Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ አስተዳደር ታጥረው በተቀመጡ ቦታዎች ላይ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ እወስዳለሁ አለ

የአዲስ አበባ አስተዳደር ታጥረው በተቀመጡ ቦታዎች ላይ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ እወስዳለሁ አለ

ቀን:

በመሀል አዲስ አበባ ለዘመናት ታጥረው በተቀመጡና ግንባታ ባልተካሄደባቸው ቦታዎች ላይ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ እንደሚወስድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሀል አዲስ አበባን በድጋሚ መገንባት ያስፈልጋል በማለት ነዋሪዎችን ማስነሳቱ ይታወሳል፡፡ አስተዳደሩ በርካታ ኪስ ቦታዎችን ለባለሀብቶች ቢሰጥም፣ ባለሀብቶቹ ግንባታ ከማካሄድ ይልቅ አጥረው የያዟቸው ቦታዎች በርካታ ናቸው፡፡

እነዚህ ሕግን ያልተከተሉ አሠራሮች በነዋሪዎች ላይ ቅሬታ እያሳደሩ መሆኑ በተገኙ መድረኮች እየተገለጸ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የ2007 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ካካሄደ በኋላ፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አሠራሩን ማጥበቅ እንደሚያስፈልገውና የወጡ ሕጐችን በብቃት ማስፈጸም እንደሚገባ መግባባት ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃየሎም ጣውዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለመልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች ተይዘው ወደ ግንባታ ያልተገባባቸው ቦታዎች ያለባቸውን ችግር በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት በዓመቱ ወደ ሥራ ለመግባት ታቅዷል፡፡ በዚህ መስክ ያለውን ችግር አቶ ኃየሎም ሲያስረዱ፣ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አስፈላጊውን ሥራ ቀደም ብሎ ማጠናቀቅ ቢችልም ለተወሰኑ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት የማቅረብ ችግር አጋጥሟል፡፡ ‹‹ከዚህ በተጨማሪም ሙሉ በሙሉ ቦታው እስኪፀዳም ግንባታ በመጀመር በኩል መጓተት አለ፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ከመሠረተ ልማት ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት ይኖርብናል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማትም በተሰጣቸው ቦታ ላይ ተነሺዎችን በማይጐዳ ሁኔታ ግንባታ እንዲካሄዱ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

በርካታ አልሚዎች የወሰዷቸውን ቦታዎች አጥረው ማስቀመጣቸውን በተመለከተም፣ ‹‹በዚህ በኩል ያሉ ችግሮችን በመለየት ውል እንዳይራዘም በማድረግ መሬቱን ወደ መሬት ባንክ የማስገባት ሥራ ይሠራል፤›› በማለት አቶ ኃየሎም ተናግረዋል፡፡ መሥሪያ ቤታቸው ከወትሮው በተለየ ዘንድሮ ጠንካራ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ አስገንዝበዋል፡፡

በመልሶ ማልማት ሥራ ከተያዙት አንዱ የሸራተን አዲስ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ይገኝበታል፡፡ ለዚህ ቦታ በ2002 ዓ.ም. ነዋሪውን የማንሳት ሥራ ቢጠናቀቅም በዚህ ቦታ ላይ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ጋራዥ ባለመነሳቱ ብቻ ወደ ግንባታ ሳይገባ ቆይቷል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ተለዋጭ ቦታ የተሰጠው የራሱን ግንባታ ሳያካሂድ ከዚህ ቦታ ላይ የመነሳት ፍላጐት አላሳየም ተብሏል፡፡ ነገር ግን የአካባቢው ነዋሪዎች ቦታውን ከለቀቁ ከአምስት ዓመት በላይ ተቆጥሯል፡፡  

ከዚህ በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስፋፊያ፣ አሮጌው ቄራ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ማስፋፊያ፣ ተክለ ሃይማኖት መልሶ ማልማት፣ ሸበሌ ሆቴል ጀርባ መልሶ ማልማት ቦታዎች ይገኛሉ፡፡

እነዚህና ሌሎች በሒደት ላይ ካሉ የመልሶ ማልማት ቦታዎች ላይ ነዋሪዎች እንዲነሱ ቢደረግም፣ የተወሰኑ መኖሪያ ቤቶችንና መንግሥታዊ ተቋማትን ማንሳት ባለመቻሉ ቦታዎቹ ታጥረው ለዓመታት እንዲቀመጡ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም የነዋሪዎችን ኑሮ አስቸጋሪ ከማድረጉም በላይ በተነሱበት ምክንያት ላይም ጥያቄ እያነሱ እንደሚገኝ እየተገለጸ ነው፡፡ አቶ ኃየሎም እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ከመሠረተ ልማት ድርጅቶች ከኤሌክትሪክ፣ ከውኃ፣ ከቤቶች ልማት ጋር በተጠናከረ ሁኔታ በጋራ በመሥራት መሬቱን ነፃ በማድረግ ወደ ልማት ለማስገባት እየተሠራ ነው፡፡

‹‹አስቸጋሪ ሁኔታ እንኳ ቢፈጠር ግንባታውን ከሥር ከሥር ለማካሄድ ዕቅድ ተይዟል፤›› በማለት አቶ ኃየሎም የዘንድሮን ዕቅድ አስረድተዋል፡፡

ከንቲባ ድሪባ ኩማ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፣ 360 ሔክታር መሬት በመልሶ ማልማት ፕሮግራም ለማልማት ታቅዷል፡፡ ይህ ልማት የሚካሄደው እንደ አዲስ ሲሆን፣ ለቦታው ለቤቶች ልማት፣ ለቢዝነስና ለባለ ኮከብ ሆቴል የሚውል ነው፡፡  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ90 ባለሀብቶች የተሰጠ መሬት ግንባታ ያልተካሄደበት በመሆኑ መናጠቁን ገልጸዋል፡፡

ከንቲባው እንዳሉት፣ በተካሄደው ግምገማ በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ወስደው ግንባታ ያላካሄዱ አልሚዎች ከፍተኛ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ አልሚዎች ለምን ግንባታ እንዳላካሄዱ በሚመረመርበት ወቅት የከተማው አስተዳደር ችግር አንዱ ምክንያት ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በዚህ ምክንያት አስተዳደሩ ያለበትን ችግር በመቅረፍ በዚህ ዓመት ወደ ግንባታ እንዲገባ ግፊት እንደሚደረግ፣ አልሚዎቹ ወደ ግንባታ የማይገቡ ከሆነ ግን ዕርምጃ ይወስዳል በማለት ከንቲባው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...