Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከአሳሳቢነት ያለፈው የአዕምሮ ጤና ችግር

ከአሳሳቢነት ያለፈው የአዕምሮ ጤና ችግር

ቀን:

ብርድና ፀሐይ የተፈራረቀበት ጠይም ገፁ ተጎሳቁሏል፡፡ የተንጨባረረ ፀጉሩ ታጥቦ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ እንደ መቁሰል ባለው ከንፈሩ የሚያኝከው ጫት ድቃቂ የተለጠፈበት ቢሆንም የመጥረግ ሐሳብ ግን የለውም፡፡ ሥሩ የተበላና ያደፈ ሱሪውን በሁለት እጆቹ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ እንደያዘ በራሱ ዓለም በሐሳብ ጭልጥ ብሎ በዝግታ ይራመዳል፡፡

ማንንም የማይተናኮል ቢሆንም ያዩት ከርቀት ይሸሹታል፡፡ በጎናቸው ሲያልፍ  ድንገት ያዩት ደግሞ እንደ መጮህ ብለው የሚገቡበት እስኪጠፋቸው ይርበተበታሉ፡፡ እሱ ግን በዙሪያው ስላሉ ነገሮች ግድ አይሰጠውም፡፡ ሸሽተውት ሲሮጡ እንኳ ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ ፍፁም በሆነ ዝምታ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ወደ ገሀዱ ዓለም የሚመለሰው ጫቱን ሲጨርስ መንገደኛን ግዙልኝ ለማለት ነው፡፡

ጫት ሲያስፈልገው ድንገት ወደ አንዱ መንገደኛ ጠጋ ይልና እጁን ዘርግቶ ‹‹ጫት ግዛልኝ›› ሲል ይጠይቃል፡፡ የለመዱት ዝም ብለውት መንገዳቸውን ሲቀጥሉ አዲስ የሆነባቸው ደግሞ ፊታቸው የቆመውን የአዕምሮ ሕመምተኛ እንዳዩ ተደናብረው እሱንም ያስደነብሩታል፡፡ የጠየቃቸውን ስላልሰጡት አይበሳጭም ወይም ድንጋይ አይወረውርባቸውም ዝም እንዳለ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ የቦሌ መስመርን የሚያዘወትሩ ያውቁታል፡፡ በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኘው ይህ ወጣት ዕጣ ፈንታው እብድ ተብሎ እንደ አንዳች ማስፈራሪያ ማኅበረሰቡ ሲሸሸው ሲያርቀው፣ በየጎዳናው ሲንከራተት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡

     በቤተሰብዎ የአዕምሮ ሕመምተኛ ባይኖር እንኳን ቢያንስ በቀን አንዴ በመንገድዎ ላይ የአዕምሮ ሕመምተኛ ሰው ሳያዩ አያልፉም፡፡ ሐፍረታቸውን ሳይሸፍኑ ዕርቃናቸውን መንገድ ሲሻገሩ፣ አንዳች ነገር ያባረራቸው ይመስል ድንገት ከጎንዎ ፈትለክ ብለው ሲሮጡ፣ ወደ መንገደኛው ዞረው ሲቆጡ፣ ድንጋይ ሲወረውሩ አልያም ለብቻቸው ሲስቁ ያጋጥማሉ፡፡ እንደማንኛውም ጤናማ ሰው ራሳችውን ጠብቀው ንፁህ የለበሱ ነገር ግን አልፎ አልፎ ከመስመር ወጣ ያለ ድርጊት የሚፈፅሙ የአዕምሮ ጤና የራቃቸውን ተመልክተው ይሆናል፡፡ አልያም በየመንገዱ ያሉ ቆሻሻዎችን ጠርገው ሲያነሱ፣ ወይም ኑሯቸውን በቆሻሻ ክምር ላይ አድርገው በራሳቸው ዓለም ሆነው ኑሮን ሲገፉ አይተው ተገርመው ይሆናል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች በየምክንያቱ ጤናቸውን የሚያጡ የአዕምሮ ሕመምተኞችን ቢያንስ በቀን አንዴ ሳያዩ መዋል ከባድ ነው፡፡

እነዚህን የአዕምሮ ሕመምተኞች ብዙዎች እንደ ሰው ሳይሆን እንደ አውሬ ሲሸሿቸው፣ ሲያባርሯቸውና ሲሳለቁባቸው ይታያሉ፡፡ በፖለቲካ፣ በፍቅር አበደ እያሉ ያለሙያቸው ስለሕመምተኛው የጤና መጓደል መንስኤ ያሉትን መላምት የሚሰጡም አሉ፡፡ የአዕምሮ ጤናው የተጓደለበት ሰው አከተመለት ብሎ በሚያምን ማኅበረሰብ ውስጥ ሕሙማኑ በሕክምና መረዳት እንደሚችሉ የሚያምኑ ከስንት አንድ ናቸው፡፡

 የአዕምሮ ጤና በባዮሎጂካል፣ በሳይኮሎጂካልና በማኅበራዊ ችግሮች ይከሰታል፡፡ ባዮሎጂካል በሆነ መንገድ የአንድ ሰው የአዕምሮ ጤና የሚታወከው በአዕምሮ ውስጥ ያሉ ኬሚካሎች ሚዛን ሲዛባ፣ የአንጎል መዋቅራዊ ይዘት መዛባት እንዲሁም ከዘር በሚወረስ የአዕምሮ ጤና ችግር ነው፡፡ በሥነ ልቦናዊ የአዕምሮ ጤና መታወክ ደግሞ በልጅነት ጊዜ የሚያጋጥም በደል፣ ከወላጅ ጋር ባለው ግንኙነት በሚፈጠር ክፍተት፣ በሕይወት የሚያጋጥሙ ከባድና አደገኛ ክስተቶችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ አካባቢያዊ ተፅዕኖ እንዲሁ ሕፃኑ የሚያድግበት የኑሮ ደረጃ በማኅበራዊ መንገድ ለሚከሰቱ የአዕምሮ ጤና ችግሮች ምክንያት ናቸው፡፡

እነዚህን ምክንያት አድርገው የሚከሰቱ የጤና ችግሮች የሚያስከትሉት የጤና ችግር ክብደትና ቅለት እንዲሁም የሚያሳዩዋቸው ምልክቶች ለየቅል ናቸው፡፡ በሚያስከትለው ችግር ውስብስብነት በአንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሳይኮሲስ (Psychosis) ሲሆን፣ ታማሚው እርስ በርሱ የሚጣረስና የተምታታ ንግግር፣ ወጣ ያለ ባህሪ፣ ረዘም ላሉ ሰዓታት ሳይንቀሳቀስ በአንድ ዓይነት አኳኋን የመቆየት፣ ከእውነታ ጋር የመጋጨት ምልክቶችን ያሳያል፡፡

በአስከፊነቱ ከሳይኮሲስ ቀጥሎ የሚገኘው ኒውሮሲስ (Neurosis) የሚባለው ነው፡፡ ታማሚዎች ከፍተኛ የመደናገጥ የመደናበር ሁኔታ (panic presentation)፣ ከባድ ጭንቀት (generalized anxiety)፣ የተወሰኑ ነገር ግን ትርጉም የማይሰጡ ነገሮችን በደመነፍስ ሆኖ በተደጋጋሚ ጊዜ የማድረግና የመሳሰሉትን ነገሮች ያደርጋሉ፡፡ ሌላ የተለያዩ መገለጫዎች ያሏቸው የአዕምሮ መታወኮችም አሉ፡፡

በዓለም ላይ 450 ሚሊዮን ሰዎች በተለያዩ የአዕምሮ ጤና ችግሮች እንደሚሰቃዩ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያሳያል፡፡ አደንዛዥና አነቃቂ ንጥረ ነገሮችን መጠቀም፣ በአንጎልና በአዕምሮ ላይ የሚፈጠሩ የጤና ችግሮች በዓለም ላይ ለሚፈጠሩ አብዛኛዎቹ ሞቶችና በሽታዎች ዋነኛ መንስኤ ናቸው፡፡ ከአሥር እስከ 14 በመቶ የሚሆኑ የተለያዩ የጤና ችግሮች እንዲከሰቱም ምክንያት ናቸው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው አ10 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊ ልጆችና ጎልማሶች ቢያንስ በአንዱ የአዕምሮ ጤና ችግር ይሰቃያሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 ይፋ የተደረገ አንድ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአሁኑ ወቅት አራት በመቶ አልያም 322 ሚሊዮን የሚሆኑ የዓለም ሕዝቦች በከባድ የድብርት በሽታ ይሰቃያሉ፡፡ በየዓመቱም 788 ሺሕ ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ፣ ራሳቸውን የማጥፋት ሙከራ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር ደግሞ አብላጫውን ቁጥር ይይዛል፡፡ 75 በመቶ የሚሆነው ራስን የማጥፋት ድርጊት የሚፈፀመው በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ ነው፡፡ ከ15 እስከ 29 የዕድሜ ክልል ውሰጥ ለሚገኙ ወጣቶች ሞትም ዋነኛ መንስኤ ነው፡፡

ከቀናት በፊት በጳውሎስ ሆስፒታል አስተባባሪነት በአዳማ ከተማ ተዘጋጅቶ በነበረው ትኩረቱን በአዕምሮ ጤና ላይ ባደረገው ሥልጠና ላይ ችግሩ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ ጥናት ቀርቦ ነበር፡፡ በጤናው ዘርፍ ከባድ ጫና እየፈጠሩ ካሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መካከል የአዕምሮ ጤና ችግር ግንባር ቀደም ነው፡፡ በተለይም በገጠራማው የአገሪቱ ክፍሎች በስፋት ከሚከሰቱ በሽታዎች 11 በመቶ የሚሆነው በአዕምሮ ጤና ችግር የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደ ስኪዞፌርኒያና ድብርት ያሉት የአዕምሮ ጤና ችግሮች በጤናው ዘርፍ የተጋረጡ ከዋና ዋናዎቹ አሥር በሽታዎች መካከልም መሆናቸውን ጥናቱ ያሳያል፡፡

 ጥናቱን ያቀረቡት ሳይካትሪስቱ ዶ/ር ክብሮም ኃይሌ፣ ‹‹በኢትዮጵያ የአዕምሮ ጤና ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናቶች መደረግ የጀመሩት አሁን ላይ ነው፡፡ ጥናቶቹ የሚያሳዩትም የአዕምሮ ጤና ችግር እየጨመረ መጥቶ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ለአዕምሮ ጤና መጓደል መንስኤ የሆኑ ነገሮች እየበዙ መምጣታቸው ነው፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አደንዛዥና አነቃቂ ንጥረ ነገሮችን አላግባብ የመጠቀም ነገር ተስፋፍቷል፡፡ ግጭቶችም እንዲሁ እየተበራከቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የሕመሙ ደረጃና ጥልቀት የተለያየ ቢሆንም 17 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የአዕምሮ ጤና ችግር አለባቸው፡፡ ይህም ካለው ወደ 100 ሚሊዮን ከሚጠጋ የሕዝብ ቁጥር አንፃር ሲታይ የችግሩ አሳሳቢነት ምን ያህል ደረጃ መድረሱን ያሳያል፡፡

የአዕምሮ ሕሙማንን በሕክምና መርዳት እንደሚቻል ታምኖ የተለያዩ የሕክምና ዘዴዎችን ጥቅም ላይ ማዋል የተጀመረው ከሰባት ሺሕ ዓመታት በፊት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይሰጡ የነበሩ ሕክምናዎች በብዛት ቀላል ራስ ምታትን እንዲሁም እርኩስ መንፈስን ያስወጣሉ ተብሎ ይታሰቡ የነበሩ ናቸው፡፡ አንደኛው የሕክምና ዓይነት በጥንታዊ ግሪኮች የሕክምና ጠበብት ይሰጥ የነበረው ብለድ ሊቺንግና ፐርጂንግ ነበር፡፡ የዚህ ሕክምና መሠረት ሰዎች የሚታመሙት በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኙ ሆርሞኖችና ሌሎች ኬሚካሎች ሚዛን መዛባት ነው የሚለው የወቅቱ ፍልስፍና ነበር፡፡ ሚዛኑን ተስተካክሎ ታማሚው ወደ ጤንነቱ እንዲመለስም የአካል ክፍሉን በስለት በመቁረጥ ደም እንዲፈሰው፣ አልያም እንዲያስታውክ ይደረግ ነበር፡፡

የአዕምሮ ችግር ያለባቸውን ከማኅበረሰቡ ነጥሎ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ማጎርም ከሕክምና ይቆጠር ነበር፡፡ ታማሚው በደሙ ውስጥ የሚገኘውን የስኳር መጠን እንዲቀንስ በማድረግ ሕመምተኛው ራሱን እንዲስት የሚደረግበት ኢንሱሊን ኮማ ቴራፒም እ.ኤ.አ ከ1927 እስከ 1960 ድረስ ይሰጥ ነበር፡፡ ሕመምተኛው ሲዠር የሚቀሰቅሱ መድኃኒቶች እንዲወስድና አካሉ እንዲዳከም የሚደረግበት ሜትራዞል ቴራፒም እ.ኤ.አ እስከ 1982 ድረስ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ አንጎል ውስጥ የሚገኝ ክፍልን ቆርጦ በማውጣት የሕመም ስሜቱ እንዲቀንስ ይደረግበት የነበረውም ሎቦቶሚ የዘመናዊ የአዕምሮ ሕክምና መሠረት ነበር፡፡

የሕክምና ሳይንስ በተራቀቀበት በአሁኑ ዘመን የአዕምሮ ታማሚዎች እንደየ ሕመማቸው ክብደትና ቅለት በማማከር አገልግሎት፣ በመድኃኒትና በክትትል ወደ ራሳቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ እያስከተለ ያለው ጉዳት አሁንም ድረስ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ እንደ አሜሪካ ያሉ ያደጉ አገሮች ለአዕምሮ ሕክምና በዓመት እስከ 147 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጡ ዶክተሩ ያቀረቡት ጥናት ያሳያል፡፡ በመጪዎቹ 20 ዓመታት ውስጥም ለአዕምሮ ጤና የሚወጣው ወጪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 16 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚደርስም ያመለክታል፡፡

በታዳጊ አገሮች ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያሳየው ግን ለአዕምሮ ጤና የተሰጠው ትኩረት እምብዛም ሲሆን፣ የሚያዝለት በጀትም በእጅጉ ዝቅተኛ የሚባል አይነት ነው፡፡ የሕክምናው ተደራሽነትም እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡ ለሕክምና ከሚያዘው በጀት የበለጠ ሕክምናው ተደራሽ ባለመሆኑ አገራቱ ከሚያጡት አምራች ኃይል አንፃር ሲገመገም ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላቸው እንደሚገኝ ጥናቱ ያሳያል፡፡

 17 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም ካለው ውስን የሕክምና ተደራሽነት፣ እንዲሁም የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ችግር ምክንያት ሕክምና የሚያገኙት ከስንት አንድ ናቸው፡፡ እንኳንስ አንዳንድ በባለሙያ ምክር አገልግሎት መፍትሔ ማግኘት የሚችሉ ቀርቶ አዕምሯቸውን ስተው በየቤቱ የታሰሩ፣ በየመንገዱ ድንጋይ የሚወረውሩም ተገቢውን ሕክምና እንደማያገኙ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

‹‹በጠና ከታመሙ ውስጥ አሥር በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ሕክምና የሚያገኙት፡፡ 90 በመቶ የሚሆኑት ሕክምና አያገኙም፤›› የሚሉት ዶ/ር ክብሮም ታማሚዎች በሕክምና መረዳት እንደሚችሉ አምኖ ወደ ሕክምና መስጫ ተቋማት የመውሰድ ባህሉ ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር ያለው የጤና አገልግሎቱና ፍላጎቱም እንደማይመጣጠን ይናገራሉ፡፡ የማኅበረሰቡ የንቃት ደረጃ ይህንን ያህል ነውና ‹‹እብድ ነው ለይቶለታል›› ከማለት ባለፈ በሕክምና መረዳት እንደሚችል አለማመኑም ትልቅ ችግር ነው፡፡ አንዳንድ የአዕምሮ ሕመም ተጠቂ የሆነ ልጅ ያላቸው ወላጆች ልጃቸው ወደ ውጭ እንዳይወጣ አስረው ሊያስቀምጡት ሊደብቁት እንደሚችሉም ጥናቱ ያሳያል፡፡

‹‹በሁሉም የሕመም ደረጃ ላይ የሚገኝ ታማሚ በሕክምና ሊረዳ ይችላል፤›› የሚሉት ዶክተሩ በወቅቱ ሳይታከሙ ቀርተው የህመሙ ደረጃ ወደ ሳይኮሲስ ከፍ ካለ በሕክምና ሙሉ ለሙሉ የመዳን ዕድሉ ጠባብ እንደሚሆን፣ እንዲያም ሆኖ በከፊልም ቢሆን የሕመም ስሜቱ ሊቀንስ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ሕመማቸው የመጨረሻ ደረጃውና ከባዱ የአዕምሮ ሕመም ስኪዞፌርኒያ ላይ የደረሰ 70 በመቶ የሚሆኑት ሕሙማን በሚደረግላቸው ሕክምና ከሕመም ስሜት ነፃ ይሆናሉ፡፡ የተቀሩት 30 በመቶ የሚሆኑት ግን ረዘም ያለ ሕክምናና ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡

‹‹እንደ ወባ አልያም ሌላ በሽታ በአንዴ የሚድን አይደለም፡፡ መድኃኒቱም ረዘም ላለ ጊዜ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ አንዳንዶች ግን በቃ ድነናል ብለው በራሳቸው ውሳኔ መድኃኒቱን መውሰድ ያቋርጣሉ፡፡ ከዚያም ሕመሙ እንደገና ያገረሽባቸዋል፤›› በማለት ተገቢውን ሕክምና ማግኘት ከተቻለ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ነገር ግን ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ዶ/ር ክብሮም ገልፀዋል፡፡  እንደ ድብርት ያሉ የሕመም ዓይነቶች ግን  ሙሉ ለሙሉ በሕክምና መዳን እንደሚችሉ አክለዋል፡፡

ረዘም ላሉ ዓመታት የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት በብቸኝነት ይሰጥ የነበረው የአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነበር፡፡ ይህም ሕክምናው ለታካሚዎች ተደራሽ እንዳይሆን አድርጎት መቆየቱ ይነገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከአማኑኤል በተጨማሪ ኮተቤ አካባቢ ተጨማሪ የሕክምና መስጫ ተቋም እንዲገነባ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ አስሩም ክፍላተ ከተማ በተመረጡ አሥር የመንግሥት ጤና ጣቢያዎች ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተመላላሽ ታካሚዎች ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡ በተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎችም ሕሙማን አልጋ ይዘው የሚታከሙባቸውና አገልግሎት የሚሰጥባቸው አሠራሮች የተዘረጋባቸው የጅማ፣ የመቐለ፣ የሀሮማያና የዲላ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡

‹‹ማኅበረሰቡ በየአካባቢው የሚገኙትን አገልግሎቶች ስለማያውቅና ተቋማቱ ባሉባቸው አንዳንድ ችግሮች የተነሳ ቀጥታ ወደ አማኑኤል መምጣት ይመርጣል፤›› የሚሉት ዶ/ር ክብሮም ለተዘጋጁት አማራጮች ቅድሚያ ሰጥቶ አገልግሎቱን መጠቀም ግድ እንደሚል ተናግረዋል፡፡ በየተቋማቱ ያሉ ባለሙያዎች እጥረትም ሌላው ችግር ነው፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ የሚገኙ ሳይካትሪስቶች ቁጥር 75 አካባቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአዕምሮ ጤና መታወክን ለመከላከል በተናጠል ሳይሆን በፖሊሲ ደረጃ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ፣ የተማከለ ሕክምና መስጠት የሚቻልበትን አሠራር መዘርጋት ወሳኝ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ ማንኛውም የሕክምና ባለሙያ የአዕምሮ ሕክምናን በተወሰነ መጠን መስጠት የሚያስችለውን ሥልጠና ወስዶ ወደ ሥራ እንዲገባ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ዶክተሩ አብራርተዋል፡፡ 

    

    

    

    

    

    

    

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...