Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየልጅነት ዜማዎች

የልጅነት ዜማዎች

ቀን:

ጨለምለም ስላለ አካባቢው ቤታቸው ለመግባት በሚጣደፉ ሰዎች ተሞልቷል፡፡ መሀል ፒያሳ አራዳ ሕንፃ አቅራቢያ ያለ አንድ መደብር ጉዟቸውን ገታ አድርገው በተሰባሰቡ ሰዎች ተጨናንቋል፡፡ መደብሩ የልጆች የሙዚቃ አልበሞች የሚሸጡበት ሲሆን፣ ከተሰቀለው ስፒከር የሚሰማው የልጆች ህብረ ዝማሬ ከሩቅ ይጣራል፡፡ ‹‹በዛ በበጋ›› ን የመሰሉ ዕድሜ ጠገብ መዝሙሮችና እንደ ‹‹አበባየሽ ወይ›› ያሉ የዓውደ ዓመት ዜማዎች ይደመጣሉ፡፡ ክሊፖቻቸው በሕፃናት የተሠሩ መዝሙሮችም ይገኙበታል፡፡ ‹‹ዛሬ ልደቴ ነው›› የተሰኘውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው መዝናኛ እንዲሁም መማሪያ እንዲሆኑ መዝሙሮቹን እያማረጡ ይሸምታሉ፡፡

የልጆች አልባሳት አልያም መጫወቻ በሚሸጡ መደብሮች፣ በሲኒማ ቤቶች አቅራቢያና በሙዚቃ ቤቶች ለልጆች የተዘጋጁ መዝሙሮችን ለገበያ የሚያቀርቡ መደብሮችና ግለሰቦች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት መሰል ሲዲዎችና ዲቪዲዎችን የሚያዘጋጁ ባለሙያዎች አነስተኛ ነበሩ፡፡ ዛሬ ዛሬ ተከታታይ ክፍል ያላቸው የልጆች መዝሙሮችን በቋሚነት የሚያዘጋጁ እንዲሁም አሳትመው የሚያከፋፍሉ ተቋሞች እየበዙ ነው፡፡

ገበያው ላይ አመዛኙን ቁጥር የያዙት ለዓመታት ከልጆች አንደበት ያልተለዩ የድሮ መዝሙሮችን በአዲስ መልክ አቀናብረው ያቀረቡ ናቸው፡፡ ልጆችን ፊደል፣ ቁጥር፣ የእንስሳት ዓይነት፣ የሰውነት ክፍሎችና ቋንቋ በሙዚቃ ለማስተማር የተዘጋጁ ዲቪዲዎችም አሉ፡፡ በተጨማሪም በዓውደ ዓመትና በተለያዩ ክብረ በዓሎች የሚዜሙ መዝሙሮችን የሚያቀርቡ ባለሙያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ፒያሳ፣ ካሳንችስ፣ መርካቶ፣ ቦሌና ሲኤምሲ መሰል መዝሙሮች ለገበያ ከሚቀርቡባቸው ሰፈሮች ጥቂቱ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹የኢትዮጵያ ልጆች ጨዋታ›› የተሰኘው ስብስብ በኢትዮጵያ ልጆች የመዝናኛና የመረጃ ማዕከል የተዘጋጀ ነው፡፡ በልዩ ልዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሙዚቃዎችን ያካትታል፡፡ ልጆችን ሊያዝናኑ ከሚችሉቱ ‹‹ልጅነቴ ማርና ወተቴ››፣ ‹‹እንዲች እንዲች››ና ‹‹እሹሩሩ›› ይጠቀሳሉ፡፡ አስተማሪ ከሚባሉቱ ደግሞ ‹‹ጤናችን በእጃችን››፣ ‹‹ጎበዝ ችግኝ ትከሉ››ና ‹‹የስሜት ሕዋሳት›› ይጠቀሳሉ፡፡

‹‹የልጅነት ሕይወት›› በሚል በሕይወት ማሞ በተከታታይ ክፍል የታተሙ ዲቪዲዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ‹‹ወንድሜ ያዕቆብ››፣ ‹‹መሀረቤን አያችሁ ወይ››፣  ‹‹ጉልበቴ በርታ በርታ››፣ ‹‹የልጅነት ጊዜ ጨዋታ›› እና ‹‹ድንቡሼ ገላ››ን የመሰሉ ዘመን የተሻገሩ መዝሙሮች ይገኙበታል፡፡

ከልጆች ወደ ልጆች በአፍ ይተላለፉ የነበሩ መዝሙሮች ታትመው መቅረባቸው መልካም ቢሆንም፣ ስለሚሠሩበት ጥራት ጥያቄ የሚያነሱ አሉ፡፡ በሌላ በኩል መዝሙሮቹን ለልጆቻቸው የሚገዙ ቤተሰቦች ወይም የሚገለገሉባቸው ትምህርት ቤቶች ውስን በመሆናቸው ዘርፉ ትርፋማ እንዳልሆነ የሚያስረዱ ባለሙያዎች ጥቂት አይደሉም፡፡

ተስፋዬ ፈንቴ የዘ አራዳ ኢንተርቴመንት ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ ‹‹ልጅነቴ›› ካሳተማቸው ተከታታይ ዲቪዲዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ከአራት እስከ አሥር ዓመት ድረስ ላሉ ልጆች ትምህርታዊ ይዘት ያላቸው ሥራዎች ላይ ያተኩራሉ፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ገበያው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም ብዙ ይቀረዋል፡፡ የተሻለ ገበያ ያለው በአዲስ አበባ ቢሆንም ባህርዳር፣ ጎንደርና መቐለም በመጠኑ ይሸጣሉ፡፡ ትኩረት ሊቸረው የሚገባው ግን ለሥራዎቹ ጥራት ነው ይላል፡፡ ቤተሰቦች ለልጆቻቸው ጠቃሚ የመሰላቸውን ነገር ከመሸመት ወደ ኋላ አይሉምና አዘጋጆች ይህን ፍላጎት ከግምት አስገብተው ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ማቅረብ አለባቸው፡፡

ውጭ አገር ከተሠሩ የልጆች መዝሙሮች ዜማ ወስዶ ግጥሙን በኢትዮጵያ ቋንቋ በመቀየር ከሚቀርቡ፣ ቱባ (አገርኛ) መዝሙሮች ቢዘጋጁ መልካም ነው ይላል፡፡ ዘወትር የሚሰሙና ዜማቸው የሕዝብ የሆነ መዝሙሮች ከሚደጋገሙ አዳዲስ ግጥምና ዜማ መዘጋጀት አለበት፡፡ ሙሉ ትኩረታቸውን በልጆች ሙዚቃ ያደረጉ አዘጋጆች እንዲሁም ለልጆች ሙዚቃ የሚሆኑ ስቱዲዮዎች ቢኖሩ ዘርፉ እንደሚሻሻል ተስፋዬ ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል የመዝሙር ስብስቦችን የሚሸምቱ ቤተሰቦች ቢኖሩም፣ ልጆቻቸው የውጭ አገር ሥራዎች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የሚያበርታቱ ብዙ መሆናቸውን ይተቻል፡፡

‹‹ኢትዮጵያዬ›› የበዓል ባህላዊ ሙዚቃዎችን የያዘ ቪሲዲ ነው፡፡ ‹‹አበባየሽ ወይ››፣ ‹‹ገና››ና ‹‹ቡሄ›› የሚሉ ሙዚቃዎች በሕፃናት ከተሠሩ ክሊፖች ጋር ይታያሉ፡፡ የ‹‹ኢትዮጵያዬ›› ፕሮዲውሰር እንዲሁም በሙዚቃ ቅንብር፣ በግጥም፣ በዜማና በዝግጅት የተሳተፈው በባህል ሙዚቃ የሚታወቀው አቶ ዳምጤ መኮንን (ባቢ) ነው፡፡

በ1989 ዓ.ም. ‹‹የወዳጅ ጌጦች›› የተሰኘ የልጆች አልበም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ከሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር በተውጣጡ ልጆች ከተሠሩ ሙዚቃዎች ‹‹ጎዳና ነው ቤቴ›› የተሰኘው በአጭር ጊዜ እውቅና ያገኘ ነበር፡፡ በልጆች ሙዚቃ ዘርፍ መሠራት ከሚገባው ከፊሉ እንኳን እንዳልተሠራ አቶ ዳምጤ ይናገራል፡፡

ልጆችን ለማስተማርና ስለ ባህላቸውም እንዲገነዘቡ ለማድረግ የሚረዱ ሙዚቃዎች በስፋት መዘጋጀት አለባቸው የሚለው ባለሙያው፣ የታወቁ የልጆች መዝሙሮች መታተማቸውን ታሪክን ለትውልድ ከማስተላለፍ አንፃር ያየዋል፡፡ ‹‹ሕፃናት ስለ አገራቸውና ባህላቸው ዛሬ ካላስተማርናቸው ነገ የሚተካ ሰው ይጠፋል፤›› ይላል፡፡

ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ የልጆች ሙዚቃ ዝግጅት ፈታኝ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ትርፋማ አለመሆኑ ከቅጂ መብት ጥሰት ጋር ተደማምሮ ባለሙያዎች ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ ያግዳል፡፡ አቶ ዳምጤ በበኩሉ፣ መዋለ ሕፃናት፣ በየክልሉ ያሉ የትምህርት ቢሮዎች፣ ትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎችም የሚመለከታቸው ተቋማት ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ይላል፡፡

መዝሙሮቹ ተቀዳሚ ግባቸው ያደረጉት ወላጆችና መዋለ ሕፃናትን ነው፡፡ በልዩ ልዩ መንገድ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን፣ መዝሙሮቹን እንደ አማራጭ የሚጠቀሙ አሉ፡፡ በዴስትኒ አካዳሚ ለነርሰሪና ኪንደርጋርደን ተማሪዎች መሰል መዝሙሮች ይከፈታሉ፡፡ ትምህርት ቤቱ የተከፈተው ከአሥር ዓመት በፊት ሲሆን፣ ቀድሞ የውጭ አገር መዝሙሮችን ይጠቀሙ ነበር፡፡ አሁንም በእነዚህ መዝሙሮች ቢገለገሉም የአገር ውስጡንም ይቀላቅላሉ፡፡

የትምህርት ቤቱ ባለቤት ወ/ሮ ሐረገወይን ገረሱ እንደምትናገረው፣ ከኢትዮጵያ ውጪ ያለን ባህልና ታሪክ መሠረት አድርገው የሚዘጋጁ መዝሙሮችን ከመጠቀም የአገር ውስጥ የተሻለ ነው፡፡ ‹‹የኔነት ስሜት አላቸው፤›› በማለት ትገልጻቸዋለች፡፡ ሙዚቃዎቹን በዋነኛነት ለትምህርት ባይጠቀሙባቸውም፣ አንደ መዝናኛና አጋዥ ማስተማሪያ ይመለከቷቸዋል፡፡ እሷ እንደምትለው፣ አብዛኞቹ መዝሙሮች ልጆች ደጋግመው የሚያዳምጧቸውና ዘለግ ላለ ጊዜ ትኩረታቸውን የሚስቡ አይደሉም፡፡

ዘርፉ ገና በጅማሮ ላይ በመሆኑ የጥራት ደረጃው ላይ ጥያቄ ለማንሳት ይከብዳል ብትልም፣ በጥራት ቢሠሩ ሰፊ ፍላጎት እንዳለ ታስረዳለች፡፡ በእርግጥ በመዝሙሮቹ መገልገል ትምህርት ቤቶች ከሚያራምዱት ሥርዓተ ትምህርትና የኢኮኖሚ አቅማቸው ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ በሁሉም ቤተሰብ ቤት መግባት የሚችሉ ሥራዎች መቅረብ አለባቸው ትላለች፡፡ ሕፃናት ሊወዷቸው የሚችሉና ተከታታይነት ባለው ሥራ የሚካተቱ ገፀ ባህሪዎች ቢፈጠሩ በቀላሉ ለልጆች እንደሚስቡ ታስረዳለች፡፡

ሐሳቧን በከፊል የምትጋራው የሁለት ልጆች እናት ወይዘሮ መዓዛ ይርጋ ከዓመት በፊት መገናኛ አካባቢ ካገኘችው አዟሪ ልጆችን ፊደል የሚያስተምር ሲዲ፣ የልደት መዝሙሮች ስብስብና የሕፃናት ጨዋታዎች ስብስብ ከሕፃናት አልባሳት ሱቅ መዝዛቷን ታስታውሳለች፡፡ የመጀመሪያ ልጇ ፊደል በሲዲው እንድትማር ለማድረግ ብትሞክርም ልጇን ብዙም ሊስባት አልቻለም፡፡ ከዚያ በበለጠ ‹‹ቴሊታቢስ›› የተሰኘው የውጭ ተከታታይ ፊልም ይማርካታል፡፡ ልጇ ስለ አመጋገብ፣ ስለ አለባበስና ጨዋታ ብትማርበትም በባህሪዋ ላይ ተፅዕኖ ያሳደሩ ነገሮች ከፊልሙ መልመዷን ትናገራለች፡፡

በእሷ ዕይታ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ የልጆች መዝሙር አልበሞች ሕፃናትን ለረዥም ሰዓት የሚገዙ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለመዱ ጀበና፣ ዕጣን ማጨሻ፣ መሶብን የመሳሰሉ ቁሳቁሶች ተጠቅሞ ልጆችን ለማስተማር የሚደረገው ጥረት ቢያስደስታትም፣ የበለጠ ማራኪ መሆን አለበት ትላለች፡፡ አንዳንድ የፊደል ግድፈቶች ያሉባቸው ሲዲዎች መስተካከል እንዳለባቸውም ታክላለች፡፡ ትክክለኛ መረጃ የማይሰጡ ከሆነ በትምህርት ቤቶች ጥቅም ላይ የሚውሉበት አጋጣሚ ይጠባል፡፡

ማጀቢያ ሙዚቃዎችና ቀለማት ሕፃናትን የሚማርኩ መሆን አለባቸው፡፡ ልጆችን ማስተማር ዓላማ ያደጉት ደግሞ በሕፃናት ዕድሜ መጠን መቅረብ አለባቸው፡፡ የቴክኖሎጂ ማደግን ተከትሎ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ተበራክተዋል፡፡ ልጆች ለመዝናናት ወይም ለመማር ከሚጠቀሙባቸው አማራጮች ጋር የሚወዳደሩ መዝሙሮች መቅረብ አለባቸው ትላለች ወይዘሮ መዓዛ፡፡ አንዳንዴ ቁጥር አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት እየተባሉ የሚቀርቡ ሥራዎች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ አዘጋጆች ከሚያገኙት ገቢ ባሻገር ልጆችን ታሳቢ በማድረግ ሊታሰብበት ይገባል ስትልም ታክላለች፡፡

የልጆች መዝሙሮች ግጥምና ዜማ የሚጽፈው አቶ አይሳነው ተከተል ‹‹ዳንኪራ››ና ‹‹የነገ ፍሬዎች›› የተሰኙ አልበሞች አሳትሟል፡፡ ‹‹ፓርክ እንይ››፣ ‹‹ጠብታ ውኃ›› እና ‹‹የፊደል ገበታ›› በተሰኙ መዝሙሮች ማኅበራዊ ጉዳዮች ይዳሰሳሉ፡፡ አቶ አይሳነው እንደሚለው፣ ሕፃናትን አሰልጥኖ በተዋጣ መንገድ መዝሙሮች እንዲቀርቡ ማድረግ ከባድ ነው፡፡ በብዛት ጥራት የጎደላቸው ሥራዎች የሚቀርቡትም ሕፃናትን በሚፈለገው መንገድ ለማዘጋጀት ስለሚከብድ ነው፡፡ እሱ በየሰፈሩ እየዞረ፣ መዋለ ሕፃናት እያጠያየቀም ሕፃናት ይመለምላል፡፡ የቤተሰቦቻቸው ፍቃድ አለማግኘትና ኅብረተሰቡ ለዘርፉ የሚሰጠው አነስተኛ ቦታ ሥራውን ከባድ የሚያደርግበትን አጋጣሚ ይጠቅሳል፡፡

በትምህርት፣ በአገርና ሌላም ርእሰ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ መዝሙሮች በሕፃናት እድገት ከፍተኛ ሚና ቢጫወቱም ከሚመለከታቸው በቂ ትኩረት አልተሰጣቸውም ይላል፡፡ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር የሚጋራው ሐሳብ የልጆች ሙዚቃ በትልልቅ ተቋሞች መሠራት እንዳለበት ነው፡፡ አዘጋጆች፣ አሳታሚዎች፣ አከፋፋዬችና ሻጮች ትርፋማ ካልሆኑ በዘርፉ ስለማይቀጥሉ የሚመለከታቸው ተቋሞች ርብርብ ያሻል ሲልም ያክላል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን ከሰጡን አንዱ መርካቶ አካባቢ ፊልምና ሙዚቃ የሚያከፋፍለው አቶ እሱባለው ጋሹ ነው፡፡ የልጆች መዝሙሮች ገበያ ክረምት ላይ እንደሚጨምር ይናገራል፡፡ በተለይም አስተማሪ የሆኑት ተፈላጊ ናቸው፡፡ ገበያው ወቅታዊ ቢሆንም በማራኪ መንገድ የሚዘጋጁ መዝሙሮች ቢበራከቱ የተሻለ ይሸጣሉ ይላል፡፡ የሙዚቃ አልበም ሻጩ መሐመድ ሁሴንም የእሱባለውን ሐሳብ ይጋራል፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የልጆች መዝሙር አልበሞች ቁጥር ከመበራከቱ ባሻገር የገዥዎች ቁጥርም ጨምሯል፡፡ መሐመድ በልጆቹ ላይ ካስተዋለውና ከደንበኞቹ ምላሽ ተነስቶ የልጆች መዝሙሮች በየዕድሜ ደረጃው ታሳቢ ሆነው ቢሠሩ መልካም ነው ይላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...