ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ ብራዛቪል አስተናጋጅነት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ውድድሩ የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች (የአፍሪካ ኦሊምፒክ) ከስፖርታዊ ውድድርነቱ ባሻገር በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች ተበታትና ለቆየችው አፍሪካ አንድነትና ዲፕሎማሲያዊ የጋራ ግንኙነት መጠናከር ብሎም ለሕዝቦቿ የእርስ በርስ ወዳጅነት መጐልበትና ለአህጉሪቱ ኅብረት ዓላማ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ይነገርለታል፡፡
የኦሊምፒክ ፍልስፍናን መነሻ ያደረገው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች አካላዊ፣ አዕምሮአዊና ሥነ ምግባራዊ ሁኔታዎችን አካቶ ዋነኛ ትኩረቱም ስፖርት ለሰው ልጆች አገልገሎት በማዋል ሰላማዊ ዓለምን ለሰው ልጆች መፍጠር በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ኢትዮጵያ በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ለሚኖራት ተሳትፎ የአንበሳው ድርሻ በመያዝ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የማስፋፋት ሥራው እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የመላው የአፍሪካ ጨዋታዎች እስካሁን አሥር ጊዜ ተካሂዷል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የተሳታፊ አገሮች ስፖርተኞችና ውድድሩ የሚካሄድባቸው የስፖርት ዓይነቶችና ብዛትም በተመሳሳይ እየጨመረ እንደሚገኝም እየተነገረ ይገኛል፡፡ የዘንድሮው 11ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ውድድር ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገው ደግሞ የ2016 ሪዮ ዴጄኔሮ ኦሊምፒክ ከመካሄዱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ የሚከናወን መሆኑ ሲሆን፣ ይህም ለኢትዮጵያም ሆነ ለአህጉሪቱ አገሮች ዝግጅት ይረዳ ዘንድ ጠቀሜታ እንዳለው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት በቀለ ቀደም ሲል መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ከተጀመረበት እስካሁን ድረስ በተካሄዱት ውድድሮች ያለውጤት የተመለሰችበት ወቅት እንደሌለው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዚሁ በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1965 በ5,000 ሜትር የመጀመሪያውን የነሐስ ሜዳለያ ማስመዝገብ የቻለው በሻምበል ማሞ ወልዴ አማካይነት ነበር፡፡ በመሆኑም ከሁለተኛው እስከ አሥረኛው ድረስ በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ለኢትዮጵያ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ አትሌቶች ምሩጽ ይፍጠር፣ መሐመድ ከድር፣ ፊጣ ባይሳ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ጌጤ ዋሚ፣ አሰፋ መዝገቡ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ስለሺ ስህን፣ መሠረት ደፋር፣ እጅጋየሁ ዲባባና ታሪኩ በቀለን የመሳሰሉ እንደሚጠቀሱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይፋ ያደረገው መግለጫ ያስረዳል፡፡
የፊታችን ቅዳሜ መስከረም 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍጻሜውን እንደሚያገኝ በሚጠበቀው 11ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች፣ ኢትዮጵያ ተሳትፎ ያደረገችው በ11 የስፖርት ዓይነቶች ማለትም ፓራሊምፒክን ጨምሮ በአትሌቲክስ፣ በብስክሌት፣ በውኃ ዋና፣ በቦክስ፣ በወርልድ ቴኳንዶ፣ በሜዳና ጠረጴዛ ቴኒስ፣ በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ፣ በክብደት ማንሳትና በባድሜንተን ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ የተመዘገበው ሜዳለያ በ10,000 ሜትር ወርቅና ነሐስ፣ በአትሌት ፀበሉ ዘውዴና አዱኛ ታከለ እንዲሁም በ1,500 ሜትር መኰንን ገብረ መድህን ወርቅ፣ በ20 ኪሎ ሜትር ዕርምጃ ሴቶች ዓይናለም እሸቱ ብር፣ አስካለ ቲክሳ የነሐስ ሜዳለያ አስመዝግበዋል፡፡ በ800 ሜትር ሴቶች ጫልቱ ሹሜ ነሐስ አስመዝግባለች፡፡ በአጠቃላይ ሁለት የወርቅ፣ አንድ የብርና ሦስት የነሐስ በድምሩ ስድስት ሜዳለያዎች ተመዝግበዋል፡፡
ወደ ኮንጎ ብራዛቪል ያቀናው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ወደ ሥፍራው ከማምራቱ በፊት ‹‹ይመዘገባል›› ብሎ በዕቅድ የያዘው የሜዳሊያ ብዛት ስምንት ወርቅ፣ 10 ብርና 12 የነሐስ በድምሩ 30 ሜዳሊያዎችን ማግኘት እንደነበርም ተነግሯል፡፡