– በመጪው እሑድ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ይጀመራል
– ትልቁ የትራንስፖርት ታሪፍ ስድስት ብር ነው
የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ከመጪው እሑድ መስከረም 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት እንደሚጀምር፣ የአገልግሎት ደኅንነቱንም ለመጠበቅ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የተካተተበት ቡድን መዋቀሩን የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ሣራካ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ መጀመርን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላትና ከተመረጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ጥንቃቄን በተመለከተ ማክሰኞ መስከረም 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ ወቅት ንግግር ካደረጉት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች መካከል የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ከፍተኛ የደኅንነት ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ምክንያት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት፣ የፌዴራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተካተቱበት የደኅንነት ጥበቃ ቡድን መዋቀሩን ገልጸዋል፡፡ በዋናነት የትራንስፖርት አገልግሎቱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆን ለማድረግ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛውን ኃላፊነት መውሰዱንም ተናግረዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎቱ በተለያዩ የፍጥነት ገደቦች እንደሚሰጥ፣ በኩርባዎች፣ በተሽከርካሪዎችና በእግረኞች መሸጋገሪያ አካባቢዎች የሚኖረው ፍጥነት ዝቅተኛ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ባቡሩ ከመስመሩ ከወጣ ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል በመሆኑ በትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ አደጋ የሚያስከትል እንከን ዜሮ ፐርሰንት እንዲሆን ሁሉንም ያሳተፈ ጥንቃቄ ይደረጋል ብለዋል፡፡ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ጉዳቱን ለመቀነስና አስፈላጊውን ዕርዳታ ለመስጠት፣ በትራንስፖርት ሚኒስቴር ሥር 18 ሌሎች ተቋማትን የካተተ ኮማንድ ፖስት (የዕዝ ማዕከል) መቋቋሙንም አቶ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ጽሕፈት ቤት ሆኖ በኮርፖሬሽኑ ሥር የተደራጀው የትራንስፖርት ማኔጅመንቱ ክፍል የቻይናው ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቻ የሆኑት ኢንጂነር ሔኖክ ቦጋለ በበኩላቸው፣ መንገደኞችና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ከባቡሩ የትራንስፖርት አገልግሎት የትራፊክ አጠቃቀም ሥነ ሥርዓት ጋር እንዲናበቡ ጠይቀዋል፡፡
እግረኞች በተፈቀዱ የእግረኛ ማቋረጫ ቦታዎች ብቻ እንዲጠቀሙ፣ አሁን የሚታየው አጥር ዘሎ ማቋረጥ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ሲጀመር የሚታሰብ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡
መረጃ ሰጪ ጽሑፎችን እንዲሁም አስገዳጅ ምልክቶችን መጠቀም ከሁሉም የሚጠበቅ ግዴታ መሆኑን፣ ወደ ባቡሩ የመስመር ክልል ተሳፋሪዎች ከመግባታቸው በፊት ወዴት እንደሚሄዱ ማወቅ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
የባቡር ክልል ውስጥ ባቡሩ የለም ብሎ መግባት ለአደጋ እንደሚያጋልጥ የተናገሩት ኢንጂነር ሔኖክ፣ ከላይ ያለው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይልና ሌሎች ምልክት ሰጪ መሣሪያዎች አገልግሎት ላይ በመሆናቸው ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የጦር መሣሪያ ወይም ስለት ይዞ ወደ ባቡር ትራንስፖርቱ መግባት እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡
የትራንስፖርት ታሪፍ ምጣኔን የተናገሩት ደግሞ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ጥላሁን ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ ትራንስፖርተሮች ታሪፍን በመገምገም እስከ ሁለት ኪሎ ሜትር (ስምንት የባቡር ፌርማታዎች) ሁለት ብር፣ እስከ አራት ኪሎ ሜትር (እስከ ስድስት የባቡር ፌርማታዎች) አራት ብርና ከአራት ኪሎ ሜትር በላይ ወይም ከመነሻ እስከ መድረሻ ስድስት ብር እንዲሆን መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውጪ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላት እንዲሁም አረጋውያን የትራንስፖርት አገልግሎቱን በነፃ እንዲያገኙ መታሰቡን አስረድተዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለመጠቀም ሁለት ዓይነት የትኬት አገልግሎት እንደሚኖር፣ አንደኛው የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ሥርዓት ሲሆን ይህም ተሳፋሪዎች ወደ ባቡሩ ሲገቡ ባቡሩ ላይ ለተገጠመ የክፍያ መቁረጫ ማሽን (POS) የኤሌክትሮኒክ ካርዳቸውን አስጠግተው ማስነበብ፣ ይህንኑ ተግባርም ሲወርዱ መድገም እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
ይህንን በሚያደርጉበት ወቅት ማሽኑ በኤሌክትሮኒክ ካርዱ ላይ የተሞላውን ሒሳብ በተጓዙበት ኪሎ ሜትር አስልቶ የሚቀንስ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ሌላው የትኬት አጠቃቀም ለመጓዝ በተፈለገበት መስመር የሚሸጥ ትኬት ሲሆን፣ ይህም ለመጓዝ በተወሰነበት ወቅት በሥፍራው የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተሳፋሪዎች ይህንን ዘመናዊ ትራንስፖርት ሲጠቀሙ አያጭበረብሩም ተብሎ እንደሚታሰብ፣ ምክንያቱ ደግሞ የተቀመጠው ታሪፍ አቅምን ያገናዘበ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን አጭበርብረው የሚገኙ ተሳፋሪዎች የዋጋውን አሥር እጥፍ እንደሚቀጡ ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱ የሚሰጠው በዝቅተኛ ዋጋ በመሆኑና ኮርፖሬሽኑ ደግሞ የባቡር መሠረተ ልማቱን ለመዘርጋት ከቻይና መንግሥት የተበደረውን ከ470 ሚሊዮን ዶላር በላይ መመለስ ስለሚገባው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ድጎማ እንዲያደርግ እንደሚጠየቅም ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከቻይና ያስመጣው ተቆጣጣሪ ኩባንያ ለኦፕሬሽን አገልግሎቱ ሠርተፊኬት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኩባንያው በአጠቃላይ የባቡር መስመሩና ተሽከርካሪው ላይ ፍተሻ በማድረግ 40 የሚሆኑ መታረም የሚገባቸው ስህተቶችን ነቅሶ ማውጣቱን የገለጹት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ኮርፖሬሽኑም ይህንን ተቀብሎ በማረም ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡