Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአስቴርና ማዲንጎ በ‹‹እወድሃለሁ››

አስቴርና ማዲንጎ በ‹‹እወድሃለሁ››

ቀን:

2008 ዓ.ም. ሊገባ ሰዓታት ቀርተዋል፡፡ አብዛኛው የመዲናችን መንገዶች እንቁጣጣሽን ለመቀበል በጓጉ ሰዎች ተሞልተዋል፡፡ ወደ ግዮን ሆቴል የሚወስደው መንገድ ደግሞ ከሌሎች ጎዳናዎች በተለየ ተጨናንቋል፡፡ ‹‹እወድሃለሁ›› የሚል ስያሜ የተሰጠውን የአስቴር አወቀና ማዲንጎ አፈወርቅ የአዲስ ዓመት ኮንሠርት ለመታደም ከአመሻሹ ጀምሮ ታዳሚዎች ወደ ቦታው አቅንተዋል፡፡

በሆቴሉ አቅራቢያ የአስቴር ፎቶግራፍ የታተመባቸው ቲሸርቶች ይሸጡ ነበር፡፡ ቲሸርቱን ይገዙ የነበሩት በአመዛኙ ወጣቶች ሲሆኑ፣ ኮንሠርቱን የታደሙት ደግሞ በተለያየ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው፡፡ በዕድሜ የገፉ ጥንዶች፣ ጎልማሶች እንዲሁም በቡድን የሄዱ ወጣቶች በቦታው ተገኝተዋል፡፡ በታዳሚዎቹ መካከል የሚታየው የዕድሜ ልዩነት ከሌሎች ኮንሠርቶች አንፃር የሰፋ ነው ለማለት ይቻላል፡፡

መድረኩ ለሰዓታት የተመራው በዲጄዎች ነበር፡፡ በዐል ተኮር እንዲሁም ሌላ ሙዚቃ ካስደመጡ መካከል ዲጄ ዊሽ ይገኝበታል፡፡

መጀመሪያ ወደ መድረክ የመጣው ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ነበር፡፡ ሞቅ ያለ አቀባበል የተደረገለት ማዲንጎ፣ በቅርቡ ካወጣው ‹‹ስወድላት›› የተባለ አልበሙ ላይ የመረጣቸውን አቀንቅኗል፡፡ ማዲንጎ አልበሙን ካወጣ በኋላ ከኃይሌ ሩትስ ጋር ተጣምሮ በላፍቶ ሞል ያቀረበው ኮንሠርት ይጠቀሳል፡፡

በኮንሠርቱ ‹‹አይደረግም›› ከተባለውና ከጥቂት ዓመታት አስቀድሞ ከወጣው አልበሙ መካከልም ዘፍኗል፡፡ በተለይም በባህላዊ ሙዚቃዎቹ ብዙዎች ትከሻቸውን ሲፈትሹ ተስተውሏል፡፡ አብዛኛው ታዳሚ በሆቴሉ ፋውንቴን አካባቢ የነበረው መድረክ ስር ተገኝቷል፡፡ ለቪአይፒ በተሰጠው ፎቅ ላይ ሆነው ኮንሠርቱን የተከታተሉም ነበሩ፡፡

አስቴር ወደ መድረክ የወጣችው ወደ አምስት ሰዓት ገደማ ነበር፡፡ ከመዝፈኗ አስቀድሞ ታዳሚው ዘለግ ባለ ጭብጨባና ፉጨት ተቀብሏታል፡፡ የኮንሠርቱ የመጀመርያ ዘፈኗ የሆነውን ‹‹አገሬን አልረሳም››ን ስታቀነቅንም፣ ብዙዎች አብረዋት ይዘፍኑ ነበር፡፡ ስሟን አቆላምጠው እየጠሩ ፍቅራቸውን የሚገልጹ፣ በሞባይሎቻቸው ለመቅረፅ ከቁመታቸው በላይ የሚንጠራሩም ነበሩ፡፡

አስቴር በአዲስ ዓመት ዋዜማ በኢትዮጵያ የመጨረሻ ኮንሠርቷን ያካሄደችው ከአምስት ዓመት በፊት በሚሊኒየም አዳራሽ ነበር፡፡ የመጨረሻ አልበሟ ‹‹እወድሃለሁ››ን ከለቀቀች ሁለት ዓመት አስቆጥራለች፡፡ በዕለቱ ከቀደሙት ሥራዎቿ ተወዳጅ የሆኑ ዘፈኖቿን አቅርባለች፡፡ መድረክ ላይ ከወዲያ ወዲህ እያለች ስትወዛወዝ ታዳሚዎች ሞቅ ያለ ድጋፍ አሰምተዋል፡፡ እሷም በመድረክ ላይ ከአድናቂዎቿ ጋር በመገናኘቷ የተሰማትን ሀሴት በተደጋጋሚ ገልጻለች፡፡ ‹‹ናፍቄአችኋለሁ… ፍቅራችሁ ያጠግበኛል… አበጃችሁ ጨፍሩ››ና ሌሎችም በየዘፈኖቿ መካከል ጣል ጣል ያደረገቻቸው አስተያየቶች ነበሩ፡፡ አስቴር ዘመን ተሻጋሪና ተወዳጅ ዜማዎቿን ከማዲንጎ ጋር እየተፈራረቀች አስደምጣለች፡፡

ከምሽቱ ስድስት ሰዓት ሊሆን አሥር ሰኮንዶች ሲቀሩት ጀምሮ ያሉት ሰኮንዶች ተቆጥረው (ካውንት ዳውን ተደርጎ) ሲጠናቀቅ ርችት ተተኩሷል፡፡ ሰማዩ በህብረ ቀለማት ደምቆ ሳለ በየዓመቱ አዲስ ዓመት መምጣቱን ከሚያበስሩ ሙዚቃዎች አንዱ የሆነው የአስቴር ‹‹እዮሀ አበባዬ… መስከረም ጠባዬ›› ተደምጧል፡፡ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር መሠረት አዲስ ዓመት የሚገባው እኩለ ሌሊት ላይ እንዳልሆነ የሚያስረዱ ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ 12፡00 ሰዓት ላይ የአዲስ ዓመት መባቻ ርችት መተኮስ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...