Sunday, October 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው እንደገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት]

  • እንኳን አደረስዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለምኑ?
  • ለአዲስ ዓመት ነዋ፡፡
  • አንተ ሥራ ቀይረሃል እንዴ?
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • ከበዓሉ በፊት እንኳን አደረሰህ አልከኝ፡፡
  • ለዋዜማው ነዋ፡፡
  • የበዓል ቀን ቴክስት ላክልኝ፡፡
  • ምን አጠፋሁ ታዲያ?
  • በዓሉም አልፎ እንኳን አደረሰህ ትለኛለህ?
  • የመልካም ምኞት መግለጫ ነዋ፡፡
  • ምኞት ምን ያደርጋል? ዋናው ተግባር ነው፡፡
  • ከእናንተ ተምሬ ነዋ፡፡
  • ምኑን?
  • ይኼን ባህሪ ነዋ፡፡
  • እንዴት?
  • እናንተ ሁሌም ትመኛላችሁ እንጂ ተግባር ላይ የት አላችሁበት?
  • አልገባኝም እባክህ?
  • ያው መልካም አስተዳደር ይሰፍናል፣ ሙስና ይቀረፋል ምናምን እያላችሁ ትመኛላችሁ እንጂ መቼ ትተገብሩታላችሁ?
  • እ…
  • ለዚያ ነው ከእናንተ ተምሬ ነው ያልኩት፡፡
  • ለመሆኑ ሪፖርቶቹ የት አሉ?
  • የምን ሪፖርት?
  • አዲስ ሥራ የምንጀምርበት ዘመን መሰለኝ፡፡
  • እ… እየተሠራ ነው፡፡
  • ይህን የቤት ሥራ ከሰጠሁህ እኮ ወር ሆኖታል፡፡
  • አዎ ግን ችግር አለ፡፡
  • የምን ችግር?
  • ሠራተኛው ይከፈለኝ እያለ ነው፡፡
  • ደመወዝ መከፈል ቆሟል እንዴ?
  • አይ ደመወዝ አይደለም፡፡
  • ታዲያ ምንድነው?
  • የውሎ አበል፡፡
  • የምን የውሎ አበል?
  • ክቡር ሚኒስትር የአንዳንድ ዲፓርትመንት ሠራተኞች የውሎ አበል ይከፈላቸዋል፡፡
  • በምን ስሌት?
  • በርካታ እንግዶችን ስለሚያስተናግዱ ተብሎ፡፡
  • ደመወዝ ይከፈላቸዋል አይደል እንዴ?
  • እንደውም በወር የሚያገኙት የውሎ አበል ክፍያ ከደመወዛቸው ጋር ሲነፃፀር የትዬለሌ ነው፡፡
  • ጭራሽ?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ተሻለ?
  • የሚሻለውማ ለሌሎቹም መክፈል ነው፡፡
  • ምንድነው የሚከፈለው?
  • የውሎ አበሉ ነዋ፡፡
  • እሱ ነው የአንተ ምክር?
  • ከልጅ ልጅ ቢቆዩ ዓመትም አይቆዩ አይደል የሚባለው፡፡
  • ዓመት አትቆይም እያልከኝ ነው?
  • ያው ሹም ሽር ደርሷል ብዬ ነው፡፡
  • ቢደርስስ?
  • ወጥ የሆነ አሠራር ያስፈልጋላ፡፡
  • አሁን ለሌላው ሠራተኛ አስበህ ነው ወይስ ለራስህ አስበህ ነው?
  • እኔስ ብሆን ልጅዎት አይደለሁም?
  • ስለዚህ የሪፖርቱ አለመቅረብ ዋናው ምክንያት ይኼ ነው እያልከኝ ነው?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • በል በአፋጣኝ ሠራተኛውን ስብሰባ ጥራልኝ፡፡

 

[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸውን አስጠሯት] 

  • ሪፖርቱን ምን አደረስሽው?
  • የቱን ሪፖርት?
  • ባለፈው ሳምንት ያዘዝኩሽን?
  • እየሠራሁት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እስካሁን አላለቀም?
  • የሚመለከታቸው ሠራተኞች በሚገባ ስለማይተባበሩኝ ነዋ፡፡
  • ለምን?
  • የውሎ አበል ጉዳዩ ነዋ፡፡
  • ወይ ይኼ የውሎ አበል ነገር፤ ደመወዝ ይከፈላችኋል አይደል እንዴ?
  • ማን በደመወዙ ይኖራል?
  • ታዲያ በምንድነው የሚኖረው?
  • በደመ – አበሉ ነዋ፡፡
  • ማን ነው የፈቀደላቸው ለመሆኑ?
  • የክፍሉ ኃላፊዎች ናቸዋ፡፡
  • እኔ ሳላውቅ?
  • ክቡር ሚኒስትር የኑሮ ውድነቱ እኮ አይቻልም፡፡
  • ስለዚህ መፍትሔው አበል ነው?
  • ሌላ መፍትሔም አለ፡፡
  • ምንድነው እሱ?
  • የኑሮ ውድነቱን መቆጣጠር፡፡
  • እኔ እናንተን ራሱ መቆጣጠር አቅቶኛል፡፡
  • መጀመሪያ ራስዎትን ይቆጣጠሩ፡፡
  • ምን አልሽ?
  • አይናደዱ ማለቴ ነው፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ጓደኛ ሚኒስትር ደወሉ]

  • በዓል እንዴት አለፈ ክቡር ሚኒስትር?
  • ድግሱ እንዴት አለፈ ማለትህ ነው?
  • ለመሆኑ እየተዘጋጁ ነው?
  • ለምኑ?
  • ለደስታ ወይም ለሐዘን፡፡
  • የምን ደስታና ሐዘን ነው?
  • ወቅቱን ረሱት እንዴ?
  • እኮ ምንድነው?
  • ያው በዘመኑ መጀመሪያ ላይ በዓላት አሉ ከዚያም የእኛ ዋናው በዓል አለ፡፡
  • የትኛው በዓል?
  • ሹም ሽሩ ነዋ፡፡
  • እ…
  • ለማንኛውም አንድ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
  • የምን ኮሚቴ?
  • ተሿሚዎችን የሚመለምል፡፡
  • እኔ የሌለሁበት?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እ…
  • አሁን የደወልኩት ሰው እንዲጠቁሙኝ ነው፡፡
  • የምን ሰው?
  • ሊሾም ይገባዋል የሚሉትን ነዋ፡፡
  • ከየት?
  • ከእርስዎ መሥሪያ ቤት፡፡
  • አንድ ሰው ነው ልጠቁምህ የምችለው፡፡
  • ማን ነው እሱ?
  • እኔው ነኝ፡፡
  • የእርስዎ አማካሪ እንዴት ነው?
  • ስለእሱ ምን እንደማስብ ታውቃለህ?
  • ምንድነው የሚያስቡት?
  • አህያ ታውቃለህ አህያ ነው፡፡
  • አህያ የሚያማክረው እኮ አህያን ብቻ ነው፡፡
  • እየሰደብከኝ ነው?
  • ራስዎትን እየሰደቡ ነው እንጂ፡፡
  • ለመሆኑ ምንድነው መሥፈርቱ?
  • ብሔርንና ጾታን ያማከለ መሆን አለበት፡፡
  • ሌላስ?
  • የትምህርትና የሥራ ብቃቱ እንደተረጋገጠ ሆኖ ማለት ነው፡፡
  • በቃ?
  • ከዚህ በላይ ምን እንፈልጋለን?
  • የፓርቲ ታማኝነትስ?
  • ክቡር ሚኒስትር ከፓርቲ በፊት ያለው እኮ አገር ነው፡፡
  • እ…
  • ፖለቲካና ፓርቲ የሚኖረው ቅድሚያ አገር ስትኖር ነው፡፡
  • እሱማ ልክ ነው፡፡
  • ስለዚህ ብቃት ያላቸው ሰዎች አገሪቷን ማገልገል ከፈለጉ ቦታ ሊያገኙ ይገባል፡፡
  • ለፓርቲው ታማኝ ባይሆኑም?
  • ለአገርና ለሕዝብ ታማኝ ከሆኑ ይበቃል፡፡
  • እና እኛን አሽቀንጥራችሁ ልትጥሉን ነው ማለት ነው?
  • እሱ ወደፊት የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡
  • ይህ ጉዳይ እኮ እንቅልፍ የሚነሳኝ ነው፡፡
  • ለእዚህ ነው እኮ ዕረፍት የሚያስፈልግዎት፡፡
  • የምን ዕረፍት?
  • መተኛት አለብዎት፤ በቂ ዕረፍት ማግኘት አለብዎት፡፡
  • የዓመት ዕረፍት ልውሰድ ታዲያ?
  • ሌላ ዕረፍት ቢወስዱ አይሻልም?
  • ሌላ ምን ዕረፍት?
  • ከሥልጣን ዕረፍት ቢወስዱስ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤት እየሄዱ ነው] 

  • ክቡር ሚኒስትር በጣም ነው የገረመኝ፡፡
  • ምኑ ነው የገረመህ?
  • በኤርትራ ያሉት ተቃዋሚዎች ጉዳይ፡፡
  • እኮ ምኑ ገረመህ?
  • መጣላታቸው ነዋ፡፡
  • መቼ ተስማምተው ያውቃሉ?
  • ደግሞ ከመንግሥት ጋር ለዓመት ያህል ይገናኙ ነበር፡፡
  • መረጃ ያቀብሉን ነበር፡፡
  • መንግሥት ግን የሚገርም የስለላ አቅም ነው ያለው፡፡
  • ይህ እኮ የተካንበት ነው፡፡
  • ሌላ ግን ያሳዘነኝ ነገር አለ፡፡
  • ምንድነው ያሳዘነህ?
  • ከኤርትራ ተገንጥለው የመጡት ተቃዋሚዎች በአንዴ ጀግና ሆኑ፡፡
  • ታዲያ ምኑ ነው የሚያሳዝንህ?
  • እነሱ ጀግና መሆናቸው ነዋ፡፡
  • ምን ችግር አለው?
  • ስንቱ እዚህ ለአገሩ እየለፋ ዞር ብሎ የሚያየው የለም፣ እነሱ አገር ሲወጉ ቆይተው ሲመለሱ በአንዴ ጀግና ሆኑ፡፡
  • ከጥፋታቸው ስለተመለሱ ነው ጀግና የሆኑት፡፡
  • አጥፍተው የማያውቁ ጀግና አይባሉም እንዴ?
  • መጽሐፍ ቅዱስ የምታነብ መስሎኝ?
  • እንዴት?
  • ጌታ እኮ ዘጠና ዘጠኙ በጐቹን ትቶ የጠፋበትን አንድ በግ ሊፈልግ እንደሄደ እንዳትረሳ፡፡
  • ስለዚህ?
  • እኛም 99 ሚሊዮኑን ሕዝብ ትተን የጠፉትን ልንፈልግ ሄድና፡፡
  • ስለዚህ የጠፋው ልጅ ታሪክ ሊደገም ነዋ፡፡
  • የትኛው?
  • ጠፍቶ የነበረው ልጅ ሲገኝ እኮ ታላቅ ድግስ ተደርጎለታል፡፡
  • እናስ?
  • ስለዚህ እኛ ተስፋ የለንማ?
  • ለምኑ?
  • ለ40/60 ነዋ፡፡
  • የምን 40/60 አመጣህ?
  • ያው የጠፉት በጐች ስለተመለሱ ለእነሱ ማበረታቻ ይሰጣቸዋል ብዬ ነዋ፡፡
  • ጥሩ ሐሳብ አመጣህልኝ፡፡
  • እና እኔ ጀግና ለመባል ምን ላድርግ?
  • ጀግንነት የሚጠይቀውን ማድረግ ነዋ፡፡
  • ኤርትራ ደርሶ መምጣት ነው?
  • ሞክረው እስቲ?
  • ባለፈው እንዲሁ ስታስገርሙኝ ነበር፡፡
  • በምኑ?
  • ለዳያስፖራው እንደዚያ ስታሸረግዱ፡፡
  • እንዴት?
  • አገር ውስጥ ያሉ ጀግኖች ይወደሱ፡፡
  • እነሱም ይወሰዳሉ፡፡
  • ለመሆኑ ክቡር ሚኒስትር…
  • ለመሆኑ ምን?
  • ኤርትራ የቀሩት በአሥር ሺሕ የሚቆጠሩ ናቸው ይባላል፡፡
  • ይህ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ነው፡፡
  • እንዴት?
  • የቀሩት ጥቂቶች ናቸው፡፡
  • ማናቸው የቀሩት?
  • በሽተኞች፣ አቅመ ደካሞችና የኪነት አባላት ናቸው፡፡
  • ስለዚህ ከኪነት አባላቱ እንጠብቃ፡፡
  • ምን?
  • ነጠላ ዜማ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ለሁለት ሳምንት ያክል የፓርቲ ስብሰባ ላይ ቆይተው አመሻሹ ላይ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ባለቤታቸው በአግራሞት ተቀብለው ስለቆይታቸው ይጠይቋቸው ጀመር]

እኔ እምልክ...? ውይ... ውይ... በመጀመሪያ እንኳን በሰላም መጣህ፡፡ እሺ ...ምን ልትጠይቂኝ ነበር? ይህን ያህል ጊዜ የቆያችሁት ለስብሰባ ነው? ስብሰባ ብቻ አይደለም። ከስብሰባ ውጪ ምን ነበር? በተለያዩ መሪ ሐሳቦች የተዘጋጁ ሥልጠናዎችን...

[ክቡር ሚኒስትሩ ለሁለት ቀናት የተካሄደውን የፓርቲያቸውን የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ አጠናቀው ወደ ቢሯቸው ሲመለሱ ቢሯቸው ውስጥ አማካሪያቸው አንድ ጽሑፍ በተመስጦ እያነበበ አገኙት]

ምንድነው እንደዚህ መስጦ የያዘህ ጉዳይ? መጡ እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያወጣውን መግለጫ እያነበብኩ ነው፡፡ ግን እኮ ፊትህ ላይ የመገረም ስሜት ይነበባል፡፡ አዎ፣ መግለጫው ላይ...

[ክቡር ሚኒስትሩ እየጠራ ያለውን ሞባይል ስልካቸውን ተመለከቱ፣ የህዳሴ ግድቡ ተደራዳሪ መሆናቸውን ሲያውቁ ስልኩን አነሱት]

ሃሎ... ጤና ይስልጥኝ ክቡር ሚኒስትር? ጤና ይስልጥልኝ ክቡር ተደራዳሪ... የጥረትዎን ፍሬ በማየትዎ እንኳን ደስ አለዎት፡፡ እንኳን አብሮ ደስ አለን፣ ምን ልታዘዝ ታዲያ? የውኃ ሙሌቱንና አጠቃላይ የግድቡን የግንባታ ሁኔታ...