Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሞባይል ባንክ አገልግሎት በይፋ ሥራ ጀመረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአምስት አነስተኛ የፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት አማካይነት በሙከራ ደረጃ ሲተገበር የቆየው በሞባይል ገንዘብ የማስተላለፍ አገልግሎት፣ በሌሎች የንግድ መስኮችም ላይ መተግበር እንደሚጀመር ተገለጸ፡፡ ከወዲሁ የግል ኩባንያዎች በአገልግሎቱ ለመጠቀም ስምምነት ማድረግ ጀምረዋል፡፡

ማክሰኞ ጳጉሜን 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል ይፋ የተደረገው የሞባይል ባንክ አገልግሎት፣ በአገር ውስጥ ከሚደረገው በሞባይል ገንዘብ የመላክና የመቀበል ተግባር በተጨማሪ፣ የውጭ ኃዋላን የማስተናገድ አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡

ኤም-ብር የሚል ሥያሜ የተሰጠው ገንዘብን በሞባይል የማስተላለፍ አገልግሎት፣ በአዲስ ብድርና ቁጠባ፣ በአማራ ብድርና ቁጠባ፣ በደደቢት ብድርና ቁጠባ፣ በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማኅበርና በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አማካይነት አገልግሎቱ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በትግራይ ክልል የደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም በኩል ለተረጂዎች የሚሰጠውን ገንዘብ በሞባይል ስልክ አማካይነት ሲያስተላልፍ መቆየቱም ስኬታማ ተሞክሮ እንዲኖረው አስችሏል ተብሏል፡፡

ይህንን ተከትሎ በአምስቱ ተቋማት አማካይነት የተቋቋመው አዶይ አሳታፊ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አክሲዮን ኩባንያ፣ ሞስ አይሲቲ ኮንሰልታንሲ ሰርቪስስ ከተባለው ቴክኖሎጂ አመንጪ ጋር በመሆን በአሁኑ ወቅት የንግድ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው ብቃት ላይ ደርሷል የተባለውን የሞባይል ክፍያ ሥርዓት በአገር ደረጃ ይፋ አድረገዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ የኤሌክትሮኒክ ክፍያዎችን በሚመለከት ከሦስት ዓመት በፊት ያወጣውን መመርያ መሠረት በማድረግ እየተንቀሳቀሰ የቆየው ኤም-ብር፣ በአንድ ሺሕ የብድርና ቁጠባ ቅርንጫፎች በኩል ሲሰጥ የቆየው ገንዘብ የማስተላለፍ፣ የርቀት ትምህርት ክፍያን የማስተናገድ፣ እንደ ውኃና ስልክ ወዘተ ያሉትን የአገልግሎት ክፍዎችን የማስተናገድ፣ የዲኤስቲቪ አገልግሎት ክፍዎችን የማስተላለፍ፣ በነዳጅ ማደያዎች የክፍያ አገልግሎቶችን መፈጸም፣ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ ቴክኖሎጂዎችን ለሚያቀርቡ ኩባንያዎች ክፍያዎችን መፈጸም፣ ገንዘብ በቁጠባ ተቋማቱ በኩል እንዲጠራቀምና ወጪ እንዲደረግ ማስቻል ከሚጠቀሱት ተግባራቱ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ይህንን ተከትሎም ቶታል ኢትዮጵያ በተመረጡ 15 የነዳጅ ማደያዎቹ የሞባይል ክፍያ እንዲፈጸም የሚያስችለውን ስምምነት ማድረጉ ታውቋል፡፡ ከነዳጅ ክፍያዎች በተጨማሪም በቶታል ማደያዎች አካባቢ በሚገኙ ሱቆች ለሚፈጸሙ ግዥዎችም አገልግሎቱ ጥቅም ይሰጣል ተብሏል፡፡ ከቶታል ባሻገር አዙሪ ቴክኖሎጂስ የተባለውና በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ ቴክኖሎጂዎችን የሚያመርተው ኩባንያም በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ በገጠር ለሚገኙ 50 ሺሕ ተጠቃሚዎች በሞባይል አማካይነት ክፍያ ለማስተናገድ የሚያስችለውን ስምምነት ፈጽሟል፡፡

የሞስ አይሲቲ ቴክኖሎጂ የቢዝነስ ልማት ኃላፊ አቶ ወሰን መግራ ሺበርጫ እንዳስታወቁት፣ የሞባይል ክፍያ አገልግሎቱ ምንም ዓይነት የኢንተርኔት ኔትወርክ የማይፈልግና ከፍተኛ የሞባይል ኔትወርክ ጥራት የማያስፈልገው ቴክኖሎጂ  ይጠቁማል፡፡ በዓለም አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማት የሚጠቀሙበትን፣ ‹‹አንስትራክቸርድ ሰፕሊመንታሪ ሰርቪስ ዳታ-ዩኤስኤስዲ›› የሚባለውን የቴክኖሎጂ ሥርዓት መዘርጋቱን የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ሥራ አስኪያጅ አቶ አዋሽ አብተው አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት አንድ ሺሕ የብድርና ቁጠባ ተቋማት እየሰጡ ያሉት ቅርንጫፎች በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ አራት ሺሕ እንደሚያድጉ ሲገለጽ፣ አገልግሎቱም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ይዳረሳል ተብሏል፡፡

አገልግሎቱን የጀመሩት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ፣ በኬንያ ለ40 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን ‹‹M-Pesa›› የተባለውን የሞባይል ክፍያ አገልግሎት፣ ኤም-ብር በጥቂት ጊዜ ውስጥ እንደሚቀድም ገልጸዋል፡፡ የኬንያው የሞባይል ክፍያ ሥርዓት በአሁኑ ወቅት የ40 ቢሊዮን ዶላር የክፍያ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ኤም-ብር በአንፃሩ እስካሁን የመቶ ሚሊዮን ብር የክፍያ አገልግሎት ማከናወኑ ታውቋል፡፡

 

 

 

 

 

 

                                                                                                                                          

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች