Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት ኢትዮጵያዊ ሥራ አስፈጻሚ ተሾመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅትን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲመራ በነበረው የህንዱ ኩባንያ ምትክ አቶ ጎሳዬ መንግሥቴ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ተሾሙ፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ በህንዱ ኩባንያ ኢንዲያ ፓወር ግሪድ ምትክ ባለፈው ሳምንት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሾሟቸው አቶ ጎሳዬ፣ በተለያዩ ተቋማት የኃይል አቅርቦትና ጥናት ክፍሎችን በበላይነት ሲመሩ የነበሩ ናቸው፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ያገኙት አቶ ጎሳዬ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኢነርጂ ኢኮኖሚክስ ስኮትላንድ በሚገኘው ዳንዲ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2001 እስከ 2005 ድረስ በቀድሞው የመሠረተ ልማት ሚኒስቴር ውስጥ የኃይል ማስፋፊያና የልማት ዲፓርትመንት ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ይህ ኃላፊነት ወደ ማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር በተላለፈበት ወቅት ወደዚሁ ተቋም በመዘዋወር በተመሳሳይ ኃላፊነት እ.ኤ.አ. ከ2005 እስከ 2009 አገልግለዋል፡፡

ይኼው ተመሳሳይ ኃላፊነት ወደ ውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በተላለፈበት ወቅትም ወደዚሁ ተቋም ተዘዋውረው፣ አዲሱን ሹመት እስካገኙበት ጊዜ ድረስ የኃይል ጥናትና ልማት ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡

የአቶ ጎሳዬን ሹመት አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ ‹‹አቶ ጎሳዬ በኢነርጂ ኢኮኖሚክስ የማስተርስ ዲግሪ ያለው፣ የረጅም ጊዜ የሥራ ልምድ እንዲሁም የዘርፉን መውጫ መግቢያ የሚያውቅ ነው፡፡ በመሆኑም ለውጥ ያመጣል ብለን የምናምንበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሰሞኑን ለፋና ብሮድካስት መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ቀርበውላቸው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መቆራረጥን የተመለከተ ነበር፡፡

የኤሌክትሪክ መስመሮቹ ማርጀት ዋነኛው ችግር ቢሆንም፣ አገልግሎቱን የሚሰጠው ድርጅት ሠራተኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ፊውዝ እየነቀሉ እንደሚያቋርጡ፣ ኃይል የተቋረጠበት አካባቢ ነዋሪዎች በገንዘብ ሲደልሉዋቸው ፊውዙን ወደ ቦታው በመመለስ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚለቁ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ፈተና ላለበት ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት አቶ ጎሳዬ ችግሩን በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የሕዝብ ቅሬታ ያለበትና የመልካም አስተዳደር ችግር የተንሰራፋበት ተቋም መሆኑን ቀድሜ አውቃለሁ፡፡ ቁርጠኝነት የሚያስፈልገው ኃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን ትክክለኛ አመራር ካለ የማይፈታ ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡

የሰው ኃይል ዋናው ፈተና እንደሆነ የገለጹት አቶ ጎሳዬ፣ ትክክለኛ አመራር ከሌለ ሠራተኛውም እንደማይሠራና ዋልጌ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ዋና ትኩረቴ አሁን ያለው ሥርዓት ይሠራል ወይስ አይሠራም የሚለውን መፈተሽ እንጂ፣ የሌባና ፖሊስ ዓይነት አካሄድ አልሄድም፤›› ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ሳይፈራ ዋልጌ ሠራተኞችን የሚያጋልጥበት ሥርዓት እንደሚዘረጋ የገለጹት አቶ ጎሳዬ፣ ኅብረተሰቡ ችግሩን በደንብ ከተረዳ ድጋፍ ሊያደርግና የመፍትሔው አካል ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡

በተለይ ባለፈው ክረምት ወቅት በነበረው የዝናብ እጥረት ምክንያት ግድቦች ውኃ ባለመሙላታቸው በኃይል አቅርቦት ረገድ አስቸጋሪ ዓመት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ያለውን ችግርና የሚደረገውን የመፍትሔ እንቅስቃሴ ለኅብረተሰቡ በማሳወቅ ተባባሪ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ (ለዚህ ዘገባ ታምሩ ጽጌና ውድነህ ዘነበ አስተዋጽኦ አድርገዋል)

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች