በላይነሽ ቀለሜ የአሥረኛ ክፍል ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በ2008 ዓ.ም. ነበር፡፡ በጊዜው ያመጣችው ውጤት ወደ መሰናዶ ትምህርት የሚያስገባት ባለመሆኑ በአቅራቢያዋ በሚገኝ ቀበሌ በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ድጋፍ እንድታደርግ ተመርጣ መሥራት ጀመረች፡፡ በሥራው ላይ ባሳየችው ጠንካራ እንቅስቃሴ ተመርጣ በየዓመቱ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚሰጠውን የግብርና ኤክስቴንሽን ትምህርት የመማር ዕድሉን አገኘች፡፡ ሙሉ ወጪዋን ሸፍኖ እንድትማር የሚረዳት ሳሳካዋ አፍሪካ አሶሲዬሽን ነው፡፡
በጃፓናዊ ምግባረ ሰናይ ዩኢሺ ሳሳካዋ አማካይነት የተመሠረተው ሳሳካዋ አፍሪካ አሶሲዬሽን እንዲህም በሥሩ ለሚተዳደሩ ሳሳካዋ ግሎባል 2000 እየተባሉ በየአገሮቹ የሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለመመሥረት በአፍሪካ መንቀሳቀስ ከጀመረ 30 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ታዲያ ተቋሙ ወደ አፍሪካ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው የምሥራቅ አፍሪካ በተለይ በአትዮጵያና በሱዳን የተከሰተው ድርቅና ያስከተለው የረሃብ ቸነፈር ነበር፡፡
የግብርና ባለሙያዎችን በማሠልጠን ረገድ ትልቁን ድርሻ የሚወጣው ሳሳካዋ በኤክስቴንሽን አገልግሎት ረገድ (ሴፍ) በሚባለው ፕሮግራሙ በአሁኑ ወቅት ከዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ማለትም ከሐሮማያ፣ ከጅማ፣ ከአዳማ፣ ከሰመራ፣ ከጅግጅጋ፣ ከባህር ዳር፣ ከሐዋሳ፣ ከመቐለ እንዲሁም ከወሎ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡ እንደ በላይነሽ ያሉ የዕድሉ ተካፋዮች በየዩኒቨርሲቲዎቹ የሁለት ዓመት ተኩል ሥልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡
በአማራ ክልል ታች ጋይንት ወረዳ የኤክስቴንሽን ትምህርት የመማር ዕድል ያገኘችው በላይነሽ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቅርንጫፍ በሆነው ዘንዘልማ በሚገኘው ኮሌጅ ትምህርቷን እየተከታተለች ትገኛለች፡፡
ገጠራማ ቦታዎች የሚገኙት አርሶ አደሮች ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን መሬት እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ግንዛቤው ስላልነበራቸው ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ግብርና ሲዳክሩ፣ ሲያልፍም በረሃብ ሲሰቃዩ ዘመናት አስቆጥረዋል፡፡ የበላይነሽ ሚና አርሶ አደሩ የተሻለ ጥቅም ማግኘት የሚችልበትን የአስተራረስና የአመራረት ዘዴ ማሳየት ማስተማር ነው፡፡
በዚህ መሠረትም በላይነሺ በንድፈ ሐሳብ የተማረችውን የድንች አዘራር ትምህርት በጋይንት ወረዳ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ለሁለት ወራት ያህል ልምድ ስታካፍላቸው ቆይታለች፡፡ ዳገት ቁልቁለቱን ሳትል በወረዳና በየቀበሌዎቹ የገበየችውን ትምህርት እስካሁን ለ20 አርሶ አደሮች አካፍላለች፡፡
‹‹አርሶ አደሮቹ እስካሁን ምርታማ የሚያደርጋቸውን መሬት ከግንዛቤ ማነስ ምክንያት ታቅፈውት ሲኖሩ ነበር፤›› የምትለው በላይነሽ በትምህርቷ የቀሰመችውን ዕውቀት ለአርሶ አደሩ ለማስተማር እንቅስቃሴ በምታደርግበት ወቅት የነበረው የአመለካከት ችግር ሥራዋን ፈታኝ አድርጎባት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
‹‹ለረዥም ዓመታት በባህላዊ መንገድ ሲያርሱ የነበሩ አርሶ አደሮች ትክክለኛው መንገድ ይኼ ነው ስንላቸው ለመቀበል ያንገራግራሉ፡፡ ይኼ ትንሽም ቢሆን ሥራችንን ያከብደዋል፤›› ትላለች ያላትን ለማካፈል በምታደርገው ጥረት የሚገጥማትን ችግር ስትገልጽ፡፡
በዘጠኙም ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው ይህ የትምህርት ፕሮግራም በትምህርትና በቴክኖሎጂ በመታገዝ የገበሬውን አስተራረስ ማዘመን፣ ከዝቅተኛ የምርት መጠን ወደ ከፍተኛ የምርት ዕድገት መሸጋገር ቀዳሚ ዕቅዱ ነው፡፡
ለዚህም ተማሪዎቹ ወደ አርሶ አደሩ በመውረድ በግብርናው ላይ የሚታዩ ችግሮች ላይ ጥናት በማድረግ ምርቱ ምን ያህል እንደሆነ፣ ምን ዓይነት የአስተራረስና የአመራረት መንገድ እንደሚከተሉ፣ ውጤቱ እንዲሁም የገበያ ትስስርን በተመለከተ ጥናት ማድረግ ቀዳሚ ሥራቸው ነው፡፡ ከአርሶ አደሩ ጋር የነበራቸውን ቆይታም ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለተወጣጡ መምህራኖች በጥናታቸው አካተው ያቀርባሉ፣ ይገመገማሉ፡፡
አማረ ዋሴ በአማራ ክልል ደጅ ማርያም ቀበሌ ነው የሚሠራው፡፡ የኤክስቴንሽን የልማት ጣቢያ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ዘንድሮ ነው፡፡ በስንዴ ምርት ላይ ሥልጠና የወሰደ ሲሆን፣ ከመሬት ዝግጅት እስከ ግብይት ድረስ ያለውን ሒደት ለገበሬው በጥንቃቄ ያስተምራል፡፡ ነገር ግን አርሶ አደሩ የተባለውን ሳይተገብር ሲቀር ሥራውን የበለጠ እንደሚያወሳስበው ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም ገበሬው ዝግጅቱን በትክክለኛው ወቅት መሠረስ ካልቻለ ሥራውን ያጓትተዋል ይላል፡፡
በትግራይ ክልል በራያ አዘቦ መኖሪያውን ያደረገው እንይ አብርሃ የሦስተኛ ዓመት የአዘዕርት ልማት ተማሪ ነው፡፡ ከ60 ገበሬዎች ጋር የመስክ ሥራ ያከናወነ ሲሆን፣ ቀድሞ የነበረውን የማረስ ሒደት ወደ ቴክኖሎጂ እንዲቀየሩ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ እንደተቻለ ይናገራል፡፡ ከምረቃ በኋላም በአካባቢው ያለውን የግብርና እንቅስቃሴ ለመለወጥ ሞዴል ገበሬዎችን በመምረጥ ትምህርቱን ማወራረስ እንደሚያስፈልግ ያምናል፡፡
የአገሪቱ ገበሬዎች በአማካይ የሚያርሱት መሬት አንድ ሔክታርና ከዚያ በታች በመሆኑ ባለው ነገር በቂ ማምረት እንዲችሉ የተሻሻሉ ግብዓቶችን የመጠቀም፣ ዘመናዊ ማረሻዎችን መጠቀም፣ በመስመር መዝራትና የገበያ ትስስር መፍጠር የመሳሰሉትን አስፈላጊነት የልማት ጣቢያ ተማሪዎች ለአርሶ አደሩ ደጋግሞ ማስረዳት ግድ ይላቸዋል፡፡
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኤክስቴንሽን ትምህርት ክፍል የፕሮግራም ተባባሪ ኮአርዲኔተሩ አዛነው አባሎ ስለትምህርት ዝግጅቱ ሲያስረዳ የልማት ጣቢያ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፎቻቸውን ካቀረቡ በኋላ የሚሰጣቸውን አስተያየት ተቀብለው ለስምንት ወራት ከአርሶ አደሩ ጋር ቆይታ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ፡፡
እ.ኤ.አ. 2011 በሳሳካዋ ግሎባል 2000 ድጋፍ አማካይነት ትምህርቱ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣ እስካሁን በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሩ ከ180 በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ገበሬው በመውረድ ድጋፋቸውን እየሰጡ እንደሚገኙ አቶ አዛነው ገልጸዋል፡፡
በገበያ ትስስር፣ በድኅረ ምርት ጥራትና አያያዝ እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ሊመጣ የሚችለውን ጉዳት ለመታደግ እንዲሁም ገበሬው ከግብርናው መጠቀም ያለበትን ጥቅም እንዲያገኝ ከአርሶ አደሩ ጋር በቅርበት መሥራት ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ለግብርናው መሻሻል በአፍሪካ አራት አገሮች ላይ የሚሠራው ሳሳካዋ ግሎባል 2000 በተለይ በኤክስቴንሽኑ ዘርፍ ኢትዮጵያ ላይ እንደተሳካለት ይነገራል፡፡ የመጀመርያው ምዕራፍ ለመጀመር በሁለት ዓመት ውስጥ ለውጦችን ማስመዝገብ የቻለው ሳሳካዋ በተለይ በሁለተኛው ምዕራፍ እንቅስቃሴው ማለትም እ.ኤ.አ. ከ1995 እስከ 2003 ባለው ጊዜ ውስጥ በተመዘገበው ለውጥ መንግሥት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ፈንድ በመመደብ ለገበሬዎች ምርጥ ዘር ተገዝቶ እንዲያሠራጭ ያነሳሳ አካሄድ መፍጠር ችሎ ነበር፡፡