የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት የአሁኗ ሩሲያ ከሶሪያ ጋር የኢኮኖሚና የፖለቲካ ትስስሯን የጀመረችው፣ ሶሪያ ከፈረንሣይ ቅኝ ግዛትነት ነፃ ልትወጣ የወራት ጊዜያት ሲቀሩ ነበር፡፡ በ1938 ዓ.ም. ጥር ላይ የተደረሰው ስምምነትም ሩሲያ ለሶሪያ የፖለቲካ ድጋፍ፣ እንዲሁም ሶሪያ ለምትመሠርተው የመከላከያ ኃይል ወታደራዊ ዕርዳታ ማድረግንም ያካትታል፡፡ በ1943 ዓ.ም. በአገሮቹ መካከል የተፈረመው እርስ በርስ ያለመጠቃቃት (Non-aggression Pact) ስምምነት ደግሞ የአገሮቹን ግንኙነት ይበልጥ ያጠናከረ ነው፡፡
ከ50 ዓመታት በላይ የዘለቀው የሁለቱ አገሮች የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የመከላከያ ኃይል ትብብር ይበልጡኑ ጎልቶ የታየው በሶሪያ የፕሬዚዳንቱ በሽር አል አሳድ መንግሥት ይውረድልን አብዮት ከተቀሰቀሰ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን የበሽር አል አሳድ መንግሥት እንዲወድቅ በሶሪያ ሸማቂዎችን ሲረዱ፣ ሩሲያ ደግሞ ከበሽር ጎን ቆማለች፡፡
ኢራን በበኩሏ የሶሪያን መንግሥት የምትደግፍ ሲሆን፣ እንደ ሩሲያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላት ቻይና ግን ዝምታን መርጣለች፡፡
በሶሪያ ከአራት ዓመታት በፊት የተቀሰቀሰው አብዮት እንደ ሌሎቹ የዓረብ አገሮች በቶሎ በቁጥጥር ሥር የዋለ ወይም መንግሥት ያስቀየረ አይደለም፡፡ ይልቁንም ጦርነቱ ከፍቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትና አዋቂዎች የጦርነቱ ሰለባ እንዲሆኑ፣ ከአራት ሚሊዮን በላይ ደግሞ እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡
በአገሪቱ የከተሙት የእስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ተዋጊዎች በአገሪቱ የሚገኙ ቅርሶችን እያወደሙ ይገኛሉ፡፡ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡ ኢኮኖሚው ተንኮታኩቷል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የበሽር አል አሳድን መንግሥት መገርሰስም ሆነ ሸማቂዎችን መደምሰስ አልተቻለም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሩሲያና አሜሪካ በሶሪያ ጉዳይ ከአንድ አቋም ላይ አለመድረሳቸው ነው፡፡ አሜሪካ ሸማቂዎችን ስታስታጥቅ፣ ሩሲያ ደግሞ መንግሥትን ትረዳለች፡፡
በሶሪያ አብዮት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሩሲያ የሶሪያን መንግሥት በወታደራዊ ቁሳቁስ ለመርዳት ቁርጠኛ ውሳኔ ያሳየችው ደግሞ በያዝነው ሳምንት ነው፡፡ ሜል ኦንላይን እንደዘገበው፣ ሩሲያ የአል አሳድ ጠንካራ ይዞታ በሆነችው ላቲካ ሰባት የሚደርሱ ቲ – 90 ታንኮችን አስገብታለች፡፡ የአል አሳድን መንግሥት የምትቃወመው አሜሪካ ከታንኮች በተጨማሪ ከባድ የጦር መሣሪያዎች ወደ ሶሪያ መግባታቸውን አሳውቃለች፡፡ አሜሪካም ሆነች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን፣ ሩሲያ ለሶሪያ መሣሪያ እየሰጠች መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ፣ ሩሲያ የሶሪያ መንግሥትን በመሣሪያ እንደምትረዳ በይፋ በገለጹበት ማግሥት ነው፡፡
በሶሪያ ግዛት የሩሲያ ታንኮችና ብዛት ያላቸው ከባድ የጦር መሣሪያዎች መግባታቸው፣ አሜሪካ ሩሲያን በሶሪያ ወታደራዊ የጦር ሠፈር ልትመሠረት ነው ወደሚለው ድምዳሜ አድርሷታል፡፡ የፔንታጎን ቃል አቀባይ ካፒቴን ጄፍ ዴቪድ፣ “የመሣሪያዎችና የሰዎች እንቅስቃሴ እያየን ነው፡፡ በደቡብ ላቲካ አካባቢ ሩሲያ የአየር ኃይል ጦር ሠፈር እየመሠረተች መሆኑን ያመላክታል፤” ማለታቸውን ዘገባው ያስረዳል፡፡
ሩሲያ ከዚህ አስቀድሞ 200 የሚጠጉ የባህር ኃይል አባላት ወደ ሶሪያ ልካለች ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላቭሮቭ፣ “ሶሪያን ለመርዳት ዓለም አቀፍ ሕጎችን ተከትለናል፤” ሲሉ ከየአቅጣጫው እየተሰነዘረባቸው ላለው አስተያየት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አሜሪካና የባህረ ሰላጤው አገሮች ሩሲያ ትልቅ የሚባል ወታደራዊ ኃይል በሶሪያ እያስገባች ነው ማለታቸውን በተመለከተም፣ “ሩሲያ ሶሪያን በጦር መሣሪያ መርዳቷን ትቀጥላለች፤” ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
ሩሲያ የጦር መሣሪያዎችን ሶሪያ ማስገባቷ አሜሪካ በሶሪያ ያላት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ያወሳስብባታል፡፡ ምክንያቱም አሜሪካ በሶሪያ የሚገኘውን የአይኤስ ታጣቂ ቡድን በአየር ለመምታት የምትጠቀመው የሶሪያን የአየር ክልል ነው፡፡
አሜሪካም ሆነ ሩሲያ ጠላታቸው አይኤስ እንደሆነ ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ አሜሪካ በአንድ በኩል በሶሪያና በኢራቅ መንግሥት እመሠርታለሁ የሚለውንና ማንኛውንም ዓይነት ቅርስ እያጠፋ የሚገኘውን አይኤስ ለማጥፋት በአገሪቱ የአየር ድብደባ የምታደርግ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል አል አሳድን ለመጣል የሚዋጉ ሸማቂዎችን ትረዳለች፡፡ አል አሳድን ለመጣል የሚዋጉት ደግሞ የአይኤስ ቡድን አባላትም ናቸው፡፡ ሩሲያ በበኩሏ አይኤስን ለማጥፋት፣ የበሽር አል አሳድን መንግሥት መደገፍ ግድ መሆኑን ትናገራለች፡፡ አሜሪካ ደግሞ የሩሲያ ሶሪያ መገኘት ነገሮችን ያወሳስባል ስትል ሥጋቷን ትገልጻለች፡፡
ሩሲያ የበሽር አል አሳድ መንግሥት አብዮት ከተነሳበት ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ከጎኑ አልተለየችም፡፡ የጦር መሣሪያና የባለሙያ ድጋፍ ታደርጋለች፡፡ የሶሪያ ወታደሮችን ስለ ጦር መሣሪያዎች አጠቃቀም ታሠለጥናለች፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ እንደሚሉት፣ በመስከረም ማብቂያ በኒውዮርክ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ የሚሳተፉት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የሶሪያን ጉዳይ በዩክሬን ስላለው ግጭት፣ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚና በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን አስመልክተው ንግግር ያደርጋሉ፡፡
በዓረብ አገሮች የሚታየው ቀውስና ከዚሁ ጋር ተያይዞ አውሮፓን ያጥለቀለቀው የስደተኞች ማዕበል፣ ብዛት ያላቸው አገሮች ራሳቸውን ኃያል ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ለማደናቀፍ ታስቦ የተቀነባበረ ችግር መሆኑንም አስመልክተው ፑቲን አስተያየት ይሰጣሉ ተብሏል፡፡
አሜሪካና አጋሮቿ ሰርጎ ገቦችንና አይኤስን እየተዋጋ የሚገኘውን የአል አሳድ መንግሥት ይቃወማሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካ መራሹ ጦር በኢራቅና በሶሪያ በሚገኙ የአይኤስ ቡድን አባላት ላይ የአየር ድብደባ ያካሂዳል፡፡
አሜሪካና አጋሮቿ በሶሪያ ብጥብጥ ከተጀመረበት ከአራት ዓመት ወዲህ በሶሪያ ጉዳይ ጣልቃ ቢገቡም፣ የሩሲያ ትብብር ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ነው፡፡ በሶሪያ ለሦስት ጊዜያት ያህል መፈንቅለ መንግሥት ሲደረግም ሆነ ከዚያ ቀድሞ ሩሲያና ሶሪያ የጋራ ትብብራቸው አልሻከረም፡፡
ሩሲያ በሶሪያ አብዮት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሳይሆን በፊትም ቢሆን ከሶሪያ ጎን በመቆሟ ትታወቃለች፡፡ በ1950ዎቹ እርስ በርስ ላለመጎዳዳት የተፈራረሙት ውል ደግሞ ሩሲያን ከሶሪያ እንዳትለይ ያደርጋታል፡፡ ከአብዮቱ ጀምሮም ለአል አሳድ መንግሥት የቀኝ እጅ በመሆን ቆማለች፡፡ ሆኖም የጦር መሣሪያና ወታደራዊ ኤክስፐርቶች ከመላክ ውጪ ወታደሮቿን ወደ ሶሪያ አለማስገባቷን አሳውቃለች፡፡ ነገር ግን ኮማንዶዎቿ መግባታቸው ደግሞ ይነገራል፡፡
ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና አሜሪካ ሩሲያ በላቲካ የጦር ሠፈር የመገንባት ዕቅድ አላት ያሉትንም ሩሲያ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች፡፡ ወታደራዊ ቁሳቁሶች ከማቅረብ እንደማትቆጠብ ግን አሳውቃለች፡፡
በሶሪያ የርስ በርስ ግጭት ከተቀሰቀሰበት ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ 250 ሺሕ የሚጠጉ ሶሪያውያን መሞታቸው ይነገራል፡፡ ከጦርነቱ በፊት 23 ሚሊዮን የሚጠጋው ሕዝብ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ በግማሽ ያህል ቀንሷል፡፡ ብዙዎቹም ወደ አውሮፓ እየተሰደዱ ነው፡፡ ይህም በአውሮፓ ላይ ቀውስ ፈጥሯል፡፡