‹‹አሜሪካና ሌሎች የጥላቻ ኃይሎች በያዙት የጥላቻ መንገድና በአሻጥር ከቀጠሉ ሰሜን ኮሪያ በማንኛውም ጊዜ በኑክሌር ኃይል ለመጋፈጥ ዝግጁ ናት፡፡››
የሰሜን ኮሪያ የአቶሚክ ኤጀንሲ ዳይሬክተር መናገራቸውን የዘገበው የአገሪቱ የዜና አገልግሎት ነው፡፡ ሰሜን ኮሪያ ማክሰኞ ዕለት ባወጣችው መግለጫ የኑክሌር ኃይሏን በማዘመንና ጥራቱንና መጠኑን በመጨመር፣ ከአሜሪካም ሆነ ከአጋሮቿ የሚሰነዘርባትን ማንኛውም ጥቃት ለመከላከል እንደምትጠቀምበት አስተውቃለች፡፡ በዚህም መሠረት ሁሉንም የኑክሌር ጣቢያዎቿን ዝግጁ በማድረግ ሥራ ማስጀመሯም ተገልጿል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች የተገለለችውና ድህነት የሚጫጫናት ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ፕሮግራሟን ዓለም አቀፍ ጫና መፍጠሪያ እያደረገች ነው ይላሉ፡፡ የኑክሌር አረሮቿም የአሜሪካ ግዛቶችን ሊመቱ ይችላሉ በማለት ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይህ የሰሜን ኮሪያ መግለጫ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ በምሥሉ ላይ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ወጣቱ ኪም ጆንግ ኡን በወታደራዊ ሹማምንቶች ተከበው ይታያሉ፡፡