Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአርቲስት ሰብለ ተፈራ (1968 እስከ 2008 ዓ.ም.)

አርቲስት ሰብለ ተፈራ (1968 እስከ 2008 ዓ.ም.)

ቀን:

ትርፌ በብዙዎች ህሊና የተቀረጸች ገፀ ባህሪ ነች፡፡ ዘወትር ቅዳሜ አመሻሽ ላይ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) እየቀረበ ያለውና ‹‹ቤቶች›› የተሰኘውን ሲትኮም (አስቂኝ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ) ተወዳጅ ካደረጉ አንዷ የቤት ሠራተኛዋ ትርፌ ናት፡፡ ‹‹ትንንሽ ኮከቦች›› ከዓመታት በፊት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ይተላለፍ የነበረ የሬዲዮ ድራማ ነው፡፡ ለአምስት ዓመታት የቀረበው ድራማው ካሳተፋቸው መካከል የእማማ ጨቤ ገፀ ባህሪ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ትርፌና እማማ ጨቤ ተመልካቾችን ከቴሌቪዥኖቻቸው፣ አድማጮችንም ከሬዲዮኖቻቸው ያስተሳሰሩ አይረሴ ገፀ ባህሪያት ናቸው፡፡

ሁለቱን ገፀ ባህሪዎች ተላብሳ ትጫወት የነበረው ሰብለ ተፈራ፣ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ካገኙ ዝነኛ ተዋንያን መካከል ትጠቀሳለች፡፡ መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም.  በመኪና አደጋ ሕይወቷ ያለፈው አርቲስት ሰብለ ሥርዓተ ቀብር መስከረም 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ከቀኑ በ9፡00 ሰዓት ተፈጽሟል፡፡

ተዋናይት፣ አዘጋጅና ፕሮዲውሰር ሰብለ የተወለደችው በግንቦት 18 ቀን 1968 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ወሎ ሰፈር አካባቢ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በተባበሩት መንግሥታት ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በንፋስ ስልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች፡፡ ወደ ጥበብ የተሳበችው በልጅነቷ ነበር፡፡ በ1984 ዓ.ም. የአርቲስት ተስፋዬ አበበን የኪነ ጥበብ ማዕከል ተቀላቀለች፡፡ አቶ ተስፋዬ (ፋዘር) የነፃ ትምህርት አገልግሎት የሚሰጡበት ማዕከላቸው ካፈራቸው ተዋንያን አንዷ የሆነችው ሰብለ፣ ከሕዝብ የተዋወቀችው ‹‹ጭንቅሎ›› በተሰኘ ቴአትር ነበር፡፡

በቴአትር ጥበባት ከወጋገን ኮሌጅ ዲፕሎማ ያገኘች ሲሆን፣ ከህልፈቷ በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት በዲግሪ መርሐ ግብር የቴአትር ትምህርት እየተከታተለችም ነበር፡፡ ሰብለ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች፣ በመድረክ ቴአትርና በፊልም ሥራ ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ ከ30 በላይ ቴአትሮችና ከ20 በላይ የሚሆኑ ፈልሞች ሠርታለች፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጪ በርካታ አገሮችን ተዘዋውራም ሥራዎቿን አቅርባለች፡፡

‹‹አምታታው በከተማ››፣ ‹‹ጓደኛሞቹ››፣ ‹‹12 እብዶች በከተማ››፣ ‹‹ሰቀቀን››፣ ‹‹ወርቃማ ፍሬ››፣ ‹‹ሕይወት በየፈርጁ››፣ ‹‹የሠርጉ ዋዜማ››፣ ‹‹ላጤ››፣ ‹‹እኩይ ደቀመዝሙር››፣ ‹‹እንቁላሉ››ና ‹‹ሩብ ጉዳይ›› ከተወነችባቸው ቴአትሮች ጥቂቱ ናቸው፡፡ ከሠራችባቸው ፊልሞች መካከል ‹‹ፈንጂ ወረዳ››፣ ‹‹ያረፈደ አራዳ››፣ ‹‹ማግስት›› እና ‹‹ትንቢት›› ይጠቀሳሉ፡፡

ሰብለ ፊልም ፕሮዳክሽን የተባለ ድርጅት አቋቁማ ትንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን፣ ‹‹ርጥባን›› የተባለ ቴአትር ፕሮዲውስ አድርጋለች፡፡ ቴአትሩ በአዲስ አበባ የቴአትርና ባህል አዳራሸ (ማዘጋጃ ቤት) ለአራት ዓመታት ታይቷል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት የተሠራው ‹‹አልበም›› የተሰኘ ፊልም አዘጋጅና ፕሮዲውሰርም ነበረች፡፡ ሰብለ በበርካታ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ማስታወቂያዎቿም ትታወቃለች፡፡

ሱዳን አቤይ ውስጥ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ሰላም አስከባሪ ኃይል ያቀረበችው ተውኔት ከኢትዮጵያ ውጪ ሥራዎቿ መካከል ይጠቀሳል፡፡ ‹‹ሴት ወንድሜ›› የተሰኘ ቴአትር በእስራኤል፣ ‹‹የኛ እድር›› የተባለ ቴአትር በእንግሊዝና ‹‹የዳዊት እንዚራ›› ን በደቡብ አፍሪካ አሳይታለች፡፡ በቅርቡ ለስድስት ወራት ያህል ‹‹የኛ እድር››ን በአሜሪካ አቅርባለች፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ቤተ ክርስቲያኖችንና ገዳማትን በማገልገል በመንፈሳዊ ማኅበራት ትሳተፍ እንደነበር ከታሪኳ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በ1999 ዓ.ም. ከአቶ ሞገስ ተስፋዬ ጋር ትዳር የመሠረተችው ሰብለ፣ ሕይወቷ ያለፈው የአዲስ ዓመት ዕለት ንፋስ ስልክ አካባቢ ከባለቤቷ ጋር ይጓዙ በነበረበት ወቅት በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ነው፡፡ አደጋው የደረሰው ባለቤቷ ያሽከረክር የነበረው መኪና ከቆመ ከባድ መኪና ጋር ተጋጭቶ ነው፡፡ ከአደጋው በኋላ ባለቤቷ ቢታሰርም በዋስ እንደተለቀቀም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በ40ኛ ዓመቷ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው ሰብለ ሕልፈት እንደተሰማ ብዙዎች ሐዘናቸውን በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል፡፡

ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው የመኪና አደጋ ጉዳይም መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይም ይኸው ጉዳይ ተነስቶ ነበር፡፡ ሰብለ በኪነ ጥበቡ አያሌ ሥራዎችን ማበርከት ስትችል በድንገት መቀጠፏ ስሜታቸውን የነካ ጥቂት አይደሉም፡፡ በቀብሩ ዕለት ወደ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሚወስዱ ሁሉም መንገዶች በአርቲስቷ ቤተሰቦች፣ የሙያ አጋሮችና አድናቂዎች ተሞልተው ነበር፡፡ በቀብሩ ላይ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድርን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ተገኝተው ነበር፡፡

አቶ አሚን በሰብለ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፣ ‹‹በኪነ ጥበቡ ባበረከተችው አስተዋጽኦ አርአያ መሆን የምትችል ናት፤ በሥራዎቿ ዘወትር በተሰበረ ልብ እናስታውሳታለን፤›› ብለዋል፡፡

ሰብለ የ16 ዓመት ወጣት ሳለች ነበር ወደ አርቲስት ተስፋዬ ማዕከል ያመራችው፡፡ ከሁለት ዓመት በላይም በማዕከሉ ተምራለች፡፡ አርቲስት ተስፋዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ችሎታዋ ከዕድሜዋ በላይ ነበር፡፡ የሚሰጣትን ገፀ ባህሪ በጥቂት ቀናት ውስጥ አጥንታ በአስደናቂ ብቃት ትተውን ነበር፡፡ አሳዛኝም አስቂኝም ገፀ ባህሪ ተላብሳ ብትተውንም፣ ዝንባሌዋ ወደ አስቂኙ ነበር፡፡ ‹‹ያኔ እኛን ሁሉ ታስቀን ነበር፤ ልዩ ሆነው ከተፈጠሩ ተዋንያን አንዷ ነች፤ ነባር ተዋንያንን ሁሉ ታስተምር ነበር፤›› ይላሉ፡፡

‹‹ጭንቅሎ›› የተሰኘውን ቴአትር ከሠራች በኋላ በቴአትር፣ በፊልምም በመሳተፍ ችሎታዋን እንዳጎላች ይናገራሉ፡፡ ‹‹ትወና የተሰጣት ነበረች፤ በተለይ በማሳቅ ግንባር ቀደም ነበረች፤›› የሚሉት መምህሯ፣ ‹‹የማትገኝ ጽጌረዳ ተቀጠፈች›› ሲሉ የተሰማቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሥራዎቿ ሁሉ ‹‹የወንደላጤው መዘዝ›› የተሰኘውን ቴአትር ይወዱላታል፡፡ በቴአትሩ ላይ የቤት ሠራተኛ ሆና ትተውን ነበር፡፡ ተመልካቾች በትወናዋ ተመስጠው ያዩ እንደነበርና በሌሎችም ሥራዎቿ አድናቆትን ያገኘች እንደነበረች ያወሳሉ፡፡ ህልፈቷን የሰሙበትን ቅጽበትም ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ድንገተኛ ሞት ስለሆነ እጅግ ያስደነግጣል፤ መርዶዋን ከሰማን በኋላ በዓሉም በዓል አልሆነልንም፤›› ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...