Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ታላቁ የህዳሴ ግድብን እንዲያጠኑ ከተመረጡት የውጭ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ራሱን አገለለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ሁለት ጉዳዮችን እንዲያጠኑ ከመረጧቸው ሁለት ኩባንያዎች መካከል፣ የኔዘርላንዱ ኩባንያ በፈቃዱ ራሱን ከጥናት ሥራው ማግለሉ ተሰማ፡፡

የግብፅ አህራም ኦንላይን የኔዘርላንዱ ኩባንያ ዴልታ ሬዝ አደረሰኝ ባለው የኢሜይል መልዕክት፣ ‹‹የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ገለልተኛና ደረጃውን የጠበቀ ጥናት ለማካሄድ በቂ ዋስትና አይሰጠኝም›› እንዳለ ይገልጻል፡፡

‹‹ይህንን ፈታኝ የጥናት ሥራ በብቃት ለመውጣት በቂ ዕውቀትና ባለሙያ፣ እንዲሁም በአካባቢው በቂ የሥራ ልምድ እያለኝ ለመውጣት በመገደዴ አዝናለሁ፤›› ማለቱም ተዘግቧል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ዴልታ ሬዝ አለ የተባለውን ቢያደርግም የሚያስጨንቅ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ምክንያቱ ደግሞ በሦስቱ አገሮች ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ የጥናቱን ሥራ በዋናነት እንዲሠራ የተመረጠው የፈረንሣዩ ኩባንያ ቢአርኤል ኢንጂነርስ መሆኑን፣ የዴልታ ሬዝ ኃላፊነት ከዋናው አጥኚ የሚሰጠውን የጥናት ኃላፊነት መወጣት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ኢንጂነር ጌድዮን አስፋው፣ በሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴ የውስጥ ደንብ መሠረት መረጃዎች ለሚዲያ የሚወጡት በጋራ ስምምነት በመሆኑ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች ኩባንያው በትክክል ራሱን ማግለሉን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ኩባንያውን በድጋሚ ለማነጋገር ጥረት እየተደረገ መሆኑንና እ.ኤ.አ. በኦክቶበር 2015 የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ለመምከር በግብፅ ካይሮ ይገናኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስትር ሆሳም አል ሞግሃዚ የህዳሴውን ግድብ የተመለከቱ ጉዳዮችን ግብፅ በውኃና መስኖ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ብሔራዊ ተቋማትም እንደምትከታተል ሰሞኑን ገልጸዋል፡፡ በማከልም ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ እየተደረገ ስላለው ድርድርና አጠቃላይ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ሙሉ መረጃ እንዳላቸው፣ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ በድርድሩ ስለወሰኑ እንጂ ግብፅ ሌሎች አማራጮች አሏት በማለት ለግብፅ መገናኛ ተቋማት ባለፈው ረቡዕ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡

የኢትዮጵያ አቻቸው አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች