Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አሥር የአሜሪካ የንግድ ድርጅቶች ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ከንግድ ማኅበረሰቡ ጋር መከሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በውጭ ንግድ አገልግሎት ቢሮው አማካይነት አሥር የአሜሪካ ኩባንያዎችን በዚህ ሳምንት ለአንድ ቀን በአዲስ አበባ መስተናገዳቸውን አስታወቀ፡፡ ድርጅቶቹ ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ከንግድ ማኅበረሰቡ ጋር መክረዋል፡፡ እነዚህ የንግድ ድርጅቶች በአሜሪካ መንግሥት አማካይነት ወደ አፍሪካ የተላከ ትልቁ የንግድ ልዑካን ቡድን አካል መሆናቸውን ገልጿል፡፡

ኩባንያዎቹ ከመንግሥት ባለሥልጣናትና በተመሳሳይ ዘርፍ ከተሰማሩ የንግድ ድርጅቶች ጋር ተገናኝተው፣ በአሜሪካና በአፍሪካ መካከል በንግድ ዙሪያ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ማጠናከር ስለሚቻልባቸው ሁኔታዎች መወያየታቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ጉብኝት የአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር ‹‹ትሬድ ዊንድስ›› የተሰኘ የአፍሪካ የንግድ ልዑካን አካል ሲሆን፣ ዓላማው ከ100 በላይ የሚሆኑ የአሜሪካ ኩባንያዎች በስምንት ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች ገበያ እንዲገቡ ማስቻል ነው፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሺያ ሃስላክ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ኢትዮጵያ በአፍሪካ ባለው የኢኮኖሚ ዕድገት ረገድ በቀዳሚነት የምትጠቀስ አገር ነች፡፡ አገሪቷ በንግድና ኢንቨስትመንት ረገድ ያላትን ቁርጠኝነት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዷ አሳይታለች፡፡ የአሜሪካ መንግሥትም ሆነ የአሜሪካ የንግዱ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ወሳኝ አጋር እንደሆነች ይገነዘባሉ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ትሬድ ዊንድስ›› የልዑካን ቡድን የፕሬዚዳንት ኦባማ አስተዳደር በአፍሪካ በንግድ ላይ መሰማራት የተሰኘ ዘመቻ አካል ሲሆን፣ የአሜሪካ መንግሥት ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መድቦ በልማትና በንግድ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

‹‹ፕሬዚዳንት ኦባማ ኢትዮጵያን መጐብኘታቸው አሜሪካ ኢትዮጵያን እንደ ወሳኝ አጋር እንደምትቆጥር ማሳያ ነው፤›› ያሉት አምባሳደሯ፣ የልዑካን ቡድኑ መምጣት የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ተከታይ አካል መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በአሜሪካ ኤምባሲ ከፍተኛ የንግድ መኰንን ታኒያ ኮል በበኩላቸው፣ ‹‹በኢትዮጵያ በንግዱ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ በርካታ የአሜሪካ ኩባንያዎችን አማክራለሁ፡፡ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ዝቅተኛ ሙስናና ተመራጭነት ያለው የአገሪቷ መገኛ ገበያው እጅግ ሳቢ እንዲሆን ያደርጉታል፤›› ብለዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በዚህ ሳምንት ከረቡዕ እስከ ዓርብ በደቡብ አፍሪካ ተገኝቶ በዚያ ካሉት የንግድ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ጋር የቀጣና አመራሮች፣ እንዲሁም እንደ ማኪንሲ፣ ሳሶልና ፎርድ ሞተር ኩባንያ ያሉ ትላልቅ የአፍሪካና የአሜሪካ ኩባንያዎች በተገኙበት መድረክ ውይይት እንደሚያካሂድ ይጠበቃል፡፡ የአሜሪካ የንግድ ዲፕሎማቶች ከተለያዩ 20 የአፍሪካ አገሮች ወደዚያው በማቅናት ገበያ ተኮር የሆነ የማማከር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

አብዛኛዎቹ የአሜሪካ ኩባንያዎች በአኅጉሪቱ የሚገኙ ሌሎች ገበያዎችንም በመጐብኘት ላይ ይገኛሉ፡፡ የንግድ ልዑካኑ በአጠቃላይ የሚጐበኟቸው አገሮች አንጐላ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡

በእያንዳንዱ አገር በሚኖራቸው ቆይታ እነዚህ የአሜሪካ ኩባንያዎች ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ለወደፊቱ የንግድ አጋር ሊሆኑ ከሚችሉ በአገሮቹ በመንቀሳቀስ ላይ ካሉ ሌሎች የንግድ ድርጅቶች ጋር ይገናኛሉ ተብሏል፡፡ በዚህ የልዑካን ቡድን የተሳተፉ ኩባንያዎች በሙሉ የሚያቀርቧቸው ዕቃዎችና አገልግሎቶች ለየአገሮቹ ገበያዎች ያላቸውን አግባብነት በሚመለከት የአሜሪካ ኤምባሲ ባልደረቦች በሚገባ ፈትሸው ማረጋገጣቸውን ኤምባሲው አስታውቋል፡፡  

የአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴርና በአገሮቹ የሚገኙ ኤምባሲዎች በጥቅሉ የንግድ ልዑካኑንና በተቀባይ አገሮች የንግድ ድርጀቶችን ያማከሉ 400 ያህል መድረኮችን የማመቻቸት ዕቅድ እንዳላቸው ኤምባሲው አስረድቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች