በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የትራንስፖርት ማኔጅመንት ችግር ለመፍታትና ዘመናዊ የትራፊክ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ከዓለም ባንክ 170 ሚሊዮን ዶላር ብድር መገኘቱ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ እንደገለጹት፣ የዓለም ባንክ በሰጠው ብድር የከተማውን የትራንስፖርት ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ የማሻሻል ሥራ ይከናወናል፡፡ የከተማውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ጥናት በመጠናቀቁ፣ ሥራውን ተግባራዊ ለማድረግ ለከተማው አስተዳደር የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ዋስትና በመስጠቱ የዓለም ባንክ ለፕሮጀክቱ ብድር ለማቅረብ ስምምነት ላይ መደረሱን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ከፈረንሣይ መንግሥት በተገኘ የ50 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ በአዲስ አበባ ከተማ የፈጣን አውቶቡስ ፕሮጀክት ጥናት ዘንድሮ እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡
ከንቲባው እንዳሉት፣ በዚህ ፕሮጀክት ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ባለበት ከጎፋ ተነስቶ በመርካቶ በኩል እስከ እንቁላል ፋብሪካ ድረስ 16 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መንገድ፣ ለፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት ብቻ እንደሚሰጥ ተደርጎ ይገነባል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከአንበሳ አውቶቡስ ድርጅትና ከፐብሊክ ትራንስፖርት ሰርቪስ ድርጅት በተጨማሪ፣ ራሱን የቻለ ሌላ መንግሥታዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅት እንደሚቋቋም ከንቲባ ድሪባ ገልጸው፣ የባቡር አገልግሎትም ሰሞኑን የሚጀምር በመሆኑ የከተማው የትራንስፖርት ችግር መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ገልጸዋል፡፡
አዲሱን የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ተቋም ለማቋቋም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ከመሆኑም በላይ፣ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አውቶቡሶችን እንዲያቀርብ ክፍያ መፈጸሙ ተመልክቷል፡፡
ከመንግሥት የትራንስፖርት ዘርፍ ተሳትፎ በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ 500 አዳዲስ አውቶቡሶችን አስገብቶ አገልግሎት እንዲሰጥ መመቻቸቱን ከንቲባ ድሪባ ተናግረው፣ እነዚህ አውቶቡሶች ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር እንዲገቡ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትም ቅድሚያ እንዲሰጣቸው መወሰኑን አስረድተዋል፡፡ ሲከናወኑ የቆዩ በርካታ ሥራዎች ዘንድሮ ችግሩን በመቅረፍ በኩል አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ከንቲባው ገልጸዋል፡፡