Saturday, June 10, 2023

ከኤርትራ ኢትዮጵያ የገባው ትሕዴን ግዳጅ ምን ነበር?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትሕዴን) ወይም በትግርኛ ምህፃረ ቃሉ ዴምሒት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ትጥቅ ትግል ከከፈቱ አማፂያን ትልቁ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ መቀመጫውን በኤርትራ ለ14 ዓመታት ያደረገው ይኼው ቡድን አባላት መካከል በአዲስ ዓመት ዋዜማ ጳጉሜን 6 ቀን 2007 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ ድንበር አካባቢ ከሻዕቢያ ጦር ጋር ውጊያ ገጥመው፣ ወደ ሱዳን ለመግባት መገደዳቸውም በስፋት ተዘግቧል፡፡

ቁጥራቸው አንድ ሺሕ አካባቢ ይደርሳል የተባሉት ወታደሮች (እርግጥ ከሱዳን የተገኙ መረጃዎች ቁጥራቸውን 683 ያደርጉታል) በቡድኑ መሪ በአቶ ሞላ አስገዶም እየተመሩ በሁመራ በኩል ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ከመካከላቸው አንድ ወታደር ይህንን ሚስጥራዊ ጉዞ ለሻዕቢያ በማሳወቁ ድንበር አካባቢ ግጭቱ ሊፈጠር እንደቻለ፣ ከብሔራዊ የመረጃና የደኅንነት አገልግሎትና ከፌዴራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል የተሰጠው መግለጫ ያመለክታል፡፡

መግለጫው፣ ‹‹የኤርትራ መንግሥት መረጃው ከደረሰው በኋላ በድንበር አካባቢ የነበረ ኃይሉን በፍጥነት ወደ ኦምሃጀር በማንቀሳቀስ መንገድ ዘግቶ ለማቆም ሙከራ ያደረገ ቢሆንም፣ በሞላ አስገዶም የሚመራው ኃይል ኦሞሃጀርና ቀጥሎም ሱቅ አልከቲር በሚባል የድንበር ኬላ ላይ የጠበቀውን የኤርትራ መንግሥት ሠራዊት ሙሉ በሙሉ በመደምሰስና በጠላት እጅ ሊወድቅ ይችላል ብሎ የገመተውን ንብረትና ተሽከርካሪ በማቃጠል ወደ ሱዳን ሀምዳይት ተሻግሯል፤›› ሲልም ያትታል፡፡

በሁለት የተለያዩ ግንባሮች በተደረገው ውጊያ ከኤርትራ መንግሥት በኩል በርካታ ወታደሮች መደምሰሳቸውን የጠቆመው መግለጫው፣ በሞላ አስገዶም ከሚመራው ኃይልም ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ታጣቂዎች የመሞትና የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል፡፡ ነገር ግን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሰባት ታጣቂዎች በውጊያው መሞታቸውን ዘግበዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሞላ አስገዶምና ከሌሎች ታጣቂዎች ጋር ለአንድ ዓመት ያህል የቆየ ሚስጥራዊ የሆነ የግንኙነት ሥርዓት በመመሥረት በጋራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውቋል፡፡ በመጨረሻም ግዳጃቸውን በሚፈለገው መንገድ አጠናቅቀው ከኤርትራ እንዲወጡ የተደረገው መንግሥት በወሰነው ጊዜ እንደሆነም ገልጿል፡፡

የእነ ሞላ አስገዶም ግዳጅ ምን ነበር?

ከመንግሥት መግለጫ ለመረዳት እንደሚቻለው፣ በኤርትራ መንግሥት አማካይነት የተደራጁ የጥፋት ኃይሎችን ዓላማ ለማሰናከል እነ ሞላ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡ ለአብነት ያህልም የሻዕቢያንና የግንቦት 7 የጥፋት ተልዕኮ እንዳከሸፉ ተጠቅሷል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ብረት ያነሱ ኃይሎች ኅብረት እንዲፈጥሩና እንዲጠናከሩ በኤርትራ መንግሥትና በግንቦት 7 የተዘጋጀው ኅብረት ውስጥ ትሕዴን አባል መሆኑን፣ መሪው ሞላ አስገዶም ደግሞ ምክትል ሊቀ መንበር መሆኑ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠውን ግዳጅ ለመወጣት መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረለትም ተመልክቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ‹‹አጠቃላይ ሒደቱን መንግሥት በሚፈልገው መንገድ ሲመሩት ከቆዩ በኋላ ግዳጃቸውን እጅግ አኩሪ በሆነ መንገድ ፈጽመው ኃይላቸውን እንዳለ ከነሙሉ ትጥቁ በመያዝ ወደ እናት አገራቸው ተመልሰዋል፤›› ሲል መግለጫው ያትታል፡፡

ኅብረቱ ከተመሠረተ ከጥቂት ቀናት በኋላ እነ ሞላ መልቀቃቸው ምን ያህል የታሰበበት ነው? ለምንስ ለቀቁ? ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ የተሰጠበት አይመስልም፡፡ እነ ሞላ ከኤርትራ መንግሥትና ከሌሎች አማፂያን የሚያገኙትን መረጃ ለብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት በማቀበል አስፈላጊ ጥንቃቄ እንዲደረግ ማገዛቸውም ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም በመንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀው የግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አሜሪካ ተቀምጠው አርበኞች ግንባርን ጨምሮ የተፈጸመውን ውህደት በሊቀመንበርነት መምራት የለባቸውም የሚል የጋራ አቋም እንዲይዙ በማድረግ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ሳይወዱ ተገደው ወደ አስመራ እንዲገቡ መደረጉም እንደ ስኬት ተገልጿል፡፡ የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አስመራ ለመሄድ መገደድ እንደ ስኬት የተወሰደበት ምክንያት ግን አልተገለጸም፡፡

እርግጥ ነው ውህደቱ በመከናወኑ ደስተኛ የነበሩትን የኤርትራን መንግሥትና ግንቦት 7ን ከውህደቱ በመውጣት ወሸመጣቸው እንዲቆረጥ ማድረጉ ተመልክቷል፡፡ ይህ ዶ/ር ብርሃኑ ደስታቸውን ለመግለጽ ወደ አስመራ በተጓዙ ማግስት መከናወኑ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ተጨማሪ ደስታ መፍጠሩን ማየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይኼ ‘እጅግ አኩሪ’ ግዳጅ ነውን? ነው ወይስ ዶ/ር ብርሃኑ ወደ አስመራ ሲጓዙ እንደ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የመጥለፍ ያልተሳካ ዕቅድ ነበር?

መስከረም 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ፈርስት ዶት ኮም ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የትሕዴን ሊቀመንበር አቶ ሞላ፣ ‹‹ከመንግሥት ጋር እየሠራን ስለነበር እኛ ነን ሆን ብለን ጥምረቱን የመሠረትነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ በመግለጫው ላይ ግን ጥምረቱን እንዲቀላቀሉ በኤርትራ መንግሥትና በግንቦት 7 ጥሪ እንደተደረገላቸው ተገልጿል፡፡

አቶ ሞላ አስገዶም ማን ናቸው?

አቶ ሞላ አስገዶም በተለያዩ ጊዜያት ለሚዲያ ከሰጧቸው ቃለ ምልልሶች ለመረዳት እንደሚቻለው የሕወሓት ታጋይ ነበሩ፡፡ ከድል በኋላ እስከ 1987 ዓ.ም. አዲስ አበባ ተመድበው የተለያዩ ወታደራዊ አገልግሎቶችን ሰጥተዋል፡፡ ሆኖም በ1987 ዓ.ም. ከተቀነሱት የጦር ሠራዊቱ አባላት አንዱ ሆነዋል፡፡ ይህንን ውሳኔ ‘ሰለባ ሆንኩበት’ ሲሉም ይገልጹታል፡፡ ይህን ቂም ቋጥረው የቆዩት አቶ ሞላ በ1993 ዓ.ም. ትሕዴን ሲቋቋም ከመሠረቱት 30 ሰዎች አንዱ ሆነዋል፡፡

እንደ አቶ ሞላ ገለጻ፣ ትሕዴን የተቋቋመው የሕወሓት መሪዎች የሕዝቡን ፍላጎት፣ የታገለበትንና ብዙ መስዋዕትነት የከፈለበትን ዓላማ ወደ ጎን በመተው ወደ ግል ጥቅማቸው አተኩረው ሕዝቡ ላይ ብዙ ግፍና በደል እያደረሱ በመምጣታቸው ነው፡፡ ይህን መስመር ለማስያዝና ሕወሓትን ከሥልጣኑ ማስወገድ የሚቻለው በትጥቅ ትግል ብቻ እንደሆነም በተደጋጋሚ ሲገልጹ ነበር፡፡ ሰላማዊና ፖለቲካዊ ትግል የሕወሓትን ዕድሜ ከማራዘም ባሻገር ለውጥ ያመጣል ብለው እንደማያስቡም ይገልጹ ነበር፡፡

ትሕዴን ከተቋቋመ ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ በአቶ ፍሰሐ ኃይለ ማርያም ተድላ ይመራ ነበር፡፡ በ2000 ዓ.ም. አቶ ፍሰሐ ከተገደሉ በኋላ ነው አቶ ሞላ ትሕዴንን መምራት የጀመሩት፡፡ አቶ ፍሰሐ የተገደሉት በኢትዮጵያ ነው ወይስ በኤርትራ የሚለው ጉዳይ ላይ እስካሁን የተረጋገጠ መረጃ አልተገኘም፡፡

አቶ ሞላ ለትግራይ ሕዝብ ወይም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቆመ ድርጅት እየመሩ መቀመጫቸውን ኤርትራ ለምን እንዳደረጉ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ‹‹ድጋፍ እናገኛለን ማለት ዓላማችንን እነሱ [የኤርትራ መሪዎች] ይመራሉ ማለት አይደለም፡፡ ተፅዕኖ እስካልተፈጠረብን ድረስ ድጋፍና እገዛ ካገኘን ከኤርትራም፣ ከሱዳንም፣ ከግብፅም ይሁን ከአሜሪካ ችግር የለውም፤›› ብለው ነበር፡፡ በተጨማሪም የኤርትራ መንግሥት ለኢትዮጵያ አንድነትና እኩልነት እንደሚሠራና ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚሠራ ነው የሚለውን ትችት እንደማይቀበሉት ገልጸው ነበር፡፡

ከኤርትራ ተመልሰው ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ከኢትዮጵያን ፈርስት ዶት ኮም ዋና አዘጋጅ ቢንያም ከበደ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት አቶ ሞላ፣ ሁሉንም አቋማቸውን ማለት ይቻላል ቀይረዋል፡፡ ለአብነትም የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመበታተን እንጂ ለአንድነቷ አይሠራም የሚለውን ገምግመው መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡ የትጥቅ ትግሉም ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ነገር እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹በየጊዜው ሁኔታዎችን እየገመገምን በሄድን ቁጥር የትጥቅ ትግሉ ትርጉም የሌለውና አዋጭ እንዳልሆነ ተረድተናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ራሳቸው ካደረጉት ግምገማ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አብረው መሥራታቸው የአቋም ለውጥ ለማድረግ ሚና መጫወቱንም አቶ ሞላ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በሒደት ግን የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥተን ከመንግሥት ጋር በየጊዜው እየተገናኘን ጠለቅ ያለ ውይይትና ድርድር አድርገን ረዘም ላለ ጊዜ አብረን ስንሠራ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት በመግለጫው እነ ሞላ የአቋም ለውጥ እንዲያደርጉ ሁለት ጉዳዮች እንደረዱ ጠቅሷል፡፡ የመጀመሪያው አገሪቱ በማስመዝገብ ላይ ያለችው ፈጣን ልማትና ዕድገት የፈጠረው ተፅዕኖ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ የኢትዮጵያን ልማትና ሰላም የሚያደናቅፉ ኃይሎችን አጀንዳ እየተረዱ መምጣታቸው ነው፡፡

የትሕዴን ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

የተመድ ሪፖርቶችን ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎች ትሕዴን ወደ 20,000 የሚጠጉ ወታደሮች እንዳሉት ይጠቁማሉ፡፡ አቶ ሞላ ራሳቸው በአንድ ወቅት ከ10,000 በላይ ወታደሮች እንዳሏቸው ገልጸው ነበር፡፡ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከራሳቸው ወታደሮች ይልቅ የሚያምኗቸውና ጥበቃ የሚያደርጉላቸው የትሕዴን ወታደሮች እንደሆኑም ሲነገር ነበር፡፡ ለዚህ ታማኝነታቸውም የተሻለ ጥቅማ ጥቅም እንደሚያገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አቶ ሞላን ጨምሮ የትሕዴን አባላት በውህደቱ የመሪነት ሚና ለመውሰድ የነበራቸው ፍላጎት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ዶ/ር ብርሃኑ መሪነቱን እንዲወስዱ በመፈለጋቸው ቅሬታ እንደተፈጠረ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህንን አጋጣሚ እንደተጠቀመበት አንዳንድ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡

ትሕዴን በ2005 ዓ.ም. ከሌሎች አምስት ታጣቂ ቡድኖች ጋር ጥምረት ከፈጠረ በኋላ የተሻለ ጥንካሬ ላይ እንደሚገኝም ተዘግቦ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የመንግሥት መግለጫ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ኤርትራ ውስጥ የቀሩትና መውጣት ያልቻሉ የቡድኑ አባላት በሽተኞች፣ በየቦታው የነበሩ እስረኞች፣ የኪነት ቡድን አባላትና ሌሎች አቅመ ደካሞች ብቻ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፤›› በማለት የቡድኑ ህልውና ያበቃለት እንደሆነ ይገልጻል፡፡

ከዚህ በተቃራኒ ኤርትራ ውስጥ የቀረው ትሕዴን እንዳወጣው በተገለጸው መግለጫ፣ ‹‹በቅርብ ጊዜ በትግሉ የቆዩና ግላዊ ጥቅማቸው የተነካባቸው ጥቂት ግለሰቦች ትግሉን ባሻቸው መንገድ ሊጠመዝዙት ስላልቻሉና በአብዛኛው ታጋይ ተይዘው መፈናፈኛ ስላጡ ተስፋ ቆርጠው ከትግል ሜዳ ሸሽተዋል፤›› ሲል ያትታል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ጥቂት ግለሰቦች›› ሲል የጠቀሳቸው ታጋዮች መውጣት የያዘውን ትግል እንደማያደናቅፈው ገልጿል፡፡ መግለጫው ትሕዴን ምን ያህል ታጣቂዎች እንዳሉት ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡

የትሕዴን ምክትል ሊቀመንበር አቶ መኰንን ተስፋይ ከቪኦኤ የትግርኛ አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ከሱዳን ተሻግረዋል የተባሉት ታጣቂዎች ቁጥር በጣም የተጋነነ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አቶ ሞላ በአመራር ብቃታቸው ላይ በመገምገማቸውና የጥምረቱ ሊቀ መንበር ሆነው ባለመመረጣቸው ደስተኛ እንዳልነበሩም አክለዋል፡፡

የሱዳን ሚና      

የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን በማደራጀትና በመደገፍ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ሱዳን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡ መግለጫው፣ ‹‹ምን ጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና ልማት የቅርብ አጋር የሆነው የሱዳን መንግሥትም እነዚህን ታጣቂዎች ሱዳን መሬት ውስጥ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ከኤርትራ መንግሥት ወታደሮች ጥቃት በመከላከል፣ አስፈላጊውን ምግብና መጠለያ በማቅረብ፣ በውጊያው ለቆሰሉ የቡድኑ ታጣቂዎች ተገቢውን የሕክምና ዕርዳታ በመስጠትና በመጨረሻም ኃይሉን ከነሙሉ ትጥቁና ድርጅቱ በተሽከርካሪ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ድረስ በማጓጓዝ በሰላም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ በኩል ላደረገው ታሪክ የማይረሳ ከፍተኛ አስተዋጽኦ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም የጋራ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉ ከፍተኛ ምሥጋና ያቀርባል፤›› ሲል የሱዳንን አስተዋጽኦ ይዘረዝራል፡፡

ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ ጋር ግንኙነቷን አመዛዝና ለመጓዝ የምትጥረው ሱዳን ለመምረጥ የምትገደድ ከሆነ፣ ውግንናዋ ከማን ጋር እንደሆነ ያሳየ ውሳኔ ነውም ተብሎለታል፡፡

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፣ በቅርቡ ኢትዮጵያ ልትወረኝ እያሴረች ነው ብላ ኤርትራ መግለጿ ይታወሳል፡፡ ለ14 ዓመታት የታገሉትን የትሕዴን ተዋጊዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ‘አገር ወዳጆች’ እና ‘ጀግኖች’ እያለ ማወደስ መቀጠሉ በማኅበራዊ ሚዲያዎችም ሆነ በተለያዩ ዘዴዎች አስተያየታቸውን በሰጡ ዜጎች አልተወደደለትም፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -