የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዓመታዊ የአገሪቱን የነዳጅ ፍጆታ ለመሸፈን የሚያካሂደውን ዓለም አቀፍ ጨረታ በመተው፣ በድርድር ከኩዌት መንግሥት ለመግዛት የተከተለውን አቅጣጫ ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች ተቃወሙ፡፡ ድርጅቱ ተቃውሞውን አልተቀበለም፡፡
የአንዳንድ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተወካዮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ ግዢ ጨረታ ማውጣት በመተው የተለያዩ የነዳጅ ውጤቶችን ከኩዌት በድርድር በመግዛት ላይ ይገኛል፡፡ ዕርምጃውን የተቃወሙት የኩባንያ ተወካዮች ውሳኔው አገሪቱን ዋጋ እንደሚያስከፍላት ይናገራሉ፡፡
‹‹አንደኛ ከኩዌት የሚገዛው ነዳጅ ውድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከኩዌት ለሚገዛው ነዳጅ በበርሜል 0.30 ዶላር ጭማሪ ይከፍላል፡፡ ወይም በአንድ የነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ የ60 ሚሊዮን ብር ጭማሪ አለው፤›› ይላሉ፡፡
የኩባንያው ተወካዮች በሁለተኛ ደረጃ የሚያነሱት የነዳጅ ጥራት ጥያቄ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በአሁኑ ወቅት በመግዛት ላይ ያለው ነዳጅ የሊድ (እርሳስ) እና ሰልፈር መጠን ከፍተኛ በመሆኑ በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በበኩሉ የቀረቡትን ወቀሳዎች አስተባብሏል፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ ከኩዌት መንግሥት ነዳጅ በቀጥታ መግዛቱ የተለያዩ ጠቀሜታዎች አሉት ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዓመታዊ የነዳጅ ፍላጎት ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተቀራራቢ በሆነ ቁጥር፣ በዓመት አሥር በመቶ በማደግ በአሁኑ ወቅት ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ደርሷል፡፡ አገሪቱ ለነዳጅ ግዢ የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከወጪ ንግድ የምታገኘው ደግሞ በዓመት ሦስት ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አገሪቱ ላላት የአውሮፕላን ነዳጅ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ከኩዌት የሚገዛ ሲሆን፣ 50 በመቶ የሚሆነውን የናፍጣ ፍላጎት የምታሟላው ከኩዌት በድርድር በሚገዛ ናፍጣ ነው፡፡ ሰባ አምስት በመቶ የሚሆነው የቤንዚን ፍጆታ ከሱዳን መንግሥት ይሸመታል፡፡ ሃያ አምስት በመቶ የሚሆነው የቤንዚን ፍጆታና 50 በመቶ የናፍጣ ፍጆታ የገዛው በግልጽ ጨረታ ከነዳጅ ነጋዴዎች ነው፡፡ የኩዌቱን ነዳጅ የሚያቀርበው የኩዌት መንግሥት ንብረት የሆነው ኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ 20 በመቶ ቤንዚንና 50 በመቶ የሚሆነው ናፍጣ የሚመጣው ሳዑዲ ዓረቢያ ከሚገኘው ያንቡ የድፍድፍ ነዳጅ ማጣሪያ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የዕለት የቤንዚን ፍጆታ አንድ ሚሊዮን ሊትር፣ ናፍጣ 5.8 ሚሊዮን ሊትር፣ የአውሮፕላን ነዳጅ 1.8 ሚሊዮን ሊትር ነው፡፡ ዓመታዊ የነጭ ጋዝ ፍላጎት ደግሞ 260,000 ሜትሪክ ቶን ነው፡፡ ኅብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ምድጃዎች በስፋት መጠቀም በመጀመሩ የነጭ ጋዝ ፍላጎት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በ13 የመጠባበቂያ ነዳጅ ዴፖዎች የሚገኙ ሲሆን፣ 360,000 ሜትር ኪዩብ የማጠራቀም አቅም አላቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከኩዌት ነዳጅ መግዛት የጀመረችው ከኩዌት መንግሥት ጋር ረዥም ጊዜ የፈጀ ውይይት ከተደረገ በኋላ እንደሆነ አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሚኒስትሮቻችን ሁለት ሦስት ጊዜ ወደ ኩዌት የተመላለሱ ሲሆን፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከኩዌት የነዳጅ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ከስምምነት ላይ በመድረሳቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡
በተደረሰው ስምምነት መሠረት 70 በመቶ የአውሮፕላን ነዳጅ ፍጆታ፣ 50 በመቶ የናፍጣ ፍጆታ ከኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን መገዛት መጀመሩን አቶ ታደሰ አስታውሰዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የአውሮፕላን ነዳጅ አቅርቦት ኢትዮጵያ ለኩዌት ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት ወደ 100 በመቶ አድጓል፡፡
ባለፈው ሳምንት በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በአቶ አህመድ ሺዴ የሚመራ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑክ ወደ ኩዌት ተጉዞ፣ ከኩዌት የነዳጅ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በወቅቱም አቶ አህመድ የኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሚያቀርበውን የናፍጣ መጠን እንዲጨምር ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከተቻለ የኢትዮጵያን 100 በመቶ የናፍጣ ፍላጎት እንዲያሟሉ ካልሆነ ግን 70 በመቶ እንዲሸፍኑ ጥያቅ አቅርበዋል፡፡
የኩዌት ባለሥልጣናት በበኩላቸው ቀደም ብለው የገቡዋቸው በርካታ ውሎች ስላሉ፣ 100 በመቶ መሸፈን እንደማይችሉ ገልጸው 70 በመቶ የሚለውን ጥያቄ (በ20 በመቶ ማሳደግ) ግን ገምግመው ምላሽ እንደሚሰጡ ለኢትዮጵያ ልዑክ አስረድተዋል፡፡
‹‹ከኩዌት ነዳጅ የመግዛት ዕድልን በብዙ ልምምጥ ያገኘነው ዕድል ነው፤›› የሚሉት አቶ ታደሰ፣ ከኩዌት ነዳጅ መገዛቱ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡
‹‹ከኩዌት በምንገዛበት ወቅት 90 ቀናት የመክፈያ ጊዜ ይሰጡናል፡፡ ሱዳን የምትሰጠን 30 ቀናት ነው፡፡ ነዳጅ ነጋዴዎች ከ30 እስከ 45 ቀናት ብቻ ነው የሚሰጡን፡፡ የኩዌት ነዳጅ አቅርቦት አስተማማኝ ነው፡፡ ባሉት ቀነ ገደብ ያቀርባሉ፡፡ የዋጋ ክለሳ እንደ ነጋዴዎቹ በየጊዜው አያደርጉም፡፡ የሚጠቀሙት የራሳቸውን መርከቦች በመሆኑ ርካሽ መርከብ ሲፈልጉ ጊዜ አያቃጥሉም፤›› የሚሉት አቶ ታደሰ፣ የዋጋ ልዩነትን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ዝርዝር ጠቀሜታዎችን መመልከት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡
‹‹ለምሳሌ እኛ ለኩዌት በበርሜል የምንከፍለው ፕሪሚየም ክፍያ (ትራንስፖርትና አገልግሎት) 4.50 ዶላር ነው፡፡ ለነዳጅ ነጋዴዎች በበርሜል 4.10 ዶላር ነው፡፡ ከነጋዴዎች ስንገዛ ኢንሹራንስ የምንከፍለው ራሳችን ነን፡፡ ነጋዴዎቹን ኢንሹራንስ ጨምሩበት ብንላቸው ዋጋቸው ሰባት ዶላር ይገባል፡፡ የኩዌት ግን ኢንሹራንስን ጨምሮ 4.50 ዶላር ብቻ ነው፤›› ብለዋል አቶ ታደሰ፡፡
የነዳጅ ጥራትን አስመልክቶ ለቀረበው ተቃውሞ በሰጡት ምላሽ የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት በአሁኑ ወቅት የሚገዛው ቤንዚን ከእርሳስ ነፃ የሆነ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ሊድ ያለው ቤንዚን መግዛት አቁመናል፡፡ ዓለም ሊድ ያለው ቤንዚን መግዛት አቁሟል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ከኩዌት የምትገዛው ናፍጣ ውስጥ ያለው የሰልፈር መጠን 0.2 በመቶ ሲሆን፣ ከነጋዴዎች የሚገዛው ናፍጣ 0.05 በመቶ ሰልፈር ይዘት አለው፡፡ የናፍጣ ዋጋ ባለው የሰልፈር መጠን ይወሰናል፡፡ 0.2 በመቶ ሰልፈር ያለው ናፍጣ በበርሜል 57.76 ዶላር፣ 0.05 በመቶ ሰልፈር ያለው 58.76 ዶላር፣ 0.005 በመቶ 60.16 ዶላር፣ 0.001 በመቶ 61.16 ዶላር ዋጋ አለው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹0.001 በመቶ ሰልፈር ያለውን ናፍጣ ገዝቶ ማምጣት ይቻላል፤›› የሚሉት አቶ ታደሰ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት መኪኖች ዕድሜ ጠገብ በመሆናቸው የሰልፈር ይዘቱ ዝቅተኛ የሆነ ናፍጣ ገዝቶ ማምጣቱ ጠቀሜታ እንደሌለው ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት መኪኖች በአብዛኛው አሮጌ በመሆናቸው ከፍተኛ የካርቦን ልቀት አላቸው፡፡
‹‹በአገራችን ያሉት ብዙዎቹ መኪኖች ሦስት መንግሥታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ናፍጣ ገዝተን ብናመጣ መኪኖቹ ነዳጁን በአግባቡ መጠቀም የሚችሉ ባለመሆናቸው አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል ብቻ ይሆናል፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ ሌሎች አገሮች ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ነዳጅ ሲያስገቡ የመኪና ዕድሜ ገድበው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ኬንያ ከስምንት ዓመት በላይ ዕድሜ ያለውን መኪና ማስገባት አይቻልም፡፡ በናይጄሪያ ከአምስት ዓመት በላይ ያለውን መኪና ማስገባት አይቻልም፡፡ ወደ እኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ ይህን ማድረግ አይቻልም፡፡ አንድ ኤንትሬ የጭነት መኪና አሥር ቤተሰብ ያስተዳድራል፡፡ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ናፍጣ ከማስመጣታችን በፊት ዕድሜ ጠገብ ተሽከርካሪዎችን ማስወገድ አለብን፡፡ በርካታ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ አሮጌ መኪኖችን በአሁኑ ወቅት ማስወገድ አይቻልም፡፡ ምናልባት ያን ማድረግ የሚቻለው ወደ መካከለኛ ገቢ አገርነት ስንሸጋገር ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
የነዳጅ ኩባንያ ተወካዮች የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እ.ኤ.አ. ለ2016 የሚውል ነዳጅ ለመግዛት ነሐሴ 17 ቀን ጨረታ ማውጣት የነበረበት ቢሆንም፣ እስካሁን ጨረታውን አለማውጣቱን ይህም የጨረታ ግዢ ሙሉ በሙሉ ቀርቷል የሚል ሥጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ ታደሰ ድርጅታቸው ጨረታ ማውጣቱን እንዳልተወ፣ የጨረታ ሒደቱ እንዲዘገይ የተደረገው ከኩዌት የሚገዛው የነዳጅ መጠን እስከሚታወቅ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የኩዌት መንግሥት የሚያቀርበው የነዳጅ መጠን ከታወቀ በኋላ ጨረታው እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ተጨማሪ የአውሮፕላን ነዳጅ እንዲያቀርቡ ጠይቀናል፡፡ የሚያቀርቡትን የናፍጣ መጠን የፍጆታችንን 70 በመቶ እንዲሆንም ጠይቀናል፡፡ ምላሻቸውን አይተን ጨረታውን እናወጣለን፤›› ብለዋል፡፡
ከሱዳን እስከ 80 በመቶ ቤንዚን የሚገኝ በመሆኑ የተቀረው 20 በመቶ ለጨረታ የሚቀርብ ሲሆን፣ ኩዌት ከናፍጣ ፍጆታ 70 በመቶ ልታቀርብ ትችላለች፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት 800,000 ሜትሪክ ቶን ናፍጣና 60,000 ሜትሪክ ቶን ቤንዚን ለመግዛት ጨረታ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡