በአቶ ሞላ አስገዶም የተመሩ የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትሕዴን) አባላት ከኤርትራ መንግሥት ታጣቂዎች ጋር ድንበር አካባቢ ውጊያ በማድረግ ጳጉሜን 6 ቀን 2007 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ሱዳን ገብተው፣ መስከረም 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ መንግሥት ገልጿል፡፡ መንግሥት ከዚህ ታጣቂ ቡድን ጋር ለአንድ ዓመት የቆየ ሚስጥራዊ ግንኙነት ማድረጉንም አስታውቋል፡፡ ትሕዴን በ1993 ዓ.ም. በ30 ታጣቂዎች የተቋቋመ አማፂ ቡድን ሲሆን፣ ‘ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ መስዋዕት የከፈለበትን የትግል ዓላማ ወደ ጎን የተወ በመሆኑ ሊወገድ ይገባል’ በሚል ዓላማ ወደ ትጥቅ ትግል የገባ ነው፡፡ በተመድ እስከ 20,000 ታጣቂ እንዳለው የተነገረለት በኤርትራ የቀረው ትሕዴን ጥቂት አባላቱን በማጣቱ ጉዳቱ የተጋነነ አይደለም ሲል፣ መንግሥት ግን ህልውናው አክትሟል ብሏል፡፡ የተገኘውም ስኬት ትልቅ ነው ሲል ገልጾታል፡፡ አቶ ሞላ አስገዶም የቀድሞ የሕወሓት ታጋይ ሲሆኑ፣ በ1987 ዓ.ም. ከተቀነሱ የጦር ኃይሉ አባላት አንዱ ናቸው፡፡ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ የትሕዴን ሊቀመንበር ነበሩ፡፡ አቶ ሞላ ከመንግሥት ጋር ባደረጉት ጥልቅ ውይይት አቋማቸውን መለወጣቸውን ሲናገሩ፣ ኤርትራ እንዳሉ የገለጹት ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ መኰንን ተስፋይ ግን የአመራር ብቃታቸው ጥያቄ ተነስቶበት ነበር ብለዋል፡፡ ነገር ግን በቅርቡ ኤርትራ ውስጥ የሚገኙ ሸማቂ ቡድኖች ‘አገር አድን ንቅናቄ’ የተባለ ጥምረት ሲፈጥሩ፣ ምክትል ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተመርጠው ነበር፡፡ ይሁንና ከሦስት ቀናት በኋላ ከ800 በላይ ታጣቂዎቻቸውን ይዘው ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡ ዝርዝሩን ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡