Tuesday, February 27, 2024

‹‹የመኖሪያ ቤት ኪራይ ችግርን ለመፍታት የተዘጋጀው ሕግ በአዲሱ ዓመት ይፀድቃል››

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አቶ ድሪባ ኩማ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ የ2007 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸምና የ2008 ዓ.ም. የዕቅድ አቅጣጫዎችን በተመለከተ፣ ረቡዕ ጳጉሜን 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ከንቲባው በሰጡት መግለጫ አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አካሂዶ ድክመቱንና ጥንካሬውን መለየቱን አስታውቀው፣ በመሠረተ ልማት ግንባታና በካፒታል ፕሮጀክቶች መልካም ስኬት ማስመዝገቡን አስታውቀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያገኛቸውን ስኬቶችን በማስመልከት ከንቲባ ድሪባ ኩማ ይኼንን ብለዋል፡፡ ‹‹የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ በከተማ ደረጃ ያስገኘውን ውጤትና የነበሩበትን ፈተናዎች ገምግመናል፡፡ በግምገማው ውጤቶች ላይም ተግባብተናል፡፡ ከዕድገት አኳያ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሥር በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ከ15 በመቶ በላይ አድጓል፡፡ የአገልግሎት ዘርፍ ከ15 በመቶ በላይ አድጓል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ በአጠቃላይ በከተማው ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ 61.5 በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡ የኢንዱስትሪ ዘርፍ 37 በመቶ፣ የግብርና ዘርፍ ከአንድ በመቶ በታች ድርሻ ነበራቸው፡፡ የኢኮኖሚው ሁኔታ በአገር አቀፍ ደረጃ በነበረው ልክ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በከተሞች በዋነኝት ኢኮኖሚው የሚመሠረተው በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ነው፡፡ የግብርና ድርሻ በአንፃሩ አነስተኛ ነው፡፡ ከድኅነት ወለል በታች የሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል ከ22 በመቶ በታች ነው፡፡ የሥራ አጥነት ምጣኔ 23 በመቶ ነው፡፡ በትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጀመርያው ዓመት ላይ የሥራ አጥነት ምጣኔ ከ30 በመቶ በላይ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ወደ 23 በመቶ ወርዷል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በሚመለከት በልማት የሚፈቱ ችግሮች ልማቱን በማስፋት እየተፈቱ የሚሄዱ ናቸው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥን በመሚመለከት እንደ አንድ መሠረታዊ ተግዳሮት ታይቷል፡፡ የኅብረተሰብን እርካታ የበለጠ ለማረጋገጥ በቀጣይነት እንሠራለን፡፡ ይኼም በመንግሥትና በድርጅታችን (ኢሕአዴግ) የሚሠራ ብቻ ሳይሆን፣ ኅብረተሰቡንም ማሳተፍ ይኖርብናል ብለን እንገምታለን፤›› ብለዋል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫውን የተከታተለው ውድነህ ዘነበ በወቅቱ የተነሱ ዋነኛ ጥያቄዎችንና የከንቲባውን ምላሽ እንዲህ አቅርቦታል፡፡

 

ጥያቄ፡- አስተዳደሩ ባካሄደው የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መዋቅሩም ሆነ መዋቅሩን የሚመራው አመራር ላይ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር እንከንና የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያ በሰፊው እንደታየ ተገልጿል፡፡ ይህንን ለማጥራት ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿልና የሚወሰደው ዕርምጃ ምንድነው? ቀደም ሲል ከተከናወነው በምን ይለያል?

አቶ ድሪባ፡- በመዋቅር ማስተካከልና አመራሩን ተጠያቂ ከማድረግ ጋር በተያያዘ፣ እንደሚታወቀው በ2007 በጀት ዓመት መጨረሻ ሁለት ተያያዥ ግምገማዎችን አካሂደናል፡፡ አንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ አፈጻጸምን በተመለከተ ነው፡፡ ይህንን ግምገማ ስናካሂድ የሚታዩ ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ምን ውጤት ተገኘ? የሚለው ይገመገማል፡፡ ሁለተኛው ባለፉት አምስት ዓመታት ምን ችግር አጋጠመ? የሚለው ይገመገማል፡፡ ምን ውጤት ተገኘ? የሚለውን በመግቢያዬ ላይ ጠቅሻለሁ፡፡ ከታዩት ችግሮች አኳያ የአመራርና የሰው ኃይሉ ብቃትን በሚመለከት ገምግመናል፡፡ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ያሉ አመራሮችና የሰው ኃይል ምን ይመስላል? ውጤት ለማምጣት የነበረው ድክመት ምንድነው? ድክመት እንዲከሰት ከማድረግ አኳያ አመራሩና ተልዕኮውን ለማሳካት የተመደበው የሰው ኃይል ነው ተጠያቂ የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ይህን በሚመለከት በግምገማችን እንዳየነው የተወሰኑ ሴክተሮች ውስጥ ከልማትና ከመልካም አስተዳደር አኳያ የተለዩ ድክመቶች አሉ፡፡ ድክመቶቹ በዋናነት የአመራር አቅም ማነስ፣ የሰው ኃይል አቅም ጋር የሚያያዙ ሆነው የተወሰኑ የሥነ ምግባርና አልፎ አልፎ በቁርጠኝነት ተልዕኮዎችን አለማሳካት የተከሰቱ ናቸው፡፡ እነዚህ መታረም እንዳለባቸው ገምግመናል፡፡

ሁለተኛው ግምገማ የ2007 ዓ.ም. ግምገማ ሲሆን፣ በዚህ ዓ.ም. ተመሳሳይ ችግር እንዳለባቸው ያየናቸው ሴክተሮች አሉ፡፡ እነዚህን መሥሪያ ቤቶች በሰው ኃይል መልሰን ማጠናከር ይኖርብናል፡፡ የአመራር ችግር ያለባቸውን ከማዕከል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ አመራሮችን መልሶ የማደራጀትና የማሻሻል ሥራ መሥራት ይኖርብናል፡፡ ይህ ሥራ ገና በጅምር ላይ ያለ ነው፡፡ አልተጠናቀቀም፡፡ የመለየት ሥራ፣ የአመራር አቅም ማሳደጊያና የአቅም ግንባታ ሥራ የሚያስፈልጋቸው፣ አሠራርና አደረጃጀት የሚያስፈልጋቸው ተቋማት ተለይተዋል፡፡ በመለየት ላይም እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ከዚህ ግምገማ ተነስተን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ያሉትን ተቋማት የሚያስተካክልና የሰው ኃይል አጥረት ያለባቸውን ደግሞ በአዲስ መልክ የሰው ኃይል የመመደብ ሥራ ይሠራል፡፡ ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እናስገባለን፡፡

በዚህ ማዕቀፍ መሠረት ከመስከረም ጀምሮ የማስተካከል ሥራ እንሠራለን፡፡ ተጠያቂ የሚሆኑ አመራሮችና ባለሙያዎች ይኖሩ ይሆናል፡፡ እየተለየ ነው ያለው፡፡ አሁን ምን ያህል አመራር ተጠያቂ እንደሚሆን ቁጥር መጥራት አይቻልም፡፡ እንደየጥፋቱና በሥራው ላይ ባስከተለው ልክ ተጠያቂ የሚሆን ይኖራል፡፡ በሥራው ላይ የተከሰተው ችግር የተለያየ እንደመሆኑ ከአመራር ጋር ብቻ ማያያዝም ተገቢ አይደለም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የከተማውን አደረጃጀት በሚመለከት አዲስ ምክረ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ቀርቧል፡፡ ለምሳሌ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎትን በሚመለከት አዲስ አበባን የሚያህል ዓለም አቀፍ ‹ሜትሮፖሊታን› ከተማ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቱ ግዙፍ መሆን አለበት፡፡ በሙያተኛ መመራት ይኖርበታል፡፡ አሁን የማዘጋጃ ቤት ተቋም ከመንግሥት ሥራ ጋር የተቀላቀለ ነው፡፡ ፕሮፌሽናል አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል ደረጃ ላይ እንደማይገኝ በጥናት ለይተናል፡፡ ስለዚህ የሰው ኃይል ብቻ ሳይሆን፣ የአደረጃጀት ችግርም አለ፡፡ ይኼን ለማድረግ አሠራርና የሰው ኃይልን ማደራጀት አለብን፡፡ ምናልባት ከመስከረም በኋላ ወደ ትግበራ እገባለን፡፡

ጥያቄ፡- መልካም አስተዳደር ለማስፈን እስካሁን በተጓዛችሁበት መንገድ ለውጥ ይመጣል ብላችሁ ታስባላችሁ?

አቶ ድሪባ፡- በአገር አቀፍ ደረጃና በድርጅታችን ጉባዔ እንዳየነው የመልካም አስተዳደር ችግር ከልማት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ከልማት ጋር የሚያያዘውን ልማትን በማስፋፋት ብቻ ነው የሚፈታው፡፡ ለምሳሌ የቤት ልማትን ብንወስድ የቤት እጥረት ባለበት ሁኔታ ከቤት ጋር ተያይዞ የሚነሳ የመልካም አስተዳደር ችግርን መፍታት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የቤት ግንባታ ማፋጠን ያስፈልጋል፡፡ የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ ምርት ማሻሻልና አቅርቦትን ማስፋት ይኖርብናል፡፡ የአቅርቦት እጥረት ባለበት የኑሮ ውድነትን መፍታት አስቸጋሪ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከልማት ጋር የሚያያዘውን ልማቱን በማስፋት ነው መቅረፍ የሚቻለው፡፡ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚያያዘውን ችግር ለመፍታት መፍትሔዎቹ ይታወቃሉ፡፡ የአቅጣጫ ችግር አይደለም ያለው፡፡ መፍትሔውን በተሟላ ሁኔታ መተግበር ያለመቻል ችግር ነው፡፡ መፍትሔው የማይተገበረው ደግሞ በአቅም ችግር፣ በቁርጠኝነት ችግርና በአመራር አቅም ማነስ ነው፡፡  በዋናነት የምናደርገው፣ ያለውን አቅጣጫ በብቃት የሚፈጽም አመራርና የሚያስፈጽም ተቋምና ተጠያቂነት የሰፈነበት ሥርዓት ነው መዘርጋት ያለብን፡፡ በተለይ ይህንን ችግር ለመፍታት የሕዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ ሲባል ሕዝብ በስብስባ ተገኝቶ ተናግሮ ይሄዳል ብቻ ሳይሆን፣ ችግሩን ለመፍታት ተፅዕኖ ማሳደር የሚችል ሲሆን ነው፡፡ ሁሉም ሰው ለሕግ የበላይነት መሥራት ይኖርበታል፡፡ ይህንን ሥራ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

ጥያቄ፡- የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት በቀረቡ ሦስት ፕሮግራሞች በርካታ ሕዝብ ተመዝግቧል፡፡ ነገር ግን ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ምዝገባ እንደሚካሄድ ሰሞኑን ተገልጿል፡፡ ይህ እንዲሆን የተፈለገው ለምንድነው?

አቶ ድሪባ፡- የቤት ልማት ዳግም ምዝገባ እንዲካሄድ የተፈለገው ቁጠባ ላይ ችግር በማጋጠሙ ነው፡፡ እንደምታውቁት ከ968 ሺሕ ሰው በላይ ተመዝግቧል፡፡ አሁን በአግባቡ እየቆጠበ ያለው ከግማሽ በታች ነው፡፡ ስለዚህ ተመዝጋቢው በአግባቡ የማይቆጥብ ከሆነ የቤት ባለቤት ለመሆን እውነተኛ ፍላጎት አለ ወይ? የሚለው ጉዳይ ማጣሪያ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ማጣሪያ ለማድረግ ‹ባዮሜትሪክስ› በተባለ ቴክኖሎጂ የተመዘገበ ሰው ዳግም እንዲመዘገብ በማድረግ ማጣራት ይደረጋል፡፡ ተመዝጋቢው ቆጥቦ ቤት የማግኘት አቅም አለው ወይ? የተመዘገበው ሰው የአዲስ አበባ ነዋሪ ብቻ ነው ወይ? የሚለውም ይጣራል፡፡ ቤት ለማግኘት የሚደረገውን ቁጠባ በምናይበት ጊዜ ከባንክ የደረሰን ሪፖርት ከግማሽ በታች ነው፡፡ በአግባቡ እየቆጠበ ያለው፡፡ ይህን ማጥራት ይኖርብናል፡፡ እውነተኛ የቤት ችግር ያለበት የከተማ ነዋሪ ነው ወይ? የሚለውን ማየት ይኖርብናል፡፡ ቤት ማስተላለፍን በመተለከተ 39 ሺሕ ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቋል፡፡  ኤሌክትሪክ፣ የውኃና የፍሳሽ መስመር መዘርጋት ነው የሚቀረው፡፡ ይህ እንደተጠናቀቀ በ2008 ዓ.ም. ይተላለፋል፡፡ ሕጉ የሚለው ግንባታው ከ80 በመቶ በላይ ከተጠናቀቀ ይተላለፋል ነው፡፡ ግን በዚህ ደረጃ እንዳለ ከሚሆን በተቻለ መጠን መቶ በመቶ ግንባታውንና መሠረተ ልማቶችን አጠናቀን ማስተላለፍ መልካም ነው በሚል ነው፡፡ አብዛኛው ሥራ በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ በ2008 ዓ.ም. ይተላለፋል፡፡

ጥያቄ፡- የአዲስ አበባና ዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን በቴክኒክ ደረጃ ሥራው መጠናቀቁ ይነገራል፡፡ ነገር ግን እስካሁን የፖለቲካ ውሳኔ አላገኘም፡፡ በቀጣዩ ዓመት ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ይሆናል ወይ?

አቶ ድሪባ፡- የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላንን በሚመለከት፣ እንደሚታወቀው ሁለቱ የአስተዳደር ክልሎች ማስተር ፕላን በጋራ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡  ማስተር ፕላኑ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች አስተዋጽኦ ያደረጉበት ነው፡፡ ይህ ልምድ የመጣው የፈረንሣይ ሊዮን ከተማ ሲሆን፣ የአውሮፓ ጎረቤት የሆኑ ከተሞች እንዴት ተሳስረው እንደሚለሙና እንዴት ፈጣን ዕድገት እንዳስመዘገቡ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ከተሞቹ ጎን ለጎን ከሆኑ እርስ በርስ በብዙ ነገሮች ይገናኛሉ፡፡ በውኃ፣ በወንዞች፣ በፍሳሽ መስመርና በተለያዩ መሠረተ ልማት ግንባታዎች ይገናኛሉ፡፡ እኛ ጋ ስንመጣ ሦስት ዓመት የፈጀ ጥናት ተሠራ፡፡ ይህንን የሚመራ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ  ማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤት በጋራ ተቋቋመ፡፡ ፕላኑ በመሠረቱ ችግር የለውም፡፡ የሥልጣኔ ምልክት ነው፡፡ ሁለት የአስተዳደር አካላት የተቀናጀ ዕቅድ ይዘው መሥራታቸው በምንም ዓይነት አንዱ የሌላውን አስተዳደራዊ ሥልጣን የሚነካ አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ በጋራ እንልማ ነው፡፡ አንዱን መሬት ወደ ሌላ የመውሰድ ዓላማም የለውም፡፡ በቅንጅት የማልማት ጉዳይ ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ከክልሉ መንግሥት ጋር ተነጋግረንበታል፡፡ የአዲስ አበባ  ከተማ አስተዳደር ሥልጣን ያለው በራሱ ክልል ላይ ነው፡፡

ስለዚህ የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በተመለከተ ከማስተር ፕላን አልፎ የአካባቢ ልማት ጥናት (LDP) ተሠርቷል፡፡ ስለዚህ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ መሬት ማውረድ ጀምረናል፡፡ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ማለት ነው፡፡ የቀረው ሕጋዊ ማዕቀፍ ማፅደቅ ነው፡፡ ይህም በቅርቡ ይፀድቃል፡፡ የአዲስ አበባ ምክር  ቤት ያፀድቀዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የኦሮሚያና የአዲስ አበባን በተመለከተ አንድ መድረክ እየተዘጋጀ ነው፡፡ በጋራ ዓይተን እልባት ለመስጠት መድረኩ እየተዘጋጀ ነው፡፡  የኦሮሚያ  ክልል መንግሥት ከዚህ የተለየ አቋም የለውም፡፡ በጋራ መሥራ እንዳለብን በተደጋጋሚ ተነጋግረናል፡፡ ይኼን ነገር ያልተገነዘቡ አካላት አሉ፡፡ እነሱ ጋ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ባላቸው ሥጋት ላይ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ቀጣይ ሥራ ይኖረናል፡፡ ይህንን የክልሉ መንግሥት ይሠራል፡፡ ሳናቅድና ሳንሠራ ከተሞቹ በራሳቸው መንገድ እየተገናኙ ነው፡፡ ከተሞቹ እየተያያዙ ነው ያሉት፡፡ ይህ በታቀደ መንገድ መታገዝ ይኖርበታል፡፡

በቀጣይነት በሚኖረው መድረክ መንግሥት በማስተር ፕላኑ ላይ የመጨረሻ ዕልባት ይሰጣል፡፡ ክልሉ የተለየ አቋም ስለሌለው፣ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የማልማት ሥራ ይቀጥላል፡፡ አዲስ አበባም እንዲሁ የማልማት ሥራውን ይቀጥላል፡፡ የውኃና የመሠረተ ልማት፣ ወዘተ በእነዚህ ደግሞ በጋራ ለመሥራት ጥረት ይደረጋል፡፡ ይኼ ለሁለቱም የጋራ ጥቅም እንጂ፣ አንዱ ተጠቅሞ ሌላውን የሚጎዳ ነገር የለውም፡፡  ለሁለቱ ሕዝቦች፣ ለሁለቱ አስተዳደሮች የጋራ ጥቅም የሚሰጥ ነው፡፡ ብዥታ ውስጥ ያሉ፣ ነገሩ ያልገባቸውን በማስረዳት ወደ ሥራ እንገባለን፡፡   

ጥያቄ፡- ማስተር ፕላኑ ለውይይት በቀረበበት ወቅት በተለይ ካድሬዎችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል፣ በሕገ መንግሥቱ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ልዩ ጥቅም ማግኘት አለባት የሚለውና ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል የሚለውን አንቀጽ 49 በማንሳት፣ ቅድሚያ ሕግ መውጣት አለበት የሚል መከራከሪያ አቅርበው ነበር፡፡ ይህ እንዴት ይታያል?

አቶ ድሪባ፡- ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የሚያገኘውን ልዩ ጥቅም በተመለከተ፣ ፓርቲው (ኢሕአዴግ) ነው የሚያየው፡፡ ፓርቲው የደረሰበት ውሳኔ እኔ መረጃው የለኝም፡፡ ፓርቲውንና የክልሉን መንግሥት የሚመለከት ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት አጥንቶ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከአዲስ አበባ የሚያገኘው ጥቅም ካለ የሚወሰን ነው የሚሆነው፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር የሚወስነው ጉዳይ አይደለም፡፡ በክልል ደረጃ የሚታይ ነው፡፡

ጥያቄ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የኑሮ ውድነትን ከሚያባብሱት መካከል የመኖሪያ ቤት ኪራይ  ዋጋ ንረት ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት መንግሥት ከሌሎች አገሮች ልምድ በመውሰድ ረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ሕጉ ካለመፅደቁም በላይ እየተጓተተ ያለበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ድሪባ፡- የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ችግርን ለመፍታት ሕግ እየተዘጋጀ ነው ያለው፡፡ ሕጉ በ2008 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል፡፡ በተወሰነ ደረጃ ተጓቷል፡፡ ሐሳቡ አዲስ ስለሆነ የሕጉ ዝግጅት ልምድ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ መኖሪያ ቤት ቆጥበው ማግኘት ለማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በኪራይ አገልግሎት የሚሰጥ መኖሪያ ቤት የመገንባት ዕቅድ ተይዟል፡፡ ይህንን ዕቅድ ለማሳካት ከጀርመን ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ሞዴሎች እየታዩ ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም. ወደ ግንባታ ለመግባት እየተሞከረ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚሆን ቦታ የሚጠይቁ በርካታ ባለሀብቶች ቢኖሩም መስተንግዶ ላይ እየተጉላሉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ውጪም የአገልግሎት ተቋማት ለመገንባት የቦታ ጥያቄ ያቀረቡ በሊዝ ሕጉ ምክንያት እየተስተናገዱ ባለመሆኑ የሊዝ ደንቡና መመርያ ይሻሻሉ ይሆን?

አቶ ድሪባ፡- አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን የሚመልስ መመርያ አለ፡፡ በመመርያ ውስጥ የሚወድቁትን እያስተናገድን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉትን በተለይ ሆቴልና የተለያዩ የአገልግሎት ተቋማት ለመገንባት የቦታ ጥያቄ የሚያቀርቡ አሉ፡፡ እነዚህ በልዩ ጨረታ እንዲስተናገዱ ነው የሚደረገው፡፡ ባለፈው ዓመት የተወሰኑ ልዩ ጨረታዎችን አውጥተናል፡፡ ዘንድሮም በጨረታ እንሄዳለን፡፡ ከዚህ ውጪ አንሄድም፡፡ ባለሀብቶች በጨረታ ቦታ የመግዛት ፍላጎት የላቸውም፡፡ በቀጥታ እንዲሰጣቸው ነው የሚፈልጉት፡፡ በተለይ ከውጭ የሚመጡ ባለሀብቶች መሬት በቀጥታ እንዲሰጣቸው ነው የሚፈልጉት፡፡ ‹‹እኛ ወደ ጨረታ ከምንገባ ካፒታል ይዘን ስለምንመጣ ቅድሚያ ይሰጠን፤›› ይላሉ፡፡ አንዳንዱ ተቀባይነት ያለው አለ፡፡ በተለይ ባለአምስትና ከዚያ በላይ ሆቴል የሚገነቡ ከሆኑ ካፒታል ከውጭ ስለሚያመጡ በልዩ ሁኔታ ይስተናገዳሉ፡፡ አስተማማኝ ካፒታል ያላቸው ፕሮጀክቶችን የሚገነቡ ከሆነ አስተዳደሩ ያስተናግዳል፡፡ ከዚህ በተረፈ ከሊዝ አዋጅ በታች ያሉት የሊዝ ደንቡና መመርያ ለማሻሻል ጥናት እየተደረገ ነው፡፡ እስከ መስከረም ወይም እስከ ጥቅምት አገልግሎት ላይ ሊውሉ ይችላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -