Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ዋዜማው

ትኩስ ፅሁፎች

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የ2008 ዓ.ም. መባቻን ምክንያት በማድረግ ያሰናዳው መርሐ ግብር ጳጉሜን 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ዝግጅቱን ታድመዋል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሚያከናውኗቸውን ካሳወቁ መካከል የግብርና ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ንግድ ሚኒስቴር፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ይገኙበታል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ወጣትና አንጋፋ ድምፃውያንም ሲያቀነቅኑ፣ የፌዴራል ፖሊስ ማርሽ ባንድም በፎቶው እንደሚታየው ዝግጅቱን አቅርቧል፡፡  

(ፎቶ በዳንኤል ጌታቸው)

**********

ሦስቱ አልተግባብቶዎች

ሦስት ሰዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው ራሰ በራ ነበር፡፡ ሁለተኛው ከመቆሸሹ የተነሳ እከክ ይዞት ነበር፡፡ ሦስተኛውም ንፍጣም ነበር፡፡

እነዚህም ሰዎች ልዩ ባህሪያት እንዳላቸው ተስማምተው ‹‹ስለዚህ አብረን እንሂድ፡፡›› ተባባሉ፡፡ አብረውም እየሄዱ ሳለ ንፍጣሙ ሰውዬ ‹‹አውሮፕላን ሲያልፍ ‘ሁሁሁ,,,,,,,’ ይላል፡፡›› ብሎ የአውሮፕላኑን አስተላለፍ ያሳየ በመምሰል አፍንጫውን ይጠርጋል፡፡

እከካሙም ሰው እጆቹን በማቆላለፍ ‹‹ኧረ አንድ ቀን ሁለት ፍየሎች እንደዚህ እያደረጉ ሲጣሉ አየሁ፡፡›› ብሎ የፍየሎቹን ፀብ ያሳየ መስሎ ቁስሉን ያካል፡፡

ራሰ በራውም ‹‹ምን ዓይነት ውሸታሞች ናችሁ!›› ብሎ የተገረመ በመምሰል መላጣውን በእጆቹ ሸፈነ ይባላል፡፡

  • የወግ ገበታ

**********

አዳምና ሔዋን

ቀዳማዊው ጽልመት ሲወርድ በዙሪያቸው

ቅጠሎች ደከሙ ሞገስ ሰልችቷቸው፤

በጠራው ፀጥታ ውበት አጋጥማቸው

ዘዴዎችዋን ሁሉ ገለጸላቸው፡፡

በጠራራው ፀሐይ መካነ ገነት

ፀሐይ ይሞቃሉ ወፍም መላእክት፤

አስተማረቻቸው ሰማያዊ ምክር

ከቃጠሎው ንዳድ ከሃሩር ሲሸሹ ከሞቃቱ አየር

ያዩት ነገር የለም ከህልም በስተቀር፡፡

እጆቻቸውንም ውበት ጠፋፈረች

እንዲበርድላቸው ምንጯ ውስጥ ነከረች

ቀኑም ዘመም ሲል ሲቃረብ ሌሊቱ፤

ወዲያው አንቀላፉ ቆነጃጅቶችም እንደሚተኙቱ፤

ከዚያም አረፍ ብላ ጥቂት እንደቆየች፤

ነቅታ ከአፈራቸው አይላ አበበች፡፡

  • ከማርጆሪ ፒክቶል (1883 እስከ 1922)

ትርጉም ዳዊት ዘኪሮስ

********

የሰው ነገር – በችሎት ፊት

አንድ ሲራራ ነጋዴ መንገድ ሲሔድ ቆይቶ ቀን በምሳ ሰዓት ከአንድ ዛፍ ሥር አረፍ ብሎ ምሳውን ቆሎ ቆርጥሞና ውሃ ጠጥቶ ጉዞውን ሲቀጥል ሁለት መቶ ጠገራ ብር ረስቶ ሄደ።

አንድ ገበሬ አግኝቶለት ያንን ገንዘብ ሊሰጠው ከኋላ እየሮጠ ተከተለውና ‹‹ሰውዬ ቆም ብህ ጠብቀኝ፤ ጥለኸው የሔድከው ገንዘብህን አግኝቼልሃለሁ፤›› አለው። ነጋዴውም ‹‹ያገኘኸው ገንዘብ ስንት ነው?›› ሲለው ‹‹ሁለት መቶ ብር›› አለው።

ነጋዴው ግን ‹‹እኔ የጠፋብኝ ገንዘብ ሦስት መቶ ብር ነው። አንዱን መቶ ብር የት ደብቀህ ነው ሁለት መቶ ብር የምትሰጠኝ። ሞልተህ ካላመጣህ አልቀበልህም እከስሃለሁ። እንዲህ በዋዛ አንላቀቅም›› አለው።

ገበሬውም ገንዘቡን እንደያዘ ወደ ኋላ ተመለሰ። ነጋዴው የመሠረተው የውሸት ክስ በይግባኝ ተይዞ ወደ አፄ ቴዎድሮስ ሲቀርብ የሁለቱን አባባል ካዳመጡ በኋላ ነጋዴውን ምን ያህል ገንዘብ ነው የጠፋህ? ሲሉት ‹‹ሦስት መቶ ጠገራ ብር ነው›› አላቸው።

ገበሬውንም ‹‹ምን ያህል ገንዘብ አገኘህ?›› ሲሉት ‹‹ሁለት መቶ ጠገራ ብር ብቻ ነው›› አለ።

ከዚያ በኋላ ‹‹አንተ ነጋዴው ጠፋብኝ የምትለውን ሦስት መቶ ብር ከጣልህበት ቦታ ፈልገህ አግኝ። ሁለት መቶ ብር ያገኘኸው ገበሬ ደግሞ ሁለት መቶ ብር ጠፋኝ የሚል ሌላ ሰው እስከሚመጣ ድረስ ራስህ ልትጠቀምበት ትችላለህ›› ሲሉ ፈርደው ፋይሉ ተዘጋ።

  • መጋቤ አእላፍ መክብብ አጥናው ‹‹አምስተኛው ጉባኤ – የአባቶች ጨዋታ›› (2005 ዓ.ም.)

************

ጉዳቷ ሥነ ልቦናዊ በመሆኑ ፓራሊምፒያኗ ከእንግዲህ እንዳትወዳደር ተከለከለች

የ23 ዓመቷ እንግሊዛዊት ቻርሎቴ ዊልኪንሰን ምንም እንኳ ቀደም ሲል በአካል ጉዳተኞች ስፖርታዊ ውድድር በመሳተፍ ለአገሯ ሜዳሊያ ያስገኘች ቢሆንም ከዚህ ወዲህ በተመሳሳይ ውድድር እንድትሳተፍ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

ዘ ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው ወጣቷ እ.ኤ.አ. 2011 ላይ መታጠቢያ ቤት ውስጥ መውደቋን ተከትሎ ለአራት ዓመታት በአካል ጉዳተኝነት ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡ በአካል ጉዳተኞች እስፖርታዊ እንቅስቃሴ በመሳተፍም ለአገሯ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች፡፡ ቢሆንም በቅርብ በተደረገላት ምርመራ ሥነ ልቦናዊ እንጂ ምንም ዓይነት የአካል ጉዳት (ፓራላይዝድ አለመሆኗ) ተረጋግጧል፡፡ በተለያየ አጋጣሚ ተመሳሳይ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ይህ ነው የሚባል አካላዊ ጉዳት ሳይኖርባቸው ነገር ግን ፓራላይዝድ የመሆን ስሜቶችን ሊያስተናግዱ እንደሚችሉ ዘገባው ያመላክታል፡፡

በቅርቡ ለሚደረግ ዓለም አቀፍ ፓራሊምፒክ በመዘጋጀት ላይ የነበረችው ቻርሎቴ በነገሩ ልቧ መሰበሩን ገልጻለች፡፡

*******

ሁለት የአምስት ዓመት ሕፃናት አጥር ሰርስረው ከማቆያ

አመለጡ

በሩሲያ ሁለት የአምስት ዓመት ወንዶች ከነበሩበት ሕፃናት ማቆያ ቅጥር መውጣት የሚያስችላቸውን መንገድ በስርሰራ በማበጀት አምልጠው በመጨረሻ መያዛቸው የተዘገበው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ ማግኒቶጎርስፍ በሚሰኘው ከተማ ከሚገኘው መዋለ ሕፃናት ያመለጡት እነዚህ ሕፃናት አጥር ሰርስሮ ማምለጡን ለቀናት ሳያቅዱበት እንዳልቀሩ ተጠቅሷል፡፡

በከሰዓት ክፍለ ጊዜ ከመዋለ ሕፃናቱ ያመለጡት ሕፃናቱ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት በመጓዝ በመጨረሻ ጃጓር መኪና ከሚሸጥበት መደብር መድረሳቸውን ሞስኮ ታይምስ ዘግቧል፡፡ በመደብሩ ላገኟት ሠራተኛ መኪና መግዛት እንደሚፈልጉ ነገር ግን በቂ ገንዘብ እንደሌላቸው ገልጸውላታል፡፡

ዘገባው እንደሚያመለክተው ሕፃናቱ በመጨረሻ በአቅራቢያ ወደሚገኘ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲሸኙ ሕፃናቱ ባመለጡበት ክፍለ ጊዜ የነበረው ተረኛ መምህር መባረሩም ተረጋግጧል፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች