Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  አዲሱ ዓመት የመስጠትና የማካፈል ይሁን!

  አሮጌው ዓመት ተሸኝቶ አዲሱ ዓመት ተጀምሯል፡፡ በአዲስ ዓመት መልካሙን ነገር ሁሉ መመኘት የነበረና ያለ በመሆኑ፣ እንኳን ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ተሸጋገራችሁ፡፡ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የደስታና የብልፅግና ይሆን ዘንድ ምኞታችንን እንገልጻለን፡፡ ይህ የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫ የሰመረ እንዲሆን ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲሱን ዓመት የመስጠትና የማካፈል ይሆንለት ዘንድ ተገቢ ነው፡፡ መንግሥት፣ እያንዳንዱ ዜጋ፣ የንግዱ ኅብረተሰብ፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበረሰቡ፣ የፍትሕ አካላት፣ ፖለቲከኞች፣ ወዘተ አዲሱን ዓመት የመስጠትና የማካፈል እንዲያደርጉት ጥሪ ይቀርብላቸዋል፡፡

  መንግሥት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አገሪቱን ለማስተዳደር የሚያስችለውን ፓርላማ በቅርቡ ሥራ ያስጀምራል፡፡ የፓርላማው ትልቁ ኃላፊነት የሕግ አውጪነት ሥልጣን ሲሆን፣ ሕዝቡ በወጉና በአግባቡ በሕግ የበላይነት ጥበቃ ሥር መተዳደሩን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩ ዋስትና የተሰጣቸው መሠረታዊ መብቶች ሳይሸራረፉ መከበራቸውን በመከታተል ለሕዝቡ አደራውን ሲወጣ እንደሰጠና እንዳካፈለ ይቆጠራል፡፡ አስፈጻሚው አካል ከተሰጠው የሥልጣን ክልል በማናለብኝነት እንዳይወጣ፣ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዲሰማው የመቆጣጠርና ሥራውን የመከታተል ተግባር የፓርላማው ስለሆነ ሕዝብ ብዙ ይጠብቃል፡፡ ፓርላማው ለሕዝቡ ይስጥ፡፡ ያካፍል፡፡ አዲሱን ዓመት ብሩህ ያድርገው፡፡

  የፍትሕ ሥርዓቱ ከሙስና ፀድቶ ፍትሕ ያሰፍን ዘንድ ሕዝብ ይጠብቃል፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ አካላት ማለትም ዳኞች፣ ዓቃቢያነ ሕጎች፣ ጠበቆችና የመሳሰሉት ፍትሕ እንዲኖር በነፃነትና በኃላፊነት መንገድ ሲሠሩ የመስጠቱና የማካፈሉ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ሕዝብ በተፈጥሮ የተቀዳጃቸው መብቶች እንዳይሸራረፉ፣ ፍትሕ በገንዘብ እንዳይናድና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የበኩላቸውን ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ በፍትሕ እጦት መብቶቻቸውን የተነፈጉ፣ በሐሰተኛ ክሶች ያለ ኃጢያታቸው የተወነጀሉ፣ በራስ ወዳዶችና በክፉዎች ሴራ ለእስር የተዳረጉ ዜጎች እንባ የሚታበስበት አዲስ ዓመት ይሆን ዘንድ፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ሁሉ ራሳቸውን ለሕግና ለህሊናቸው ያስገዙ፡፡ የመስጠትና የማካፈል አካል ይሁኑ፡፡ አዲሱን ዓመት የፍትሕ ያድርጉት፡፡

  የመንግሥት አስፈጻሚው አካል በአዲሱ ዓመት በገባው ቃል መሠረት አገሪቱን በፍትሐዊነት ይምራ፡፡ በመልካም አስተዳደር እጦትና በፍትሕ ማጣት እንባውን እያዘራ ያለ ሕዝብ ይታደግ፡፡ በየመዋቅሩ ውስጥ ተሰግስገው አገር የሚዘርፉና ሕዝብን የሚያደኸዩ ሙሰኞችን ለቃቅሞ ያስወግድ፡፡ ለሕግ ያቅርብ፡፡ በቡድንተኝነትና በኔትወርክ የተሳሰሩ የጥፋት ኃይሎችን ያራግፍ፡፡ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማፈን ሕዝቡን የሚያስለቅሱ በየቦታው የበቀሉ አምባገነኖችን ከሕዝቡ ጫንቃ ላይ ያንሳ፡፡ ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ የነጠሩ ፖሊሲዎች ተቀርፀው ሥራ ላይ እንዲውሉ የሕዝቡን ተሳትፎ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ያረጋግጥ፡፡ አቅምና ችሎታ ሳይኖራቸው ሥልጣን የተሰጣቸውን ልግመኞችና ዳተኞች ያሰናብት፡፡ ይህ ለአዲሱ ዓመት ለሕዝብ የሚሰጥ ስጦታ ይሁን፡፡ የመስጠትና የማካፈል ምሳሌ ይሁን፡፡ አዲሱን ዓመት ያፍካው፡፡

  በአገሪቱ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ በአዲሱ ዓመት ራሳቸውን ያድሱ፡፡ ከጥላቻና ከጨለምተኝነት አስተሳሰብ ወጥተው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይንቀሳቀሱ፡፡ በአገሪቱ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በኃላፊነትና በያገባኛል መንፈስ ይነጋገሩ፡፡ በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆን ስለሌለበት የመነጋገሪያው መድረክ በአስቸኳይ ሥራውን ይጀምር፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ የሚሰፋው ወይም የሚጠበው በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ባህሪ ምክንያት ስለሆነ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ቀናነት ሲባል ሁሉም ለሰጥቶ መቀበል መርህ ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን በጠላትነት እየተያዩ በአንድ የፖለቲካ ዓውድ ውስጥ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ስለማይቻል ራሳቸውን ለመልካም ነገር ያዘጋጁ፡፡ በተለይ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ አገር እየመራ ስለሆነ፣ ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን አመቺ ሁኔታ መፍጠር አለበት፡፡ እነሱን ያገለለና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን የሚያጠፋ የአውራነት ጉዞው ጠቃሚ አለመሆኑን ይረዳ፡፡ ይህ ዓይነቱ ጉዞ አይጠቅምም፡፡ ተገቢም አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥታዊም አይደለም፡፡ በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በአዲሱ ዓመት በዚህ መንፈስ ለመንቀሳቀስ ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡ ለሕዝቡም የአዲስ ዓመት ስጦታ በማድረግ የመስጠትና የማካፈል አርዓያዎች ይሁኑ፡፡ በአዲሱ ዓመት ተስፋ ይፈንጥቁ፡፡

  የንግዱ ማኀበረሰብ ለአገሩ የሚያደርገው አስተዋጽኦ የበለጠ ጎልቶ የሚታየው በሥነ ምግባር ሥራውን ሲያከናውን ነው፡፡ ከሥነ ምግባር አፈንግጠውና የኅብረተሰቡን ባህላዊ እሴቶች ንደው በሕዝብ ላይ አደጋ የደቀኑ ወገኖችን የማረቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ብዙኃኑ በሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ በሚሠሩበት አገር ውስጥ ከመጠን በላይ በሆነ ራስ ወዳድነት ውስጥ ተዘፍቀው፣ የግብይት ሥርዓቱን መላቅጡን የሚያጠፉትንና ጤናማ ውድድር እንዳይኖር የሚያደርጉትን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ በንግድ ማኅበራትም ሆነ በንግድ ምክር ቤቶች አማካይነት ሊታገላቸው ይገባል፡፡ ምርት በመደበቅ፣ የግብይት ሰንሰለቱን በማዛባት፣ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት በመፍጠርና የሕዝቡን ሕይወት በማናጋት ላይ የሚገኙት እነዚህ ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች አንድ መባል አለባቸው፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትንና በየደረጃው የሚገኙ ሹማምንትን በሙስና በመበከል የግብይት ሥርዓቱን እያጠፉት ነውና የንግድ ማኅበረሰቡ ይንቃ፡፡ ይታገላቸው፡፡ በዚህም ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን ያሳይ፡፡ ጤናማና ፉክክር ያለበትና ለሁሉም የተመቻቸ ፍትሐዊ የውድድር ሜዳ እንዲፈጠር የበኩሉን ይወጣ፡፡ ይህንን በስኬት ከተወጣ ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ ትልቅ ስጦታ እንደሰጠ ይቆጠራል፡፡ የመስጠትና የማካፈል በጎ ተግባር ተባባሪ ይሆናል፡፡ አዲሱን ዓመት ያበራዋል፡፡

  የሲቪል ማኅበራት፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት፣ የግልና የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወዘተ በየተሰማሩበት መስክ ለአገር ጠቃሚ የሆኑ ተግባራትን ያከናውኑ፡፡ ፍትሕ እንዳይጓደል፣ መልካም አስተዳደር እንዳይጓደል፣ ሙስና አገርን እንዳያጠፋ፣ ተገቢ ያልሆኑ አሠራሮች እንዳይሰፍኑ፣ የአገልጋይነት መንፈስ እንዳይጠፋና የአገርና የሕዝብ ጥቅም ቀዳሚ እንዲሆን ይትጉ፡፡ የመስጠትና የማካፈል ግንባር ቀደም ተዋናይ ይሁኑ፡፡ አዲሱን ዓመት ያሸበረቀ ያድርጉት፡፡

  በዚህ አዲስ ዓመት ከአሮጌው ዓመት የተላለፉ የማይጠቅሙ ተግባራት እንዳይቀጥሉ መደረግ አለበት፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ከራሱ ቤት ጀምሮ በየተሰማራበት መስክ የበኩሉን ከተወጣ አገር ዴሞክራሲያዊትና የበለፀገች ትሆናለች፡፡ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ሥራቸውን ሲያከናውኑ፣ መብታቸውንና ግዴታቸውን ለይተው ሲያውቁ፣ ለሕገወጦች ቀዳዳ አይከፈትም፡፡ ማንም አምባገነን እየተነሳ ልርገጣችሁ ማለት አይችልም፡፡ ሁሉም ዜጋ ለአገሩና ለወገኑ ከልቡ ከሠራ ካለው ላይ እንደሰጠና እንዳከፈለ ይቆጠራል፡፡ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ፍትሕ በእኩልነት ተደራሽ እንዲሆን፣ የአገርና የሕዝብ ጠንቅ የሆነው ሙስና እንዲጠፋ፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊና አምባገነናዊ አስተሳሰቦች ቦታ እንዳይኖራቸው ከእያንዳንዱ ዜጋ እስከ አገር መሪዎች ድረስ የመስጠትና የማካፈል መንፈስ ሊያድርባቸው ይገባል፡፡ ዜጎች በሙሉ በአዲስ ዓመት ለእንዲህ ዓይነቱ መልካም ተግባር ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡ ለአዲሱ ዓመት ድምቀት ግንባር ቀደም ይሁኑ፡፡ አዲሱ ዓመት የመስጠትና የማካፈል ይሁን!  

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...

  ኢትዮጵያ በብድርና ዕርዳታ የምታገኘው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ፓርላማው አሳሰበ

  በብድር የተገኘ ገንዘብ በሥልጠናና ውሎ አበል መልክ እንዳይባክን ተጠየቀ የሕዝብ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...