መስከረም 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ከረፋዱ 4 ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ ጅማ በለገሀርና በሄርማታ ገበያ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች አዲሱን ዓመት በተረጋጋ መንፈስ አልተቀበሉም፡፡ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ላይ ታች ሲሉ ዋሉ ነበር ያሳለፉት፡፡
‹‹አዌይቱ›› ይሉታል፡፡ የጅማን ከተማ አቋርጦ የሚያልፍ ወንዝ ነው፡፡ አንዳንዴ የከፋቸው ሰዎች ራሳቸውን ወርውረው ያጠፉበታል፡፡ በክረምት ወራት በአቅራቢያው የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ሲበላም ከርሟል፡፡ ነገር ግን ከቦታው አልፎ መንደር ውስጥ አይገባም ነበር፡፡
አሁን ሁኔታዎች ተቀይረዋል፡፡ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ዘንድ ድንገት ከተፍ ይልና ያራውጣቸዋል፡፡ እስካሁን በሰው በሕይወት ላይ ያደረሰው አደጋ ባይኖርም፣ ተረጋግተው እንዳይኖሩ አድርጓቸዋል፡፡ ቀላልና ከባድ ጉዳትም በነዋሪዎቹና በቁሳቁስ ላይ አድርሷል፡፡ እንስሳት በልቷል፡፡ ከቤት ንብረት አፈናቅሏቸዋል፡፡ እንዲህ ማድረግ ከጀመረም አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነዋሪዎቹም ከዛሬ ነገ ይሻላል በሚል ጠብቀዋል፡፡ ገንዘብ አዋጥተው ግድብ ሠርተውለታል፡፡ ሊያቆመው ግን አልቻለም፡፡
ረቡዕ ጳጉሜን 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ከወትሮው የጠነከረ ክንዱን አሳረፈባቸው፡፡ ወደ ሄርማታ የገበያ ሥፍራ የሚወስደው መንገድ ላይ ያሉ ነዋሪዎች በጎርፉ ክፉኛ ተጐድተዋል፡፡ ከመንገዱ አንደኛው ጥግ የሚገኙት ቤቶች በጎርፉ ተጥለቅልቀዋል፡፡ መሄጃ ያጡ እናቶች ከፈረሰው በረንዳ ላይ ግራ እንደተጋቡ ተቀምጠዋል፡፡ አንደኛዋ እናት እግራቸው ቆስሏል፡፡ ከቀናት በፊት ቤታቸው ጐራ ያለውን ጐርፍ ለመቀነስ ጥረት ቢያደርጉም፣ ሥፍራውን በጎበኘንበት ወቅት ሳሎኑና ማዕድቤቱ ተጥለቅለቆ ነበር፡፡ ቅዝቃዜውን አልቻሉትም፡፡ ከጐናቸው በከሰል ማንደጃ እሳት አቀጣጥለው ሙቀት ለመፍጠር ይጥራሉ፡፡
ቤት ውስጥ የሚገኙ ዕቃዎች ከፊሎቹ በአንድነት ታስረዋል፡፡ የተቀሩት ደግሞ በጐርፉ ተንሳፈዋል፡፡ ሙሉ ቤቱ በጐርፉ የተጥቀለቀለ ቢሆንም አማራጭ የሌላቸው እናት ከውስጡ ከማደር አላገዳቸውም፡፡ ከጐናቸው የሚገኙ ጐረቤቶቻቸው ግን ማደሪያቸውን በረንዳ ከጣሉት ዳስ ካደረጉ ቀናት ተቆጥሯል፡፡ ረቡዕ ከቀትር በኋላ ድንገት በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ቤታቸው ፈርሷል፡፡ ንብረታቸውን እስኪያወጡም ፋታ አልሰጣቸውም፡፡ ሙሉ ንብረታቸው ከወደቀው ቤት ሥር ቀርቷል፡፡ በከፊል መሬት ከተኛው ጣሪያ ሥር በግማሽ ከሚታየው የሽቦ አልጋ በስተቀር ምንም አይታይም፡፡ በመሆኑም እንደሌሎቹ ጎረቤቶቻቸው አካባቢውን ለቅቀው መውጣት አልቻሉም፡፡ ንብረታቸውን መጠባበቅ ይዘዋል፡፡
በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኘው ጽዮን ፃዲቅ ተወልዳ ያደገችው በዚህ ቤት ውስጥ ሲሆን፣ የዘመናት ይዞታቸው መሆኑን ‹‹አያቴም ይኖር የነበረው እዚሁ ነው፤›› ስትል ትናገራለች፡፡ ለስድስት ሆነው በሚኖሩበት ቤት ውስጥ ጐርፍ ሲገባ የመጀመሪያው አልነበረም፡፡ ደጋግሞ ገብቷል፡፡ ነገር ግን ጋብ ሲል ተመልሰው ከቤታቸው ይገቡ ነበር፡፡ እንዳሁኑ ሜዳ ላይ ጥሏቸው አያውቅም፡፡
ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮአቸው ከቀለብ ተርፎ ቤቱን ማስገንባት የሚያስችል ገንዘብ የላቸውም፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ ቢሠራም የሚያኖረን አይመስለኝም፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ ጎርፍ ስለሚገባ ዕጣ ፈንታው መፍረስ ነው፤›› የምትለው ጽዮን፣ መንግሥት ተለዋጭ ቤት ቢሰጣቸው ትመርጣለች፡፡ ይሁን እንጂ ተገቢውን ዕርዳታ እንዳላገኙ ‹‹የመጀመሪያ ቀን የቀበሌ ሰዎች መጥተው ጎብኝተውን ነበር፡፡ ነገር ግን ተመልሰው አልመጡም መፍትሔም አልሰጡንም፡፡ እኛም አማራጭ ስላልነበረን ንብረቱን ለመጠበቅ ውጭ ለማደር ተገደናል፤›› ስትል ሁኔታውን ትገልጻለች፡፡
መንደሩ የተጨናነቀ ሲሆን የፈሳሽ ማስወገጃ ቦይ አልተበጀለትም፡፡ ከዚህ ቀደም ቦይ እንደነበረው የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በመንደሩ የተገነቡት ሕንፃዎች በውኃ መውረጃነት የሚያለግሉትን ቦዮች እንደዘጓቸው ይናገራሉ፡፡
ከእነጽዮን ቤት ቀጥሎ በሚገኘው ግቢ ውስጥ ጥቂት የማይባሉ መኖሪያ ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ከመግቢያው ጀምሮ ግቢውን የሞላው ጐርፍ ወደ ውስጥ ለመግባት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ የጐርፉ መጠን በጥቂት የቀነሰ ቢሆንም፣ አሁንም በውስጡ ለመቆየት አዳጋች ነው፡፡ ባለቤቶቹም በራቸውን ዘግተው በየቤተ ዘመዱ ቤት መዋል ማደር ከጀመሩ ቀናት አልፈዋል፡፡ አልፎ አልፎ ንብረታቸውን ለማየት ለአፍታ ከሚመጡ ሰዎች በቀር ወደ ግቢው ብቅ የሚል የለም፡፡ የጐርፍ አደጋው በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ ከገበያ ሥፍራው ገብቶ ብዙዎቹን ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪዎች አክስሯል፡፡
አደጋው ከደረሰባቸው አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አንዱም የአቶ ከማል አባጊዲ የእህል ወፍጮ ቤት ይገኝበታል፡፡ የወትሮው ሥራውን ያቆመው ወፍጮ ቤቱ በሰዎች ተሞልቷል፡፡ ግድግዳው እስከ ግማሽ ድረስ በውኃ ረጥቧል፡፡ ውስጡም ቀዝቅዟል፡፡ የተደረደሩት የእህል ወፍጮ ማሽኖች ሥራ አቁመዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በውኃ የራሱትን ዲናሞዎች ሲፈቱ ይታያሉ፡፡ በማዳበሪያ የተሞሉ በውኃ የራሱና የጓጎሉ ዱቄቶችና ጥራጥሬዎች በየጥጉ ቆመዋል፡፡ የወፍጮ ቤቱ ባለቤት አቶ ከማል መረጋጋት አይታይባቸውም፡፡ ቁጣ ከፊታቸው ይነበባል፡፡ ለስምንት ዓመታት አገልግሎት የሰጠው ወፍጮ ቤቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ በጐርፍ ተጠቅቷል፡፡ የከዚህ ቀደሙን እንደምንም ብለው ካስተካከሉ በኋላ መሥራት ይጀምሩ ነበር፡፡ የአሁኑ ግን በቀላሉ አልተዋቸውም፡፡ ‹‹በያዝነው ወር ብቻ አራት ጊዜ ጐርፍ ገብቷል፡፡ የዚህኛው ግን የባሰ ሆነ፤›› ይላሉ፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የጐርፍ አደጋው የተከሰተው ዓርብ ሌሊት ሲሆን፣ በቦታው ባለመኖራቸው ብዙ ንብረት ወድሟል፡፡ አምስት የእህል ወፍጮ ተበላሽቶባቸዋል፡፡ ዲናሞዎቹም እንደዚሁ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፡፡ 20 ኩንታል ጥራጥሬና 5 ኩንታል ዱቄት እንዳጡ፣ ከ100,000 ብር በላይ የሚገመት ኪሳራ እንደደረሰባቸውም ይናገራሉ፡፡
በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚከሰተው ጐርፉ አንዳንዶች ቀን የሠሩበትን ማሽን ምሽት ቆጥ ላይ እንዲሰቅሉ አስገድዷቸዋል፡፡ ‹‹አንድ ሞተር 100 ኪሎ ግራም ይመዝናል፤ በየቀኑ ማውጣት ማውረድ የማይታሰብ ነው›› የሚሉት አቶ ከማል፣ ይኼ ዘለቄታዊነት ያለው አማራጭ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደ አማራጭ ሲጠቀሙ ቢከርሙም፣ ከአደጋው መትረፍ እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ በዚህ መልኩ መቆየት እንደማይቻልና መንግሥት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥበትም ጠይቀዋል፡፡
አደጋው በተለያዩ ቀናት የተከሰተ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የማይደርስባቸው የነበሩ ቦታዎችን ሁሉ አጥለቅልቋል፡፡
አጋጣሚው በፈጠረባቸው መደናገጥና ኪሳራ ሕይወታቸውን ለማጥፋት ሙከራ ያደረጉ እንዲሁም እዚህ ነኝ ሳይሉ ከአካባቢው ተሰውረው የነበሩ ሰዎች አጋጥመውናል፡፡ አምስት ዓመታት ያህል በሄርማታ የገበያ ሥፍራ ነግደዋል፡፡ የብዙዎቹ ነጋዴዎች ንብረት በጎርፍ ሲወድም ከያዙት ቦታ አንፃር ንግድ ቤታቻውን አልደፈረም ነበር፡፡ ከቀናት በፊት የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ግን ‹‹ከማንም በላይ ኪሳራ አድርሶብኛል›› ይላሉ፡፡
ሰፈሩን ያጥለቀለቀው ጐርፍ ሌሊት 11 ሰዓት አካባቢ ጥራጥሬ ወደሚሸጥበት ሱቅ ጐረፈ፡፡ ከቀናት በፊት በአካባቢው የጐርፉ አደጋ ተከስቶ የነበረ ቢሆንም፣ ምንም እንደማይከሰት በመተማመን የተለየ ጥንቃቄ አላደረጉም፡፡ ከበረንዳው የነበሩ ጥቂት ኩንታል እህሎች ሲተርፉ ቤቱ ውስጥ የነበረው ሁሉ በጎርፉ ወደመ፡፡ ሁኔታውን የሰሙት ጠዋት አንድ ሰዓት አካባቢ ነበር፡፡ ክስተቱ አስደነግጧቸው ራሳቸውን የማጥፋት ሙከራ አድርገዋል፡፡ የሰፈር ሰዎች ደርሰው አስጣሏቸው፡፡ አካባቢውን ጥለውም ተሰወሩ፡፡
በርካታ ሰዎች ስልክ በመደወል እንዲመጡ ወተወቷቸው፡፡ ሰዓታት ባለፉ ቁጥር ራሳቸውን የመግዛት አቅማቸው ጎለበተ፡፡ በነጋታውም ወደ ቀዬአቸው ተመለሰሱ ‹‹ሱቄ ውስጥ የነበረው እህል በሙሉ በብድር የመጣ ነው፡፡ ብዙ ጊዜም ትርፉን ተጠቅሜ ዋናውን ለአበዳሪዎቼ እመልሳለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው የምሠራው፤›› የሚሉት ነጋዴው፣ በብድር ያመጡት 12 ኩንታል ዱቄት፣ 20 ካርቶን ሳሙና፣ ሰባት ኩንታል ሩዝና ሌሎችም በጐርፉ ተበላሽተው አገኙ፡፡ 75 በመቶ የሚሆን ንብረታቸው በጐርፉ ወድሟል፡፡ ከቀናት በፊት ዘጠኝ ቤተሰብ ያስተዳድሩበት የነበረው ንግድ ተንኮታኩቶ ገደል ገብቷል፡፡
ገና ለገና ገንዘባችን ሳይመለስ ይቀራል የሚል ሥጋት ያደረባቸው አበዳሪዎቻቸውም እዳቸውን እንዲመልሱ መወትወት ይዘዋል፡፡ ሌላ የገቢ ምንጭ የሌላቸው ነጋዴውም ገንዘብ ሊያበድሯቸው የሚችሉ ሰዎች በሚፈላለግ ላይ ናቸው፡፡ ‹‹ዕዳ ከፍዬ ቤተሰቦቼን ማስተዳደር የምችለው ሌላ አበዳሪ ሳገኝ ነው፤›› በማለት አደጋው በሥራቸው ላይ የፈጠረው ችግር አሳሳቢ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
አጋጣሚው ብዙዎችን ያሳዘነና የዕለት ጉርሳቸውን የከለከለ ነው፡፡ ለዓመታት በጥቃቅን ንግድ የተሰማሩ በቀዬው የቆዩ ነዋሪዎች ለነገ ብለው የቋጠሩት ገንዘብ ሳይኖር መና አስቀርቷቸዋል፡፡ የአሁኑን ያህል የከፋ ባይሆንም ‹‹ከዚህ ቀደም ሌሊት ተከስቶ በነበረ ጐርፍ መንግሥት ወደ አንድ አዳራሽ ወስዶን ፍራሽና ብርድ ልብስ አቅርቦልን እናድር ነበር፤ አሁን ግን ጭራሹን ትቶናል›› ያሉት ለገሀር አካባቢ የሚገኙት ወ/ሮ ጽጌ ሉሌ ናቸው፡፡ የ50 ዓመቷ ወ/ሮ ጽጌ፣ ተወልደው ያደጉት እዚሁ አካባቢ ሲሆን፣ አካባቢው በጎርፍ መጠቃት የጀመረው ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ወ/ሮ ጽጌ ከልጆቻቸው፣ ከእናታቸው፣ ከወንድምና ከእህቶቻቸው ጋር ለገሀር አካባቢ በሚገኘው ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፣ ብቸኛ የቤተሰቡ ገቢ የነበረው ከምግብ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ነበር፡፡ ‹‹ሽሮ እሸጥ ነበር፡፡ በዚህ ቤተሰቡን አስተዳድራለሁ፤›› በማለት ከዕለት ጉርስ የሚተርፍ ገንዘብ እንደማያገኙበት ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን ከቀናት በፊት የተፈጠረው ጐርፍ ሥራቸውን እንዲያቆሙ አስገድዷቸዋል፡፡ አካባቢው ከመበላሸቱ አንፃርም ደንበኞቻቸው አልጐበኟቸውም፡፡ በመኝታ ቤትነት፣ በምግብ ቤትነትና እንደሳሎን የሚገለገሉባት ክፍል ግድግዳ እስከ ግማሽ ርሷል፡፡ ከአንድ ቀን በፊት በሳሎን ውስጥ የደረደሯቸው አልጋ፣ ሶፋ፣ ጠረጴዛና ትናንሽ መቀመጫዎች ለቀናት በረንዳ ነበሩ፡፡ በውኃ ርሰዋል፣ ጨቅይተዋልም፡፡
ወ/ሮ ጽጌ፣ የወትሮው እንቅስቃሴያቸውን ሊጀምሩ እየተዘጋጁ ቢሆንም ድንገት ከተፍ የሚለው ጐርፍ አሁንም ሥጋታቸው ሆኗል፡፡ እንደ ሌሎቹ ነዋሪዎች ሁሉ ልዋጭ ቤት ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡
ችግሩ ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው በክረምት ወራት እንደሆነ የተናገሩት የጅማ ከተማ አስተዳደር አቶ ሰለሞን አበበ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የችግሩን አሳሳቢነት በመመልከት ከአምስት ዓመታት በፊት በወንዙ ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች ተለዋጭ ቤት ተሠርቶላቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፈቃደኛ ሆነው ቦታውን መልቀቅ አልቻሉም፡፡ ‹‹ይህ የሁሉም ሰው አቋም ነበር፡፡ ችግሩን እንደገና መመልከት ያስፈልጋል፤›› ያሉት አስተዳደሩ፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንቅስቃሴ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
‹‹በአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም ነጋዴዎች ይገኛሉ፡፡ ለነዋሪዎቹ ተለዋጭ ቤትም ይዘጋጃል፡፡ ለነጋዴዎቹም እንዲሁ የተዘጋጀ የንግድ ቦታ አለ፡፡ ወደ እዚያ ይዘዋወራሉ፤›› ሲሉ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጠተው በመንቀሳቅ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡