Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሕገወጥ መንገድ ጣውላ ሲያመርት የተገኘው የህንድ ኩባንያ በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ተጠያቂ ሆነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሻይ ቅጠል ልማት ለማካሄድ ፈቃድ ወስዶ፣ ነገር ግን በሕገወጥ መንገድ ጣውላ ሲያመርት የተገኘው የህንዱ ኩባንያ ቬርዳንታ ሐርቨስት፣ አሁን ደግሞ በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ተጠያቂ ሆነ፡፡

ቬርዳንታ ሐርቨስት ቀጥሮ ጉልበታቸውን ሲበዘብዝ ነበር የተባሉት አብዛኞቹ ሕፃናት ከሰባት ዓመት በታች እንደሆኑ፣ የተወሰኑት ደግሞ እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 250 ሕፃናትን በመቅጠር ሲያሠራ መገኘቱን፣ ከጋምቤላ ክልል የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ የጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን፣ ጉደሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮናስ ከፑምሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቬርዳንታ ሐርቨስት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሕፃናቱን ጉልበት ሲበዘብዝ ቆይቷል፡፡

‹‹ሕፃናቱን ሲያሠራ ቢቆይም ቃል የገባውን ክፍያ በመቀነስ ሕፃናቱ ቅሬታቸውን ይዘው ወደኛ መጥተዋል፤›› በማለት አቶ ዮናስ ገልጸው፣ ‹‹ጉዳዩ በዞን ደረጃ እየታየ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሕፃናቱ መብት መጠበቅ አለበት፡፡ እኛ ሕፃናት እንዲህ ያለ ሥራ መሥራት የለባቸውም የሚል አቋም ነው ያለን፤›› ብለው የህንዱ ኩባንያ የፈጸመውን ተግባር ኮንነዋል፡፡ ይህንን ሕገወጥ ተግባር የፈጸመውን ይህ ኩባንያ የሚወስድበት ዕርምጃ በቀጣይ እንደሚታወቅም አቶ ዮናስ አክለው ገልጸዋል፡፡

ቬርዳንታ ሐርቨስት ሕፃናቱ ከአቅማቸው በላይ የእርሻ ሥራዎችን፣ የምንጣሮ፣ የቁፋሮ፣ የቦይ ቀዳዳ ሲያሠራ መቆየቱ ታውቋል፡፡ ዞኑ ይህንን ያልተገባ ተግባር በአሁኑ ወቅት በአስተዳደር ደረጃ መያዙን አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ቬርዳንታ ሐርቨስት ይህንን ውንጀላ ተቃውሟል፡፡ ‹‹የእኛ ሠራተኞች ሕፃናት ልጆቻቸውን ይዘው ነው የሚመጡት፡፡ ልጆቹ በፕሮጀክት ሳይቱ ሲጫወቱ ይውላሉ፡፡ ሰሞኑን አንድ ሰው መጣና ሕፃናት ቀጥራችሁ ታሠራላችሁ አለን፡፡ እኛም ቀጥረን እንደማናሠራና የሠራተኛ ልጆች መሆናቸውን አስረድተን የተፈጠረውን አለመግባባት ፈትተናል፤›› በማለት የቬርዳንታ ሐርቨስት ረዳት ሥራ አስኪያጅ ሚስተር አሩፕ ኩመር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም ሲሉም ሚስተር አሩፕ ስለተፈጠረው ጉዳይ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አቶ ዮናስ እንዳሉት፣ ቀደም ሲል ይህ ኩባንያ ትልልቅ ዛፎችን በሕገወጥ መንገድ በመጨፍጨፍ ጣውላ ሲያመርት መቆየቱንና የተወሰነ ጣውላ እንደተያዘበት አስታውሰው፣ ተቆርጠው የወደቁ ዛፎችን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ክልሉ መመርያ እንዲሰጥ መጠየቃቸውንም አስረድተዋል፡፡

የህንዱ ኩባንያ በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን ጉማሬ ወረዳ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ 3,012 ሔክታር መሬት ለሻይ ቅጠል ልማት ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ቦታ መሰጠቱ አግባብ አለመሆኑ ተጠቅሶ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎችና የአካባቢ ጉዳይ ተሟጋቾች ቅሬታ ቢያቀርቡም፣ መሬቱን የሰጠው ግብርና ሚኒስቴር ቦታው ላይ ያሉት ዛፎች ትልልቅ ሳይሆኑ ቁጥቋጦ ናቸው በማለት ሲቀርብ የነበረውን ቅሬታ ውድቅ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ኩባንያው ጣውላ በሕገወጥ መንገድ ሲያመርት በመገኘቱ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ሰኔ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከሦስት ዓመታት በኋላ ቬርዳንታ ሐርቨስት በዓለም አቀፍ ሕግጋትም ሆነ በኢትዮጵያ ሕግ በፅኑ የተከለከለውን የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ማካሄዱ፣ በአካባቢው ባለሥልጣናት ቁጣ መቀስቀሱ እየተነገረ ነው፡፡

‹‹ሠራተኛ መቅጠር ከፈለገ በሠራተኛና በአሠሪ ሕግ መሠረት መሆን ይኖርበታል፤›› በማለት አቶ ዮናስ ኩባንያው የፈጸመው ተግባር ሕገወጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋት ሉዋክ ቱሉና ምክትላቸው ኢንጂነር ኦሌሮ ኤፒዮ በጉዳዩ ላይ መረጃው እንዳልቀረበላቸው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች