Thursday, September 21, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሥልጣን ድልድልና ሹም ሽር ሥነ ምግባርንና ብቃትን ማዕከል ያደረገ ይሁን!

በአዲሱ ዓመት ትልቅ ግምት ከሚሰጣቸው ዓበይት ጉዳዮች መካከል፣ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የመንግሥትን አስፈጻሚ አካል በሚመራው ካቢኔና በተዋረድ በሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የሚካሄደው የሥልጣን ድልድልና ሹም ሽር ነው፡፡ በቅርቡ አሥረኛውን ጠቅላላ ጉባዔ ያካሄደው ኢሕአዴግ ከሕዝብ የተሰጠውን አደራ ለማስፈጸም በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በሙስናና በፍትሕ ችግሮች ላይ ቁርጠኛ አቋም መያዙን አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ሕዝብ ብዙ ነገሮች ይጠብቃል፡፡ ብቃትና ሥነ ምግባር ያላቸው እንዲመሩት ይመኛል፡፡ ቃልና ተግባርም ይገናኙ ዘንድ ይፈልጋል፡፡ የሥልጣን ድልድልና ሹም ሽሩም ሥነ ምግባርንና ብቃትን ማዕከል እንዲያደርግ ይጠብቃል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በተለያዩ የግምገማ መድረኮቹ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ለሥርዓቱ ጭምር ፀር መሆናቸውን ተረድቶ ሊዘምትባቸው መሆኑን በግልጽ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን በኢሕአዴግ ውስጥ ግምገማ ባህል ቢሆንምና ከዚህ በፊት በተደረጉ ግምገማዎች ወሳኝ የተባሉ ዕርምጃዎች ቢወሰዱም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋለው ቁርጠኝነት ግን እየተልፈሰፈሰ ነው፡፡ በኢሕአዴግ የግምገማ ባህል መሠረት ብቃት የሌላቸውና አጥፊ ሹማምነት ቢገመገሙም፣ ውጤቱ እየታየ አይደለም፡፡ ያጠፋ ተገምግሞ ከኃላፊነቱ መነሳት ሲኖርበት ወይ ሹመት ይጨመርለታል፣ ወይም የያዘውን ሹመት ይዞ ሌላ ቦታ ይዛወራል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ግምገማውን አፈር ያበላዋል፡፡

ሕዝቡ በመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ በሙስና፣ በፍትሕ እጦትና በተለያዩ አስተዳደራዊ ጉድለቶች የሚያለቅስባቸው ሹማምንት በግምገማ ወቅት ሒሳቸውን ካወራረዱ በኋላ፣ ምንም ሳይነኩ ተኩራርተው ይቀጥላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የሕዝብ ምሬት እየባሰበት ይሄዳል፡፡ ግምገማ በራሱ ውጤት ባይሆንም፣ ለለውጥ መንገድ ካላመቻቸ እርባና ቢስ ይሆናል፡፡ በተለይ በገዥው ፓርቲ ግምገማ የተካሄደባቸው አመራሮችና አባላት በሹመት ላይ ሹመት እየተደረበላቸው ግምገማን ጡንቻ አልባ ሲያደርጉት፣ ሌላውም ግምገማን በመናቅ የፈለገውን ለማድረግ ይነሳል፡፡ ሕዝብም ማልቀሱን ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ ግምገማ ጡንቻውን ያሳይ፡፡ ለሕዝብ የአገልጋይነት መንፈስ የሌላቸው ሹማምንትም ይሰናበቱ፡፡ በሕግም ይጠየቁ፡፡ በተግባር ይረጋገጥ፡፡

ሌላው ኢሕአዴግ ለዓመታት ሲሸሸው የቆየው አንዱ ጉዳይ ሹመት ብቃትን መሠረት ያላደረገ መሆኑ ነው፡፡ የፓርቲ አባልነትንና ታማኝነትን ታሳቢ ያደረገው ይኼ የተለምዶ የሹመት አሰጣጥ አገርን እየበደለ ከመሆኑም በላይ፣ ሥራና ሙያተኛን እየለያየ ነው፡፡ ወሳኝ የተባሉ ሹመቶችን ብቃት የሌላቸው ግለሰቦች እየተቆጣጠሩዋቸው ሥራን መሥራትም ሆነ መምራት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በአመራርም ሆነ በኤክስፐርት ደረጃ ለተለያዩ ቦታዎች የሚመጥኑ ሰዎች እያሉ፣ አቅምም ሆነ ብቃት የሌላቸው እየተሾሙ ሥራዎች እየተበደሉ ነው፡፡ አገርን በተገቢው መንገድም ማስተዳደር እያስቸገረ ነው፡፡

አገራቸውን ለማገልገል የሚፈልጉ የሥነ ምግባር፣ የትምህርት ዝግጅትም ሆነ የሥራ ልምድ ያላቸው ብቁ ዜጎች በፖለቲካ አቋም ልዩነት ቢኖራቸው እንኳ፣ ለቦታው እስከመጠኑ ድረስ መሾም አለባቸው፡፡ የእነሱ ኃላፊነት ለአገር መሥራትና በፖሊሲው መሠረት ማስፈጸም እንጂ የግድ የድርጅት አባልነት አይጠበቅባቸውም፡፡ እንዲህ ዓይነት ብቁና ንቁ የሆኑ ባለሙያዎችና አመራሮች የሚፈለጉት ከፖለቲካው ይልቅ አገር ስለምትበልጥ ነው፡፡ ከፍተኛ ሥነ ምግባር፣ የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ያላቸው ዜጎች ቁጥር ደግሞ ብዙ ነው፡፡ አገሪቷ አንጡራ ሀብቷን ከስክሳ ያስተማረቻቸው ዜጎች በመብራት እየተፈለጉ ኃላፊነት ይሰጣቸው፡፡ ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ ለአገር ይሰጥ፡፡ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ በአንክሮ መክሮ ውሳኔ ላይ መድረስ አለበት፡፡ ሥነ ምግባርና ብቃት ያላቸውን ያፈላልግ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የሚታየው አደገኛ ጉዳይ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ ግለሰቦችን ይመለከታል፡፡ እነዚህ በቢሮክራሲው ውስጥ በስፋት የተሰገሰጉት ሥነ ምግባርና ብቃት የሌላቸው ኃይሎች ሕዝብን ካለማክበራቸውም በላይ፣ ለአለቆቻቸውም ጭምር አይታዘዙም፡፡ እነዚህ በማናለብኝነት ስሜት ራሳቸውን የቆለሉ ግለሰቦች ከሕጋዊ አሠራር ይልቅ ሕገወጥነትን በማስፋፋት፣ የግልጽነትንና የተጠያቂነትን አሠራር በማዳፈን፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማፈን፣ ሙስናን እንደ ሰደድ እሳት በማቀጣጠል፣ ቡድንተኝነትን በማጠናከርና ሕዝብን በማስለቀስ ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ አደገኛ ኃይሎች ተጠራርገው ካልወጡ በስተቀር ሥራን ማከናወንም ሆነ መምራት አይቻልም፡፡ በግምገማ ወቅት ተቧድነው ገብተው ንፁኃንን አንገት በማስደፋት ሥልጣናቸውን እያጠናከሩ ለአገርም ለሕዝብም ጠንቅ ሆነዋል፡፡ ሥነ ምግባርና ብቃት የሌላቸው እነዚህ ኃይሎች በአሻጥር ተሳስርው አገር እየጎዱ ነው፡፡ በአስቸኳይ ይወገዱ፡፡ በፍጥነት፡፡

መንግሥት ከሚታማባቸው በርካታ ችግሮች መካከል የማስፈጸም አቅም ማነስና የአቅመ ቢሶች መብዛት ነው፡፡ ዕቅድ ተለጥጦ ይያዝና አፈጻጸሙ አይረቤ ሲሆን፣ የአፈጻጸም ችግር ነበር ተብሎ እንደ ዋዛ ይነገራል፡፡ ይኼ ለዓመታት ሲንከባለል የመጣ ችግር አገሪቱ በሙሉ አቅሟ እንዳትንቀሳቀስ ሰቅዞ ይዟታል፡፡ ግምገማዎችም ለብ ለብ በመሆናቸው የሚሠራውም የማይሠራውም አንድ ላይ አብሮ ይነጉዳል፡፡ አቅም የሌላቸው አቅም እንዲገነቡ፣ ብቃት የሌላቸውም ብቃት እንዲያገኙ ማድረግ ሲገባ ከመነዳሪው ተቀዶ፣ ጎማው ተቦትርፎ በቸርኬ እንደሚነዳ መኪና አገር ለአደጋ እየተጋለጠች ነው፡፡ በጣም በርካታ ባለሙያዎችና ልሂቃን ባሉበት አገር ውስጥ የአመራር ተሰጥኦ የሌላቸው ሰዎች እስከ መቼ እንቅፋት እንደሆኑ ይቀጥላሉ? ይኼ በብርቱ ሊታሰብበትና አጣዳፊ መፍትሔ ሊፈለግለት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የብቃት ያለህ መባል አለበት፡፡

መንግሥት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን በብቃት ለማሳካት፣ አገሪቱን ሰንጎ የያዛትን ድህነት ለመቀነስ፣ የበለፀገችና የታፈረች ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባትና የተጀመረውን ልማት ዘላቂ ለማድረግ የሚፈልግ ከሆነ፣ የሥልጣን ድልድሉንና ሹም ሽሩን በሚገባ ሊያስብበት ይገባል፡፡ መንግሥት የሕዝብ አደራ አለብኝ ሲል ለይስሙላ መሆን የለበትም፡፡ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ነገሮችን እየጠበቀ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ይስፈን፣ ፍትሕ ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ይሁን፣ የሕግ የበላይነት ይኑር፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ፣ አስፀያፊው ሙስና ይዘመትበት፣ ወዘተ እያለ ነው፡፡ የሕዝብ አደራ አለብኝ የሚለው መንግሥትም ሥነ ምግባርና ብቃት ያላቸውን ይሹም፡፡ ብቃትና ሥነ ምግባር የሌላቸውን ያራግፍ፡፡ ግምገማ የይስሙላ አይሁን፡፡ በመሆኑም የሥልጣን ድልድልና ሹም ሽር ሥነ ምግባርንና ብቃትን ማዕከል ያደረገ ይሁን!        

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...