀርነት መፍትሔ በውጭ ሰዎች ሳይሆን በእኛው አፍሪካውያን መፈታት አለበት የሚለው ነጥብ ሆነ፡፡ አፍሪካ በራስዋ መፍትሔ ካላገኘች አታድግም የሚለውን ነገር አመንኩ፡፡ ለዚህ ደግሞ ተምሬ ወደፊት እንደምገኝ ሰው ለአፍሪካ መፍትሔ ፈጣሪ መሆን እንዳለብኝ፣ ድህነትንና ረሃብን ለማጥፋት የራሴን አሻራ ማሳረፍ እንደሚኖርብኝም ወሰንኩ፡፡ እየጻፍኩ፣ ሐሳብ እያመጣሁ አፍሪካውያን የራሳችንን መፍትሔ እየፈለግን የዕድገታችን ንድፍ መቅረፅ ስለሚኖርብን፣ ይህንን ከሚያደርጉ ሰዎች መካከል አንዱ መሆን አለብኝ ብዬ ነበር ያቀድኩት፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ኢኮኖሚክስ ማጥናት አለብኝ፡፡ የኢኮኖሚክስ ትምህርቴንም እስከ ፒኤችዲ ማድረስ አለብኝ ብዬ ነው ያቀድኩት፡፡ በሙያዬ ጠንካራና ብቁ ለመሆን እስከ ዶክትሬት ዲግሪ መድረስ እንደሚኖርብኝም አስቀምጫለሁ፡፡ ከዚህ ጐን ለጐንም ኢኮኖሚክስን ሳጠና ስለግብርናም መማር እንደሚኖርብኝ ሁሉ የዕቅዴ አካል አድርጌ ጽፌ ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- ግብርናን ከኢኮኖሚክስ ትምህርቱ ጋር አጣምሮ ለመማር የፈለጉበት ምክንያት ምን ነበር?

ዶ/ር እሌኒ፡- በዚህች ባለችኝ ዕድሜዬ ያየሁት ትልቁ ድክመት የግብርናው ዘርፍ ነው፡፡ አፍሪካውያን ራሳችንን መመገብ ያልቻልነው ግብርናው ላይ ባለው ችግር ስለሆነ፣ ከሁሉም በላይ መጀመሪያ መፈታት ያለበት የረሃብ አጀንዳ ነው ከሚል እምነት ነው፡፡ ስለዚህ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ውስጥ ግብርና ላይ አተኩሬ በመማር ዶክትሬቴን በዚሁ እይዛለሁ ብዬ ነው ዕቅዴን የጻፍኩት፡፡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ እሠራለሁ፡፡ መጻሕፍት እጽፋለሁ የሚሉትን ምኞቶቼን በሙሉ ዕቅዴ ውስጥ አካተትኩት፡፡ ይህንን በዝርዝር የጻፍኩትን ዕቅዴን ከጨረስኩ በኋላ ለወላጆቼ አሳየኋቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ዕቅድዎትን ተቀበሉት?

ዶ/ር እሌኒ፡- ምን ክርክር አለው? ከዚያ ልክ ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ ስደርስ ደግሞ የመጀመሪያ ቀን የኮርስ ቡኬን ወስጄ የምወስዳቸውን ኮርሶች እንዴት እንደማጠና ሌላ ዕቅድ አወጣሁ፡፡ ኮርሶቹን ከመውሰዴ በፊት ቀድሜ አጠናሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በዚያን ያህል ደረጃ፣ በዚያ ዕድሜዎ ያቀዱትን ዕቅድ አሳክተዋል? ወይም እያሳኩት ነው? ተግባር ላይ አውቄዋለሁ ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር እሌኒ፡- አሳክቼዋለሁ፡፡ ግን ባስቀመጥኩት የአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ አልጨረስኩም፡፡ ለምሳሌ በአሥር ዓመት ውስጥ ዶክትሬቴን እይዛለሁ ብዬ ያስቀመጥኩት ዕቅድ በ15 ዓመቱ ነው የተሳካው፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያቱ ምንድነው?

ዶ/ር እሌኒ፡- በመሀል የተለያዩ ሥራዎች ላይ በመቆየቴ ጊዜው ትንሽ ተራዘመ፡፡ መስመሩ አልተቀየረም እንጂ እደርስበታለሁ ያልኩትን ምንም ያህል ጊዜው ቢገፋ አሳክቼዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ዓይነቱን ዕቅድ ባወጡበት ጊዜ ወጣት ነበሩ፡፡ እንዲያውም አፍላ ወቅት ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ዕቅዱን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያሰነካክልዎ ችግር አልገጠመዎትም?

ዶ/ር እሌኒ፡- የሚያሰነካክለኝ ነገር አልነበረም፡፡ ወላጆቼም እጅግ ያበረታቱኝ ነበር፡፡ የወላጆቼ መንፈስ ጠንካራ ነው፡፡ ሁሌም የፈለግሽውን ነገር መሥራት ትችያለሽ ነበር የሚሉኝ፡፡ አንድ ሐሳብ ሳመጣ ይኼማ አይሆንም የሚለኝ በአካባቢዬ አልነበረም፡፡ ሌላው ቀርቶ በእኛ ቤተሰብ የቤት ሥራ ሠርታችኋል ወይ አንባልም፡፡ ምን ውጤት አመጣችሁ ተብለን አንጠየቅም፡፡    

ሪፖርተር፡- ለምን?

ዶ/ር እሌኒ፡- ምክንያቱም ቤተሰቦቼ በእኔ ላይ ትልቅ እምነት ነበራቸው፡፡ ለሰዎች ሲያስተዋውቁኝና ስለኔ ሲናገሩ የእኛ ልጅ ወደፊት አገር የምትመራ ናት እያሉ ነበር፡፡ በእርሷ ሙሉ እምነት አለን ብለውም እኔን ለሌሎች ይገልጻሉ፡፡ ወላጆቼ ለእኔ የነበራቸው ይህ የጠነከረ እምነታቸው እኔንም ልበ ሙሉ አደረገኝ፡፡ ጠንክሬ መማር እንዳለብኝ፣ የምማረውም ለራሴ መሆኑን እንድገነዘብ አደረገኝ፡፡ በእነርሱ እምነት ምክንያት በራሴ እምነት እንድጥል አደረገኝ፡፡ ኮንፊደንስ ሰጠኝ፡፡ እንዲያውም እዚያ ዕቅድ ላይ ከአሥር ዓመት በኋላ የተመድ ዋና ጸሐፊ መሆን እችላለሁ ብዬ እንድጽፍ ያደረገኝ ይኼው ጠንካራ እምነት ነው፡፡ በእነርሱ አስተሳሰብ የአገርና የዓለም መሪ መሆን ትችያለሽ ብለው ጭምር ስላሳደጉኝም ነው፡፡ እኔ በግሌ ቤተሰብ ከዚህ በላይ ለልጆቹ የሚሰጠው ነገር የለም እላለሁ፡፡ ይህንን ያህል መተማመን ማሳደር፣ ይህንን ያህል እምነት ልጅ ላይ መጣል ከባድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዕቅዴ ነው ብለው ካሰቡት ውስጥ በተለይ በአፍሪካ ያለውን ችግር መቀየር በማለት ያስቀመጡትን ሐሳብ እያሳካሁ ነው ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር እሌኒ፡- እየሞከርኩ ነው፡፡ ለምሳሌ የገበያ ችግር አለ፡፡ ስለግብርና፣ ስለምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አስብ ነበር፡፡ ረሃብንም የማጥፋት ዕቅድ ነበረኝ፡፡ በኋላ ላይ ማምረት ብቻ አይደለም፣ ምርትን ማሸጋገርና መነገድ ላይ ራሱን የቻለ ጉድለት እንዳለ ተረዳሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህ መቼ የመጣ ሐሳብ ነው?

ዶ/ር እሌኒ፡- ወደ ማስተርስ ትምህርቴ ስገባ ነው፡፡ ይህ የገበያ ሁኔታ ደግሞ ብዙ ያልተጠና ነው፡፡ በውጭ አገር የምትሰማው ደግሞ ነፃ ገበያ ነፃ ገበያ የሚል ነው፡፡ የዚህ ሐሳብ ድምዳሜም መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ገበያውን ለቆ ነፃ ገበያ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ገበያው በራሱ ይስተካከላል የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ እኔም ይህንን ጉዳይ መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ መንግሥት ወጥቶም ቢሆን ገበያው ያልተስተካከለበት ብዙ ቦታ አለ፡፡ መንግሥት በወጣበትና ነፃ ገበያ በተባለበት አካባቢም ቢሆን ነፃ ገበያ የማይሠራ መሆኑ ታይቷል፡፡ ስለዚህ ነፃ ገበያው እንዳለ ሆኖ መንግሥት ሊጫወተው የሚችለው የራሱ የሆነ ሚና ሊኖር ይገባል የሚለውን ሐሳብ ማውጠንጠን ውስጥ ገባሁ፡፡ ምክንያቱም የፈረንጆቹ አመለካከት በነፃ ገበያ የመንግሥት ሚና መኖር የለበትም የሚል በመሆኑ፣ መንግሥት ያለበት ነፃ ገበያ ለአፍሪካም መፍትሔ ሊሆን ይችላል ከሚል ሐሳብ ነው፡፡ ይህ ነገር ትኩረቴን ስቦ በዚህ ጉዳይ ብዙ መጻሕፍት አነበብኩ፡፡ አሁን ነፃ ገበያ ይባላል እንጂ የሌለበት ቦታ አለ የሚለውን ነገር መጨበጥ ቻልኩ፡፡ ነፃ ገበያን የሚጠላ ባይኖርም፡፡ ነገር ግን ከነፃ ገበያ ጀርባ ደግሞ ተቋማት አሉ፡፡ እምነት የሚፈጥሩ ሕጐች አሉ፡፡ አሠራሮች አሉ፡፡ የሰው አቅም ግንባታ አለ፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሲኖሩ ነው ነፃ ገበያው የሚሠራው፡፡ ይህንን ለማስቀመጥ ደግሞ የግል ዘርፉ ብቻውን የሚሠራው አይሆንም፡፡ ስለዚህ የግድ መንግሥትና የግል ዘርፉ አብሮ መሥራት መቻል አለበት የሚል ሐሳብ ውስጥ መግባት ጀመርኩና ከመምህራኖቼ ጋር ሁሉ መከራከር ጀመርኩ፡፡  

ሪፖርተር፡- የክርክራችሁ ጭብጥ ምን ነበር?

ዶ/ር እሌኒ፡- እናንተ በምትሉት ነገር አልስማማም የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ የምርት ገበያ ሥርዓትን የደረሱበት በኋላ ነው፡፡ ይኼ ገበያ መስተካከል አለበት የሚለውን  አጠነከርኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደዚህ ሐሳብ የወሰደዎት ምንድነው? በተግባር የተመለከቱትስ ነገር ነበር?

ዶ/ር እሌኒ፡- እንዲህ ያለውን አስተሳሰቤን በማራምድበት ጊዜ የደርግ ወቅት ስለነበር ኢትዮጵያ መምጣት አልቻልኩም፡፡ ግን ለማስትሬት ጽሑፍ ልሠራ ወደ ማሊ ሄድኩ፡፡ ጥናቴን የምሠራው በገበያ ችግር ላይ ነው፡፡ የገበያው ችግር ምንድነው? ብዬ ስጠይቅ በሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ምላሽ አገኘሁ፡፡ ጥራት የለም፡፡ የምርት ጥራት ማረጋገጫ የለም፡፡ የምርት ልኬቱ ወይም መጠን የዋዥቀ ነው፡፡ በዋስትና የሚሠራበት አይደለም፡፡ ልኬት ይጭበረበራል፡፡ ብዙ የመረጃ ጉድለቶች መኖራቸውን የሚያመላክቱ ምላሾች አገኘሁ፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሲፈጠር ለመቅረፍ የተፈለገው ሁሉ በማሊም የነበረው ችግር ተመሳሳይ ነበር፡፡ ይህንን በደንብ ያየሁት ከ20 ዓመታት በፊት ተማሪ እያለሁ በማሊ የተመለከትኩት ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ለአፍሪካ መፍትሔ የሚሆን ነገር እፈጥራለሁ የሚለው ዕቅዴን በመጠኑም ቢሆን፣ በገበያ ሥርዓት በመግባት በአቅሜ እያደረግኩ ነው ብዬ የማስባቸው ነገሮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ዶክትሬትዎን ለመያዝ ተፈትነው እንደነበረና ከፕሮፌሰርዎ ጋር እንደተጋጩም ይወራል፡፡

ዶ/ር እሌኒ፡- ኢኮኖሚክስ ማለት በወንዶች የበላይነት የተያዘ ዘርፍ ነው፡፡ ማስተርስ፣ ባችለር እና ዶክትሬቴን ስማር ከአንዷ በስተቀር ፕሮፌሰሮቹ በሙሉ ወንዶች ናቸው፡፡ በዶክትሬት ስመረቅ እኔ ብቻ ነበርኩ ሴት፡፡ አንዳንድ ባለትዳሮች ነበሩ፡፡ እኔም ባለትዳር ነበርኩ፡፡ ኢትዮጵያ መጥቼም እህል ገበያ ላይ ጥናት ባደረግኩበት ጊዜ ነፍሰ ጡር ነበርኩ፡፡ ጥናቴን ጨርሼ ተመለስኩ፡፡ እርጉዝ ብሆንም ወልጄ ጥናቴን እያጠናሁ እቀጥላለሁ የሚል ዕቅድ ይዣለሁ፡፡ እንዲህ ማድረጌም ችግሩ አልታየኝም፡፡ ለፕርፌሰሬም ልወልድ ነውና የተወሰነ ጊዜ እንደምቆይ እንዴት ነው የምነግረው ብዬ ከአንድ ሴት ጓደኛዬ ጋር ተመካከርኩ፡፡ ለትምህርቱ ፍላጐት የላትም እንዳይለኝ ነው የፈራሁት፡፡ የሠራሁትን ሥራ ይዤ ሄጄ አስረድቼው ለስድስት ወር ዕረፍት እንደምወስድ ስነግረው፣ ስመለስ ደግሞ የምሠራውን ሥራ ዕቅድ አቀረብኩለት፡፡ ለምንድነው ዕረፍት የምትወስጂው አለኝ፡፡ ልወልድ ነው አልኩት፡፡ ይኼኔ በጣም ተበሳጨ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ለምን?

ዶ/ር እሌኒ፡- እንኳን ደስ አለሽ እንደማለት የያዘውን እስክርቢቶ ወረወረ፡፡ ‹በጣም አዝናለሁ ብዙ ተማሪዎች እኔ ዘንድ ለመማር ይፈልጋሉ፡፡ ከአንቺ ጋር በኢትዮጵያ ገበያ ዙሪያ ጥሩ ሥራ ጀምረን ነበር፡፡ ይህንን በማድረግሽ ግን በጣም አዝናለሁ፡፡ ጊዜዬን አጠፋሁ› ብሎ ተናገረኝ፡፡ በጣም ተናደድኩ፡፡ እንባዬ መጣ፡፡ እንደሚመስለኝ ይህንን ሁሉ ያለው ሴት ስለሆንሽ ትወልጃለሽ ከዚያ ነገሩን ትተያለሽ በሚል ነው፡፡ እንባዬ መጣ፡፡ ወጣሁ፡፡ ዕረፍቴን ወሰድኩ፡፡ ወለድኩ፡፡ ስድስት ወር ቆይቼ በዕቅዴ መሠረት ተመለስኩ፡፡ የሠራሁትን ጽፌ ሰጠሁት፡፡ እዚያ ጽሑፌ ላይ ግን አንድ ማስታወሻ ጻፈ፡፡

ሪፖርተር፡- ምን የሚል?

ዶ/ር እሌኒ፡- ‹ከእናትነት እንቅልፍሽ እንደነቃሽ አይቻለሁ፣ ጥሩ ጽፈሻል› የሚል ነው፡፡ ይህም ጽሑፍ ቢሆን ተገቢ አልነበረም፡፡ የበለጠ ያናደደኝ እሱ ነው፡፡ እየተናደድኩም ቢሆን ቀጠልኩ፡፡ የሚቀጥለውንም በጥሩ ሁኔታ ሠራሁ፡፡ ይህንን ሁሉ የማደርገው መሀል ላይ እቤቴ እየሄድኩ ልጄነ እያጠባሁ በመመለስ ነው፡፡ ማታም የእራት ሥራ ይጠብቀኛል፡፡ ለባለቤቴም ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ትምህርቴን ከሌሎች እኩል ጨረስኩ፡፡ ያመጣሁትም ውጤት ለሽልማት የሚያበቃኝ ሆነ፡፡ ፕሮፌሰሩ ጥሩ ደብዳቤ ጻፈልኝ፡፡ እንደዚህ ሆኖ ጨረስኩ፡፡ መጨረሻ ላይም ባመጣሁት ውጤት ሽልማት እንደማገኝ ኢሜይል ተላከልኝ፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ ከዚሁ ፕሮፌሰር ጋር ቤኒን አገር በአንድ ፕሮጀክት ላይ እየሠራን ነበር፡፡ ኢሜይሉ ሲመጣልኝ እሱ አጠገቤ ነበርና ዞር ብዬ አፈጠጥኩበት፡፡ ታስታውሳለህ ወይ? የዛሬ ሦስት ዓመት አንቺ ጊዜዬን አጠፋሽ ብለህ የተናገርከውን ዛሬ እግዚአብሔር አሳየኝ ብዬ አለቀስኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ገበያ ወጥተው ገበያውን አይተዋል፣ ሰምተዋል፣ ተመልክተዋል፡፡

ዶ/ር እሌኒ፡- አይቼዋለሁ፡፡ እውነት ለመናገር ገና ብዙ ሊሠራ የሚገባው ነገር አለ፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እኮ ገና ጫፉን ነው የነካነው፡፡ የመጋዘን ችግሩ ከተቀረፈ ብዙ ለውጥ ይመጣል፡፡ ሰሞኑንም የድረ ገጽ ግብይት ተጀምሯል፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ ይበልጥ ግን ተፅዕኖ የሚኖረው የመጋዘን አገልግሎት ሲሻሻል ነው፡፡ ሲስፋፋና ሲሻሻል ብዙ ምርቶችን ወደ ምርት ገበያው ማስገባት ይቻላል፡፡ ብዙ ምርቶች ሲገቡ ሥርዓት ያለው ግብይት እያደገ ይመጣል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከአርሶ አደር ጀምሮ እስከ ግብይቱ ድረስ በጥራት የማምረትና የምርት ዕድገት መጨመር አለበት፡፡ የምርቶች መያዣ ጆንያ ሳይቀር ለግብይት ሥርዓት መቀላጠፍ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ የምርት ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች አቅርቦትና የመሳሰሉ አገልግሎቶች በደንብ መደራጀት አለባቸው፡፡ እኔ አሁን እንደማስበው በምርት ገበያው ሥራ ላይ እሴት መጨመር የሚችሉና ግን ያልተፈጠሩ አገልግሎቶች አሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

ዶ/ር እሌኒ፡- የትራንስፖርት አገልግሎት አንዱ ነው፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ በጣም ደካማ ነው፡፡ ለምሳሌ ከምርት ገበያው ምርት ለማውጣት የሚፈልግ ሰው ማጓጓዣ ለማግኘት ሦስት ቀናት ያስፈልጉታል፡፡ ምርቱ ከተጤነ በኋላ የተለያዩ ችግሮችም ይታያሉ፡፡ ስለዚህ የሎጂስቲክሱ ሥራ ላይ ገና ይቀረናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በመጋዘን አገልግሎት ዙሪያም መሠራት ያለበት ነገር አለ፡፡ መጋዘን ምርቱን ለማስቀመጫ ብቻ ሳይሆን የጥራት ደረጃ መፈተሻም በመሆኑ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶች የጥራት ደረጃቸውን እንዲይዙ ከመጋዘኑ ጐን ክሊኒክ ሊኖር ይገባል፡፡ ዕድሉ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ አገልግሎቶች እስካሁን ለምን አልተፈጠሩም?

ዶ/ር እሌኒ፡- ይህንን ጉዳይ እኔም ራሴ አጠናለሁ ብያለሁ፡፡ ምክንያቱም አብረው መሄድ ያለባቸው አገልግሎቶች ከምርት ገበያው ጋር አላደጉም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ወደፊት መኖር አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከምርት ገበያው ከወጡ በኋላ መለስ ብለው አይተውታል?

ዶ/ር እሌኒ፡- አልፎ አልፎ እሄዳለሁ፡፡ አዲሱ ሥራ አስፈጻሚም ጐበዝ ነው፡፡ በስልክም አገኘዋለሁ፡፡ ሥራ ሰጀምርም ሄጄ አይቼዋለሁ፡፡ ሰሞኑንም አግኝቸዋለሁ፡፡ ሒደቱ ጥሩ ነው፡፡ በሰዎች ላይ እምነት እየጣለ ነው፡፡ ሲስተሙ ግን አንድ ቦታ ላይ ቆሟል፡፡ ይህንን ለማንቀሳቀስ እየተሠራ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የማግዘው ነገር የለም ይላሉ?

ዶ/ር እሌኒ፡- የምደግፍበት አሠራር ባይኖርም በሐሳብ ርቄያለሁ ማለት አይደለም፡፡ አሁን የያዝኩትን ሥራ ከጨረስኩ በኋላ ከምርት ገበያው አሠራሮች ጋር ተየያዥ የሆኑ ሥራዎችን መሥራቴ አይቀርም፡፡ አሁን ግን ዝግጁ አይደለሁም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ምን እየሠሩ ነው?

ዶ/ር እሌኒ፡- አሁንም በአፍሪካ የገበያ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ችግሮችን ይቀርፋል ብዬ በማምንበት ተመሳሳይ ሥራ ውስጥ ነኝ፡፡ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዓይነት ተቋም በጋና እንዲቋቋም አድርገናል፡፡ እንዲያውም የጋና ፕሬዚዳንት በተገኙበት ፕሮጀክቱ ሥራ ጀምሯል፡፡ የጋናው ምርት ገበያ (ጂሲዋይ) ይባላል፡፡ የእኛ (ኢሲኤክስ) ወደፊትም በአፍሪካ ውስጥ ብዙ የምርት ገበያዎች እየፈጠረ ነው፡፡ የጋናው ተጀምሯል፡፡ በታንዛንያም ተመሳሳይ ተቋም ለመፍጠር እየተዘጋጀን  ነው፡፡ በካሜሩንም ተመሳሳይ ተቋም ለመፍጠር ጥናቱን ጨርሰን ፈቃድ አግኝተናል፡፡ እንዲህ እያልን ቀስ በቀስ እንሄዳለን፡፡   

ሪፖርተር፡- ጋናን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ዘመናዊ የግብይት ተቋማት አልነበሩም ማለት ነው?

ዶ/ር እሌኒ፡- አንዳቸውም አልነበራቸውም፡፡ የሚገርመው ጋና መካከለኛ ገቢ አላቸው ከሚባሉ አገሮች ውስጥ ያለች ነች ቢባልም፣ የሚገርምህ በኢትዮጵያ ከነበረው የግብይት ሥርዓት ምንም ያልተሻለ አሠራር የነበራት ነች፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ጉዳዮች የደከመ ነው፡፡ ሁሉም ነገር በባህላዊ አሠራር ነው፡፡ ሥርዓት አልነበረም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ አስተያየት ሲሰጡ ለምርት ገበያ በጣም ገና ነን ይላሉ፡፡ ‹እኛ እንኳ እንደ ኢትዮጵያ አይደለንም፣ ምንም የለንም› ሲሉ እኔን ይገርመኛል፡፡ በኢትዮጵያ ይህንን የምርት ገበያ ስንጀምር ከጋና ባነሰ ሁኔታ ላይ ነበርን፡፡ በሌላ አንፃር ሳየው ደግሞ እኛ ራሳችንን ዝቅ አድርገን ነው የምናስበው የሚባለውም ያስቆጭሃል፡፡

ሪፖርተር፡- በሕይወትዎ ተፈትኜበታለሁ፣ ወይም ከባድ ፈተና ገጠመኝ ብለው የሚጠቅሱት ነገር አለ?

ዶ/ር እሌኒ፡- ብዙ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ነገር ግን ለእኔ ትልቁ ብዬ የምገልጸው የኢትዮጵያ ምርት ገበያውን ሐሳብ ወደ መሬት ለማውረድ የገጠመኝ ፈተና ነው፡፡ ይህንን ሐሳብ ወደ መሬት ለማውረድ በምንሠራበትና ሰውን ለማሳመን በምንቀሳቀስበት ጊዜ የገጠመኝ ፈተና በሕይወቴ ገጥሞኝ የማያውቅ ነው፡፡ ወደፊትም ይገጥመኛል ብዬ አላስብም፡፡ በተለይ በተለያዩ ክልሎች እየዞርን ባለድርሻ አካላትን፣ ገበሬዎችንና ነጋዴዎችን ለማነጋገር በተጠሩ ስብሰባዎች የገጠሙኝ ብዙ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ የምርት ገበያው መፈጠር ያናደዳቸው ሰዎች ያወርዱብኝ የነበረው ስድብ የሚዘገንን ነበር፡፡ እየተነሱ አንቺ ምን ታውቂያለሽ በማለት ጭምር ሲጮኹብኝ ነበር፡፡ እንዲያው ይህንን ነገር እንዴት ነው የምወጣው ብዬ እፀልይ ሁሉ ነበር፡፡ በጩኸት ጭምር ሲናገሩኝ በስብሰባ አዳራሹ መድረክ ላይ ሆኜ እፀልይ ነበር፡፡

ይህቺ ከአሜሪካ መጥታ የማናውቀውንና የማያስፈልገንን ነገር በግድ ልታሠራን ነው በማለት መናገራቸው ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ሊገለጽ የማይችል ቃል ሁሉ እየተጠቀሙ ሞግተውኛል፡፡ በአንዳንድ ስብሰባዎች ላይ የሚነገረውን ስሰማ ለሕይወቴ ሁሉ ፈርቼ ነበር፡፡ የሰው ቅሬታና ንዴቱ በጣም ኃይለኛ ነበርና ለእኔ አስቸጋሪው ወቅት ይህ ነበር፡፡ በትዕግሥትና በአክብሮት መልስ መስጠት ነበረብኝ፡፡ የሰውን ስሜት ለማብረድ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረብኝ፡፡ አብረህ በንዴት መልስ ብትሰጥ አብረህ ገደል መግባት ስለሚሆን ይህንን ስሜት ለመቀየር ብዙ ተፈትኛለሁ፡፡    

ሪፖርተር፡- የምርት ገበያውን አፈጣጠር አስታውሱኝ እስቲ?

ዶ/ር እሌኒ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የምርት ገበያ ያስፈልጋል ብዬ የተናገርኩት እ.ኤ.አ. በኅዳር 2002 ነው፡፡ በወቅቱ ረሃብ ተከስቶ ዕርዳታ ነበር፡፡ ምንድነው ችግሩ? ወደ ዕድገት ለመሄድ እየተሞከረ፣ ግብርና ላይ ብዙ ሥራ ለመሥራት እየተሞከረ ምን ተከሰተ? በሚለው ጉዳይ ላይ ከዓለም ባንክ ጋር ስብሰባ ተደረገ፡፡ በዚህ ኮንፈረንስ ላይ እንድገኝ ተጋበዝኩ፡፡ ስጋበዝም አንቺ ስለኢትዮጵያ አጥንተሻል፡፡ ስለዚህ በሙያሽ በገበያ ዙሪያ ስላለው ችግር ነይና አስተያየት ስጪ ተባልኩ፡፡ በዚህ ውይይት ላይ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋም ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ የነበረኝ መረጃ 20 እና 30 ሰው ይገኛል የሚል ነበር፡፡ ስብሰባውም ግዮን ሆቴል እንደሚካሄድ ነው የተነገረኝ፡፡ ስብስባው ከመደረጉ አንድ ቀን ቀደም ብዬ ከዋሽንግተን አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ በስብሰባው ቀን ወደ ግዮን ሆቴል ስሄድ ግን የስብሰባው ቦታ ተቀይሯል፡፡ ስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ነው የሚካሄደው ተባልኩ፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩም [አቶ መለስ ዜናዊ] ይገኛሉ ተባለ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን እኔ ምንም መረጃ የለኝም፡፡ ሄድኩ፡፡ እንደተባለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ለምን እንደሆነ ባላውቅም የምፈልገውን ነገር ለማድረግ ይህ ለእኔ ጥሩ አጋጣሚ ነው አልኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

ዶ/ር እሌኒ፡- ዛሬ ይህንን ነገር በደንብ ካቀረብኩ የሚቀርበው ሐሳብ ለተፈጻሚነቱ ዕድል አለው ብዬ እምነት ስላደረብኝ፡፡ በዚያን ወቅት ኑሮዬ ውጭ ነው፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ሐሳብ አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን ያጠናሁት ስለምርት ገበያ ስለነበረ በወቅቱ የነበረው ስብሰባም በዚህ ዙሪያ ስለሆነ አጋጣሚውን እጠቀምበታለሁ ብዬ ወሰንኩ፡፡ እንደ አንድ ባለሙያ ቀርበሽ ተናገሪ ስባል ዕድሉን እጠቀምበታለሁ ብዬ ወሰንኩ፡፡ ዕድሉን አገኘሁና ለኢትዮጵያ የምርት ገበያ ያስፈልጋል አልኩ፡፡ ነገሩንም በዝርዝር አቀረብኩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በደንብ አዳመጡኝ፡፡ ብዙ ጥያቄዎች ቀረቡልኝ፡፡ መልስ ሰጠሁ፡፡ ስብሰባው ባለቀ ማግሥት ንግድ ሚኒስቴር ሄደሽ ነገሩን አስረጂ ተባልኩ፡፡ ለባለሙያዎች ትንታኔዬን አቀረብኩ፡፡ ይህ በሆነ በሦስተኛው ቀን ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ የኢኮኖሚ አማካሪ ክቡር አቶ ነዋይ ገብረ አብ ዘንድ ቀርበሽ ሐሳብሽን አብራሪ ተባልኩ፡፡ ስለዚህ አጀማመሬ እንዲህ ነው፡፡ ሌላ የተፈጠረ ነገር የለም፡፡ ተጋበዝኩ ተናገርኩ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የተናገርኩበት ቦታና ጊዜ አመቺ ሆኖ የምፈልገውን ነገር ማሳካት ቻልኩ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት ወደ ሥራው መግባት ቻሉ?

ዶ/ር እሌኒ፡- ከዚያ በኋላማ ኢትዮጵያ መጥተሽ ቢሮ አቋቁሚ ተባልኩ፡፡ የምትሠሪበት ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመድቡሽ እንጠይቃለን ተባለ፡፡ ተጠየቀ፡፡ ላቀረበችልን ሐሳብ እዚሁ ሁና ትሥራ ተብሎ ተጠየቀ፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ መጣሁ፡፡ አቶ ነዋይ አገኙኝና ያኔ ያወራነውን ነገር አልረሳነውም፡፡ ሥራውን ጀምሪ አሉ፡፡  ስትራቴጂው ላይ ምክር ስጪ ተባልኩ፡፡ በመጣሁ በስድስተኛ ወር አንድ ወረቀት ጻፍኩ፡፡ ይህ ጽሑፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድ ቀርቦ ለአገሪቱ እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል ተብሎ ተወሰነ፡፡ ግብረ ኃይል ተቋቋመ፡፡ የግብረ ኃይሉ መሪ ሆንኩ፡፡ እንዴት ተግባራዊ ይሁን? ሲባል ሐሳቤ ጥሩ ቢሆንም ወደ ተግባር ለመግባት ግን አከራካሪ ነገሮች ገጥመውት ነበር፡፡ ቢሆንም ጥናቱ አልቆ እንደገና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀረበ፡፡ በዚህም ላይ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ ስጪ ስባልም ብዙ ተከራከርን፡፡ ምክንያቱም በአንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ የአመለካከት ልዩነት ነበረን፡፡

ሪፖርተር፡- የሐሳብ ልዩነቱና አከራካሪው ነገር ምን ነበር? ሊገልጹልኝ ይችላሉ?

ዶ/ር እሌኒ፡- አንድ ምሳሌ ሊሆን የሚችለውና እስካሁንም ድረስ ያልተፈታው የምርት ገበያው ባለቤትነት የግሉ ዘርፍና የመንግሥት (የሁለቱም) ይሁን የሚል ነበር፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት ብቻ ሆኖ ከታየ ዕይታው ጥሩ አይደለም፡፡ አሠራሩም ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል የሚል አመለካከት ስለነበረብኝ ነው፡፡ የመንግሥት መሆኑ የቢሮክራሲ ችግሮች ሊኖሩት ይችላሉ በሚል ለገበያው የበለጠ አገልግሎት ሰጪ  መንፈስ እንዲኖረው፣ የግል ዘርፉ ተሳትፎ ይኑረው የሚለው ሐሳብ ግን ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነበር ያከራከረን፡፡ የእኔን ሐሳብ ለመደገፍ ሥራውን በፍጥነት ለመጀመር አያመችም ተባለና አሁን ባለን አቅም እንሥራው ተብሎ ውሳኔ ላይ ተደረሰ፡፡ በዚህ ሐሳብ እኔ ብዙ አልተስማማሁም፡፡

ሪፖርተር፡- ስምምነቱ ሳይኖር ሥራውን መጀመር ወይም ኢትዮጵያ ተመልሶ መሥራት አልከበደዎትም?

ዶ/ር እሌኒ፡- አዎ፡፡ በሐሳቡ ባልስማማበትም ሥራው ሊሠራ ይችላል ወይ? የሚለውን ነገር አሰብኩበት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቀኖናዊ ሳይሆን እንደ ሁኔታው መሆን አለብህ፡፡ ግን በሁለተኛው ከሆነ እውነትም ኢንቨስተር መፈለጉ ራሱ ሌላ ሥራ ሊሆን ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ሐሳብ ብቀበል እንዴት አድርገን መንግሥታዊ መንፈስ ሳይኖረው ኮሜርሻል የሆነ ድርጅት እንዴት በሌላ መንገድ እንዲፈጠር ልሞክር ብዬ የአባልነት መዋቅር እንዲፈጠር ሐሳብ አመጣን፡፡ አባል መብት እንዳለውና ቦርድ ላይ ለመቀመጥና ድምፅ ለመስጠት እንዲቻል ሁሉ የሚያደርግ ሐሳብ ይዘን ቀረብን፡፡ ሌላው ቀርቶ የድርጅቱ ገቢ ለመንግሥት ፈሰስ እንዳይሆን በሕግ እንዲቀመጥ፣ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ደግሞ ትርፋማነቱ ከተረጋገጠ በኋላ ለግል ዘርፉ እንደሚተላለፍ መንገድ እንደሚመቻች ለማድረግ ለመደራደር ተዘጋጀሁና ቀረብኩ፡፡ ይህንን ሐሳብ ተቀበሉት፡፡ ሐሳቤ ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ሆነ፡፡ በወቅቱ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ በጣም ትንሽ ነበር፡፡ እንዳሁኑ ዳያስፖራ የሚጐርፍ አይደለም፡፡ አሁን እኮ መቼ ነው የምሄደው የሚለው ይበዛል፡፡ ያኔ ግን ብዙ አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

ዶ/ር እሌኒ፡- ለመመለስ የበለጠ ፍላጐቱ ያደረብኝ እዚህ መጥቼ ያቀረብኩት ሐሳብ ተቀባይነት በማግኘቱና አቀባበሉ የተለየ በመሆኑ ነው፡፡ አቀባበሉ በጣም አስደነቀኝ፡፡ ምክንያቱም እንደ አንድ ጥናት ያደረገ ሰው ሐሳብን ተቀብሎ ተግባራዊ እንዲደረግ ፍላጐት ማሳየት በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በሌላ ቦታ ሰው ሐሳብህን ያዳምጥና ይተወዋል፡፡ እኔን የገጠመኝ ሐሳብሽን አስረጂን? እንዴት ነው የምንሠራው? እንዴት ትረጅናለሽ? የሚለው ፍላጐትና የመንግሥት አቀባበል የሚገርም ነበር፡፡ ወደ ዋሽንግተን ስመለስ በገጠመኝ አቀባበል ደንግጬ ስለነበር ለጓደኞቼ ነገርኩ፡፡ ከጠበቅሁት ውጪ ስለመሆኑ ሁሉ ነገርኳቸው፡፡ በነገርህ ላይ ከዚያን ጊዜ ቀደም ብዬ ኢትዮጵያ ብዙም ስላልመጣሁ አቀባበሉ የተለየ መሆኑን ሳይ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ስሜት ካለማ ሥራ መሥራት ይቻላል አልኩ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሥራ መሥራት አለብኝ ስል ጓደኞቼ ሁሉ ይህ የሚታሰብ አይደለም አሉኝ፡፡ አብደሻል ወይ ያሉኝም ነበሩ፡፡ እዚህ ጥሩ ሕይወት አለሽ፣ መሄድ የለብሽም፣ ባይሆን እዚህ ሆነሽ ሥሪ አሉኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የእርስዎ ውሳኔ ምን ሆነ?

ዶ/ር እሌኒ፡- እዚህ ሆኖ መሥራትና እዚያ ሄዶ መሥራት አንድ አይደለም፡፡ የተወሰነ ጊዜ እየተመላለስኩ መሥራት እችላለሁ፡፡ ግን ሰዎቹ እንዳሉት ኢትዮጵያ ሄጄ እዚያው ሆኜ ቢሮ ከፍቼ ብሠራ የተሻለ መሥራት እችላለሁ ብዬ ቀስ በማለት ወደዚህ መምጣት እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ ሐሳቤ ሁሉ እዚህ ሆነ መጣሁ፣ ሠራሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁንስ ኑሮዎ እዚህ ነው? ሥራዎ የት ነው ሊባል ይችላል?

ዶ/ር እሌኒ፡- አሁንማ ኢትዮጵያ ውስጥ አልሠራም፡፡ በተጨባጭ ዋናው ሥራዬ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም፡፡ ኑሮዬ ግን እዚህ ነው፡፡ ወደፊት ግን የምሠራው ይኖረኛል፡፡ ለተወሰነ ዓመት ግን የሌሎች የአፍሪካ አገሮችን ማየቱን መርጫለሁ፡፡ ይህም ደስ ብሎኛል፡፡ ምክንያቱም አሁን እየሠራን ያለነው የኢትዮጵያን ምርት ገበያ ሞዴል ነው፡፡ ለሌሎች አፍሪካውያን እያስተዋወቅንና ኤክስፖርት እያደረግን ነው  ያለው፡፡ የትኛውም የአፍሪካ አገር ስሄድ የማገኘው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተሠራው ዓይነት እኛም አገር እንፈልጋለን የሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሞዴል ለእኛም ይጠቅመናል የሚለው ምኞታቸው ለኢትዮጵያ አወንታዊ አመለካከት እንዳለ አሳይቶኛል፡፡ ስለኢትዮጵያ ምርት ገበያ አፍሪካውያን አውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ  ባለፈው አሥር ዓመት የታየው ዕድገት ሁሉንም የአፍሪካ አገሮች አርክቶአል፡፡

ሪፖርተር፡- ዶ/ር እሌኒ መጽሐፍ ማንበብ፣ መዋኘትና የመሳሰሉትን ይወዳሉ? ምንድነው የሚወዱት?

ዶ/ር እሌኒ፡- አሁን ያልከውን በሙሉ እወዳለሁ፡፡ መጽሐፍ በጣም አነባለሁ፡፡ በስፖርት ደረጃ አሁን በይበልጥ የምሠራው ዎኪንግ ነው፡፡ በዕረፍት ሰዓት ባህር ያለበት ቦታ መሄድ እወዳለሁ፡፡ ዋና በጣም እወዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲያውም አስታወሱኝ፡፡ ኬንያ እያሉ እርስዎን ለማግኘት ባህር ዳርቻ መሄድ ይበቃል ይባላል?

ዶ/ር እሌኒ፡- ሞምባሳን በጣም እወዳለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ ባህር ባለመኖሩ አዝናለሁ፡፡ ቢቻለኝ ግን ባህር ጥግ ሆኖ መኖር ትልቅ ደስታ ይሰጠኛል፡፡ ወደፊት እንዲህ ያለ ሕይወት ይኖረኛል ብዬ እመኛለሁ፡፡ ጥሩ ሕይወት አለኝ፡፡ ሥራም ጥሩ እየሄደ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአፍላ ዕድሜ ውስጥ እያሉ የፍቅር ሕይወትዎ …?

ዶ/ር እሌኒ፡- ስለሱ አትጠይቀኝ፡፡ ግን ጥሩ ነገሮች አጋጥመውኛል፡፡ የማዝንበት ነገር የለም፡፡ ልጆቼ እያደጉ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ሊገቡ ነው፡፡ ልጆቼ ለኢትዮጵያ ያላቸው አመለካከት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ እኔ በእነርሱ ዕድሜ ስለኢትዮጵያ ለማወቅ ስጓጓ ነው ያደግኩት፡፡ የእነሱ ፍቅር ነው፡፡ ይህ ለእኔ ትልቅ ደስታ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- አማርኛ መናገር አቅትዎት በአስተርጓሚ ሳይቀር የሚናገሩበት ጊዜ ነበር ይባላል፡፡ በዚህ ዙሪያ ያለውን ገጠመኝ እስቲ አስታውሱኝ?

ዶ/ር እሌኒ፡- አንድ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ልመጣ አካባቢ ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ ተከሰተና በምሠራበት መሥሪያ ቤት ተወክዬ በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ቃለ ምልልስ እንዳደርግ ተፈለገ፡፡ እሷ ትጠየቅ ተባለ፡፡ በአማርኛ ቃለ ምልልስ እያደረጉኝ በምግብ ዋስትና ዙሪያ ነው የምናነጋግርሽ አሉ፡፡ እንደ አጋጣሚ እኔ የምሠራበት መሥሪያ ቤት አንዲት ሐበሻ ነበረችና ልጠቀምባቸው የሚችሉ ቃላትን በአማርኛ እንድትመልስልኝ አደረግኩ፡፡ ለምሳሌ ፉድ ሴኩሪቲ (የምግብ ዋስትና)፣ ኢንፍሌሽን (የዋጋ መዋዥቅ) የሚሉትን በአማርኛ ጽፋ ሰጠችኝ፡፡ በስልክ ስጠየቅ ቃላቱን እያየሁ ነበር የተናገርኩት፡፡ ምክንያቱም ቃላቱን አላውቅም፡፡ ቃለ ምልልስ ሳደርግም ይቺን ልጅ አጠገቤ ሁኚ ብያት የምፈልገውን ቃል እየጻፍኩ እሷ እየተረጐመችልኝ ነበር ቃለ ምልልሱን የሰጠሁት፡፡

ሪፖርተር፡- የዚህን ያህል ተቸግረው ነበር ማለት ነው?

ዶ/ር እሌኒ፡- አሁንም እኮ እውነቱን ለመናገር በየቀኑ አማርኛ እየተማርኩ ነው፡፡ ተምሬ አልጨረስኩም፡፡ በተለይ ምርት ገበያ በነበርኩበት ጊዜ ለኢንተርቪው ስጠየቅ ቀድሜ ቃላት አጥንቼ ነው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ሆኜ አንድም ቀን አማርኛ አልተማርኩም፡፡ አማርኛ በራሴና በቤተሰቦቼ እገዛ ነው የተማርኩት፡፡ መጻፍና ማንበቡን ደግሞ ቆይቶ ነው ያወቅኩት፡፡ በ17 ዓመቴ ፊደል መማር አለብኝ ብዬ ነው ራሴን ያስተማርኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ የደስታ ጊዜያት ሊኖሩዎ ቢችሉም የበለጠ የተደሰትኩት በዚህ ነገር ነው የሚሉት አለ?

ዶ/ር እሌኒ፡- የትኛውን እንደምነግርህ አላውቅም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የመጀመሪያውን ልጄን ስወልድ ነው የተደሰትኩት፡፡ እናት መሆን ከሁሉም ነገር ይበልጣል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...