እነሆ መንገድ። ከጳውሎስ ወደ ፒያሳ ልንጓዝ ነው። አላፊ አግዳሚው ወጪ ወራጁ ዝናብ ለመጠለል ታዛ እየፈለገ ይሰባሰባል። ተራ አስከባሪዎቹ ‹አንድሽም ሳትሠለፊ አትሳፈሪም› እያሉ ያስፈራሩናል። ‹‹እናንተ ሰዎች ለምን አትተውንም ግን? የት እንድረስላችሁ?›› ትላለች የመረራት መሳይ። ‹‹የት ይደረሳል ብለሽ ነው? በየደረሽበት ሁሉ መደብደብ ነው። የማንም ጉልቤ መጫዎቻ መሆን። አበቃ!›› ይላሉ አንዲት አዛውንት። ‹‹መስከረም ደግሞ ጨፈሩልኝ ብሎ ነው የሚጨፍርብን?›› ይላል ሽበት የወረረው ጎልማሳ። ‹‹ኧረ ዝም በለው ደግሞ በእኔ አሳበው በሉ ብሎ ነው እንጂ፤›› አለ አጠር ቀጠን ያለ መላጣ። ‹‹ማወራረጃ መሆኑ ነው? ታዲያ እኛ መፋረጃ እንጂ ማወራረጃ መቼ ቸገረን? ጊዜም እንደ ባለጊዜው ማባበል ከጀመረማ ምን ቀረን ልጄ?›› ያሽሟጥጣሉ አዛውንቷ። ‹‹ኑና ሠልፍ ያዙ አሁን። አባርቷል…›› ይላል ጥርሰ ወላቃው ተራ አስከባሪ። ‹‹ድሮስ? ሰማይማ ሚዛን ያውቃል። አላባራ ያለን የምድሩ ነው እንጂ፤›› ቆንጂት የአዛውቷን የአነጋገር ዘይቤ እየቀዳች ታሸሙራለች።
‹‹የቤት ኪራይ መክፈል ሳትችይ ‹ቻፒስቲክ› እየገዛሽ አሁን አንቺም ከእሳቸው እኩል ልትፖተልኪ ያምርሻል? ወገኛ…›› አላት ወላቃው። ‹ታውቀኛለህ?- ምን የሚታወቅ አለሽ?› ንትርክ ሲጀምሩ የተጠለልንበት ካፌ ባለቤት እየተንጎማለለ ገፈታትሮን በመሀላችን አለፈ። ‹‹እስካሁን ለቆማችሁበት ሁለት ሁለት ብር ዱብ ዱብ በሉ። ክፍያው ‹ቫት› አያካትትም፤›› ብሎን አረፈው። ይኼኔ በአሹቅና በሽንብራ ተቀልቦ ለአቅመ እንጀራ የደረሰውን አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ከንፈር ያስመጠጠ ደንዳና ሰውነት ያለው ጠጋ ብሎ፣ ‹‹እውነት አንተ ዘጠኝ ሱሪ ታጥቅሃል ገና ቀኑን ሙሉ ቆሜ እውላለሁ የምታደርገውን አያለሁ፤›› ሲለው ያ የምሩን ገንዘብ ሊቀበለን የመጣው ባለቤት ተብዬ ‹‹ . . . የሚባልበት ዘመን ሊመጣ ምን ቀረው ለማለት ፈልጌ ነው ኧረ?›› ብሎ ታጠፈ። እንግዲህ መተሳሰብና ቀናነትን ለማስመለስ ‹ቦዲ ጋርድ› ሊያስፈልገን ነው ማለት ነው? ወይ ዕዳ ከሜዳ አለ የተራራውን ያላየ!
ወዲያው አንዲት ታክሲ ከተፍ ስትል ሰው ታዛውን ለቆ መሯሯጥ ጀመረ። ታክሲዋ በራፍ ላይ ግብግቡ ጦፈ። አዛውንቷ አልቻሉም። ወጣቶቹ አላዘኑላቸውም። ‹‹ምናለበት እዚያው እንደ ዘመናችሁ እርስ በእርሳችሁ ብትጋፉ? ምን ቤት ነኝ እኔ?›› ይላሉ። ይኼኔ ጎልማሳው ቀድሞ ገብቶ ኖሮ ጎትቶ አስገብቷቸው አጠገቡ አስቀመጣቸው። ‹‹እንዲህ እየተጋፋችሁ ነው ገፉን ብላችሁ የምታለቃቅሱት?›› አዛውንቷ ጭራሽ ገብተው ሲቀመጡ ብሶባቸዋል። ‹‹እማማ ይኼ እኮ የታክሲ ወጉ ነው፤›› አላቸው አንዱ ከጋቢና አንገቱን አጣሞ። ‹‹ለካስ ወግም ታውቁ ኖሯል? መልስማ ማን ብሏችሁ?›› እያሉ የነካካቸውን ጭቃ ከእግራቸው ላይ መጠራረግ ጀመሩ። ይኼኔ አንድ በሃታዊ መሳይ ከየት መጣ ሳይባል ተከሰተ። ‹‹እያንዳንድሽ ብትሰሚ ስሚ! የስምንተኛው ሺሕ አንደኛው አጋንንት የተሳፈረው መኪና ላይ ነው። እግዜር እግር ሰጣችሁ። እናንተ ግን አራት እግር አማራችሁ። እሱ ጤናችሁን በዕርምጃችሁ ልክ መተረው። እናንተ ግን የባቡር ናፍቆት ገደለን እያላችሁ አላስቆም አላስቀምጠው አላችሁ። ለአንድ የአጋንንት ሰረገላ ላይ ለመውጣት ሦስት አራት ሰዓት ትሠለፋላችሁ። ወዬውላችሁ፤›› ብሎ አካባቢውን አደበላለቀው።
‹‹ደግሞ ምን ሊለን ነው? ክርስቶስ በታንኳ አልተሳፈረም እንዴ?›› ትላለች መጨረሻ ወንበር አንገቷ ላይ ጨርቅ የጠመጠመች መልከ መልካም። ‹‹የሕዝብ ሀብትና ንብረት ላይ በማናለብኝነት ተሰቅለው የሚፋንኑትን እንደመናገር፣ በሰው አናት ላይ የሚሳፈሩትን እንደመገሰጽ ታክሲ አትሳፈሩ ብሎ የትዕቢት ጠበቃ መሆን አለ?›› ይላል አጠገቧ የተሰየመ ወጣት ገርሞት። ‹‹እሱ ምን ያድርግ የጫማ ብትል የቤት ምን ወጪ አለበት? እንኳን ተጉዘንበት ቆማችሁብኝ ብሎ ሶላችን ካለቀ እሱ እንደሚለው በእግር ብናቀጥነው ምናችን ይተርፋል?›› ትላለች ሦስተኛው ረድፍ ላይ። ደግሞ ብለን ብለን በመኪና አደጋ የምናልቀው አንሶ በእግር እየኳተትን እንለቅ? የዛሬው ደግሞ ሌላ ነው!
ጉዟችን ከተጀመረ ቆያይቷል። ‹‹እስኪ ቀስ እያልክ ንዳ ሾፌር። ይኼ መንገድ እኮ ምሱ በዝቷል፤›› ይላሉ አዛውንቷ ከጀርባው ስለተቀመጡ አሥር ጊዜ ወደ ጆሮው እያሰገጉ። ‹‹አይዞዎት እማማ፡፡ 24 ዓመት ታክሲ የሾፈርኩ ሰው ነኝ። አንድ ቀን ተጋጭቼ አላውቅም፤›› አላቸው። ሾፌራችን ማረጋጋቱ ነበር። ‹‹እስኪ ማል?›› አዛውንቷ ስሜታቸው ግራ ያጋባል። የሚወደውን ታቦት ጠርቶ ማለ። ‹‹እንዲያው ምንም ተጫጭረህ ተነካክተህ አታውቅም?›› ጎልማሳው ነው የሚጠይቀው። ‹‹በጭራሽ!›› ሾፌሩ ባናየውም ደረቱ እያበጠ ነው። ‹‹24 ዓመት ነው ያልከኝ?›› አዛውንቷ ጫን ብለው ይጠይቁታል። ሾፌሩ አስረግጦ ይመልሳል። ‹‹ማነህ ወያላ አውርደኝ! አውርደኝ!›› እያሉ ታክሲዋ ገና ፍጥነቷ ሳይቀዘቅዝ ከወንበራቸው ተነሱ። ‹‹የት ሊሄዱ ነው?›› ጎልማሳው ራሱ ግራ ተጋባ። ‹‹አትሰማውም እንዴ የሚለውን? እንኳን ሰው ተሁኖ ድንጋይ ከድንጋይ ጋር በሚጋጭበት ዓለም ተጫጭሬም አላውቅ ሲል አትሰማውም?›› ረገብ እንደ ማለት ብለው መልሰው ተቀመጡ።
‹‹ተው አይፍረዱበት! እንከን አልባ ነኝ፣ ይገጩኛል እንጂ ገጭቼ አላውቅም፣ ወዘተ አስተሳሰብ የኖረበት የ24 ዓመት ውጤት ናት። ምን ያድርግ እማማ?›› ጎልማሳው ማረጋጋቱን ተያያዘው። ‹‹ምነው ኢሕአዴግ ይኼው በአደባባይ ችግሮቹን አምኖ በፀጋ ተቀብሎ እያየን? እኛ ሌላ ምን ቸገረን? ይኼው ራስን ዘወር ብሎ አይቶ ችግርን አለማመን፣ ሒስን ያለመቀበል ፅኑ አባዜ አይደለም እንዴ? ኧረ ለመሆኑ ሰውን እንደ መልዓክ አግዝፎ የማየት ችግራችን እኛም እንደ መልዓክ ለመቆጠር በአደባባይ መወጣጠራችን መስሎኝ አዙሮ እየደፋ ከመንገድ ሲያስቀረን የኖረው?›› ሲሉ ተሳፋሪዎች ዕይታቸው ተመችቶት ጭብጨባ ቃጣቸው። አጨብጭቦላቸው ያጨበጨቡበት ትዝ አሉት መሰል ግን ሁሉም መዳፉን እያፋተገ ተቀመጠ። የምንተፋፈገው ሳይበቃ አፋትገን የምናመነጨው ሙቀት ስንት ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይሆን? የስንቱን ግዝትና መሀላ አምነን አጨብጭበን የቀረንስ ምን ያህል እንሆን? መጥኔ አሉ የሰለቻቸው፡፡
ወያላው ሒሳብ ይሰበስባል። ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመችው ወይዘሮ በሞባይል ስልኳ ታወራለች። ‹‹በይ እየመጣሁ ነው ቡናውን አቀራርበሽ ጠብቂኝ። በዛችኛዋ በትንሿ ድስት አወቅሻት? ገንፈልፈል አድርገሽ ሽሮ ሥሪ። ይኼው በር ላይ ነኝ። ወየውልሽ ቴሌቪዥን ስትጎጉሪ ባገኝሽ፤›› ትላለች። ‹‹ይገርማል እኮ ዘንድሮ የምንቀጥራቸው የቤት ሠራተኞች ይሁኑ ዲሽ ተመልካቾች ግራ ያጋባል፤›› አላት ከጎኗ የተቀመጠ ወጣት። ‹‹ተወኝ እስኪ! የእኔይቱ ደግሞ ለየት ያለች ናት። ማየቱንስ ትይ። ብቻ አንድ ነገር ሳወራ ከአፌ ነጥቃ እከሌ እኮ እንዲህ የሆነው እንዲያ ተብሎ ነው። መቼ ዕለት ‹ኢንተርቪው› ሲደረግ ሰምቼዋለሁ ትልልሃለች። ይኼው በእሷ የተነሳ እንግዳ ቤቴ መጥራት እስከማፈር ደርሻለሁ። ሰሞኑን ደግሞ ሁለት ቀን ሳይበላ ዶሮው ማለቅ። ‹አለቀ?› እላታለሁ ‹እህሳ የዘንድሮ ዶሮ እንደ በፊቶቹ ሞኝ አይደሉም። ዕድሜ ለዘመነ ኢንተርኔት ነቅተዋል። መታረጃቸውን ስለሚያውቁት ኪሎ ቀንሰው ሆኗል ገበያ የሚወጡት› አትለኝ መሰለህ?›› ስትል ተሳፋሪዎች ያሽካካሉ።
ጨዋታው እንደ ጣመን ገብቷት ድምጿን ከፍ አደረገች። ‹‹ቆይ ልነግራችሁ እኮ ነው። እኔ ደግሞ ግራ ገብቶኝ መቼም የዛሬ ዘመን ሥልጣኔ አይታመን ብዬ ዶሮዎች ኢንተርኔት መጠቀም ጀምረዋል አልጀመሩም ብዬ አጣራለሁ ስል ቴሌ ካርዴን አጣራልኛ። ወይ ለኩላሊት ሕሙማን መርጃ አላዋጣሁት ወይ ለህዳሴው ግድብ አልሰጠሁት። ለራሱ ገንዘቡ ጥንቡን ጥሏል። እንኳን ስለዶሮ ንቃተ ህሊና ልናጠናበት ለራሳችንም አልሆነ።…›› እያለች ስታስቀን፣ ‹‹አርዝመው አስረውን የፈቱን የመሰለንማ እኛን ነው…›› እያለ አጠገቤ የተቀመጠ ባለ ባርኔጣ ይንሿከክብኛል። የቱን አንስተን የቱን እንደምጥል ጨንቆናል ልበል?
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹ለቅዱስ ዮሐንስ ይጠመቃል ጠላ፣ ድፍድፉ ለጠላት እስኩታው ለመላ› አሉ አበው፤›› መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ተሳፋሪዎች አንደኛው ነገር ጎነጎነ። ወያላችን ሳንቲም እየመለሰ ነው። ‹‹ዛሬስ እንዴት ወግ ደርሶሃል እባክህ? ለመሆኑ ይኼኛው ሳንቲማችንም እየተመለሰልን ያለው በሱዳን በኩል ነው እንዴ?›› አለች ወይዘሮዋ። ‹‹ትንሽ ከጠበቅን ገና ኢሳያስ አፈወርቂ ራሳቸው ይመጣሉ፤›› ወዲያ ያለው ይናገራል። ‹‹እሰይ! ታዲያ አደራውን እንደ አጀማመሩ ይኼ ዓመት የሩቅ ሩቁን ብቻ ሳይሆን የቅርቡንም ትጥቅ ያስፈታልና…›› አዛውንቷ ጨመሩበት። ‹‹ደግሞ የምን የቅርብ ጠላት አመጡብን? የቅርቡን ታቅፈን ኖሯል በሩቆቹ የምንሸልለው?›› ሲላቸው ጎልማሳው፣ ‹‹እንግዲያስ! ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ በአባልነት ብቻ ያለ ሙያ ብቃት ያለችሎታቸው በየቦታው እየተሰገሰጉ ጤና የሚነሱን ካድሬዎች ብዛት፣ በስብሰባ ብዛት የሚቃጠለው ዕድሜ፣ ኧረ ስንቱን የቅርብ ጠላት አንስቼ እጨርሰዋለሁ?›› ሲሉ ታክሲያችን መታጠፊያዋ ላይ ደርሳለች። ወያላው መጨረሻ ብሎን ወርደን ስንበታተን ከጎኔ ተቀምጦ የነበረው ተሳፋሪ፣ ‹‹እውነታቸውን እኮ ነው። ዘመነ ዮሐንስ በነካ እጁ የቅርብ የቅርቡንም ትጥቅ ቢያስፈታልን ምን አለበት?›› ብሎኝ ወደፊት ገሰገሰ። የጨው ክምር በሚናድበት ጊዜ ላይ ሆነን ስንቱን ስንሰማ፣ ‹ትጥቅ አስፈቺ ዘመን!› ሲባል ግርም ይለን ይጀምራል፡፡ ወይ አዲሱ ዓመት? መልካም ጉዞ!